Hiber Radio: ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ከእስር ከተፈታ በሁዋላ አስተላለፈው መልዕክት -ምስጋና ይደረሳችሁ!

ክብር ለኃያሉ እግዚአብሔር፣ ለሕዝብ፣ ለቤተሰቦቼ፣ ለወዳጆቼ፣ የሙያ አጋሮቼ ለሆኑት ጋዜጠኞችና የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች፣ እንዲሁም፣ ለዓለማቀፍ ማኅበረሰብ (በተለይ ለምዕራባውያን) ይሁንና፣ በዛሬዋ ዕለት ከትንሿ እስር ቤት ወጥቼ ትልቁን እስር ቤት ተቀላቅያለሁ። ልቦናቸውን በጭቆና ያደነደኑ አምባገነኖች እጄን ለ18 ዓመታት እንዲጠፍር ያዘጋጁት የግፍ ሰንሰለት፣ ይኸው በ6ኛው ዓመት በሕያው እግዚአብሔር ፍቃድና ፍትሕ በተራበው ሕዝባችን ትግል ተበጣጥሶ ወድቋል። ይህ የተበጣጠሰ ሰንሰለት የዴሞክራሲ ትግላችን መጠናከር መገለጫ ቢሆንም፣ በሀገራችን እና በሕዝባችን ላይ የጠለቀው የኅሊማ ሰንሰለት ገና እንዳልተፈታ ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት አንችልም። ሕዝብ ከጭቆና እስኪወጣ ድረስ ትግላችን ይበልጥ እየተጋጋለ መሔድ ይገባዋል።

የሀገራችን ፖለቲካ በአንድ በኩል ተስፋ፣ በሌላ በኩል አደጋ ይዞ መንታ መንገድ ላይ አቁሞናል። በበጎ ገፅታው፣ የሕዝባችን የዴሞክራሲ ጥያቄ ጎልብቶ አምባገነናዊውን ኢሕአዴግ አንገዳግዶታል። ትግሉ እዚህ እንዲደርስ ብዙ ንፁኃን ተንገላተዋል፣ ታስረዋል፣ ተገርፈዋል፣ ተርበዋል፣ ተጠምተዋል፣ ታርዘዋል፣ ተሰድደዋል፣ አካላቸው ጎድሏል፣ የሕይወት መስዋዕትነትን ከፍለዋል።ይህን ሁሉ መስዋዕትነት የከፈሉት ግን፣ ተስፋን አንግበው እንጂ ኢሕአዴግ ላይ ጥላቻ እና በቀልን ሰንቀው አይደለም። ተስፋቸው ከሁሉም በላይ የፍቅርና የመቻቻል፣ ከዚያም የፍትሕ እና የዕኩልነት፣ ብሎም የዕኩልነት እና የፍትሕ ልጅ የሆነውን የሠላም ሀገር ማየት ነው። ግባችን ብቻ ሳይሆን ትግላችንም የግድ እነዚህን እሴቶች ማዕከል ማድረግ አለበት። ስልቱን አበላሽተን ግቡን ማሳመር አንችልም። የብሔር ጥቃቶች እና የፋብሪካ ቃጠሎዎች ለትግል ያነሳሳንን ተስፋ ያጨለሙ አደጋዎች ናቸው። ዛሬ ነገ ሳይባል፣ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አሁኑኑ መቆም አለባቸው።

የሀገራችንን የፖለቲካ ጥየቄዎች በሠላማዊ መንገድ እና በድርድር ለመፍታት እንዲያስችል፣ ኢሕአዴግ ከሁሉም ተቃዋሚዎች ጋር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መደራደር ይኖርበታል። በሕጋዊ መድረኩ ላይ ካሉ ተቃዋሚዎች ጋር ብቻ የሚደረግ ድርድር በቂ አይደለም። በዚህ ረገድ የደቡብ አፍሪቃ ተሞክሮ ብዙ ትምህርት ሊቀሰምበት የሚችል ነው። ሠላምን ለማውረድ ሁሉም አማራጮች መፈተሽ አለባቸው።

ከዐፄ ኃይለሥላሴ ወደደርግ፣ ከደርግ ወደ ኢሕአዴግ የተደረጉት ሽግግሮች በአገራችን ላይ ከባድ ጠባሳ አሳርፈው ማለፋቸው የቅርብ ግዜ ትዝታችን ነው። በተለይ ታላቁ – የኢሕአዴግ – ታሪካዊ – ስህተት እንዳይደገም ከፍተኛ ጥንቃቄ እንድናደርግ ይጠበቅብናል። በሌሎች አገራት ያልታዩ ፈተናዎች ድሮም ሆነ ዘንድሮ አልተጋረጡብንም። እንደደቡብ አፍሪካ የመሳሰሉ በርካታ ሀገራት ተመሳሳይ ፈተናዎችን በጥበብ አልፈዋቸው ዴሞክራሲያዊ አገራት ገንብተዋል። ጥበቡ እና ክኅሎቱ እኛም ጋር አለ።

ከፊት ለፊታችን ብሩሕ ዘመን ይጠብቀናል። ታሪክ ከኛ ጋር ነው። እውነት ከእኛ ጋር ነው። ፍትሕ ከኛ ጋር ነው። ከሁሉ በላይ ደግሞ፣ ሁሌም ቢሆን የተበዳይ መከታ የሆነው ፈጣሪ ከኛ ጋር ነው። የድል አክሊል ይጠብቀናል። ከኛ የሚጠበቀው በትግላችን ፅናት፣ በአካሔዳችን መቻቻል፣ በመንፈሳችን ፍቅር፣ በአስተሳሰባችን ሚዛናዊነትና በተግባራችን ሠላምን ይዘን ወደፊት መጓዝን ነው።

– ቀሪ የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ!

– ምስጋና በትንሿ እስርቤት ሳለሁ ላሰባችሁኝ ሁሉ!

– ምስጋና ለዓለምዐቀፍ አጋሮቻችን!

– ምስጋና ለዴሞክራሲ ለታገላችሁት ሁሉ!

– ፅድቅ ለሰማዕቶቻችን!

– ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ ለፈጣሪ!

እስክንድር ነጋ፥ አዲስ አበባ

Hiber radio Las Vegas ይህ ህብር ሬድዮ _የወቅታዊ መረጃ ምንጭ ነው። ህብር ሬድዮ በአቤኔዘር ኮሙኒኬሽን ሴንተር እየተዘጋጀ  ከላስ ቬጋስ ከተማ፣ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 630 ሰዓት እስከሰዓት በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ  5639993994 ወይም 563999-3988 1641-793-8229 ወይም 1641-715-8596  በመረጡት ቁጥር መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ 01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *