የሕወሓት የሰሞኑ ሙሽራ ሞላ ማንነት ሲጋለጥ ! ሳይደፈርስ አይጠራም – ሳይጨልም አይነጋም

Molla_first_araival_second_drama_etv_02

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ የተለመዱ ከሆኑ ክስተቶች አንዱ ከአንዱ ጎራ ወደ ሌላው ጎራ ዘለው የሚገቡ ወይ ቶሎ ኮፍያቸውን የሚቀይሩ ሰዎችን ብዙ በስም መዘርዘር ይቻላል። የሰሞኑ የህወሓት <<ሙሽራ>> ሞላ አስገዶም ከነዚህ አንዱ ሆነው ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው።የኢህአፓና መኢሶንን ታሪክ ማንሳት ይቻላል። መኢሶን ደርግ ጉያ ተጠግቶ የትግል አጋሩን ኢህአፓን አስበልቶ መጨረሻ የደርግ ራት ከመሆን አልዳነም። ከራሱም ከኢህአፓ ዛሬም ድረስ ታሪክ የሚዘክራቸው ደርግን በአደባባይ ፋሺስት ብለው ከመታገል አልፈው በደርግ ስርም ወድቀው ለዓላማቸው ጽናት ቆመው ደርግ ላይ ተሳልቀው ጓዶቻቸውን ሳያስነኩ በክብር የተሰው እልፍ ናቸው። ከኢህአፓው ጋር ኢህአፓ ሆነው ለደርግ ተሸንፈው ጓዶቻቸውን አስበልተው የተበሉም ሆነ ዛሬም ድረስ በሕይወት ያሉ ጥቂቶች ይኖራሉ። ከህወሃት ወደ ደርግ ከደርግ ወደ ህወሓትና ሻዕቢያ ሲገቡና ሲወጡ የነበሩትን መዘርዘር ይቻላል። ምርቻ 97 እንኳ ብናነሳ በኢትዮጵአ የተቃውሞ ጎራ የነበሩ በአንዴ ታጥፈው ሌሊት ሌሊት ከህወሃት ጋር እአደሩ ቀን የተሰጣቸውን ሴራ ለመፈጸም ተንቀሳቅሰው ሕዝብ የተፋቸውን ተቃዋሚ ተብዬዎች ማንሳት ይበቃል። የሰሞኑ የሞላ ክዳት ትላንት ከኦብነግ፣ከኦነግ ከአርበኞች ግንባር ከዱ ከተባሉት የተሌ አይደለም። የተሌ የሆነው ምን አልባት ዶ/ር ብርሃኑ ኤርትራ ከገቡ በሁዋላ ስርኣቱ የነበረበትን ትልቅ ስጋት የሞላ ክዳትን ተጠቅሞ <<ተስፋ አስቆርጣለሁ>> ብሎ ያሰበ ይመስላል። ሞላን አስመልክቶ አዲስ ሊባል የሚችል ገበና በዘርዓይ ደረስ ደበሳይ ተጽፏል። ተከትሎ ቀርቧል።

ሳይደፈርስ አይጠራም –   ሳይጨልም አይነጋም

ሰላዮችን ራሳቸው በራሳቸው በመጋለጣቸው የነፃነት ትግሉን የበለጠ ይጠነክራል ይጠራል እንጂ ፍፁም አይቆምም::

ከዘርኣይ ደረስ ደበሳይ

ሞላ አስገዶም የወያኔ ተላላኪና ሰላይ ሆኖ ትግሉን የማኰላሸት ስራ የሚሰራ ብቻ ሳይሆን ከውጭ ሀገር ደላሎች ጋር በመመሳጠር የኩላሊት ነጋዴም በመሆን የትግራይ ለጋ ወጣቶችን እየመለመለ ወደ ዓረብ ሀገሮችን በመሸጥ በትግራይ ህዝብ ደም ሲነግድ የነበረ ደለላም ጭምር እንደነበር የታመኑ ምንጮች ይገልፃሉ:: ዛሬ በህፃናቱ ደም የሰበሰበውን በሚሊዮን የሚገመት ገንዘብ ይዞ ተመልሶ ወደ ኢትዮጵያ ቢገባ የሚያስገርም አይሆንም:: የሚያስገርመው ግን በአንድ በኩል ከወያኔ መንግስት የሚያገኘው ገንዘብ በሌላ በኩል ደግሞ ለአንድ ወጣት ትግራዋይ ከሶስት እስከ አምስት ሽሕ ዶላር ወደ ውጭ እየቸበቸበ የሚያገኘው ገቢ እንዲሁም የነፃነት ታጋይ ነኝ በሚል ሽፋኝ ከኤርትራ መንግስትና ከሌሎች ታጋይ ሀይሎች ይደረግለት የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ ተደማምሮ ሲታይ ይህን ሁሉ ቴክኒክ ለማቀነባበር የተጠቀመበት ስልትና ስትራተጂ አስገራሚ ነው:: የሚያሳዝነው ደግሞ በማያውቁት ጉዳይ ላይ የእሳት ራት ሆነው የቀሩ የትግራይ ወጣቶችን ነው:: ትግራይ እንደነ አሉላ አባ ነጋና ሐየሎም አርአያ የመሳሰሉትን የነፃነት አንበሶች እንዳልወለደች ሁሉ ዛሬ የጥቂት ደላሎችና ካሃዲዎች መፈልፊያና መናሃሪያ በመሆን ” የሰው ልጅ እንደ ከብት በቁሙ የሚሸጥባት የሲኦል ምድር ሆና ሳያት እጅግም ያሳዝነኛል:: ይዘገንነኛልም::

ታሪክ ራሱ ይደግማል እንዲሉ ቀደም ሲል ወያኔ በትጥቅ ትግሉ ዘመን ይጠቀምበት የነበረውን በትግራይ ህዝብ ደም ንግድ ዛሬም በደምሒት በነ ሞላ አስገዶም መደገሙ ሌላው በህዝባችን ላይ የተፈፀመ ጥቁር ታሪክ ነው:: (በዚሁ የሞላ አስገዶም የኩላሊትና የወጣቶች ንግድ በሚመለከት ሌላ ጊዜ በሰፊው ለማቅረብ እሞክራለሁ) ለዛሬው ግን ወደ ተነሳሁበት ርእስ ጉዳይ ልመለስ::

ሰሞኑን የህወሓት ሰላይ በመሆን በትግራይ ለጋ ወጣቶች ላይ የፓለቲካ ቁማር ሲጫወት የቆየው ሞላ አስገዶም የተወሰኑ የደምሒት አባላት ይዞ ከትግል ሜዳ አፈንግጦ ኰበለለ የሚል ዜና ግራና ቀኙን ሲናፈስና የተለያዩ ሰዎች በዘፈቀደ የየራሳቸውን ትርጉም በመስጠት ሲናገሩና ሲፅፉ ሰንብቷል:: ወሬው አሁንም በሰፊው በመዛመት ላይ ይገኛል:: የህወሓት መንግስትም በጉዳይ ላይ ቀጥተኛ እጅ እንዳለበት ባወጣው ይፋዊ መግለጫ አስታውቋል:: አዎ “መቆየት ደጉ ብዙ አሳየን” እንደ ተባለው ሁሉ ዕድሜ የሰጠው ሰዉ ገና ብዙ አዳዲስ የትግል ሁኔታዎችንንና ክስተቶችን ያያል::

ቀደም ሲል ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ከሌሎች ጓዶቹ ጋር በመሆን ወደ ኤርትራ ወደ ትግል ሜዳ ገባ የሚል ዜና እንደሰማሁ በአእምሮዬ ውስጥ “አለ ነገር” የሚል ስሜት ተቀላቀለብኝ:: ይህን ያልኩበት ምክንያትም በኢትዮያ አቆጣጠር በ97 በተደረገው የምርጫ ቅስቀሳና የምረጡኝ ክርክር የዶክተር ብርሃኑ ተሳትፎ ምን ያህል የኢትዮያ የፓለቲካ ድባብ እንደቀየረውና የመለስ ዜናዊ መንግስትን ከስረ መሰረቱ እንዴት እንዳናጋው ዓቅሙም ! እውቀቱም ” የፓለቲካ ብስለቱም በተግባር ስላየሁት እጅግ ከማደንቃቸው የኢትዮያ የቀውጥ ቀን ልጆች አንዱ ነው:: ዛሬ እንደገና እነ ዶክተር ብርሃኑ ይህን ሁሉ ፈተና አልፈው ወደ ትግል ሜዳው እንዲቀላቀሉ ያደረጋቸው በስተጀርባቸው ያለው ሚስጢራዊ ሀይል ምንድን ነው? ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው መልስ የአላማ ፅናት ” የሀገርና የወገን ፍቅር ” የነፃነትና የፍትሕ ጥማት” የአባቶቻችን ያልገዛም ባይነት ወኔና የሰማእታቱን አደራ ናቸው ብዬ አምናለሁ:: በአጠቃላይ “ነፃነት ወይም ሞት” የሚል የአባቶቻችን የቃል ኪዳን አሻራ አንግበው ወደ ላቀ የትግል ሜዳ መሄዳቸው ስሰማ ምናልባት የሚከተሉትን የትግል ሁኔታዎች መልክ ሊይዙና መልስ ሊያገኙ ይችላሉ የሚል ብሩህ ተስፋና እምነት አድሮብኛል::   1. የሀገራችን ምስቅልቅል የፓለቲካ ገፀ ባህርይ ፈር የሚያስይዝ ብቻ ሳይሆን የአፍሪቃ ቀንድ ታጋዮችን የሚያስተሳስር ብሩህ የትግል ጎዳና ይፈነጥቃል ” ሚሊዮኖችን ከእንቅልፍ ይቀሰቅሳል ” እንክርዳዱን ከምርቱ አንጓልሎ አንጓልሎ ይለያል ” መስመሩን አስተካክሎ ፋኖ ወደ ሀገሩ ያመራል የሚል ወለል ብሎ እንዲታየኝ አድርጎኛል::     2. እስካሁን ድረስ በትጥቅ ትግሉ ሜዳ አሉት የሚባሉትን የፓለቲካ ድርጅቶችና የተለያዩ የብሄር ብሄረሰቦች የነፃነት ታጋዮች ነን የሚሉ አንዳንድ ሀይሎች ኤርትራን መታገያ ሳይሆን መጠሊያ ! ፓለቲካን ማስተባበሪያና አንድነት መፈጠሪያ ሳይሆን መተዳደሪያ አድርገውት “ላም አለችኝ በሰማይ ወተትዋን ግን አላይ” ሆነው ቆይቷል:: አሁን ግን እነዶክተር ብርሃኑና ሌሎች ታጋዮች በአካል ፊት ለፊት ተቀራርበው ወደ አንድነትና ውሕደት የሚያመራ ቀጥተኛ ውይይት መጀመራቸው ትግሉን ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር እርምጃ ብቻ ሳይሆን ራሱን የቻለ አዲስ ውስጣዊ የጥራት ትግል እየተፋፋመ መሆኑን በነሞላ አስገደም በደምሒት

ላይ እየታየ ያለው ሁኔታ ያመላክታል:: የነ ዶክተር ብርሃኑ ኤርትራ መሄድ በወያኔና በነሞላ አስገደም ያለው እኩይ ተግባር እንዲጋለጥ ማድረጉ ራሱ ለትግሉ ጎራ ውድቀት ሳይሆን ትልቅ ድል ነው ብዬ አምናለሁ:: ሳይደፈርስ አይጠራምና ነው::   3. በኤርትራና በኢትዮያ መካከል ያለው የተዘበራረቀና የደፈረሰ ጉዳይ የኢትዮያ ህዝብ ትክክለኛ መረጃ እንዳያገኝ ” አንዳንድ ወሬ አቀባባዮች እንደፈለጉ የሚመነዙሩበትና የሚያደናግሩበት ስለሆነ ለህዝቡ ሕቡእ ወይም ሚስጢር ሆኖ ቆይቷል:: አሁን ግን ትክክለኛ መረጃ ማግኘት ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱም በሁለቱም ህዝቦች መካከል ሊኖር የሚገባው ሀቀኛና ወንድማዊ ግንኙነት እንደ ድልድይ ሆኖ ሊያገለግል የሚችል ጠንካራ ሀይል ሊፈጠር ይችላል የሚል እምነት አለኝ:: እንደ በፊቱ ሁለቱን ህዝቦች እርስ በርስ እያናከሱና የፓለቲካ መሳሪያ እያደረጉ ከመኖር ይልቅ ተደጋግፈው የጋራ ችግሮቻቸውን በጋራ የሚፈቱበትን ሁኔታ የሚያመቻች ሀይል ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለኝ::   4. በቅርቡ በዶክተር ብርሃኑ እንደተገለፀው በታጋይ ሀይሎች መካከል መተባበርና ወደ አንድ ሀገራዊ ራዕይ የሚያመራ የትግል ፈር መያዝ ማለት ነገ በተጨባጭ በተግባር ሊታይ የሚችል ” የኢትዮያ ህዝብ ጠላቶችን ዕድሜ የሚያሳጥር ” በአንፃሩ ደግሞ የኢትዮያ ህዝብን እንደ አንድ ቤተሰብ የሚያስተቃቅፍና የሚያሰባስብ ተስፋ ሰጪ ሀይል ሊሆን ይችላል የሚል ብሩህ ተስፋ አለኝ:: እየከሰመ ! እየሻገተና እየተፈረካከሰ በመሄድ ላይ የሚገኘው አረሜኔው የወያኔ ስርዓት የነ ዶክተር ብርሃኑ ወደ ትግል ሜዳው መቀላቀል ምን ያህል እንዳስደነገጠውና እንዳስጨነቀው ሰሞኑን ራሱ ካወጣው ይፋዊ መግለጫ መረዳት ይቻላል::

ሞላ አስገደምና ግብረ አበሮቹ ከመቅፅበት ወደ አሳዛኝና አስገራሚ  የጥፋት ድራማ እንዲገቡ ያደረጋቸው ምንድን ነው?   ሰሞኑን ተፈጠረ ስለተባለው የደምሒት መሪዎች ከትግል ሜዳው መሸሽና መኰብለል በሚመለከት የተለያዩ ስሜቶች ! ሀሳቦችና አስተያየቶች ሲሰጥ ሰንብቷል:: በተለይም የመንግስት ደጋፊዎችና ካድሬዎች ልክ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በመንግስት ቁጥጥር ስር መግባቱ እንደ ትልቅ የትጥቅ ትግሉ ውድቀት አድርገው ሲያወሩ እንደነበረ ሁሉ ዛሬም ለራሳቸው ተደናግረው ሌላውን ሲያደናግሩ ታይቷል:: ሌሎቹም በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የየራሳቸው የመሰላቸውን ሀሳብ ሲያስተጋቡ ይታያሉ::

በኔ እምነት በደምሒት ውስጥ የተፈጠረ ሁኔታ ከላይ ላዩ ሲታይ መሆን ያልነበረበት መጥፎ ዜና ቢሆንም በሌላ መልኩ ግን ከላይ ከ1 እስከ 4 የተጠቀሱትን ነጥቦች ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ቅደመ ሁኔታዎችን መስራት እንደተጀመሩ የሚያመላክት ነው:: ምክንያቱም  ወደ ፈታኝ የትግል መስመር በተሻገርክና ወደ አዲስ የትግል ምዕራፍ በገባህ ቁጥር መንጠባጠቡና በሀሳብ መለያየቱ የግድ ይላል:: የአላማ ፅናት! የፓለቲካ ብስለት ! ውስብስብ የትግል ስልትና ስትራተጂ በብቃት የመመራትና ያለመምራት የሚለካውም እንደአሁኑ ፈታኝ የትግል መድረክ ሲመጣ ነው:: ምርቱንና እንክርዳዱን የሚለው በዘሁ ነው::    ሗላቀር የፓለቲካ ባህል ዋናው የችግሮቻችን መንሲኤ አንዱ ነው:: ልዩነት ይዞ በጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ተቻችሎ አብሮ የመስራት ባህል ያልተለመደ ዱብ ዕዳ አድርጎ የመመልከት ችግር በብዙ ፓለቲከኞች የሚታይ ድክመት ነው:: በኤርትራ ያሉት የፓለቲካ ድርጅቶችም በመካከላቸው ሀገርንና ህዝብን ማእከል ያደረገ ” በመተማመንና በንቃት ላይ የተመሰረተ ነፃ ግንኙነት አዳብረው ቆይቷል ብሎ መናገር ያስቸግራል:: ዛሬ እስከ ውህደት የሚደርስ ነፃ ውይይት ሲጀመር ግን ስንቱን ሊያስደነግጥና ሊያስበረግግ እንደሚችል መገመቱ አያስቸግርም:: ይኽውና በደምሒት የተፈጠረው አንዱ አብነት ነው:: አፍንጫ ሲመታ ዓይን ያለቅሳል እንዲሉ ሞላ አስገደሞ ሲመታ የአዲስ አበባ መንግስት ተናጋ::    ሶስተኛው ችግር ለግል ጥቅምና ዝና ሲባል ሀገርንና ህዝብን መሸጥ የተለመደ ተግባር ሆኗል:: ሞላ አስገዶም የህወሓት የውስጥ ሰላይ በመሆን ትግሉን ብቻ አይደለም ለመጉዳት የሞኮረው:: ከህወሓት ጋር በመመሳጠር የትግራይ ለጋ ወጣቶችን በነፃ አውጪነት ስም እየመለመለ ወደ ጦርነት በማሰለፍና ወደ ውጭ ሀገር በመሸጥ በማያውቁት ጉዳይ ላይ ሰለባ እንዲሆኑ ከማድረጉም በላይ በመጨረሻ ወጣቶቹን በታትኖ የራሱን ህይወት ብቻ ለማዳን ሲል በሜዳ ላይ ጥሏቸው የፈረጠጠ መሆኑን ነው::

በደምሒት ላይ የታየው ቀውስ ለሌሎች የኢትዮያ ፓለቲካ ድርጅቶች ያለው እንድምታና መልእክት ምንድን ነው?

የህወሓት/ኢሕአዴግ መንግስት የደምሒትን እንቅስቃሴ በስለላ መረቡ አማካይነት በቅርብ ይከታተለው እንደነበርና ሞላ አስገደምና ግብረ አበሮቹም ከህወሓት በሚሰጣቸው መርሃ ግብር መሰረት የሌሎቹን የፓለቲካ ደርጅቶች እንቅስቃሴ

ውጤታማ እንዳይሆንና ባሉበት ቀጭጨው መክነው እንዲቀሩ ለማድረግ ሳይታክቱ ይሰሩ እንደነበረ ይፋ አድርጓል:: በኔ እምነት ይህ የወያኔ የስለላ ስራ በደምሒት ብቻ ተወስኖ የሚቀር አይመስለኝም:: በሀገር ውስጥ በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ እንታገላለን በሚሉ ድርጅቶቹም ጭምር የሚወሰደው እርምጃ ተመሳሳይ ነው:: በቅርቡ የአንድነት መበታተን የስርዓቱን እኩይ ተግባር ውጤት ነው:: በመድረክ አባላት ላይ እየተወሰደ ያለው ዘመቻም የዚሁ ተግባር አካል ነው:: ለምሳሌ ሞላ አስገደም በርካታ የዓረና አባላት የኛ አባላት ናቸው እያለ የውሸት መረጃ በመስጠት የወያኔ የእስርና የድብደባ ሰለባ እንዲሆኑ አድርጓል:: ዓረና ትግራይን ከጭንቅላቱ ለመምታትና ለመቆጣጠር ሲባል በአመራር አባላት ውስጥ የወያኔ ሰዎችን አሰርገው በማስገባት በየጊዜው ትርምስ ለመፍጠር በተደጋጋሚ የሚያደርጉትን ሙኮራ የአደባባይ ሚስጢር ሆኖ ቆይቷል:: ስለሆነም በአሁኑ ጊዜ የስርዓቱን የስለላ መረብ ያልነካው የኢትዮያ የፓለቲካ ድርጅት አለ ብሎ ለማመን ያስቸግራል::

መፍትሔውም አንድና አንድ ነው:: እሱም በሀገራዊ ጉዳይ ዙሪያ ሕብረት ፈጥሮ መንቀሳቀስ ነው:: ሕብሰረት ብሎም አንድነት ፈጥሮ መንቀሳቀስ ማለት ደግሞ ጥቅሙ የተበታተነውን ማሕበረሰብ አሰባስቦ ሰብኣዊ ሐይል ለማጠናከር ! የፋይናስ ዓቅም ለማጎልበት ! በመንግስት ላይ ተፅዕኖ በመፍጠር የመደራደር ዓቅምን ለማጎልበት! በዲፕሎማሲያዊ መስክም ተሰሚነት ለማግኘትና አቤት ብለን ድምፃችንን እንዲሰማ ለማድረግ ይረዳል ብቻ ሳይሆን ለሰላዮቹም ! ወሬ አቀባባዮችና አደናጋሪዎችም ዕድል አይኖራቸውም::

ካልሆነ ግን በተናጠል ድርጅት ነን እያሉ ተበታትኖ የየራሱን ጎጆ አበጅቶ መኖር ማለት ልክ በ16ኛው ክፍለ ዘመን የነበረው የየክልሉ ነገስታት በመሆን እርስ በርስ እየተጠላለፉና የስርዓቱን መጫወቻ እየሆኑ ከመኖር ውጭ ለሀገርና ለህዝብ ፋይዳ የለውም:: ፋሽኑ ወይም ጊዜው ያለፈበት የትግል ስልት ይዞ መንቀሳቀስ ደግሞ የኢትዮያ ህዝብ ሰልችቶታል ብቻ ሳይሆን በዓለም ማሕበረሰብ ዘንድም ተንቀናል:: ዛሬ በተናጠል አቤት ብንል አድማጭ አናገኝም:: አካሄዳችን ውጤት አልባ የዜሮ ድምር ጉዞ በመሆኑ ብዙ ታጋይ ዜጎች ከትግሉ ጎራ እየሸሹ የዳር ተመልካች ሆነው እንዲቀሩ አድርጓቿል::

ስለዚህ በኤርትራ ያሉት ድርጅቶች በከፊል የጀመሩትን የአንድነት ጉዞ የፈለገውን ወሬ ቢናፈስ ዋል እደር ሳይባል መጠናከር ያለበት ጉዳይ ነው:: በደምሒት የተፈጠረው ቀውስ ሆን ተብሎ መላ የፓለቲካ ድርጅቶችን የሐፍረት ሸማ ለማከናነብ ተብሎ የተደረገ እኩይ ተግባር መሆኑን ተገንዝበን ፈጣን ምላሽ በመስጠት በጥቂት ሰላዮች ለነፃነትና ለፍትሕ የሚደረገው የተባበረ ህዝባዊ ትግል በፍፁም ማቆም እንደማይቻል በተግባር ማሳየት መቻል አለብን::

ወያኔ የተጀመረውን የትብብርና የውህደት አጀንዳ በአቋራጭ ነጥቆ እንደተለመደው እሱ በሚሰጠን የቤት ስራ አጀንዳ እንድንጠመድ ለማድረግ መሆኑን ግልፅ ነው:: ስለሆነም እኛ ቀድመን በመገኘትና ነቅተን በመነሳት የፓለቲካ ድባቡን ቶሎ ብለን በመቀየር አዲስ ዜናና አዲስ ሀገራዊ አጀንዳ ይዘን መምጣት መቻል አለብን:: መፍትሔው ከሌላ ሀይል የምንጠብቀው ሳይሆን በእኛው በእጃችን ላይ ነው ያለው:: ለጋራ ሀገራዊ ጉዳይ ተባብሮ መስራት አማራጭ የሌለው ብቸኛ መንገድ ነው::

ሳይደፈርስ አይጠራምና የመጀመሪያ የትግል እርምጃ ውስጥህን ማፅዳትና መተማመን ነው:: እርግጥ ነው መሰዋእት ይጠይቃል:: ነገር ግን በሀገራችን አስከፊ ጭቆናና አረሜናዊ ስርዓት እስካለ ድረስ ትግል ይቆማል ብሎ ማሰብ ፍፁም የዋህነት ነው::

ሰላዮች ራሳቸው ባጠመዱት ወጥመድ ይወድቃሉ ይጋለጣሉ ይሞታሉ እንደጉም ይበታተናሉ

ህዝባዊ መስመር ያነገበ ትግል ግን የፈለገው መስዋትነት ይኑር ምንም ጊዜም አሸናፊ ነው

የህብር ሬዲዮን ዘገባ ህብር ሬዲዮን ከድህረ ገጻችን በተጨማሪ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን ወይም ከgoogel store Hiber radio አፕሊኬሽንን ዳውን ሎድ በማድረግና  ከዘሐበሻም ማዳመጥ ይቻላል።

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *