Hiber Radio: የዛሬ ጥምቀት በዓልን ከጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ጋር በቃሊቲ እስር ቤት!

Eskender_free_temsegen_002

ዛሬ ዛሬ የታሰሩ ጋዜጠኞችን፣የሰብኣዊ መብት ተሟጋቾችን፣የተቃዋሚ መሪዎችን፣ንቁ አባላትን እንዲሁም በስም ዘርዝረን የማንጨርሳቸው ዜጎች ስም ባላቸው እነ ቅሊንጦ፣ቃሊቲ፣ዝዋይ፣ባዶ ስድስት፣ማዕከላዊ፣ሶስተኛ፣ጎንደር እስር ቤት፣አርባ ምንጭ ወህኒና ሌላም በምንላቸው ብቻ ሳይሆን በስም የለሽም እስር ቤቶች በርካታ ንጹሃን በፈጠራ ክስ የተለየ ሀሳብ ስላቀረቡ ፍዳቸውን ይቆጥራሉ። እስክንድር ይፈታ! ተመስገን ይፈታ፣በቀለ ገርባ ይፈታ ስንል እነ እንትና ሁሉ ይፈቱ እያልን ነው።መቼ ነው እነዚህ ሁሉ ንጹሃን በአጠቃላይ የኢትዮጵአ ሕዝብ ከዚህ ግፈና ስርኣት ነጻ የሚወታው። ዛሬ ዛሬ እስክንድር ይፈታ ፣አቡበከር ይፈታ፣ሀብታሙ ይፈታ ማለት የኢትዮጵያ ሕዝብ ይፈታ እንደማለት ጭምር ነው። በዚአ አገር ነጻነት እስካልመጣ እንደምናው ታስሮ የተፈታው መልሶ የሚታሰርበት ፣በህጻናት ላይ ቦንብ ሳይቀር የሚአስወረውሩ ወረበሎች አገር የሚመሩበት የመጨረሻው መጨረሻ ላይ ደርሰናል። ለዛሬ የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ወንድም ሰሞኑን ቃሊቲ ተገኝቶ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ጠይቆ ያሰፈረውን እነሆ፦

በታሪኩ ደሳለኝ

አንጋፋውን ብርቱውን ጋዜጠኛ እስክንደር ነጋን መጠየቂያው ቦታ ላይ በመቁነጥነጥ አንገቴን አስግጌ፣ አይኔን ተክዬ እስኪመጣ እየጠበኩት ነው። በወታደር ታጅቦ “ኃይት ሃውስ” ተብሎ ከሚጠር የእስር ክፍል ሲወጣ አየሁት። ቀይ ከነቴራ አመድማ ባርኔጣ አድርጎ ከሚናፍቀው ፈገግታ ጋር እየተንጎማለለ ወደኔ እየመጣ ነው። ግርማው፣ ኩራቱ እንዴት ደስ እንደሚል!? እንደዛ የጓጓሁት ሳየው ብርክ ያዘኝ ለካ ጀግና ፊት መቆም ያሰደንግጣል? መጠየቂያው ቦታ ላይ መሃላችን የተጋደሙት እንጨቶች ተቃቅፎ ሰላምታ ለመለዋወጥ ከለከሉን። ለሰላምታ እጁን ዘረጋለኝ እነዚህ እጆች ስንት የፃፉ፣ ብዙ የገነቡ፣ ስንቱን ወደፊት ያመጡ የእስክንደር ነጋ እጆች ናቸው። እጁን ሰምኩት። እንባዬ መጣ ዝም ብያ አየሁት “ተሜ እንዴት ነው?” አለኝ ያለውን ነገር ነገርኩት በተራው እሱ ዝም አለኝ። “ሲብሰከሰክ” ተመለከትኩት። ግርም የሚለኝ እስክንድር ጋር ስሄድም ቀድሞ “ተሜ እንዴት ነው” ብሎ ነው የሚጠይቀኝ። ተሜ ጋር ስሄድም “እስኪው እንዴት ነው” ነው የሚለኝ። እንዚህ ሁለት ሰዎች “መቼ ነው እየተያዩ የሚያወሩት?” እላለሁ። እስክንድር ሲያወራ መስማት ማለት “እንደ መስቀል ወፍ በዓመት አንድ ጊዜ መጥታ እንደ ምትሄደው፣ በጠዋት እንደምትወጣው ለስለስ ያለችው ፀሃይን በየሰከንዱ ማግኝት ማለት ነው። “የኃላው ከሌለ የለም የፊቱ” የሚባለው አባባል የሚሰራው እስክድርን ስመለከት ነው። በፈቀዱል 30 ደቂቃ ተጨዋውተን እስክንድርም ወደ እስር እንዳመጣጡ በወታደር ታጅቦ ዘንከት ዘንከት እያለ “ኃይት ሃውስ” ሲገባ ማየትን የመሰለ ልብ የሚሰብር ነገር ከቶም የለም። ደስ እያለኝ እስክንድርን ተሰናብቼ ከቃሊቲ እስር ቤት ስውጣ ታቦት የሚሸኙ ወጣቶች “እስይ ስለቴ ሰመረ” እያሉ ሲዘምሩ ስመለከት ታቦቱ ወደ መንበሩ በስላም በመመለሱ እና እስክንድርን በማየቴ “እስይ ስለቴ ሰመረን” መዝሙር እየዘመርኩ ተቀላቀልኳቸው። ጥር 11/ 08 ዓ.ም

ህብር ሬድዮን በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ 01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *