Hiber Radio: <<..ማዕከላዊ ውስጥ የእግር ጥፍሮቼ ተነቅለዋል በሴትነቴ ጥቃት ተፈጽሞብኛል...>> የግፍ እስረኛዋ ወጣት ንግስት ይርጋ

ንግስት በጎንደር ሰልፍ ላይ ንግስት ፍርድ ቤት ስትቀርብ

በጎንደር ከዓመት በፊት በኮ/ል ደመቀ ዘውዱ የወልቃይት የአማራ ማንነት ኮሚቴ አባል በሕወሃት ደህንቶችና በትግራይ ልዩ ሀይል በሌሊት ታፍኖ ለመውሰድ መሞከሩን በመቃወም የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ በጎንደር በተካሄደ በሰላማዊ ሕዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ በመሳተፉዋ በአሁኑ ወቅት በቃሊቲ እስር ቤት የምትገኘው ወጣት ንግስት ይርጋ በማዕከላዊና በቃሊቲ እስር ቤት እየተፈጸመባት ያለውን ግፍ አጋለጠች። በማዕከላዊ በሴትነቱዋ ጥቃት ደርሶባታል፣የእግር ጥፍሮቿ ተነቅለዋል፣የቆሰለ እግሯን እየነካኩ አሰቃዩዋት እንደነበርና በማንነቷ መሰደቧ ይፋ ሆኗል።

የሕወሃት አገዛዝ በይፋ በአማራ ሕዝብ ላይ ከከፈተው የዘር ማጥፋት ወንጀል በተጨማሪ በእስር ላይ የሚገኙ ንጹሃንን በዚህ ዘመን በሰው ልጅ ላይ ይፈጸማል ተብሎ የማይታሰብ ኢሰብኣዊ የሆነ ግፍ በትግራይ ተወላጅ መርማሪ ተብዬ አሰቃዮች ዛሬም ተጠናክሮ መቀጠሉን በንግስት ይርጋ ላይ የተፈጸመው ግፍ ጉልህ ማሳያ መሆኑን መረጃው ከወጣ በሁዋላ ሰፊ መነጋገሪያ ሆኗል።

በንግስት ላይ ተፈጸመው ግፍ ተከትሎ ቀርቧል።

ስም፡- ንግስት ይርጋ ተፈራ

ዕድሜ፡- 24 አመት

አድራሻ፡- ጎንደር ከተማ ቀበሌ 18

አሁን በእስር የምገኝበት፡- ቃሊቲ እስር ቤት

ለእስር የተዳረግሁበት ምክንያት፡- በሀምሌ ወር 2008 ዓ.ም በጎንደር ተደርጎ የነበረው ህዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ላይ ተሳትፎ አድርገሻል የሚል ነው፡፡

በይፋ የተመሰረተብኝ የክስ አይነት፡- የሽብር ክስ ሲሆን (‹‹ህዝባዊ አመጾችን››) በማደራጀትና በሰልፎቹም በመሳተፍ ‹‹የሽብር ቡድኖችን ተልዕኮ በመቀበል ለማስፈጽም መንቀሳቀስ›› የሚል ነው፡፡ የተጠቀሰው የህግ ክፍል ደግሞ የጸረ-ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3፣ 4 እና 6 ላይ የተመለከቱትን ድርጊቶች በመተላለፍ ወንጀል ከሌሎች አምስት ሰዎች ጋር በአንደኛ ተከሳሽነት ነው የተከሰስሁት፡፡

የክስ ሂደቱን የሚያየው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልድታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ነው፡፡

በእስር በምገኝበት ወቅት የሚከተሉት የመብት ጥሰቶች ተፈጽመውብኛል፡፡

  1. በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ እስር ቤት በቀዝቃዛና በጨለማ ክፍል ውስጥ ለረጅም ቀናት አስረውኛል፡፡
  2. ያለማንም ጠያቂ፣ ያለሁበት ሁኔታ ሳይታወቅ ታፍኜ ለሳምንታት እንድቆይ ተደርጌያለሁ፡፡
  3. በማታ ለምርመራ በሚል ከታሰርሁበት ክፍል እያስወጡ ሰብዓዊ ክብሬን በሚያዋርዱ ተግባራትና ማሰቃየት ተፈጽሞብኛል፡፡
  4. ክብሬን የሚነኩ፣ በማንነቴ ላይ የተመሰረቱ ስድቦች ተሰድቤያለሁ፡፡
  5. ሴትነቴን ተመስርተው ጥቃት ፈጽመውብኛል፤ ሴት ሁኜ መፈጠሬን እንድትጠላ የሚያደርጉ ተግባራትን ፈጽመውብኛል፡፡
  6. እርቃኔን አቁመው ተሳልቀውብኛል፡፡
  7. የእግር ጥፍሮቼን መርማሪዎቼ ነቃቅለዋቸዋል፡፡ ጥፍሮቼን ከነቀሉ በኋላም ጥፍሮቼ የነበሩበትን ቦታ ቁስል እየነካኩ አሰቃይተውኛል፡፡
  8. ጸጉሬን በመንቀልም የኢ-ሰብዓዊ ተግባር ሰለባ አድርገውኛል፡፡
  9. ክስ ተመስርቶብኝ ቃሊቲ ከተዛወርሁም በኋላ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ አልቆመም፡፡ ጠያቂ ገደብ ተጥሎብኛል፡፡ እኔን መጠየቅ የሚችለው ቀድሞ ስም ዝርዝራቸው ለእስር ቤቱ አስተዳደር የታወቁ የቤተሰብ አባላት ብቻ ናቸው፡፡ ያም ሆኖ የቤተሰብ አባላትም ቢሆን ከምዝገባ ዝርዝሩ ውስጥ የተካተቱ ካልሆኑ መጠየቅ አይፈቀድም፡፡ በማነኛውም የስራ ሰዓት ሳይሆን ከስድስ ሰዓት እስከ ስድስት ሰዓት ተኩል ለሰላሳ ደቂቃ ብቻ ነው የምጠየቀው፡፡ ይህ ገደብ እንዲሻሻልልኝ ለፍርድ ቤት በተደጋጋሚ አቤት ብልም መሻሻል አልቻለም፡፡

Advertisement

No comments.

Leave a Reply