Hiber radio: ድርቁ አዲስ አበባ ከተማ አፍንጫ ስር ደርሷል!

ethio_famaine_011

በሃብታሙ ምናለ

ለተወሰኑ ቀናት ከአዲስ አበባ ውጭ ወጣ ብዬ ነበር፡፡ የሄድኩት ከአዲስ አበባ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ቦታ ሲሆን ህዝቡ በችግር እና በረሃብ አለንጋ እየተገረፈ ነው፡፡ ቦታው እዚሁ ከደብረ ሊባኖስ ወረድ ብሎ በሚገኝ የኦሮሞ እና የአማራ ሰዎች በሚኖሩበት አካባቢ ነው፡፡ ደብረ ሊባኖስ አካባቢ የኦሮሞ ተወላጆች ሲኖሩ ወደታች ስንወርድ የጀማ ወንዝ ተያይዞ አዲስ ሰላምበሚባለው ቦታ ደግሞ የአማራ ነዋሪዎች ይኖራሉ፡፡ ሁለቱም ብሔረሰቦች ተከባባረውና ተፈቃቅደው እየኖሩ ቢገኝም አሁን ግን የዝናቡ መጥፋት ድርቅ በመግባቱ ፌት መነሳሳት ጀምረዋል፡፡ ብአዲን አማራን ወክዬ ለህዝቡ እየታገልኩ ነው ብሎ የሥራውን ልፋት ለማሳየት ውስኪ በመራጨት ሲያከብር በስሙ የሚነግድበት ህዝብ ግን የሚበላና የሚጠጣ በማጣት እንባ ሲራጭ ውሎ ያድራል፡፡ አንዳንድ ሰዎችን አቅሜ በፈቀደው መጠን ለማናገር የሞከርኩ ሲሆን የገለፁልኝ ነገር ቢኖር ዝናብ የጣለው ሐምሌ 23 /2007ዓ.ም የጊዮርጊስ ቀን ነው፡፡ ከእዛ በኃላ ጳጉሜ ላይ አንድ ቀን ለመጣል ሞከረና በእዛው ቀረ እኛም በመጣው ዝናብ ዘርተን ብናለብስም መሬቱን የሚያጠነክር ዝናብ ባለመጣሉ እህሉ ፍሬ አልያዘም ሲታይ ያፈራ ይመስላል ለተመለከተው ያፈራ ምርጥ ዘር ይመስለዋል፡፡ ግን ምንም ጥቅም የለውም ፍሬ አልባ ነው›› ብለዋል፡፡ ‹‹ኩሬዎች እንኳ ደርቀው ከብቶቻችንን የምናጠጣው ራቅ ወዳለ ቦታ ሔደን ነው ሁሉም ተዳክሟል ፈጣሪ ምን አርጎ ነው እንዲህ የሚቀጣን ብለው ምሬታቸውን ገልጸው በእዚህ ሁኔታ እንዴት ነው የምትቀጥሉት ብዬ ስጠይቃቸው ‹‹ርሃቡን ለአንድ ዓመት እንደምንም እንታገሳለን፡፡›› ከእዛ በላይ ግን አንድም ሰው በሃገሩ ላይ በህይወት አይገኝም ብለው ጆሮ ጭው የሚያደርግ ንግግር ተናገሩ እንዴት ነው ረሃብን ለመቻል የተነሳሱት ድፍን 365 ቀናት ወይም 8760 ሰዓታትን እንዴት ማሳለፍ ነው የሚቻለው ህመምን በማስታገሻ፤ ድካምን በማረፍ ማለፍ ይቻላል ግን ርሃብን እንዴት ነው ማለፍ የሚቻለው? ጠንካሮች ናቸው ብቻ ብሎ ማለፍ ለእኔ ንፉግነት ሆኖ ይሰማኛል ፡፡ በመንግሥት የተደረገላቸው እርዳታ በተመለከተ መንግሥት በአሁኑ ሰዓት ድምጹን ሳያሰማ ለመርዳት ጥረት እያደረገ መሆኑን ሹክ ብለውኛል ዘይትና የመሳሰሉትን ቢያገኙም በቂ ባይሆንም በቻሉት መጠን አብቃቅተው ለመጠቀም አስበዋል፡፡ ህዝቡ በጣም ችግር ላይ ወድቋል ልጆቻቸው በሃገሬው ህዝብ አረማመድ ከ45 እስከ 1 ሰዓት በከተማው ደግሞ ከ2 ሰዓት በላይ የሚፈጅ የእግር ጉዞ አድርገው ትምህርት ይማራሉ፡፡ ልጆቹ የትኛውን ይቻሉ ርሃቡን፣ መንገዱን፣ ወይስ በባዶ ሆድ እና በድካም ትምህርትን መማርን አሁንም ሁላችንም ዙርያውን እንቃኝ የእኛ ወላጆች የተገኙት ከገጠር ነው አሁን ደግሞ የገጠር ሰዎች ሲራቡ እናትና አባቶቻችን እንደተራቡ በመቁጠር ስሜታችንን እናስገዛ፡፡ በቃህ በማል ያለበትን በቃ እንበል የሸገር ነዋሪ ይሄን ሁሉ የምሬት ጩኸት ሰምቶ እንዳልሰማ በመሆን ጆሮ ዳባ ልበስ ብሏል ነገ ከእዚህ ምስኪን ገበሬ የሚቀርብለት ሰብል ከመወደድ አልፎ ሲጠፋ ምነው ያኔ በነቃሁ ኖሮ ማለቱ አይቀርም ከእዛ በፊት ቀየውን ትቶ ገበሬው ከመሄዱ በፊት የራስን ዳንኪራና የመንግሥት ቸልተኝነት ገታ አርጎ ለጉዳዩ መፍትሔ መፈለጉ ይሻላል፡፡ እኛ አፋር፣ ወሎ ፣አፋር ርሃብ ተነሳ ብለን ስንናገር በጉያችን ግን ትልቅ ችግር አስቀምጠናል፡፡ አዲስ አበባ ቁጭ ማለት ከርሃብ አያስመልጥም ችግሩ ወደእኛ ቢመጣ እንደ ጠንካራው ገበሬ ለመቻል ማንም የሚቆርጥ ልቦናና አቅም የለውም፡፡ አሁንም መንግሥትም ችገሩን በይፋ በማውጣት ትንሽ፣ ትልቅ፣ ተቃዋሚ፣ ደጋፊ፣ ጠላት፣ ወዳጅ ሳይል እንዴት መፍታት እንዳለበት በመነጋገር ለወገኖቻችን ልንደርስላቸው ይገባል ያለበለዚያ ‹‹ርሃብ አብዮትን እንደሚወልድ በደርግና በኃ/ሥላሴ ጊዜ አይተናል፡፡››

የህብር ሬዲዮን ዘገባ ህብር ሬዲዮን ከድህረ ገጻችን በተጨማሪ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 እና በአውስትራሊያ 0280725172 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን ወይም ከgoogel store Hiber radio አፕሊኬሽንን ዳውን ሎድ በማድረግና  ከዘሐበሻም ማዳመጥ ይቻላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *