Hiber Radio: ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ እና አቶ ዳንኤል ሺበሺ ዛሬም አልተፈቱም፣እነአቶ ማሙሸት አማረ በማዕከላዊ ስቃይ እየተፈጸመባቸው መሆኑ ተገለጸ

አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ በቁጥጥር ስር ከዋሉት ከአራት ወራት በላይ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ዘግይቶ ክስ የቀረበባቸው ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ እና የቀድሞ የአንድነት ፓርቲ ም/የድርጅት ጉዳይ ሀላፊ የነበረው አቶ ዳንኤል ሺበሺ ትላንት ሐምሌ 10/2009 ዓ.ም በቦሌ ክፍለ ከተማ ከፍተኛ ፍ/ቤት ቀርበው ባቀረቡት የይግባኝ አቤቱታ ላይ ብይን አግኝተዋል፡፡ ፍ/ቤቱ እያንዳንዳቸው የ50 ሺህ ብር ዋስትና አቅርበው በዋስ እንዲወጡ ብይን ሰጥቷል፡፡ዋስትናውን በገንዘብ ከፍለው ለመውጣት ቤተሰብ እንቅስቃሴ እያደረገ ሲሆን ዛሬም ሒደቱ ባለማለቁ አልተፈቱም።የመቶ ሺህ ዋስ የሚሆን ባለመኖሩ የግድ ገንዘቡ መከፈል አለበት ተብሏል። የአገዛዙ ደህንነት ማረሚያ ቤት ፎቷቸውን እንዲልክም አዟል።

በውሳኔው መሰረት በዋስ ይዉጡ ቢባልም የፍርድ ቤቱ ሂደት እስኪጠናቀቅ ከአገር እንዳይወጡ እና የቀረበባቸው ክስ በዝግ ችሎት እንዲታይ ማረሚያ ቤቱም የፎቶ መረጃቸውን ለብሔራዊ ደኅንነት እንዲልክ ውሳኔ ተላልፏል፡፡

ኤልያስም ሆነ ዳንኤል የቀረበባቸው ክስ በዝግ ችሎት ሊታይ አይገባም ብለው አቤቱታ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው፡፡ ፍ/ቤቱ ይህን አቤቱታ ሳይቀበለው ቀርቶ ክሳቸው በዝግ እንዲታይ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ በአሁኑ ሰአትም በቦሌ ክፍለከተማ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት መደበኛ ክሳቸው በዝግ እየታየ ይገኛል፡፡

ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩም ሆነ አቶ ዳንኤል ሺበሺ ድንገት ከያሉበት በአገዛዙ ደህነቶች ተይዘው ከሕዳር 08/2009 ዓ.ም ጀምሮ በእስር ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡

በፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሰረት የዋስትናው ጉዳይ አልቆ ሁለቱም ይውጡ ወይ አይውጡ ከወዲሁ የሚታወቅ ነገር የለም። አቶ ዳንኤል ሺበሺ ከእነ ሀብታሙ አያሌው ጋር በሽብር የፈጠራ ክስ ሁለት ዓመት የታሰረ ሲሆን ከእስር ከወጣ በሁዋላ የዐቃቢ ህግን ይግባኝ መሰረት አድርጎ ክሱ የቀጠለበት ሲሆን አብረውት ከተከሰሱት የሀብታሙ አያሌው ክስ ሲነሳ አቶ የሺዋስ አሰፋና አብርሃ ደስታ በተመሳሳይ ክሱ ባይነሳላቸውም አቶ የሺዋስ ከዚህ ቀደም ፍርድ ቤት ሔዶ በስህተት ነው ተመለስ በመባሉ ይታወሳል። አብርሃ ደስታ ይፈለጋል ከተባለ በሁዋላ ታቢአ ሄዶ አልተፈለክም መባሉን ጽፎ አስነብቧል። ጋዜጠኛ አናኒአ ሶሪ ከእነ ኤልያስ ጋር በተመሳሳይ ቀን ታስሮ አስቀድሞ ያለ ዋስትና ከወራት በፊት ከእስር መፈታቱ አይዘነጋም።

የእነ ዳንኤል ዋስትና ያላላቀ ሲሆን መፈታታቸውን የዋስትናው ፕሮሰስ እንዳለቀ መልሰን እናሳውቃለን። የሰው ዋስትና ማቅረብ ባለመቻሉ በቤተሰብና ወዳጆቻቸው በኩል የተጠየቀውን የመቶ ሺህ ብር ዋስትና ለማቅረብ እየተሯሯጡ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያስረዳል። አስቀድሞ ዋስትናው እንዳለቀ ሆኖ የደረሰን መረጃ የተሳሳተ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የዋስትናቸውን ጉዳይ ለመጨረስ እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ዛሬ ከአዲስ አበባ ከቅርብ ምንጭ አረጋግጠናል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሁኑ ወቅት በማዕከላዊ በእስር ላይ የሚገኙት ሕጋዊው የመኢአድ ፕሬዝዳንት አቶ ማሙሸት አማረ ከፍተኛ ስቃይ እየተፈጸመባቸው እንደሚገኝ የህብር ምኝጮች ገልፀዋል። ከከጸበል ቦታ ከወንድማቸው ጋር ታፍነው ዳግም ከታሰሩ ጀምሮ በማዕከላዊ ስቃይ እየተፈጸመባቸው መሆኑ የተገጸ ሲሆን እስካሁን የትኛውም ፍርድ ቤት አልቀረቡም። የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ለገሰ ወልደሃናም በአሁኑ ወቅት በተመሳሳይ በማዕከላዊ ስቃይ እየተፈጸመበት ሲሆን እሱም ፍርድ ቤት ቀርቦ አያውቅም።

ከዚህ ቀደም በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ማሙሸት አማረ በተለያዩ ጊዜያት በፍርድ ቤት ውሳኔ በዋስ ይውጡ ቢባሉም ሳይወጡ ራሳቸው በፈለጉ ጊዜ እንደፈቷቸው አይዘነጋም። አቶ ማሙሸት አማረ ከፕ/ር አስራት ጊዜ ጀምሮ በምርጫ 97 ከቅንጅት መሪዎች አንዱ በመሆናቸው በተደጋጋሚ የታሰሩ ሲሆን በምርጫ 2007 ዋዜማ ግንቦት 4 ከመንገድ ታፍነው ታስረው በሊቢያ በአይሲስ በተሰው ወገኖች ሳቢአ በቁጭት መስቀል አደባባይ ሰልፍ የወጣው ሕዝብ ቁጣውን በመግለጹ በሀሰት ሰልፉን አስተባብረዋል በሚል ተከሰው በአገዛዙ ደህነቶች በፍርድ ቤት ቢመሰከርባቸውም ሚያዚያ 14 ቀን 2007 ሰልፉ በተደረገት ቀን እሳቸው ምርቻ ቦርድን ከሰው ፍርድ ቤት በክርክር ላይ መሆናቸውን በፍርድ ቤት በማጻፋቸው በዋስ ይውጡ ከተባለ በሁዋላ ዋስትናው ሳይከበር ረጅም ጊዜ መታሰራቸው አይዘነጋም።ከእስር ሲወጡም ተመልሰው ወደተቃውኦ ቢገቡ እንደሚገድሏቸው ዝተው እንደነበር ከእስር በሁዋላ ለህብር ሬዲዮ በሰጡት ቃለ መጠይቅ መግለጻቸው አይዘነጋም በወቅቱም እስክሞት የጀመርኩትን ሰላማዊ ትግል እስከሚገድሉኝ እቀጥላለሁ ፈርቼ ትግሉን አላቆምም ማለታቸው ይታወሳል።

Hiber radio Las Vegas ይህ ህብር ሬድዮ _የወቅታዊ መረጃ ምንጭ ነው። ህብር ሬድዮ በአቤኔዘር ኮሙኒኬሽን ሴንተር እየተዘጋጀ  ከላስ ቬጋስ ከተማ፣ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 630 ሰዓት እስከ 8 ሰዓት በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ 5639993994 ወይም 563999-3988 ወይም 712-432-8451 በመረጡት ቁጥር መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ 01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

 

Advertisement

No comments.

Leave a Reply