ዘንድሮ ለአምስተኛ ጊዜ በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ የቀድሞ የትግል አጋሮች የነበሩት ዶ/ር አዲስ ዓለም ባሌማና አቶ ገብሩ አሥራት በመቐለ የምርጫ ክልል ሕወሓት/ኢሕአዴግንና አረና መድረክን ወክለው እንደሚፎካከሩ ታወቀ፡፡

0980a16d2dd0ad1144307bba8438926a_XL_490_280በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር እንዲሁም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ዶ/ር አዲስ ዓለም ባሌማ ኢሕአዴግን ወክለው የሚወዳደሩ ሲሆን፣ የቀድሞው የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የነበሩትና ሕወሓት ባጋጠመው ክፍፍል ከፓርቲው የተወገዱት አቶ ገብሩ አሥራት ደግሞ አረና/መድረክን ይወክላሉ፡፡

እንዲሁም በትግራይ ክልል በማዕከላዊ ዞን በማይቅነጠል የምርጫ ክልል ሕወሓት/ኢሕአዴግን ወክለው የሚወዳደሩት፣ የሕግና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ ናቸው፡፡ በዚሁ ክልል ሰሜን ምዕራብ ዞን አስገደፅምብላ የምርጫ ክልል ደግሞ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ወ/ሮ ሮማን ገብረ ሥላሴ እንደሚወዳደሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የወቅቱ የመድረክ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር መረራ ጉዲና በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሸዋ ዞን ቶኬ ኩታዩ የምርጫ ክልል የሚወዳደሩ ሲሆን፣ በዚሁ ክልል ዳንዲ 2 በተባለ ቦታ የምርጫ ክልል እንዲሁ ሌላው የመድረክ ተወዳዳሪ አቶ ገብሩ ገብረ ማርያም ተወዳዳሪ ናቸው፡፡

በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ዞን በኢተያ የምርጫ ክልል ደግሞ ኦሕዴድ/ኢሕአዴግን ወክለው የሚወዳደሩት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ ሲሆኑ፣ በዚሁ ክልል በሳጉሬ የምርጫ ክልል ደግሞ የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽፈራው ጃርሶ ተወዳዳሪ ናቸው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ባለፈው ምርጫ በአዲስ አበባ ከተማ ተወዳድረው የፓርላማ አባል የነበሩት የውኃ፣ የመስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር አቶ ዓለማየሁ ተገኑ በአቃቂ ግምብቹ የምርጫ ክልል ኦሕዴድ/ኢሕአዴግን ወክለው ይወዳደራሉ፡፡

በአማራ ክልል በጢስ ዓባይ በዘነዘልማ የምርጫ ክልል ደግሞ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ ከርዕሰ መስተዳድሩ የፀጥታ አማካሪ አቶ ሲሳይ አሰፋ ጋር ይፎካከራሉ፡፡ በዚሁ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ከተማ የምርጫ ክልል ብአዴን/ኢሕአዴግን ወክለው የሚወዳደሩት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው ናቸው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ሽታየ ምናለ ደግሞ በምዕራብ ጎጃም ዞን ጎንጅ የምርጫ ክልል እንዲሁ ብአዴን/ኢሕአዴግን ወክለው ተወዳዳሪ ናቸው፡፡

በደቡብ ክልል በከፋ ዞን ጊምቦ የምርጫ ክልል በግል የሚወዳደሩትና 1,281 የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ የቻሉት ብቸኛው የግል ፓርላማ ተወካይ ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ ደግሞ፣ ደኢሕዴን/ኢሕአዴግን ከወከሉት ዶ/ር መብራቱ ገብረ ማርያም ጋር ይወዳደራሉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *