Hiber radio: የኢትዮጵያ ቅርስ የሌባ ሲሳይ እንዳይሆን-ከእስራኤል ግልጽ ደብዳቤ ለአቡነ ማቲያስ

አቡነ ማቲያስ፣ ቴዎድሮስ አድሃኖም በእየሩሳሌም ዴር ሱልጣንን ሲጎበኙ
አቡነ ማቲያስ፣ ቴዎድሮስ አድሃኖም በእየሩሳሌም ዴር ሱልጣንን ሲጎበኙ

በእስራኤል የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አቤት እያሉ ነው።ለምልክት የቀሩ በእስራኤል የሚገኙ የአገሪቱ ቅርሶች ለታሪክና ለአገር ክብር በሌላቸው ወገኖች የኪስ ማደለቢያ ከመሆኑ በፊት እንድረስ እያሉ ነው። ግልጽ ደብዳቤያቸው ለአቡነ ማቲያስ ይሁን እንጂ አቤቱታው ለሁሉም ወገን ቅርስህን ጠብቅ በጋራ አቤት በልም ይመስላል። የደብዳቤውን ሙሉ ቃል እነሆ፡-

የካቲት 17ቀን 2008 ዓ. ም.

ግልፅ ደብዳቤ ለአባ ማቲያስ

ለአባ ማቲያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቀ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳሳት ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ብፁዕ አባታችን

ከኢትዮጵያ ቀጥሎ በእስራኤል ሀገር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቀደም ሲል አባቶቻችንና እናቶቻችን አበርከተው ያለፉት ታላቅታሪክና ቅርስ እንዳላት ይታወቃል። እርስዎም በቦታው በተለያዩ ጊዚያት በኃላፊነት አገልግለዋል። በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ሆነው ከመሾመዎት በፊት በእየሩሳሌም የገዳማቱ ሊቀ ጳጳስ በመሆን እንዳገለገሉ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው።

ብፁዕ አባታችን

በእረሩሳሌም የገዳማቱ ሊቀ ጳጳስ ሆነው በሚያገለግሉበት ወቅት የተለያዩ ችግሮች ገጥመውዎት እንደነበረ ህዝበ ክርስቲያኑም ሆነ በእስራኤል ጋዜጦች ጉዳዮን የተመለከቱ ሰዎች በግልፅ ያውቁታል። ሆኖም ግን አሁን ባሉበት የኃላፊነት ደረጃ ሁሉንም እያወቁ፤ ያንን ሁሉ ችግር የፈፀሙ ወንጀለኞች ለፍርድ መቅረብ ሲገባቸው ቤተክርስቲያኗን በእነሱ መዳፍ አስገብቶ ምእመኑ እንዲርቅ እና መነኮሳቶችም እንዲሰደዱ ማድረግ እራሱ በቤተ ክርስቲያኗ ላይ ክህደት መፈጸም እንደሆነ ሊያውቁት ይገባል።

ይህንን የማሳሰቢያ ደብዳቤ ለመጻፍ ያነሳሳን ጉዳይ እንደሚከተለው ነው።

  1. ከላይ እንደተገለፀው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በእየሩሳሌም በርካታ ይዞታ ያላት በመሆኑ ከቤቶቹ ኪራይ ብቻ በወር ከ$100,000 (ከመቶ ሺህ የአሜሪካን ዶላር)በላይ ገቢ ያላት ሲሆን ፤ ከሁሉም የሚያሳዝነው ከዚህ ቀደም በመጋቢነት የገዳሙን ንብረት ሲራስተዳድሩ የነበረናበመቶ ሽህዎች የሚቆጠር ዶላሮችለግል ጥቅምበማዋል የቤተክርስቲያንን እምነት ያጎደሉ አባ ፍስሐ ጽዮን የተባሉ ‘መነኩሴ’ በድጋሜ ከአንድ ወር በፊት መጋቢነቱን ኃላፊነት ተረክበዋል።
  2. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ገዳማት ከእየሩሳሌም ውጭ በቤተልሔም፣ በአልአዛር እንዲሁም በኢያሪኮ ይገኛሉ። የተለያዮ መነኮሳት እየተዘዋወሩ በሁሉም ገዳማት ያገለግላሉ። ሆኖም በእርስዎ አስተዳደር ዘመን አባ ተስፋ ህድጎ የተባሉት ‘መነኩሴ’ የገዳሙን አሰራር በመቃረንና አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆን ቤተክርስቲያንን በማራከስ፣ ስም በማጉደፍ፣ በመክሰስ እንዲሁም መነኮስትን በመበጥበጥ ከዛም አልፎ የገዳሙን ጥቅም የሚጎዳ ተግባር ላይ ከመሰማራታቸው በላይ ገዳሙንም ጥለው ወጥተው እንደነበረ አይዘነጋዎትም። በብዙ ምእመናንና መነኮሳት ዘንድምበሚያደርጉት መንፈሳዊነት የጎደለው ስነምግባራቸው የተነሳ ተቀባይነት እንደሌላቸውም እውነቱን ያውቁታል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሁኑ ሰዓት አባ ተስፋ በገዳሙ ውስጥ በንብረት ኃላፊነት ከመቀመጣቸውም በላይ ከአገር ቤት ለገዳሙ አገልጋዮችን ለመምረጥወደ ኢትዮጵያ መጥተው ነበር። ምን አይነት አገልጋዮችን በምን መስፈርት ሊያመጡ ይሆን የሚለው ስጋት በምእመኑም ሆነ በመነኮሳቱ ዘንድ እንዳለ ሆኖ፤ በእስዎም በእየሩሳሌም የአገልግሎት ዘመን አባ ተስፋ ምን ያህል አመፅን ይወዱ እንደነበር ያውቃሉ።

ሌላው ትልቁ አሳሳቢ ችግር ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ገዳምበእየሩሳሌም የወቅቱ ሊቀ ጳጳስ አባ ዕንባቆም በእነዚህ ወንጀለኞች ቀጥጥር ሰር ወድቀው ገዳሙን ለማስተዳደር እንደተሳናቸውና በፍርሃት እንደሚኖሩ የአደባባይ ምስጢር ነው። እነዚህ ወንጀለኛ መነኮሳት ጳጳሱን አስገድዶም ሆነ አታልሎ በማስፈረም የፈለጉትን ወንጀል መስራት የሚችሉበት ሁኔታ የተፈጠረ መሆኑ በዚሁ አጋጣሚሊታወቅ ይገባል።

በተለይ ደግሞ አባ ተስፋና አባ ፍስሐ በግላቸው ግጭት ውስጥ የነበሩ ሲሆን በግል ቅራኒያቸውን በፈቱበት ጊዜ በእስራኤል ፍርድ ቤት የተያዘውንየቤተክርስቲያኗን ገንዘብ የማጉደል ወንጀል ክስ ፋይል ሊዘጉ ሞክረው፤ እርስዎ የክሱ ፋይል እንዳይዘጋ ማድረግዎ ይታወሳል። አሁን በአጽንኦየምናሳስብዎ ካለዎት ኃላፊነትና ለጉዳዩ ቅርብነት አንፃር፤ እዚህ እየሩሳሌምውስጥ በቤተክርስቲያን ላይ በግልፅ የሚያውቁት የተፈፀመ ወንጀልላይ በአፋጣኝ እርምጃ እንዲወስዱና እየተፈጠረ ያለውን ተጨማሪ ጥፋት ሊያስቆሙ ይገባል። እነዚህ ወንጀለኞች ቅጣት እንጅ ሹመት አይገባቸውም።

እርስዎም የእምነቱ ተከታይ ምእመናን ክብሩ የተጠበቀ መንፈሳዊ አባት ማየት እንደሚፈልግ ሲገልፁ የነበሩ አባት ነዎትና የጉዳዩን አሳሳቢነት ከግምት አስገብተው አፋጣኝእርምጃዎን እንሻለን።

ጉዳዩ ያሳሰበን መነኮሳትና ምእመናን በህብረት

ከሀገር እስራኤል

ግልባጭ

  1. ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት
  2. ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት
  3. በእየሩሳሌም የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን ገዳም
  4. ለማኅበረ ቅዱሳን
  5. ለሚመለከታቸው መገናኛ ብዙኀን

ህብር ሬድዮን በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ 01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *