Hiber Radio: በማዕከላዊ በስቃይ ላይ የቆዩት የመኢአድ ሕጋዊው ፕ/ት አቶ ማሙሸት አማረ የሽብር ክስ ተመሰረተባቸው፣ዶ/ር መረራን በካቴና አስሮ ፍርድ ቤት ያቀረበው አገዛዝ ሕዝቡን ለማዋረድ መሆኑ ተገለጸ

የመኢአድ ሕጋዊው ፕሬዝዳንት አቶ ማሙሸት አማረ ድንገት በአገዛዙ ደህነቶች ከጸበል ቦታ ከወንድማቸው ጋር ታፍነው ለወራት በማዕከላዊ ከቆዩበት ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ ሐምሌ 25 ቀን 2009 ፍርድ ቤት ቀርበው የተለመደው ሀሰተና የሽብር ክስ ተመስርቶባቸዋል።በሌላ በኩል የሕወሃት አገዛዝ ዶ/ር መረራ ጉዲናን ፍርድ ቤት በካቴና አስሮ ማቅረቡ እሳቸውን ሳይሆን ነጻነት አልባውን ሕዝብ ጭምር ለማዋረድ ታስቦ የተደረገ መሆኑ ተገለጸ።

የአቶ ማሙሰትን የፍርድ ቤት ውሎ ጠቅሶ የዘገበው ጋዜጠና ጌታቸው ሽፈራው ተከታዩን ዘገባ አስነብቧል።

(በጌታቸው ሺፈራው)

የቀድሞው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዝደንት አቶ ማሙሸት አማረ ዛሬ ሀምሌ 25/2009 ዓ.ም የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን ቁጥር 652/ 2001 አንቀፅ 4 ስር የተደነገገውን ተላልፈዋል በሚል በማሴር፣ መዘጋጀትና ማቀድ የሽብር ክስ ተመሰርቶባቸዋል፡፡

አቶ ማሙሸት አማረ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ተነስቶ የነበረውን ህዝባዊ እምብይተኝነት በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል እንዲስፋፋ አባላትን በመመልመል፣ ሀገር ውስጥና ውጭ ሀገር ከሚገኙ ግለሰቦች ጋር ግንኙነት በመፍጠር፣ በጎጃምና ጎንደር የነበረውን እንቅስቃሴ በማቀናጀት በመምራት ተንቀሳቅሰዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለግንቦት ሰባት አባላትን መልምሎ ወደ ኤርትራ በመላክ፣ መንግስትን በትጥቅ ትግል ለመጣል በሰሜን ሸዋ ወታደራዊ ማሰልጠኛ በመመስረት፣ አባላትን በማሰልጠንና በማስታጠቅ ተንቀሳቅሰዋል የሚል ዝርዝር ክስ ቀርቧል፡፡

አቶ ማሙሸት አማረ ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም መንግስት አይ ኤስን ለማውገዝ በጠራው ሰልፍ ላይ ሰልፈኛው በኢህአዴግ ላይ ተቃውሞ ማሰማቱን ተከትሎ በተቃውሞው ተሳትፈሃል ተብለው ለእስር ተዳርገው የነበር ሲሆን ሰልፉ በተደረገበት ቀንና ሰዓት ከምርጫ ቦርድ ጋር በነበራቸው ክርክር ሰልፉ ላይ አለመገኘታቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ከምርጫ ቦርድ በማቅረባቸው በነፃ እንዲለቀቁ በፍርድ ቤት ቢወስንም፣ ከፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ውጭ ለተጨማሪ ቀናት ታስረው ከቆዩ በኋላ ሌላ ክስ ቀርቦባቸው እንደነበር ይታወል፡፡

አቃቤ ህግ ሚያዝያ 14 ሰልፍ ላይ እንደተገኙ ላቀረበው ክስ በዚሁ ቀንና ሰዓት ከምርጫ ቦርድ ጋር ክርክር ላይ እንደነበሩ ማስረጃ በመቅረቡ ሚያዝያ 13 ህዝብን አነሳስተው ለሚያዝያ 14 በመንግስት ላይ ተቃውሞ እንዲያሰማ አድርገዋል በሚል ሌላ ክስ ተመስርቶባቸው እና አራት ግለሰቦች መስክረውባቸው በድጋሜ በፍርድ ቤት በነፃ ተለቀዋል፡፡ አቶ ማሙሸት ባለፉት 26 አመታት ከ10 ጊዜ በላይ ለእስር እንደተዳረጉ ተገልጾአል፡፡ አቶ ማሙሸት የክስ መቃወሚያ ለማቅረብ ለነሃሴ 1/2009 ዓ.ም ተቀጥረዋል፡፡

ይህ በእንዲህ  እንዳለ በአሁኑ ወቅት በማዕከላዊ በእስር ላይ የሚገኙት ሕጋዊው የመኢአድ ፕሬዝዳንት አቶ ማሙሸት አማረ ከፍተኛ ስቃይ እየተፈጸመባቸው እንደሚገኝ የህብር ምኝጮች ገልፀዋል። ከከጸበል ቦታ ከወንድማቸው ጋር ታፍነው ዳግም ከታሰሩ ጀምሮ በማዕከላዊ ስቃይ እየተፈጸመባቸው መሆኑ የተገጸ ሲሆን እስካሁን የትኛውም ፍርድ ቤት አልቀረቡም። የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ለገሰ ወልደሃናም በአሁኑ ወቅት በተመሳሳይ በማዕከላዊ ስቃይ እየተፈጸመበት ሲሆን እሱም ፍርድ ቤት ቀርቦ አያውቅም።

ከዚህ ቀደም በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ማሙሸት አማረ በተለያዩ ጊዜያት በፍርድ ቤት ውሳኔ በዋስ ይውጡ ቢባሉም ሳይወጡ ራሳቸው በፈለጉ ጊዜ እንደፈቷቸው አይዘነጋም። አቶ ማሙሸት አማረ ከፕ/ር አስራት ጊዜ ጀምሮ በምርጫ 97 ከቅንጅት መሪዎች አንዱ በመሆናቸው በተደጋጋሚ የታሰሩ ሲሆን በምርጫ 2007 ዋዜማ ግንቦት 4 ከመንገድ ታፍነው ታስረው በሊቢያ በአይሲስ በተሰው ወገኖች  ሳቢአ በቁጭት መስቀል አደባባይ ሰልፍ የወጣው ሕዝብ ቁጣውን በመግለጹ በሀሰት ሰልፉን አስተባብረዋል በሚል ተከሰው በአገዛዙ ደህነቶች በፍርድ ቤት ቢመሰከርባቸውም ሚያዚያ 14 ቀን 2007 ሰልፉ በተደረገት ቀን እሳቸው ምርቻ ቦርድን ከሰው ፍርድ ቤት በክርክር ላይ መሆናቸውን በፍርድ ቤት በማጻፋቸው በዋስ ይውጡ ከተባለ በሁዋላ ዋስትናው ሳይከበር ረጅም ጊዜ መታሰራቸው አይዘነጋም።ከእስር ሲወጡም ተመልሰው ወደተቃውኦ ቢገቡ እንደሚገድሏቸው ዝተው እንደነበር ከእስር በሁዋላ ለህብር ሬዲዮ በሰጡት ቃለ መጠይቅ መግለጻቸው አይዘነጋም በወቅቱም እስክሞት የጀመርኩትን ሰላማዊ ትግል እስከሚገድሉኝ እቀጥላለሁ ፈርቼ ትግሉን አላቆምም ማለታቸው ይታወሳል።

በተያየዘ ዜና በዛሬው ዕለት በካቴና ታስረው ፍርድ ቤት የቀረቡት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና የትም እንደማያመልጡ እየታወቀ እሳቸውን ለማዋረድ በማሰብ እጃቸውን በካቴና አስረው ፍርድ ቤት ያቀረቧቸው ነጻነት አልባውን እየተረገጠ ዝም ብሎ የተገዛውን ሕዝብ ጭምር ለማዋረድ ማሰብ መሆኑን የአምቦ ዩኒቨርስቲ መምህሩ ስዩም ተሾመ በገጹ ላይ ገለጸ።

ጦማሪና የዩኒቨርስቲ መምህሩ ስዩም ተሾመ አያይዞም << እንደ ነፍሰ ገዳይ እጆቹ ወደኋላ የተጠፈሩት ዶ/ር መረራ ከመሰላችህ ተሳስታችኋል፡፡ እንደ አሸባሪ የጦር መሣሪያ የተደገነበት እሱ እንዳይመስላችሁ፡፡ እንዲህ የተጎሳቆለው እስረኛ ዶ/ር #መረራ_ጉዲና አይደለም!!! የታሰረው፤ የእኛ ነፃነት ነው! የእኛ እኩልነት ነው! የእኛ ፍትህ ነው! አዎ… እስረኞቹ እኛ ነን! አንደበታችን በፍርሃት ተለጉሞ ለጨቋኙ ስርዓት ብርታት ሆነን፣ ሕሊናችን በጥቅም ሱስ ታውሮ ለጭቆና መሣሪያ የሆነው እኛ ነን፡፡>> ሲል በዶ/ር መረራ ጉዲና ላይ የተወሰደውን የስርኣቱን አሳፋሪ እርምጃ አውግዟል።

<<ዶ/ር መረራ ስለ ሁላችንም ነፃነት፥ እኩልነትና ፍትህ ጥብቅና የቆመ ሰው ለእስራትና እንግልት ሲዳረግ አይተን እንዳላየ፣ ሰምተን እንዳልሰማ የሆነው እኛ ነን! ከነፃነት ይልቅ ፍርሃት ተጫነን፣ ከእኩልነት ይልቅ አገልጋይነት ተሻለን፣ ከፍትህ ይልቅ በደልን ተቀበልን፣… አዎ ዶ/ር መረራን ያሰርነው እኛ ነን፡፡ የታሰርነውም እኛ ነን! ጀግና ሰው ግን መቼም አይታሰርም፡፡ ዶ/ር መረራ ታጋይ እንጂ እስረኛ አይደለም! ጀግና ሰው እንኳን እስር ቤት ውስጥ #መቃብር ውስጥ ሆኖም ለቆመለት ዓላማ በጀግንነት ይታገላል (ያልኩት ካልገባህ “ጄ/ል #ታደሰ_ብሩ የት ነው ያለው?” ብለህ ጠይቅ)>> ሲል ሁኔታውን በምሬት ገልጿል።

Hiber radio Las Vegas ይህ ህብር ሬድዮ _የወቅታዊ መረጃ ምንጭ ነው። ህብር ሬድዮ በአቤኔዘር ኮሙኒኬሽን ሴንተር እየተዘጋጀ  ከላስ ቬጋስ ከተማ፣ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 630 ሰዓት እስከ 8 ሰዓት በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ 5639993994 ወይም 563999-3988 ወይም 712-432-8451 በመረጡት ቁጥር መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ 01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

 

Advertisement

No comments.

Leave a Reply