Hiber radio : በኢትዮጵያ በሊቢያ አሸባሪው አይ.ሲ.ስ በወገኖቻቸው ላይ ያደረሰውን ግፍ የተቃወሙ ዜጎች ዛሬም በእስር እየማቀቁ ነው፣ አቶ አለነ ማህፀንቱ ከእስር ሊለቀቅ አልቻለም

 የአይ.ሲ.ስ በወገኖቻችን ላይ ግፍ ሊፈጽም አፍኖ ሲወስዳቸው እና በኢትዮጵያ በእስር ላይ የሚገኘው አቶ አለነ ማህጸንቱ
የአይ.ሲ.ስ በወገኖቻችን ላይ ግፍ ሊፈጽም አፍኖ ሲወስዳቸው እና በኢትዮጵያ በእስር ላይ የሚገኘው አቶ አለነ ማህጸንቱ

በሊቢያ አሸባሪው አይ.ሲ.ስ በንጹሃን ኢትዮጵያውያን ላይ የተወሰደውን የግፍ እርምጃ በአገር ቤት ያለው የህወሃት ኢህአዴግ አገዛዝ የሞቱትን ኢትዮጵያውያን ማንነት አላውቅም ማለቱ ያስቆታው ሕዝብ አደባባይ ወጥቶ በአገር ቤት በስርዓቱ የሚፈጸመውን ግፍና የስርዓቱ ጡንቻ ዜጎችን ለማሰቃየት ብቻ መዋሉን ለማሳየት <<የውስጥ አንበሳ የውጭ ሬሳ>> ብሎ በታላቅ የአደባባይ ተቃውሞውን ያለ አንድ ቀስቃሽ ማሰማቱን ተከትሎ ለደረሰው ተቃውሞ የተቃዋሚ አመራር አባላትን፣በወቅቱ በጅምላ የታፈሱ በሺህ የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ከተማ ወታቶችን በልዩ ልዩ እስር ቤት እያሰቃየ፣በፈጠራ አመጽ ልታነሳሱ ነበር በሚል አንዳንዶቹን ባልነበሩበት እየከሰሰ እያሰቃየ ሲሆን አልፎ አልፎ ሁኔታውን የተረዱ አንዳንድ ዳኞች መጫወቻ ከሆነው የስርዓቱ ፍርድ ቤት ተጽዕኖ በማፈንገጥ ሕጉን ተግባራዊ አድርገው ይፈቱ የሚል ውሳኔም ሲሰጡ እንደማይከበር የህብር ምንጮች ገልጸዋል።

ሰሞኑን የአይሲስን ተቃውሞ ተከትሎ ‹‹ስብሰባን በማወክ›› ወንጀል ተከሶ ላለፉት 5 ወራት ክሱን ሲከታተል የነበረው፤ የቀድሞ አንድነት ፓርቲ ማህበራዊ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አለነ ማህፀንቱ ዳኛ በሰጠው ውሳኔ ከእስር ሊለቀቅ እንዳልቻለ ባለቤቱ ወይዘሮ ሠርካለም ገለፀች፡፡

ከትላንት በስቲያ የአራዳ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት 5ኛ ወንጀል ችሎት፤ አቶ አለነ የቀረበበትን ክስ በአግባቡ ስለተከላከለ በነፃ እንዲሰናበት ብይን ቢያስተላልፍም፤ ተከሳሹ ከሚገኝበት የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት እስካሁን ድረስከ እስር ሊለቀቅ እንዳልቻለ ታውቋል፡፡ አቶ አለነ ከእስር ያልተለቀቀበትን ምክንያት በሚመለከት ባለቤቱ መግለጹዋን ዘገባዎች ጠቅሰዋል ።በዚህም ሰባራ ባቡር ከሚገኘው ከፍተኛ ፍርድቤት መዝገብ ቤት በኩል በሌላ ወንጀል ማለትም ‹‹ሁከትን በመፍጠር ወንጀል ስለተከሰሰና ይህም መዝገብ ስላልተዘጋ ከእስር ሊለቀቅ እንደማይችል›› እንደተገለፀላት አስረድታለች፡፡ አቶ አለነ ሠባራ ባቡር በሚገኘው ከፍተኛ ፍ/ቤት የቀረበው፤ አቃቤ ሕግ የአራዳ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ለተከሳሹ የሰጠውን የዋስትና መብት በማስመልከት ይግባኝ በመጠየቁ እንደነበር ባለቤቱ ወ/ሮ ሠርካለም አውስታለች፡፡ በወቅቱም ከፍተኛ ፍርድቤቱ የተከሳሹን የዋስትና መብት በሚመለከት የዋስትናው መብቱ ታግዶ፤ ክሱን በማረሚያ ቤት ሆኖ እንዲከተታል የሚል ብይን ማስተላለፉ ይታወሳል፡፡

አቶ አለነ ማህፀንቱ በተከሰሰበት ‹‹ስብሰባን በማወክ ወንጀል›› የአራዳ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የሰጠውን የዋስትና መብት ሰባራ ባቡር የሚገኘው ከፍተኛ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ችሎት፤ የአራዳ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ውሳኔን በመሻር፤የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡ ይህን ውሳኔ ተከትሎ አቶ አለነ ለጠቅላይ ፍ/ቤት አቤታውን ቢያሰማም፤ ጠቅላይ ፍ/ቤት የሥር ፍ/ቤቱ ውሳኔ እንዲፀና በሚል ጥቅምት 17 ቀን 2008 ዓ.ም ብይን ማስተላለፉይታወሳል፡፡የሥር ፍ/ቤቱ ውሳኔ በመፅናቱ የተነሳም አቶ አለነ የዋስትና መብቱ ታግዶ፣ ክሱን ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሆኖ ሲከታተል እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስም አቶ አለነ ማህፀንቱ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በተመሳሳይ የፈጠራ ክስ በእስር ላይ የሚገኙትና በ2001 ዓ.ም የወጣውን የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀፅ 7/1/ ስር የተመለከተውን በመተላለፍ፤ የሚል ክስ በፌደራል አቃቤ ሕግ በኩል የቀረበባቸው፣ 1ኛ ተከሳሽ መሳይትኩና 2ኛ ተከሳሽ ሰጠኝ ሙሉ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጣቸው፡፡

ልደታ በሚገኘው ከፍተኛ ፍ/ቤት ተዘዋዋሪ ችሎት የአቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለማድመጥ ቀጠሮ ተሰጥቷቸው የነበሩት መሳይ ትኩና ሰጠኝ ሙሉ ምስክሮቻቸውን ሳያሰሙ ለ5ኛ ጊዜ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ይህን በማስመልከት 1ኛ ተከሳሽ መሳይ ትኩ፣ ለፍ/ቤቱ አቤቱታውን አሰምቷል፡፡ ‹‹የተከበረው ፍ/ቤት እኛም ሃሳብ አለን››በሚል በስሜት ተውጦ የተናገረው መሳይ፣ ከጥቅምት 16 ቀን ጀምሮ ምስክሮችን ለማድመጥ ተደጋጋሚ ቀጠሮ እየተሰጣቸው እንደሚገኝ፣እስካሁን ድረስም ምስክሮች ባለመደመጣቸው የተነሳ ከክፍለ ሀገር የሚመጡት ቤተሰቦቻቸው ላይ እንግልት እየደረሰ እንደሚገኝ አስረድቷል፡፡ በዕለቱ በችሎቱ የተሰየሙት ዳኛ ምስክሮች ተሟልተው እስኪቀርቡ ድረስ መታገስ እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡ ‹‹በእኔ ላይ አቃቤ ሕግ ሊያሰማው ያዘጋጀው ምስክር በፍ/ቤት ውስጥ አይቼዋለሁ›› በማለት ለችሎቱ ያስረዳው መሳይ፣ ምስክሩ እንዲደመጥልኝ ሲል ፍ/ቤቱን ጠይቋል፡፡ አቃቤ ሕግ በበኩሉ ‹‹ምስክሩ አልቀረበም›› በማለት ለፍ/ቤቱ ሲናገር ተደምጧል፡፡ ፍ/ቤቱ አቃቤ ሕግ ምስክሮቹን አሟልቶ እንዲያቀርብና ምስክሮቹን ለማድመጥም ተለዋጭቀጠሮ ለህዳር 14 ቀን 2008 ዓ.ም ሰጥቷል፡፡

አቃቤ ሕግ በመሳይ ትኩ ላይ አንድ ምስክር ያዘጋጀ ሲሆን፤ በሁለተኛ ተከሳሽ ሰጠኝ ሙሉ ላይ ደግሞ ሁለት የደረጃ ምስክሮችን እንዳዘጋጀ ለመረዳት ተችሏል፡፡ አቶ መሳይም ሆነ አቶሰጠኝ ከየካቲት 22 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡

በሌላ ዜና፣‹‹ስብሰባንበማወክ›› ወንጀል ተከሶ ላለፉት 6 ወራት ክሱን በማረሚያ ቤት ሆኖ እየተከታተለ የሚገኘው፤የቀድሞ አንድነት ፓርቲ አባል ወጣት እስማኤል ዳውድ፣ በትላንትናው እለት መከላከያ ምስክሮቹን አሰምቷል፡፡ እስማኤል፣ የቀረበበትን ክስ በሚመለከት ለመከላከል ይረዱኛል ብሎ ያሰባቸውን ሁለት ምስክሮች ያስደመጠ ሲሆን፤ ፍ/ቤቱ ብይን ለመስጠት ለህዳር 7 ቀን 2008 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ መንግስት አይኤስን ለማውገዝ በጠራው ሰልፍ ላይ በመገኘት ‹‹ስብሰባንአውከሃል›› የሚል ክስየቀረበበት እስማኤል፣ ከሚያዚያ 20 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ በእስር ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

የመኢአድ ሕጋዊው ፕሬዝዳንት አቶ ማሙሸት አማረ በተመሳሳይ የፈጠራ ክስ በሰልፉ ቀን ምርቻ ቦርድን ከሰው ፍርድ ቤት ክርክር ላይ እአሉ አገዛዙ ዐቃቤ ሕግ ሰልፉ ላይ ተገኝተው ብጥብጥ አስነስተዋል ብሎ ደህነቶችን ያስመሰከረ ሲሆን በማስረጃ ውድቅ ሲያደርጉ ዳኛ በነጻ ይፈቱ ሲል ሳይፈቱ ከእስር ቤት እስር ቤት ከአንዱ ፍርድ ቤት ሌላው ሲመላለሱ ቆይተው ከአራት ወራት በላይ ታስረው በነጸ የተለቀቁ ሲሆን ከተለቀቁ በሁዋላ በደህነቶች ክትትል እንደሚደረግባቸው እና በእስር ቤትም እአሉ ወጥተህ ፖለቲካ ውስጥ ብትሳተፍ እንገድልሃለን እንዳሏቸው ለህብር ሬዲዮ በሰጡት ቃል ገልጸው እስክሞት ድረስ ሰላማዊ ትግሌን እቀጥላለሁ ማለታቸው አይዘነጋም። አቶ ማሙሰት አማራ በቅርቡ በመኢአድ ደጋፊዎች በሰሜን አሜሪካ ስብሰባ ለማድረግ ተጠርተው በአዲስ አበባ የሚገነው የአሜሪካ ኤምባሲ ቪዛ እንደከለከላቸው መዘገባችን ይታወሳል።

የህብር ሬዲዮን ዘገባ ህብር ሬዲዮን ከድህረ ገጻችን በተጨማሪ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 እና በአውስትራሊያ 0280725172 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን ወይም ከgoogel store Hiber radio አፕሊኬሽንን ዳውን ሎድ በማድረግና  ከዘሐበሻም ማዳመጥ ይቻላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *