በሳውዲ የሚና ጀማራት አደጋው ከተከሰተ ወዲህ ሪፖርት ያላደረጉ ኢትዮጵያውያን ሀጃጆች ስም ይፋ ሆነ

Saudi_unreporeted_ethiopian_04

ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዬች እንኳን 1436 ኛዉ የኢድ አልአድሀ በአል በሰላም አደረሳችሁ እያልን መልካም ምኞታችንን ገልጸን ሳንጨርስ በሳውዲ የተሰማው አሳዛኝ አደጋን ተከትሎ ኢትዮጵያውያን በዚያ አሉ ወገኖቻቸው ሁኔታን ያሳስባቸዋል። ዛሬም ሰሞኑን ስናደርግ እንደቆየነው ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ በሳውዲ ከኢትዮጵአውያን ሀጃጆች መካከል ሪፖርት ያላደረጉት ዝርዝር መውጣትን ተከታትሎ ተጨማሪ መረጃና ማብራሪአ ይዞ ቀርቧል። ያንብቡ ለወዳጆችዎ ያድርሱ።

የማለዳ ወግ … የሚና ጀማራት አደጋና ኢትዮጵያውያን ! * አደጋው ከተከሰተ ወዲህ ሪፖርት ያላደረጉ ሀጃጆች ስም ይፋ ሆኗል! * ልዩነትና አስዎግደን ዜጎቻችን በማፈላለግ እንትጋ * የተወሰኑ ቁስለኞች ከሚናና መካ ወደ ጅዳ ሆስፒታሎች ገብተዋል * በዝርዝሩ የሌሉ የጠፉባችሁ ቤተሰቦች ካሉም አሳውቁ

የተጎዱ ኢትዮጵያውያን መኖራቸው እውነት ነው …

በሚና ጀማራት አደጋ ኢትዮጵያውያን ስለመኖራቸው ስለ መጎዳታቸው ከመንግስት አካላትም ሆነ ከሀጅ ኮሚቴው የታወቀና የተሰጠ መረጃ የለም ። ያ ማለት ግን አደጋው አልጎዳንም ማለት አይደለም ። በዘንድሮው ኢድ አል አድሃ በጸሎት በተበሰረ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ በአካል በቦታው በመገኘት የሞቱና የቆሰሉ ስለመኖራቸው ጭብጥ መረጃ ያቀበሉኝ አሉ ፣ እናም የሞቱና የቆሰሉ ኢትዮጵያውያን መኖራቸው የሚያሳዝን አውነት ነው ። እዚህ በጅዳና በሪያድ ዙሪያ ከአንድም ሁለት ሶስት ኢትዮጵያውያን በአካል ሚና ተገኝተውና ቁርጣቸውን አውቀው ለቀሩት ዘመዶቻቸው መርዶ ነግረው ሀዘን የተቀመጡ በቅርብ የማውቃቸው አሉ ! በአደጋው ከተጎዱትና ካጣናቸው መካከል በአካል የማውቀው አንድ ወዳጀ ከወንድሙ ጋር በሀጅ የመጡ ቤተሰቦቹን ለመደገፍ ወደ መካ አቅንቶ በአደጋው ህይዎቱ ማለፉን አደጋው በተከሰተ ቀን ነበር የሰማሁት ፣ ከሁሉም የሚያመው የአደጋው ሰለባ እሱ ብቻ ሳይሆን ወንድሙም ጭምር መሆኑን ትናንት ማለዳ የፎቶ ማስረጃ ጭምር ሳገኝ በጣም አዘንኩ frown emoticon ነፍሳቸውን ይማር !

ዛሬም አደራሻቸው የጠፋ በአለም ዙሪያ ወደ ለሀጃጅ የመጡ የ18 ሀገር ሀጃጆች አሉ ፣ በርካታ ሀገራት የጠፉ ሀጃጆችን ስም ዝርዝር አውጥተው በፍለጋው ተግተዋል ። አንዳንዶች የሞቱ የቆሰሉና የጠፉት ዝርዝር ይፋ አድርገዋል ! በርካታ የሚመለከታቸው ኢትዮጵያውያን ዲፕሎማቶችና የሀጅ ኮሚቴ አባላት በመካና ሚና ዙሪያ ባደረጉት ማጣራት አደጋው ከተከሰተ ወዲህ ሪፖርት ያላደረጉ ኢትዮጵያውያን ሀጃጆች 179 ደርሰዋል ! የሚመለከታቸው አካላት በጅዳ ቆንስል የፊስ ቡክ ገጽ ሀጃጆች ያሉበትን አድራሻ አለመታወቁን ዝርዝርን ከአፋልጉን መልዕክት ጋር አሰራጭተዋል ። በዝርዝሩ የተጠቀሱት ሀጃጆች አደጋው ከተከሰተበት ካሳለፍናቸው ሁለት ቀናት ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያውያኑ ሀጃጆች መሰባሰቢያ ያልቀረቡት ሲሆን በተለያየ መንገድ ለአደጋ የተዳረጉ ፣ ቦታ የጠፋባቸው ወይም ጅዳ መካ፣ መዲናና ወደተለያዩ ቦታዎች በዘመዶቻቸው የተወሰዱ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገመታል ።

በማዕከላዊነት የማፈላለግ ስራው ይሰራ … ===========================

በጅዳ ቆንስል ፊስ ቡክ ከተጀመረው የአፋልጉኝ መረጃ ልውውጥ በተጓዳኝ የጅዳ ኮሚኒቲ ምክር ቤት አፋልጉኝ የሚል መልዕክትና መረጃ አስተላልፏል ። መተባበሩ ክፉም ባይሆን አሰራሩ ውጤት እንዲኖረው ማዕከላዊ የሆነ የመረጃ ልውውጥ ቢኖር ይመረጥ ይመስለኛል ! በአንድ ማዕከላዊ የመረጃ ልውውጥ መጠቀም መረጃዎችን ከመደጋገም ያድናቸዋል ፣ ጊዜንም ይቆጥባልና በማዕከላዊነት የማፈላለግ ስራው ይሰራ !

ጅዳ ከመጡት ቁስለኞች ቤተሰብ፣ ዘመድና ወዳጀ ፍለጋ … ===================================

ከትናንት ማለዳ ጀምሮ በአደጋው የቆሰሉ ሰዎችን ወደ ጅዳ ሆስፒታሎች የማስተላለፉ ስራ መጀመሩን ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው የመረጃ መንጮች ያገኘሁትን መረጃ ማቅረቤ አይዘነጋም ። ይህንኑ መረጃ ተከትለው ቤተሰባቸውን ሲፈልጉ የነበረ አንድ ወንድም በፍለጋው ያጋጠማቸውን የገለጹበትን መልዕክት እንዲህ ይላል ” ሰላም ነብዩ ደህና አደርክ ማታ ከመካ የመጡ ቁስለኞች የት እንደሚገኙ ጠይቄህ ነበር ፣ ስፈልግ ነው ያደርኩት ፣ ሀበሻ ሊኖር የሚችለው ሙስተሽፈል ሀረስ ጠሪቅ መካ ያለው ይመስለኛል ። ከመቶ በላይ ቁሰለኛ አለ ብለዋል ፣ ግን አላስገቡንም ። ጀዋዛት ነገ አሻራ አንስቶ ስም ዝርዝር ይሰጠናል ነገ ጠዋት መጥታቹ ጠይቁ አሉን ! ሌላ ኡብሁር ያለው መሊክ አብደላ መርከዝ ጥብ 25 ሙስተሸፈል ጃምአ 15 ቁስለኞች አሉ ሀበሻ የለም ነበር ግን ሌላም እየመጡ ነው ብለዋል !” ይላል !

መረጃው ይህን ካለ የጅዳ ቆንስልና የሚመለከታቸው አካላት ወደ ጅዳ ያሉ የተለያዩ ሆስፒታሎችን በማንኳኳት በግለሰብ ደረጃ ውጣ ውረዱና ቢሮክሲው የሚቻል አይደለም ። ይልቁንም ህጋዊ የመንግስት ተወካዮች ተመድበው የጠፉ ዜጎችን ማፈላለግ ይጠበቅባቸዋል ።

መረጃ መስጠትና መቀበሉ … =================== መረጃ መስጠትና መቀበል ፣ መቀባበሉ በዚህ ወሳኝ በሆነበት ወቅት ላይ መሆናችን ልብ እንበል ፣ ልዩነትን በዚህ አደጋ ጊዜ አናስፋ ፣ የተጎዱ የተጨነቁትን ማስቀደሙን እናስቀድም ! የመንግስት ተወካዮች ስልኮቻቸውን ያንሱ ፣ የሚያቀርቧቸው መረጃዎች የተሟሉ ይሁኑ ፣ ለምሳሌ ያህል የቀረበው ዝርዝር በጥሩ የእጅ የቁም ጽሁፍ ለመጻፉ ጊዜ ባይኖር የሀጃጆችን ስም ከነ አያታቸው ሙሉ ስም መጻፍ ነበረበት ። ይህ ወደ ፊት መታረም ይኖርበታል !

የተዘረዘሩትን 179 ሀጃጆች አድራሻቸውንና ያሉበትን ሁኔታ የምናውቅ ለሚመለከታቸው የኢንባሲ ፣ ቆንስላ ፣ የሀጅ ኮሚቴ ተወካዮች ወይም ለእኔ ማቀበል የቀለላችሁ ላኩልን ፣ ዋናው በማፈላለጉ ረገድ ትብብር ልናደርግ ይገባል ! ” የወገን ጉዳይ ያገባናል !” የምንል ጉዳዩ ለሚመለከታቸውን ኃላፊዎች ከዚህ ጋር በተሰጠው ስልክ በመደዎል አናሳውቅ ! ከዚህ ጋር በቀረበው ስም ዝርዝር ስማቸው ያልተመዘገበ ነገር ግን የጠፉ የምታውቋቸው ሀጃጆች ወይም ከሀጃጅ ቤተሰቦቻቸው ጋር ወደ ሚና ጀማራት መጥተው የጠፉ ኢትዮጵያውያንን ካሉ መረጃ በማቀበል የዜግነት ድርሻችን እንዎጣ እላለሁ !

እስኪ ቸር ያሰማን !

ነቢዩ ሲራክ መስከረም 15 ቀን 2008 ዓም

የህብር ሬዲዮን ዘገባ ህብር ሬዲዮን ከድህረ ገጻችን በተጨማሪ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን ወይም ከgoogel store Hiber radio አፕሊኬሽንን ዳውን ሎድ በማድረግና  ከዘሐበሻም ማዳመጥ ይቻላል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *