Hiber radio የፈረንሳይ ፖሊሶች የኢትዮጵያዊያንን ቤተክርስቲያን እና መስጊድን ማፈራረሳቸው ታላቅ ተቃውሞ አሰነሳ፣በአሜሪካ ውስጥ የእሳት ቃጠሎ ጥቃት የተፈጸመበት የ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ በፖሊስ እየተጠና ነው

Ethio_chirstian_muslim_france_03

በታምሩ ገዳ

በአገራቸው ውስጥ በሰላም የመኖር ዋስትና ተነፍገው የተሻለ ኑሮን እና ብሩህ ተሰፋን ሰነቀው በረሃ እና ባሀር በማቋረጥ ከ ምእራብ አወሮፓ ደጃፍ ካሊ/ፈረንሳይ ከሚገኘው ብዙዎች “ጃንግል” በማለት ከሚጠሩት ጢሻ ውስጥ የተጠለሉ በርካታ ኢትዮጵያዊያን እና ኤርትራዊያን ሰደተኞች የሚገኙበት ሰፈራ ላይ ከተለያዩ ቁስ የቆረቆሩት ፣መሰባሰቢያቸው እና አምልኮተ እግዜ አብሔር/ አላሕ የሆነው ቤተክርስቲያን እና መሰጊድ ሰሞኑን በፈረንሳይ አድማ በታኝ ፖሊስ እጃቢነት በአፈራሽ ግብረ ሃይል መፈራረሳቸው የተለያዩ የዜና ማሰራጫዎች ሰሞኑን ዘግበዋል።

ሁኔታውን በማሰመልከት “ክርስቲያን ቱደይ” የተሰኘው ድሀረ ገጽ እንደገለጸው ከሆነ በስደተኞቹ መጠለያ ካምፕ ውስጥ ከሚገኙት የአምልኮ እና የመጠለያ ስፍራዎች መካከል አንዱ የሆነው ፣በርካታ ኢትዮጵያዊያን እና ኤርትራዊያን ሰደተኞች የሚገለገሉበት የቅዱስ ሚካአል ቤተ ክርስቲያን ባለፈው የካቲት 2 / 2016 እኤ አ አረፋፈዱ ላይ በአፍራሽ ገብረሃይሎች እና በቡልደዘሮች እንዲፈራርስ እና ወደ ጭቃነት እንዲለወጥ ተደረጓል። ለሰደተኞች መብት ጥብቅና የቆመው የእንግሊዙ (Help Refugees UK) ሁኔታውን በሰነድ መልክ የያዘው ሲሆን ”ምንም እንኳን የአመልኮት ሰፍራዎች እንደማይፈረሱ ቀደም ተብሎ በአካባቢው ባለሰልጣናቱ በኩል ለሰደተኞቹ ቃል የተገባ ቢሆነም የተገባው ቃልኪዳኑ ፈርሶ ሰደተኞቹ የመጨረሻ የጸሎት ፕሮግራም እንዲያደርጉ የተፈቀደላቸው ሲሆን ብዙም ሳይቆይ የአምልኮተ ሰፍራዎቹ እንዳልነበሩ ወደ ፍርሰራሺነት ተለውጠዋል። አንድ ካህን (ቄስ ተፈሪ ሹሪሞ) ከፈረሰራሹ መካከል ያገኙ ትን መስቀልን በሃዘን ተሸክመው ማየት እና ሃዘኔታውን መዘገብም ልብን በእጅጉ ይነካል” ብሏል።

በዚህ ሰሞነኛው የማፍረሰ እርምጃ በቀን ከ 200 እሰከ 500 ሰደተኞች ይገለገሉባቸው የነበሩት ቤ/ክርስቲያኑ እና መስጊዱን በሰደተኞቹ ጣቢያ እና በአውራጎዳናው መካከል ያለውን ቦታ ለማጽዳት ሲባል መፍረሳቸው የተገለጸ ሲሆን የትምህርት መሰጫ ማእከሉ ግን ለጊዜው አለመፍረሱ ተዘግቧል ። ባለፈው ጥቅምት ወር ከአንጨት ፣ ከፕላስቲክ እና ከሸራ የታነጹት ቤተ ክርስቲያኑን ጨምሮ መሰጊዱ በአጭር ማሰጠንቀቂያ መፍረሱ የ ተለያዩ ፖለቲከኞች ቀልብ እና ውግዘትን የጋበዘ ሲሆን በቅርቡ የመጠለያ ካምፑን የጎበኙት የእንግሊዙ የአረንጋዴ ፓርቲ (የ ግሪን ፓርቲ )አባል የሆኑት ሞሊይ ስቾት ካቶ “ ተገን ፍለጋ በረሃ እና ባህር አቋርጠው ከዚህ ካምፕ የደረሱ ሰደተኖች ፈጣሪያቸውን በነጻ የማምለክ መብታቸው መገፈፉ በቁስል ላይ እንጨት የመሰደድ (ጨው የመነሰነስ )ያህል ነው ። ድርጊቱም በእጅጉ ያሳዝናል፣ ያሳፍራልም።” ብለዋል።

“ሄልፕ ረፉጅስ” የተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት አፈቀላጤ በበኩላቸው በሰጡት አሰተያየት “ ቤተክርስቲያኑ ሆነ መሰጊዱ ከአምልኮ ሰፍራነታቸው ባሻገር ከአገራቸ እና ከቤተሰቦቻቸው እርቀው በባእድ አገር ለሚነከራተቱ ወገኖች ሰማያዊ ተሰፋቸውን የሚያልሙበት እና የመጡበትን ባህልን እና እምነትን የሚተገብሩባቸው ሰላማዊ ስፍራዎች ነበሩ ።” በማለት ድርጊቱን በጽኑ ኮንነዋል። ይህ የመጨረሻ ህልማቸውን “ወደ ተሰፋይቱ ምእራብ አውሮፓ አገር (እንግሊ ዝ) “ ለመሸጋገር ሲሉ ከ 5 ሺህ በላይ የተለያዩ አገር ሰደተኞች የተጠለሉበት የካሊሱ የሰደተኞች ካምፕ ባለፈው አመት ታዋቂው የ እንግሊዙ የቢቢሲ ራዲዮ የጎበኘው እና ልዩ ፕሮግራም የሰራበት ሲሆን “የምስጋና መዝሙር እና ጸሎት የሚንቆረቆርበት ጢሻ “ሲል ማወደሱ በዙዎቹ ወግ አጥባቂ አደማጮቹን እና ጋዜጦችን አሰቆጥቷል።

ትላንት ቀደመ አያቶቻቸን እግዜ አብሔርን በህገ ልቦና፣ በህገ ኦሪትና እና በህገ ወንጌል ሲቀበሉ እና ሲያምኑ ድፍን አውሮፓ እና አሜሪካ ጣኦት አምላኪዎች ነበሩ ። ዛሬም ቢሆን አውሮፓ እደሜ ጠገብ የሆኑ ህንጻ ቤተክርስቲያናትን በከፍተኛ ገንዘብ እየሸጡ ለመደብርነት እና ለመሳሰሉት ተግባራት እንዲውሉ በከፍተ ኛ ዋጋ እየሸጧቸው ይገኛሉ ። ይሁን እና ሰደተኞቹ የእኛ ወገኖች ግን በተከራዩዋቸው ህንጻዎች አሊያም ከአውሮፓ ጢሻዎች ውስጥ ሆነው ብርድ እና ሃሩር እየተፈራረቁባቸው ዘወትር ሰለ አገራቸው እና ሰለ አለምም የመጸለያቸው ጉዳይ የብዙዎችን አመለካከትን በጥሩ ጎኑ ቀይሯል።

የክርስትና እና የአሰልምና አምነቶችን ከሌላው አለም በቅድሚያ የተቀበለቸው አገራችን ኢትዮጵያ በ ዛሬዎቹ ሰደተኞች ልጆቿ ላይ የግፍ በደል ሲፈጸምባቸው ሰሞኑን የመጀመሪያው አይደለም። ባለፈው አመት ከ28 በላይ ኢትዮጵያን ሰደተኞች ከሃይማኖታቸው ጋር በተያያዘ በሃይማኖት የለሾቹ የሊቢያ ወረበሎች(አይሲሶች ) ያቺ የቀደምት ክርሲቲያኖች አገር የነበረቸው ሊቢያ በረሃ እና ባህር ላይ “ሃይማኖችንን በጭራሽ አንቀይርም፣ ማህተባችንን ም አንበጥሰም !” በማለት ሊቢያ እ ኤ አ ከ 1911 እሰከ 1943 ድረስ ረግጦ የገዛት ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያ ላይም ተመሳሳይ የቅኝ ግዛት ቀንበሩን ለመጫን ሲዳክር ታላቁ መንፈሳዊ አባት አቡነ ጴጥሮስ “እንኳን ሕዝቤ መሬቷም አተገዛለህም ፨ “በማለት በመሃል አ/አ አራዳ ጊዮርጊስ ቤ/ክርን አካባቢ በጣሊያን ነፍሰ ገዳይ ቡድን በጥይት ተደብድበው ለብዙዎች መልካም አርእያ የሆኑባት የኢትዮጵያ የቁርጥ ልጆች ፣ የሰማቱ የአቡነ ጴጥሮስ ደግሞ የመንፈስ ልጆች መሆናቸውን የሰማእትነት ጽዋን በመቀበላቸው ጉዳዩም የብሔራዊ እና አለማቀፋዊ መነጋገሪያ ርእስ ሆኖ መቆየቱ አይዘነጋም።

በተያያዘ አሳዛኝ ሃይማኖት ነክ ዜና በአሜሪካው የ ደቡባዊው የሲያትል ግዛት ውስጥ በጥቁሩ የሰብ አዊ መብት ተማጋቹ በማርቲን ሉተር ኪንግ ጎዳና አቅራቢያ የሚገኝ ንብረትነቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሆነው የደብረ ምህረት ቅዱስ ሚካአል ህንጻ ቤተክርስቲያን ባለፈው የካቲት 2 / 2016 እኤ አ ከጠዋቱ 7 ፡ 30 ኤ ም (በኢትዮጵያ የሰአት አቆጣጠር ከ ጠዋቱ 1፡ 30 ) አካባቢ በዋናው በር ላይ በተለኮሰበት እሳት መጠነኛ ጉዳት የደረሰበት መሆኑን የከተማው ፖሊስ አስታውቋል።

አንድ የቤተክርስቲያኑ ካህንን ዋቢ ያደረገው የፖሊስ እና የኮሞ ኒውስ የተባለው ድህረ ገጽ ዘገባ እንዳተተው ከሆነ በቤተክርስቲያኑ የፊት ለፊት በር ላይ በሩን ዘወትር በጸሎት ወቅት ገርበብ ለማድረግ የተሰቀለው መጋረጃ ላይ የተለኮሰው እሳት የበሩን የውጪ አካል እና ኮርኒሱን ከማቃጠሉ በስተቀር በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት አለማድረሱ ታውቋል። ፖሊስ የእሳት ቃጠሎው ሆነ ተብሎ መደረጉን ፍንጭ የሰጠ ሲሆን የቃጠሎው ትክክለኛ መንሰኤ በቤተክርስቲያኒቱ እና ልጆቿ ላይ ያነጣጠረው በተለይ በውጪው አም በሚኖረው ማህበረሰባችን ዘንድ እየተሰፋፋ የመጣው የዘውግ ተኮር ፖለቲካዊ ጥላቻ እና ፍጹም ኢ -ክርስቲያናዊ የሆነው “የእነ ኣባ እገሌ ደጋፊ እና የእነ እባ እገሌ ተቃዋሚ “ የሚለው እኩይ መንፈስ ውጤት ሰለ መሆኑ በውል አልታወቀም። ፖሊስ ከቃጠሎው ጋር በተያያዘ መርመራ በማድረግ ላይ ከመሆኑን ውጪ ተጠርጣሪዎች ሰለመያዛቸው ለጊዜው ያለው ነገር የለም።

ህብር ሬድዮን በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ ከ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *