በአሳዛኙ የሳውዲ አደጋ ከሟቾች ውስጥ ኢትዮጵያውያን ይገኙበታል ተብሏል

Saudi_accident_01

ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዬች እንኳን 1436 ኛዉ የኢድ አልአድሀ በአል በሰላም አደረሳችሁ እያልን መልካም ምኞታችንን ገልጸን ሳንጨርስ በሳውዲ የተሰማው አሳዛኝ አደጋ አስደንጋጭ ነው። በዚህ አደጋ ከኢትዮጵያ የሄዱ የዕምነቱ ተከታዮች ጭምር ሕይወት ማለፉን የተለያዩ ዘገባዎች ያስረዳሉ። በሳውዲ የሚገኘው ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ ስለ ሁኔታው የጻፈው ተከትሎ ቀርቧል። በዚህ አጋጣሚ በሳውዲ የሚገኙ የክርስትና ዕምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን በአደጋው አዝነው በወገኖቻቸው ለደረሰው ሞት የሀዘን መግለጫ በፌስ ቡክ ገጻቸው አውጥተዋል።

አሳዛኙ የሚና / ጀማራት አደጋ … ! * የሟች ቁጥር 700 በላይ የቆሰሉት ከ800 በላይ ደርሷል * ከቆሰሉትና ከሟቾች መካከል ኢትዮጵያውያን ይገኙበታል ተብሏል * የሳውዲ መንግስት ኃላፊዎች የኢትዮጵያን የሃጅ ኮሚቴ ኃላፊዎችን እንዲቀርቡ ጠይቀዋል

ዛሬ ማለዳ የሀጅን ሥነ ሥርዓት ተከትለው ሰይጣንን በድንጋይ በሚመታበት ምሳሌ በሚከዎንበት በጀማራት ድልድይ በሚወስደው መንገድ በሀጅ ተጓዦች መካከል በመጨረሻው ሰዓት በተፈጠረ ግፊያና መጨናነቅ በተከሰተ አደጋ የሟ ቾች ቁጥር ወደ 700 ከፍ ያለ ሲሆን የቆሰሉት ቁጥርም ከ800 በላይ መድረሱ ታውቋል ! የሟችና የቁስለኞች ቁጥር በየሰአታቱ በመጨመር ላይ ሲሆን የሳውዲ መንግስትና የአረቡ አለም መገናኛ ብዙሃን ከሚናና መካ በመሆን መረጃውን በሰፊው በመዘገብ ላይ ናቸው !

ምንም እንኳን ስለደረሰው አደጋ ገና መንስኤ በውል የተሰጠ ምክንያት የለም ። ያም ሆኖ ሌሊቱን ሙዝደሊፋ ላይ ጸሎት ሲያደርጉ ያሳለፉት ሀጃጆች ጸሎታቸውን ከጨረሱ በኋላ ወደ ሚና ጀማራት መምራታቸው ተጠቅሷል ። ጀማራት እንደደረሱም በሰይጣን ላይ ድንጋር የመወርወር ሥርዓት ለመካፈል በሚደረገው ሥርዓት ዛሬ ረፋዱ ላይ የደረሰው አደጋ ከዚህ በፊት ከተሚከሰተው ግፍያና መተፋፈን የተለየ እንደማይሆን ይገመታል ።

አደጋው ከደረሰ እስከ እስካሁን በመካና በሚና ዙሪያ የሚገኙ የእሳት አደጋ ፣ የአደጋ ጊዜ ተወርዋሪዎች ፣ የቀይ ጨረቃ ሰራተኞች፣ የሰራዊቱ አባላትና ፈቃደኛ የሀጅ ድጋፍ ሰጭዎች ሟቾችንና ቁስለኞች በማንሳት በመረባረብ ላይ መሆናቸው የሳውዲ መንግስት ጠቁሟል ። ከደረሰው አደጋ ጋር የአየሩ ሞቃታማ መሆን አደጋውንና የአደጋ ጊዜ ድጋፉንና አወሳስቦት ተስተውሏል ። አደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው ጥረት በከፍተኛ ሁኔታ በርብርቦቭ ሲቀጥል ቁስለኞችን ወደ ሚናና በአቅራቢያው ወዳሉ ሆስፒታሎች የመውሰዱ ድጋፍ እየተካሔደ ነው !

አደጋው የደረሰበት የጀማራት ህንጻ በርካታ አመታት በሀጅ ወቅት በሚከሰት ግፊያ በርካታ ሃጃጆች ሲሞቱበት ተስተውሏል ። ያም ሆኖ አደጋውን ለመቆጣጠር እጅግ ለህንጻው ከቢሊዮን ሪያል ከፍ ያለ ገንዘብ ወጭ ተደርጎ ህንጻው ከተሰራ ወዲህ በጀማራት ያለውን አደጋ ለመቆጣጠር ተችሎ ነበር ።

በአደጋው ላይ ኢትዮጵያውያን ስለመኖራቸው ከማለዳው ጀምሮ ለማጣራት የተለያዩ ሙከራዎችን አድርጌ ነበር ። ሆኖም የቆሰሉ አሉ የሚልና ከሁለት በላይ የሞቱ እንዳሉ ያልተረጋገጠ መረጃ ደርሶኛል ። የሞቱትን በሚመለከት ቁጥራቸው 2 ብቻ መሆኑን ያገኘሁት ሌላ መረጃ የሳውዲ መንግስት ኃላፊዎች የኢትዮጵያን የሃጅ ኮሚቴ ኃላፊዎችን እንዲቀርቡ መጠየቃቸው ከመንግስት ታማኝ የመረጃ ምንጮቸ መረጃ ደርሶኛል ። ጉደዩን በቅርብ እየተከታተልኩት ሲሆን አዳዲስ መረጃዎች እንደደረሱኝ የማቀርበው ይሆናል !

በአሳዛኙ የጀማራት ሚና አደጋ ዙሪያ በዛሬው የጀርመን ራዲዮ ጋር ቃለ ምልልስ ይኖረኛል ፣ ተከታተሉት!

ነፍስ ይማር !

ነቢዩ ሲራክ መስከረም 13 ቀን 2008 ዓም

የህብር ሬዲዮን ዘገባ ህብር ሬዲዮን ከድህረ ገጻችን በተጨማሪ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን ወይም ከgoogel store Hiber radio አፕሊኬሽንን ዳውን ሎድ በማድረግና  ከዘሐበሻም ማዳመጥ ይቻላል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *