ሦስት የሰማያዊ አባላትን ጨምሮ በዓለም ላይ የተመረጡ 20 ሴት የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ዘመቻ ሊጀመር ነው

Semayawi-womens_poltical_prisoners_02

  • ሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች የአንድ ወር ዘመቻ ያደርጉላቸዋል

በአሜሪካ መንግስት ኦፊሳላዊ ድረ ገጽ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ አስተባባሪነት በዓለም ላይ ለተመረጡ 20 ሴት የፖለቲካ እስረኞች ለአንድ ወር የሚቆይ ዘመቻና ማስታወሻ ሊደረግላቸው ነው፡፡ ከ20ዎቹ ሴት የፖለቲካ እስረኞች መካከል ሦስቱ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፣ ሁሉም የሰማያዊ ፓርቲ አባላት መሆናቸውን ነገረ ኢትዮጵያ ዘገበ። ከዛሬ 20 አመት በፊት ሴቶችን ለማብቃት፣ የጾታ እኩልነትን ለማስፈን እና የልጃ ገረዶችን ሰብዓዊ መብት ለማስጠበቅ የቤጂንግ መርሃ ጉዞ ተቀምጦ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በእነዚህ 20 አመታት ልክ ከዓለም ሀገራት በፖለቲካ እስረኝነታቸው የተመረጡ 20 ሴት እስረኞችን ለማሰብ የሚደረገው ዘመቻ መነሻው ይህ መርሃ ጉዞ ነው፡፡ በዚህ መሰረት ከኢትዮጵያ ብሌን መስፍን፣ ንግስት ወንዲፍራው እና ሜሮን አለማየሁ የተካተቱ ሲሆን ከቻይና እንዲሁ ሦስት ሴት የፖለቲካ እስረኞች ተመርጠው ይታወሳሉ፡፡ ከብዙ ሴት የፖለቲካ እስረኞች መካከል እነዚህ ጥቂቶች መሆናቸውን የጠቀሰው ድረ ገጹ በመስከረም ወር ‹‹ሴቶችን አብቋቸው፣ አትሰሯቸው!›› በሚል መርህ ዘመቻው ይደረጋል፡፡ በዚህም መንግስታት ሴቶችን በፖለቲካ አመለካከታቸው ማሰር አቁመው ማብቃት ላይ እንዲያተኩሩ መልዕክት ይተላለፍበታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ዘመቻው ለታሳሪ ቤተሰቦችና ለራሳቸው ለታሳሪዎች ብቻቸውን እንዳልሆኑና እንዳልተዘነጉ ለማሳየት ታስቦ እንደሚካሄድ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ የሰጡት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፣ በኢትዮጵያ ሦስት ሴት የፖለቲካ እስረኞች በዚህ ደረጃ መጠቀሳቸው በሀገራችን ያለውን ስርዓት ዓለም እንደተረዳውና ኢትዮጵያ በመጥፎ እንድትነሳ እያደረጋት መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡ ዘመቻው እንዲደረግላቸው ከተመረጡት መካከል ከኢትዮጵያና ቻይና ሶስት ሶስት፣ ከቬትናም፣ አዘርባጃንና በርማ ሁለት ሁለት እንዲሁም ከኢራን፣ ግብፅ፣ ኤርትራ፣ ኡዝቤኪስታን፣ ቬንዞዌላ፣ ሶሪያ፣ ሩሲያ/ዩክሬንና ሰሜን ኮሪያ አንድ አንድ ሴት የህሊና እስረኞች ናቸው ሲል ይሄው የነገረ ኢትዮጵአ ዘገባ ያስረዳል።

የህብር ሬዲዮን ዘገባ ህብር ሬዲዮን ከድህረ ገጻችን በተጨማሪ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን ወይም ከgoogel store Hiber radio አፕሊኬሽንን ዳውን ሎድ በማድረግና  ከዘሐበሻም ማዳመጥ ይቻላል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *