Hiber Radio: ኢትዮጵያ ወዴት?

confussing_trafic_light_Girma_moges_01_hiber_radio

ግርማ ሞገስ

ማክሰኞ መጋቢት 6/2008 (Tuesday March 15/2016)

የዛሬው ያረጀ አምባገነናዊ የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት እንደ ትናንቱ ታላቅ ወንድሙ የደርግ መንግስት የኢትዮጵያችንን የነገ ተረካቢዎች ህጻናት እና ወጣቶች እያሰረ እና በጥይት እየገደለ የስልጣን ዘመኑን ማራዘም ብልህነት አድርጎ ተያይዞታል። 100% መርጦኛል የምትለውን ህዝብ እየገደልክ በስልጣን ላይ መቆየት አትችልም። ያረጀው ወጣቱን እየበላ የሚኖርበት ዘመን በኢትዮጵያችን ማክተም አለበት። ወጣቱ አገሩን ካረጀው ህወሃት/ኢህአዴግ መንጋጋ ፈልቅቆ በመውሰድ ማስተዳደር መጀመር አለበት። ሰላማዊው ትግል ገና መጀመሩ ነው። እገሌ ከገሌ ሳንል በአገር ውስጥ እና በውጭ የምንኖር የአገር ሽማግሌዎችም ሆነን ተቃዋሚ ፓርቲዎች የወጣቱ ምኞት ይሳካ ዘንድ ተገቢ የአጋዥነት ሚናችንን ልንጫውት ይገባል። ለማንኛውም ይህቺ አጭር ጽሑፍ ባለፉት አራት ወሮች በኢትዮጵያችን ሰላማዊ አቤቱታ በማሰማታቸው እና ሰላማዊ ተቃውሞ በማድረጋቸው ብቻ በኦሮሚያ ክልል በጥይት ሕይወታቸውን ለተነጠቁ ህጻናት እና ወጣቶች ማስታወሻ/መታሰቢያ ትሆን ዘንድ ምኞቴ ነው።!

ኢትዮጵያ ወዴት? በሚለው ጥያቄ ዙሪያ ውይይት እንድከፍት ያነሳሳኝ ኢትዮጵያችን ባለፉት አራት ወሮች ያደረገችው የለውጥ እንቅስቃሴ፣ እንቅስቃሴውን በመምራት ላይ ያሉት ወጣቶች የምር ስራ ላይ መሆናቸው እና የህዝባችን ብስለት ተደማምረው ነው። በሰፊው እንደሚታወቀው ባለፉት አራት ወሮች የኦሮሚያ ወጣት ሳይገድል እየሞተ የለውጥ አስፈላጊነትን በሰላማዊ ተቃውሞ መፈክሮቹ ሲያሰማን ቆይቷል። ዛሬ በህይወት የሊሉትም የለውጥ ጥሪ ድምጻቸው ይሰማናል። እንግዲህ በአንድ አገር ባለፉት አራት ወሮች ያስተዋልነው አይነት በአይን የሚታይ፣ በጆሮ የሚሰማ፣ በእጅ የሚዳሰስ አልፎም በህልም ሳይቀር የሚመጣ የለውጥ እንቅስቃሴ ሲፈጠር ማንኛውም አገሩን እና ህዝቡን የሚወድ ዜጋ በጭንቅላቱ እና በህሊናው “ወዴት እየሄድን ነው?” የሚለው ጥያቄ መመላለሱ የማይቀር ነው። የዚህ ጽሑፍ ግብም በዚህ ጥያቄ ዙሪያ የኢትዮጵያን የቀድሞዎቹን የለውጥ እንቅስቃሴዎች በአጭሩ በማስታወስ እና የዛሬውን የለውጥ እንቅስቃሴ በመመርመር “ወዴት እየሄድን ነው?” ለሚለው ጥያቄ አንባቢን ሊያወያይ የሚችል መልስ መስጠት ነው። በተጨማሪ ይህ ጽሑፍ በመኪያሄድ ላይ የሚገኘውን የሰላማዊ ትግል አቅም ውቂያኖስነት ያመላክታል። የሰላማዊ ትግሉን ደህንነት እና ቀጣይነት ዘላቂ ሊያደርጉ የሚችሉ ጥቂት ምክሮችንም ይሰነዝራል።

 

ኢትዮጵያ ባለፈው በ20ኛው እና አሁን በያዝነው በ21ኛው ክፍለ ዘመን ለለውጥ በርካታ እንቅስቃሴዎች አድርጋለች። በኢትዮጵያችን በግልጽ የሚታይ እና የሚጨበት የፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት እንቅስቃሴ የተጀመረው በ1950ዎቹ በመንግስቱ ንዋይ በተመራው መፈንቅለ መንግስት እና መፈንቅለ መንግስቱን ደግፎ እና ዘውዳዊውን አገዛዝ ተቃውሞ በአዲስ አበባ መንገዶች ሰላማዊ ሰልፍ ባደረገው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ነበር ማለት ይቻላል። የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ መሬት ለአራሹ፣ የብሔር እኩልነት፣ ህዝባዊ መንግስት፣ የመናገር፣ የመጻፍ፣ የመሰብሰብ ወ.ዘ.ተ. መብቶች የሚሉትን የመብት መከበር ጥያቄዎች መፈክር ቀርጾ ቀደም ብለው የነበሩትን ጭቆናዎች ተከታታይ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፎች በማድረግ ለህዝብ አስተዋወቀ። ይህን በማድረጉ የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ በርካታ አባላቱን ለዘውዳዊው አገዛዝ የጸጥታ ኃይሎች ጥይት ከፍሏል። የዚሁ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ውጤት የሆኑት በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያ አንጋፋዎቹ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኢሕአፓ እና መኢሶንም የዴሞክራሲ ሽግግርን ጥያቄ አንስተው አንድ ትውልድ ከፍለዋል። ሻቢያ፣ ኦሌፍ እና ህወሃትም ይኸው የተማሪዎች እንቅስቃሴ የወለዳቸው ተቃዋሚ ድርጅቶች ናቸው። ያም ሆነ ይኽ ዘውዳዊውን አገዛዝ የገረሰሰው ህዝባዊ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ድል ፍሬ በአውሬው ወታደራዊ ደርግ ተሰረቀ። በዚህ አይነት እስከዚህ ድረስ የተደረጉት እንቅስቃሴዎች የተፈለገውን የፖለቲካ ለውጥ አላመጡም። ከዚያ ከደርግ ወደ ህወሃት/ኢህአዴግ የተደረገው የመንግስት ስልጣን ሽግግር ወደ ነፃነት እና ዴሞክራሲ ሽግግር ያመራል የሚል ተስፋ በብዙ ወጣቶች ዘንድ ፈጥሮ ነበር። እሱም ሳይሆን ቀርቷል። በቅርቡ ደግሞ በምርጫ 97 ሰላማዊ የፖለቲካ ስርዓት ለውጥ ሽግግር ቢሞከረም በአንድ በኩል በህወሃት/ኢህአዴግ ስልጣን ጥመኛነት እና በሌላ በኩል ደግሞ በተቃዋሚው መካከል ህብረት አለመኖር፣ የድል ሰብሳቢነት ልምድ አልባነት እና የሰላማዊ ትግል ቀጣይነት ባህል ማጣት ተደማምረው የተገኘው መለስተኛ ድል ሳይቀር ባክኖ በምትኩ በቆሻሻው መለስ ዜናዊ የሚመራ ፍጹም አምባገነንነት ሌባ መንግስት በኢትዮጵያ ነግሷል። እነዚህ ሁሉ በወጣቶች የተመሩ እንቅስቃሴዎች የፖለቲካ ምኞታቸውን (ግባቸውን) ተፈጻሚ ማድረግ ባይችሉም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ብሩህ ወጣቶችን በመስዋትነት ከፍለው ሄደዋል።

በየዘመኑ በስልጣን ላይ የነበሩት አምባገነኖች የስልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም ሲሉ የለውጥ ጥያቄ ያነሳውን ወጣት ቢፈጁም በሚያፈቅሩት ስልጣን ላይ ብዙም ሳይቆዩ እነሱም ጠፍተዋል። ካለፈው ስህተታቸው መማር አለመቻል የአምባገነኖች ሁሉ የጋራ ባህሪያቸው መሆኑን ታሪክ ደግማ ደጋግማ ታስተምራለች። እነሱም ደግመው ደጋግመው አይማሩም። ስለዚህ ዛሬም በስልጣን ላይ የሚገኘው አምባገነናዊ የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት እንደ ቀድሞው በመንግስቱ ኃይለማሪያም ሲመራ እንደነበረው አምባገነኑ ደርግ ስልጣን ከያዘ ወዲህ ባለፉት 22 አመቶች ግድም ውስጥ ቀደም ሲል በፍጹም አምባገነኑ ሟቹ መለስ ዜናዊ መሪነት አሁን ደግሞ በቀጣዩ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ መሪነት ሰላማዊ አቤቱታ እና ሰላማዊ ተቃውሞ በማሰማታቸው ብቻ በየአደባባዩ በጥይት አንደበታቸውን የተነጠቁ (የተገደሉ) ወጣቶች ቁጥር ጥቂት አይደለም። ጥቂት ልጥቀስ። እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1994 ዓ.ም. የኤርትራ ሬፌረንደም በሰላማዊ መንገድ በመቃወማቸው ወጣቶች በህወሃት/ኢህአዴግ ጥይት ተደብደበዋል። በ2001 ዓ.ም. ድህረ ኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትን ተከትሎ የተደረገውን ስምምነት በመቃወማቸው ወጣቶች በህወሃት/ኢህአዴግ ተደብድበዋል። የ2005 (እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር 1997) ምርጫን ተከትሎ በሰላማዊ መንገድ የህዝብ ድምጽ ይከበር በማለታቸው ብቻ ሰላማዊ አቤቱታቸው እንደ ወንጀል ተቆጥሮባቸው በህወሃት/ኢህአዴግ ጥይት ወጣቶች በግንባራቸው ሳይቀር በጥይት ተደብድበዋል። በየአደባባዩ የተረሸኑት ወጣቶች አይረሱንም። በ2014 (እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በህዳር ወር 2008) ዓ.ም. ጀመሮ የኦሮሚያ ወጣቶች ማስተር ፕላኑን በመቃወማቸው፣ የኦሮምኛ ቋንቋ የኢትዮጵያ የፌዴራል መንግስት የስራ ቋንቋ ይሁን በሚል በጀመሩት ሰላማዊ አቤቱታ እና ተቃውሞ የአምባገነኖችን ጥይት በግንባር፣ በአንገት፣ በደረት እና በቀረ አካላቸው እየተቀበሉ እንዲወድቁ መደረጋቸው ትኩስ ሐዘናችን ነው። የኢትዮጵያን ወጣት የነፃነት እና የዴሞክራሲ ጥም በግድያ ማቆም እንደማይቻል የማይማሩት አምባገነኖች ብቻ ናቸው።

በነፃነት እና በዴሞክራሲ መኖር የአሜሪካኖች ወይንም የእንግሊዞች ወይንም የአውሮፓውያን ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የሰው ዘር ሁሉ ምኞት እና ፍላጎት ነው። አለም አቀፋዊ መስፈርትን የሚያሟሉት ሃሳብን የመግለጽ፣ የመደራጀት፣ የመቃወም፣ መሪዎችን የመምረጥ ነፃነቶች በኢትዮጵያ የሉም።! ልብ በሉ! እነዚህ ነፃነቶች “ለሶስት ሺ አመት ‘ነፃነቷ’ ተከበሮ የኖረች ኢትዮጵያ” የምንለው አይነት “ነፃነት” አይደሉም። እነዚህ ነፃነቶች ጎረቤት ኤርትራን የሚያስተዳድረው ሻቢያ የሚለፍፈው አይነት “ነፃነትም” እንዳልሆኑ ልብ በሉ። እነዚህ ነፃነቶች የመናገር፣ የመቃወም፣ የመደራጀት፣ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ተሰብስቦ ተቃውሞ ማሰማትን፣ ወ.ዘ.ተ. የመሳሰሉትን ያካትታል። ለነዚህ ነፃነቶች መኖር ደግሞ ዴሞክራሲ የግድ መኖር አለበት። ዴሞክራሲ ከሌለ ሃሳብን የመግለጽ፣ የመደራጀት፣ የመቃወም፣ መሪዎችን የመምረጥ ነፃነቶች አይኖሩም። እነዚህ ነፃነቶች እና ዴሞክራሲ አይነጣጠሉም። ስለዚህ በነፃነት እና በዴሞክራሲ ስርዓት መተዳደር የኢትዮጵያውያንም ምኞት እና ፍላጎት በመሆኑ ላለፉት አርባ እና ሃምሳ አመታት በተከታታይ የመጣ የኢትዮጵያ ወጣት ትውልድ እነዚህን ጥያቄዎች አንስቷል።

 

በኦሮሚያ ክልልም ወጣቶች ያነሷቸው ጥያቄዎችም የተለዩ አይደሉም። የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት ይከበር፣ የዜጎቿን ሰብዓዊ መብቶች ይከበሩ፣ የዜጎች የመናገር፣ የመቃወም፣ የመምረጥ፣ የዴሞክራሲ መብቶች ይከበሩ የሚሉ ናቸው። ኢትዮጵያ የህግ-በላይነት የሚከበርባት እና የዜጎቿን መብት የምታከብር አገር እንድትሆን የሚጠይቁ ናቸው። እነዚህ ጥያቄዎች ኢትዮጵያችንን ወደ ኋላ የሚጎትቱ ሳይሆኑ ወደፊት፣ ወደ ስልጣኔ የሚገፉ ናቸው። ባለፉት አራት ወሮች እንዳስተዋልነው ከሆነ ለእዚነህ የነፃነት እና የዴሞክራሲ ሽግግር ጥያቄዎች በተለይ በኦሮሚያ ክልል የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ወጣት ያልተመጣጠነ መስዋዕት ከፍሏል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የምንኖር ኢትዮጵያውያን ዳር ቆሞ በመመልከት የምናግዘው የአምባገነኖች የገዢነት ዘመን መሆኑን የምር ልብ ልንለው የሚገባ ጉዳይ ነው። አምባገነኖች ችግሩን ይበልጥ አወሳስበው ኢትዮጵያችንን ይበልጥ ወደ ተወሳሰበ እና ልንፈታው ወደ ማንችለው ችግር ውስጥ ሊከቷት እንደሚችሉ አገር ወዳዶች በሙሉ ከወዲሁ ልናስብበት የማይገባ አብይ ጉዳይ ነው። ዛሬ አምባገነኖች ኦሮሚያን በወታደራዊ እዝ እናስተዳድራልን ማለት ጀምረዋል። ይኽ እርምጃቸው ችግሩን ይበልጥ ማወሳሰብ ነው። አምባገነኖች በተቀነባበረ ህዝባዊ እምቢተኛነት ተገደው ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንዲመጡ እስካልተደረጉ ድረስ ወይንም እንዲሄዱ እስካልተደረጉ ድረስ ቀዳሚ ግባቸው ለሆነው ስልጣን ሲሉ ችግሩን ይበልጥ ማወሳሰባቸው የማይቀር ነው። በኦሮሚያ የተነሳው መጠነ ሰፊ ህዝባዊ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ነገ በአማራው ወይንም በደቡብ ክልል ቢነሳ የአምባገነኖች መፍትሄ እነዚህንም ክልልሎች በወታደራዊ እዝ ማስተዳደር እንደሚሆን ከወዲሁ መገመት ይቻላል። ሁልሽም ተራሽን ጠብቂ መሆኑ ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የምንል አገር ወዳዶች በሙሉ በቻልነው መንገድ እና ባለን አቅም ሁሉ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ልንተባበር ይገባል። ስለዚህ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ህዳር ሁለት 2 ቀን በኦሮሚያ ጊንጪ ከተማ ተጀምሮ ባለፊት አራት ወሮች ውስጥ ወደ ቀረው ኦሮሚያ በመዝመት በወለጋ፣ በአንቦ፣ በጅማ፣ በአርሲ፣ በምስራቅ ሸዋ፣ በምዕራብ ሸዋ፣ በሰሜን ሸዋ፣ በምስራቅ ሐረርጌ፣ በምዕራብ ሐረርጌ፣ በቦረና፣ በባሌ የኦሮሚያ ክልል ዞኖች ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ውስጥ የተቀጣጠለው ሰላማዊ ተቃውሞ ቀጣይነት ሊኖረው እና ወደ ቀረው ኢትዮጵያ እንድ ሰደድ እሳት መቀጣጠል አለበት። ማለትም ሰላማዊው ህዝባዊ እምቢተኝነቱ ይበልጥ ሊሰፋ፣ ይበልጥ ሊቀናበር እና አመትም ይፍጅ ከዚያ በላይ ቀጣይነቱን እንዳያጣ ማድረግ አለብን።

ቀደም ሲል መንግስት በኦሮሚያ የተፈጠረው ተቃውሞ መንስዔው የመልካም አስተዳደር እጦት ነው ሲለን ነበር። ለመሆኑ መልካም አስተዳደር ምንድን ነው? የፖለቲካ መልካም አስተዳደር አለመኖር ህጋዊ በሆነበት አገር ህዝብን በማጭበርበር ጊዜ እያባከኑ የስልጣን ዘመንን ለማራዘም እስካልሆነ ድረስ እንዴት ስለኢኮኖሚ እና ስለ ማህበራዊ ጉዳዮች መልካም አስተዳደር ማውራት ይቻላል። ህወሃት/ኢህአዴግ በተደረጉ ምርጫዎች በሙሉ ስልጣን ላይ መቆየት የቻለው በፖለቲካ ሙስና ድምጽ በመስረቅ ነው። ይህ ደግሞ እራሱ ህወሃት/ኢህአዴግ ይሁን ብሎ ህጋዊ ያደረገው የፖለቲካ መልካም አስተዳደር አልባነት ነው። በዚህ የፖለቲካ ሙስናው ተባብረው በኦሮሚያ በ100% እንዲያሸንፍ ያገዙትን የኦፕዲኦ የፖለቲካ ሹሞች እና ካድሬዎች ዛሬ ዞሮ በመልካም አስተዳደር ማጉደል ቢከሳቸው ኩምክና ከመሆን ያለፈ ለተፈጠረው ችግር መፍትሄ አይሆንም። በዚህ የፖለቲካ ሙስና ተግባሩ ነፃ እና ፍትሃዊ ምርጫ እንዳይደረግ በየክልሉ የሚተራመሱ ፀረ-ነፃነት እና ፀር-ዴሞክራሲ ካድሬዎቹን በየጊዜው በሚደረጉ ምርጫዎች ተቃዋሚዎችን በማዋከብ፣ በማሰር እና ድምጽ በመዝረፍ የፖለቲካ ሙስና ተግባር እንዲተባበሩት ደሞዝ እየከፈላቸው አይዟችሁ ሲላቸው ከርሞ ዛሬ የህዝብ ተቃውሞ ሲፈጠር ተጠያቂዎቹ እነሱ እንጂ እኔ አይደለሁም ማለቱ የንቀቱን መጠን ያሳየናል።

ዐርብ ቀን መጋቢት አንድ 2008 (March 10/2016) ደግሞ የወቅቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ለፓርላማ በሰጡት ማብራሪያ ባለፉት አራት ወራት ውስጥ በኦሮሚያ እና በቀሩት የሃገሪቱ ክልሎች ውስጥ ለተፈጠረው የህዝብ ቅሬታ መንግስታቸው እና ፓርቲያቸው ሙሉ ኃላፊነት እንደሚወስዱ አስታወቁን። ይህ ኃላፊነትን የመቀበል እርምጃ ቀደም ብሎ መደረግ የነበረበት ትክክለኛ የመጀመሪያ እርምጃ ነው። ዘግይቶ በመምጣቱም አንቀበልም ባንልም ቃላቸውን በተግባር መደገፍ አለባቸው። ስለዚህ ፓለቲካዊ ኃላፊነትን በመውሰድ በአገሪቱ ለደረሰው ጥፋት ተጠያቂ የሆኑ የፖለቲካ ሹሞችን ከስልጣን ማባረር አለባቸው። ህጋዊ ኃላፊነትም መውሰድ አለባቸው። ስለዚህ ግድያ የፈጸሙ ወንጀለኞችን ወደ ፍርድ ቤት ማቅረብ፣ ሰላማዊ ተቃውሞ በማሰማታቸው ብቻ ለተገደሉ ወጣቶች ቤተሰቦች ካሳ መክፈል፣ እነ በቀለ ገርባን፣ እነ በቀለ ገና እና የመሳሰሉትን የኦፌኮ መሪዎች፣ አባላት፣ እና ደጋፊዎች እንዲሁም ጉዳዩን በመዘገባቸው የታሰሩ የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን እና የሰማያዊ ፓርቲ አባላትን በፍጥነት መልቀቅን ያካትታል። ችግሩ ግን “ይቅርታ መጠየቅ” እና “ስህተቴን ተቀብያለሁ” ማለት የህወሃት የቅርብ ጊዜ ማጭበርበሪያ ፈሊጥ እየሆነ መምጣቱን ካወቅን ውለን አድረናል። የህወሃት ይቅርታ ማለት አንተም ተቃውሞ አቁም እኔም ወደ ቀድሞ ገዢነት ስራዬ ልመለስ ማለት ነው። በአንድ በኩል ኦሮሚያን በወታደራዊ እዝ አስተዳደር ስር ለማድረግ ሽር ጉድ እያለ በሌላ በኩል “ይቅርታ” ማለት ቅንነትን አያሳይም። ይኽ ሁሉ የህወሃት/ኢህአዴግ ግራ እና ቀኝ እስክስታ የሚያሳየን የተነሳውን ሰላማዊ አቤቱታ እና ተቃውሞ በራሱ አነሳሽነነት ፈቅዶ (ሳይገደድ) በሰላማዊ መንገድ መፍታት ፍጹም ባህሪው እንዳልሆነ ነው። በጫካ ተወልዶ እና ተቃዋሚዎችን በመግደል አድጎ ስልጣን ላይ ከወጣ ወታደራዊ ድርጅት ዴሞክራሲያዊ ጸባዮችን መጠበቅ የለብንም። ላብራራ።

እንደሚታወቀው ህወሃት ወታደራዊ ድርጅት ነው። በጦር ሜዳዎች የገጠሙትን ተመሳሳይ ወታደራዊ ድርጅቶችን TLF (የትግራይ ተወላጆች ድርጅት), EDU, EPRA/EPRP, DERG በጦር ሜዳ ደመሰሰ። የህወሃት መሪዎች እና የTLF (የትግራይ ተወላጆች ድርጅት) መሪዎች አብረው ለመስራት ህብረት ፈጥረናል ተባብለው እራት ከበሉ በኋላ በእምነት በህውሃት ካምፕ በተኙበት በመለስ ዜናዊ ትዕዛዝ በጥይት ተደብድበው የተገደሉት። አረመኔው ህወሃት መንግስት ሊሆን አካባቢ ደግሞ የመንግስት መዋቅር (ዛሬ ፈደሬሽን የሚለንን) እንደሚከተለው አቋቋመ። በህዝብ ቁጥራቸው የሚፈራቸውን ኦሮሞዎችን፣ አማሮችን እና የደቡብ ህዝቦች በሞግዚትነት (በጠባቂነት) የሚገዙለትን (1) ኦፒዲዎ ፣ (2) ቀደም ሲል ከኢህአፓ ተገንጥሎ እራሱን EPDM ብሎ ሲጠራ የነበረው እና በስተኋላ ለTPLF የገበረውን ድርጅት (ብአዴን መሰለኝ የአሁኑ ስሙ?)፣ (3) የደቡብ ህዝቦችን የሚገዛለት (ዛሬ በኃይለ ማሪያም ደሳለኝ የሚመራው) ድርጅት ፈጥሮ እና (4) ህወሃትን ጨምሮ፣ አራቱን ያካተተ ኢህአዴግ የተሰኘ ቡድን ፈጠረ። በተጨማሪ (5) በህዝባቸው ቁጥር የማይፈራቸውን እንደ እነ ቤንሻንጉል፣ አፋር፣ ሶማሌ፣ እና የመሳሰሉትን ህዝቦችን ደግሞ አፍነው የሚገዙለት እንደ አስፈላጊነቱ የሚያነጋግራቸውን ድርጅቶች ደግሞ “አጋር ድርጅቶች” ብሎ ሰየማቸው። በዚህ አይነት ፌዴሬሽን ፈጠርኩላችሁ ብሎ ህወሃት ኢትዮጵያን ጠቅሎ በመግዛት ላይ ይገኛል።

የፈደሬሽን የሚለው አወቃቀር ትርጉም ከሞላ ጎደል አገርን በጋራ ማስተዳደርን አካባቢን ደግሞ ህዝቦች በግላቸው እንዲያስተዳድሩ የሚያስችል ዴሞክራሲን ከላይ ወደ ታች የሚያደርስ የፖለቲካ አወቃቀር ነው። በሃቀኛ ፈዴሬሽን የፌዴራል መንግስት በየመንደሩ በካድሬዎች አማካኝነት ህዝብን የሚያሰቃይበት ምክንያት አይኖርም። የህወሃት ፌዴሬሽን ግን በዘር ከፋፍሎ የመግዣ መዋቅር ሲሆን በዚህ ላይ በ 1 ለ 5 የተሰኘው ጠርናፊ መዋቅር ጨምሮበት ህወሃት እስከ ቤተሰብ ድረስ ፖለቲካዊ ቁጥጥር ማድረግ ችሏል። ደርግ እስከ ቀበሌ ድረስ ብቻ ነበር ህዝብን የሚቆጣጠረው። ህወሃት ግን ከደርግ ዘመን የከፋ አምባገነናዊ የፖለቲካ ማዕከላዊ አገዛዝ ስርዓት በኢትዮጵያ አስፍኖ ኢትዮጵያን ህዝብ እስከ ቤተሰብ ደረጃ ወርዶ አፍኖ በመግዛት ላይ ይገኛል። ስለዚህ የህወሃት/ኢህአዴግ ፈዴሬሽን መለወጥ አለበት። 1 ለ 5 የሚለውም ጠርናፊ መዋቅር መፍረስ አለበት።

ከፍ ብለን እንዳነበብነው ህወሃት ስልጣን ላይ የወጣው በምርጫ ሳይሆን በጠበመንጃ ነው። ምርጫ የሚባለው ጣጣ ውስጥ የገባውም ወዶ ሳይሆን ተገዶ ነው። ከሶቪየት ህብረት ውድቀት በኋላ ምዕራቡ (አሜሪካ እና ምዕራብ አውሮፓ) ነፃ ፉክክር እና ምርጫ አዲሱ የአለም ስርዓት ነው በማለታቸው እርዳታቸው እና ድጎማቸው እንዳይለየው ሲል የማይተዋወቀውን እና የማያምንበትን የብዙሃን ፓርቲ እና የምርጫ ፖለቲካ ስርዓት ተቀብያለሁ አለ። ከዚያ በምርጫ ህዝቡ ከስልጣን እንዳያወርደው ህወሃት/ኢህአዴግ ስልጣን ላለመልቀቅ ሙሉ በሙሉ በፖለቲካ ሙስና ተሰማራ። ነፃ ምርጫ ለማድረግ አስፈላጊ የሆኑትን ሶስቱን የመንግስት ቅርንጫፎች ጠቅሎ ያዘ፣ ነፃ ፕሬስ እንዲዳከም ወይንም እንዳይኖር አደረገ፣ የምርጫ ቦርድ ፈጣሪም እሱ ሆነ። ስለዚህ ህወሃት/ኢህአዴግ በየአምስት አመት በግንቦት ወር በኢትዮጵያ የሚደረገውን ምርጫ እንደ ጦር ሜዳ ወሰደው። በዚህ ላይ የቃዋሚ ህብረት የለም። በምርጫ ከተሳተፈ በኋላ ዛሬ በኦሮሚያ እንደምናየው ህዝባዊ እንቢተኛነት በመቀስቅስ “ድምጽ ማስከበር” የሚችል ህዝብ መፍጠር ባለመቻላችንም ታግዞ ህወሃት/ኢህአዴግ ተቃዋሚዎች ያገኙቱን ድምጽ በኃይል እየዘረፈ በምርጫ 2002 ዕ.ም. በ99.7% በቅርቡ በምርጫ 2007 ዓም ደግሞ በ100% አሸነፍኩ አለን። በጠብ መንጃ አዲስ አበባን ሲይዝ አንተ ማነህ? ያለው እንደሌለ ሁሉ ድምጽ ማስከበር የሚችል ህዝብም ሆነ ተቃዋሚ ፓርት ባለመኖሩ ከምርጫዎች በኋላም አንተ ማነህ? ሳንለው ይኸው እስከ ዛሬ ስልጣን እንደጨበጠ ይገኛል። የተቃዋሚዎች ህብረት ቢኖር እና ዛሬ በኦሮሚያ የሚገኙት ወጣቶች ከሚያደርጉት ጋር ተመሳሳይ ህዝባዊ እምቢተኛነት በማድረግ “ድምጽ ይከበር” የሚል ህዝባዊ እንቅስቃሴ በመፍጠር ድምጹን ማስከበር የሚችል ህዝብ ቢኖር ኖሮ ሁኔታውን ለመቀየር ይሞከር ነበር። ዛሬ በኦሮሚያ መሚኪያሄድ ላይ የሚገኘው ህዝባዊ እምቢተኛነት እግረ መንገዱን ከምርጫም በኋላ ድምጹን የሚያስከብር ህዝብ ይፈጥራል የሚል እምነት አለኝ። የምርጫ 2007 ዓ.ም. ምርጫ 100% አሸናፊነት የኢትዮጵያን ወጣቶች አስመርሯል። በቃን አሰኝቷል። አውቀው ሲታለሉለት ከከረሙት ለጋሾቹ (ሸሪኮቹ) ምዕራባውያን ውስጥ እንኳን አንዳንዶቹ አሁንስ አበዛኸው ብለዋል። እውነት ነው። ህወሃት/ኢህአዴግ በስብሷል። መሄድ አለበት። በአገር ውስጥ እና በውጭ የሚገኙ ተቃዋሚዎችን በሙሉ ያካተተ ሁሉን አቀፍ ህብረት መፈጠር ያስፈልጋል። ቢቻል ኢህአዴግን እና ህወሃት/ኢህአዴግ “አጋር” የሚላቸውን ድርጅቶችም ያካተተ። ካልሆነም ከህወሃት/ኢህአዴግም ሆነ ከአጋር ድርጅቶቹ ውስጥ ተራማጅ የሆኑቱን ግለሰቦች ያካተተ። ይኽን ማድረግ ሽግግሩን ሊያቀል ይችላል። የገዢው ፓርቲ አባላት በሽግግሩ ወቅትም ሆነ እና ከሽግግሩ በኋላ በሰላም በአገራቸው መኖር እንደሚችሉ እንዲሰማቸው ማድረግ ያስፈልጋል። ስለዚህ ገዢው ፓርቲም ሆነ የወቅቱ ባለስልጣኖች ያላቸው የተሻለ አማራጭ ከተቃሚው የሽግግር ህብረት ጋር መተባበር ብቻ መሆኑን በውይይት እንዲገነዘቡ ማድረግ ያስፈልጋል።

እርግጥ ነው ለሁሉም አገር የሚሆን የተቃዋሚ ፓርቲዎች ህብረት መፍጠሪያ አንድ አይነት ቀመር (ፎርሙላ) የለም። ከታሪካችንም እንደምንረዳው የፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት እና ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር መውሰድ እና ማስፈጸም የሚያስችል ህብረት መፍጠር እጅግ ፈታኝም አስሸጋሪም ጉዳይ ነው። የዴሞክራሲ ሽግግር የከሸፈባቸውም ሆነ የተሳካ ሽግግር ያደረጉ አገሮች ታሪክም የሚያስተምረን ህብረት መፍጠር ቀላል እንዳልሆነ ነው። ህብረት ለመፍጠር የዴሞክራሲ ሽግግር መሪዎች በትንሹ፥ አርቆ አስተዋይነትን፣ ብዙ ውጣ ውረድን፣ የእነ ቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ መሆኑን መረዳትን፣ ረዘም ያለ እና ቀጣይነት ያለው ጥረት ማድረግን፣ የድርድር ክህሎት አቅም መገንባትን፣ ሰጥቶ በመቀበል መርህ መመራትን እና የመሳሰሉትን እልህ አስጨራሽ ስራዎች ይጠይቃል። በዚህ አይነት የሚደረስ ስምምነት እና የሚፈጠር ህብረት (coalition) እያንዳንዱ ድርጅት ትንሽ ሰጥቶ እና ትንሽ አግኝቶ የሚፈጠር ህብረት ይሆናል። በዘውዳዊው፣ በደርግ እና በህውሃት/ኢህአዴግ እንዲሁም በምርጫ 97 የተፈጠሩ ጥሩ የለውጥ እና የዴሞክራሲ ሽግግር አጋጣሚዎች ባክነዋል። አሁን የተፈጠረው የፖለቲካ ለውጥ እንቅስቃሴ እንደቀድሞዎቹ አጋጣሚዎች ሳይባክን ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር እንዴት መግባት እንደሚቻል ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል። ወጣቶቹን ማዘዝ ሳይሆን ልንተባበራቸው እና ልናግዛቸው ይገባል።

ህብረት (coalition) ሲባል የፓርቲዎች ውህደት ሳይሆን በተያዘው የለውጥ እንቅስቃሴ ብሎውም በዴሞክራሲ ሽግግር ዙሪያ በሚቀረጽ የጋራ አጀንዳ ዙሪያ ብቻ ተባብሮ አብሮ ለመስራት የሚፈጠር ቡድን ነው። ውህደት ለረጅም ጊዜ በትናንሽ ጉዳዮች ላይ ተጋግዞ በመስራት የሚፈጠር ትውውቅን እና መተማመንን ቅድሚያ ይላል። በጋራ መስራት የሚቻሉ ነገሮችን ለይቶ አውጥቶ በእነሱ ዙሪያ ተሰባስቦ ተጋግዞ አብሮ የመስራት ባህልን መገንባት ቅድሚያ ይላል።

በመጨረሻ የሰላማዊ ትግሉን ደህንነት በመጠበቅ ረገድ ጥቂት ምክሮችን በመለገስ ጭቅጭቄን ላብቃ፡፡

(1) በስልጣን ላይ የሚገኘው አምባገነን ቡድን የተቃዋሚ መሪዎችን እና ብሩህ ለውጥ ተመኚ ወጣቶችን የሚገድለው እና የሚያስረው የሰላማዊውን ትግል ጭንቅላት በመቁረጥ ትግል ለመግደል እንደሆነ ልንዘነጋ አይገባም። ገዢው ቡድን ያሰበው እንዳይሳካለት ለማድረግ አንደኛው መድሃኒት የሰላማዊ ትግል እውቀት በማስፋፋት አዳዳሲ መሪዎች እና የሰላም ትግሉ ሰራዊት እንዲያድገ ማድረግ ነው። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣቶች የሰላማዊ ትግል እውቀት በቀጣይነት እንዲቀስሙ ማድረግ ከቻልን በስልጣን ላይ ላለው አምባገነን ቡድን ፈተናውን እናበዛበታለን ማለት ነው። ህወሃት/ኢህአዴግ ሰላማዊ ትግልን አለማወቁ ብቻ ሳይሆን በየጊዜው በሚሊዮኖች የሚፈጠሩ ወጣቶችን ማሰር አይችልም። ስለዚህ ሰላማዊው ትግል ቀጣይነት ይኖረዋል። ሁለተኛው መድሃኒት ደግሞ የታሰሩት የሰላማዊ ትግል መሪዎች እና ታጋዮች በፍጥነት እንዲፈቱ ጥያቄያችን ማቋረጥ የለብንም። በዚህ ረገድ በተለይ በውጭ የምንኖር ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ መንግስት ሸሪኮች እና ለጋሽ የምዕራቡ መንግስታት ከተሞች ሰልፎች በመውጣት የዲፕሎማሲ ጫና ማድረግ እንችላለን።

(2) ጥሩ የሰላማዊ ትግል እውቀት ያላቸው እና በየጊዜው በምድር ላይ ለሚፈጠሩ ችግሮች በፍጥነት መልስ እየሰጡ ሰላማዊ ትግሉ ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ የሚችሉ መሪዎች ሊኖሩ ይገባል።

(3) ዛሬ ቴክኖሎጂ የዴሞክራሲ ሽግግርን በከፍተኛ ደረጃ እየረዳ ነው። በእጅ ስልክ በሚሰራጩ አምባገነናዊ ጭፍጨዎች ብቻ የአለምን ህብረተሰብ ሃሳብ ማስቀየር እና በአገር ውስጥ እና በለጋሽ አገሮች መዲናዎች ትላልቅ ሰላማዊ ተቃውሞች መቀስቀስ ይቻላል። የሰላማዊ ትግል ሰራዊት የእጅ ስልኩን በመጠቀም ዜና ዘጋቢም ሊሆን ይችላል ማለት ነው። ስልጠና መስጠት ሊያስፈልግ ይችላል። እርግጥ ቴክኖሎጂ ብቻውን ህያው ሰዎችን አይተካም። ዜናዎቹን ለማብራራትም፣ ለድርድርም፣ ተቋሞችን ለመመስረት እና ለመገንባት እና ለበርካታ ጠቃሚ ተግባሮች በሰላም ትግል የሰለጠኑ ታታሪ መሪዎች ያስፈልጋሉ። አጀንዳዎች እና መፈክሮች መቅረጽ፣ ፓርቲ መገንባት፣ ህብረት (coalition) መፍጠር፣ ፕሮግራሞች እና ፖሊሲዎች ለመቅረጽ ብሎም ለማሰራጨት፣ ህዝብ በዴሞክራሲ ሽግግር እንዲያምን እና ተሳታፊ ለማድረግ እና ለመሳሰሉት ወሳኝ ስራዎች በሙሉ ብቃት ያላቸው የሰላማዊ ትግል መሪዎች ያስፈልጋሉ።

(4) ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ፍርሃትን ማስወገድ ወይንም ፍርሃትን መቆጣጠር መቻል የመጀመሪያ ጉዳይ ነው። በሰላማዊ ትግሉ መሳተፍ ሊያስከትል የሚችለውን ስቃይ እና መከራ በማሰብ ከትግሉ እራስን ማግለል ስርዓቱ የሚፈጽመው ስቃይ የተሻለ አድርጎ መቀበልን ሊያስከትል ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ የሰላም ትግሉ ሰራዊት ፍርሃትን ማስወገድ ወይንም መቆጣጠር አለበት ስንል የሰላማዊ ትግሉ ሰራዊት (በዘር፣ በቁንቋ፣ በይማኖት፣ በጾታ፣ በሃይማኖት፣ በአይዶሎጂ፣ ወ.ዘ.ተ.) እሱን ያለመሰሉትን ወይንም የመንግስት ባለስልጣናትን፣ የገዢውን ፓርቲ አባላት እና ተከታዮች በሆነ ባልሆነው ማስበርገግ የለበትም። የመንግስት ባለስልጣኖች፣ የገዢው ፓርቲ አባላት እና ተከታዮች በሽግግር ወቅት እና ከሽግግር በኋላ ስቃይ እና በቀል ይፈጸምብናል በሚል ስጋት እንዲናወጡ ካደረግን ሽግግሩን የተራዘመ እና የተወሳሰበ የማድረግ ችግር ውስጥ ልንገባ እንችላለን። ስለዚህ ፍርሃት ስለማስወገድ ስናስብ ግባችን እኛን ታጋዮችን ከፍርሃት ነፃ ማውጥት ብቻ ሳይሆን እኛን በማይመስሉ ወይንም በፖለቲካ ባላንጣዎቻችንም ዘንድ እንዳይፈሩን ማድረግንም ያካትታል።

(5) ሰላማዊ ትግሉን ከጥላቻ ነፃ እንዲሆን ማድረግ ይገባል። ጥላቻ ንጹህ በሆነ አዕምሮ እና ህሊና እንዳናስብ ያደርገናል። አዕምሮዋችን በጥላቻ ከተመረዘ የምንሰጠው ዳኝነትም ፍትሃዊ አይሆንም። በጥላቻ ከተመርዘን ወንጀል ወደ መፈጸም ልንሸራተት እንችላለን። ነገ እኝንም ሆነ እንወክለዋለን የምንለውን ወገን ሊያሳፍር የሚችል ተግባር ልንፈጽም እንችላለን። የምንቃወመው ገዢውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ስርዓት እንጂ እኛን የማይመስለውን ወይንም ተቃዋሚዎቻችን መሆን የለበትም። የሰላም ትግል ሰራዊት ከጥላቻ ነፃ የመሆን አቅም ሊኖረው ይገባል። ስለዚህ ከጥላቻ ነፃ የመሆን አቅም የመገንባት ስልጠና መስጠት ያስፈልጋል። እርግጥ የፖለቲካ ባላንጣዎቻችንንም ማፍቀር አለብን ማለቴ አይደለም። ከጥላቻ ነፃ መሆን የሰላማዊ ትግሉን ማራኪነት፣ ተአማኒነት፣ አስማኝነት እና ስኪታማነት አቅሞች ከፍ ያደርጋል ማለቴ ነው።

(6) ሰላማዊ ትግል ከጉልበትም ነፃ መሆን አለበት። ጉልበት፣ ግድያ፣ ሽብር እና የመሳሰሉት ዘዴዎች የአምባገነኖች መንገዶች ናቸው። በዚህ አይነቱ መንገድ አምባገነኖች ይበልጡናል። እኛም ጉልበት እና ግድያ መጠቀም ከጀመርን አምባገነኖች የረጅም ጊዜ ልምድ እና ቁጥር ስፍር በሌለው ለረጅም ጊዜ ባከማቹት ህይወት ማጥፊያ አቅማቸው እንዲገጥሙን እድል እንሰጣቸዋለን ማለት ነው። ባለፉት አራት ወሮች ብቻ እንኳን ምዕራቡ በኦሮሚያ ለሚካሄደው ሰላማዊ ትግል በፍጥነት ድጋፍ መግለጹን እናስታውሳለን። እኛ በሰላማዊ ትግሉ ላይ ግድያን እና ሽብርን ከቀላቀልን ግን ምዕራቡ ደንታ አይኖረውም። እንዲያውም የህወሃት/ኢህአዴግ ወታደራዊ አቅም ከፍ እስካለ ድረስ ምዕራቡ ከቀድሞ ወዳጁ ከህወሃት/ኢህአዴግ ጎን ነው የሚለጠፈው። የሚካሄደውን ሰላማዊ ትግሉም የአገር ጸጥታ እና ደህንነት ጉዳይ በማስመሰል ህዝብን አደናግሮ ለማስተባበር እና ሰላማዊው ትግል ቶሎ እንዳይንሰራራ አድርጎ ለመምታት እንዲችል ቀዳዳ ይከፍትለታል። ስለዚህ ሰላማዊ ትግላችንን ከብክለት (Contamination) በንቃት መጠበቅ አለብን። ይኽን ማድረግ ለሰላማዊ ትግላችን ቀጣይነት እና ድል አድራጊነት የምንፈጽመው የደህንነት (የጸጥታ) ስራ አድርገን መውሰድ አለብን። ጀብዱኛ ግለሰቦች ወይንም ሌሎች ሰላማዊ ትግሉን ተቀላቅለው ጥይት የሚተኩሱም ከሆነ የሶሪያ አይነት ሁኔታ በኢትዮጵያችን ለፈጠር የማይችልበት ምክንያት አይኖርም። ሰላማዊ ትግሉ በፕላን የሚመራ እና በድስፕሊን እየታነጸ መሆን አለበት። ሰላማዊ ሰልፈኞችን ተቀላቅሎ በፖሊስ ላይ ድንጊያ መወርወርም ጉዳቱ ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል። ፖሊሶች በድንጋይ ከመገደላችን በፊት እራሳችንን ለመከላከል ነው ግድያ የፈጸምነው ሊሉ ይችላሉ። ፖሊሶች እንዲፈሩን ማድረግ የለብንም። እንዲያውም የተወሰኑት እንዲቀላቀሉን ማድረግ አለብን። ብዙ የክልልም ሆነ የፌዴራል ፖሊሶችም ይህን መንግስት ከልብ በፍቅር የሚወዱት አይመስለኝም።

(7) ስለማዊ ትግላችን ከግብታዊነት ነፃ መሆን አለበት። ግብታዊ ሰላማዊ ትግል በትግላችን ሂደት ውስጥ ለምንወስዳቸው እርምጃዎች አምባገነኖች ሊሰጡ የሚችሉትን አረመኔያዊ ምላሽ በቅድሚያ የመገመት እና የመዘጋጀት እድል ስለማይሰጠን ግብታዊነትን በትግላችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።  ግብታዊ ሰላማዊ ትግል ሊገጥሙት የሚችሉትን ወሳኝነት ያላቸው እንቅፋቶች በቅድሚያ አንስቶ ተመራምሮ ተገቢ ፕላን ስለማያሰላ ውጤቱ ውድመት ሊሆን ስለሚችል ግብታዊነት ሊወገድ ይገባል። ግብታዊ ሰላማዊ ትግል በስልጣን ላይ የሚገኘውን አምባገነን መንግስት ማውረድ ቢችልም ቀደም ብሎ የተሰላ ህዝብን የመንግስት ስልጣን ባለቤት የሚያደርግ የዴሞክራሲ ሽሽግር ፕላን ስለማይኖረው የሰላማዊው ትግል ፍሬ በሽግግር ወቅት ሊከሰት በሚችል በመፈንቅለ መንግስት ወይንም በራሱ ከስልጣን በወረደው ቡድን ሊነጠቅ ይችላል። ግብታዊትግል በስልጣን ላይ የሚገኘውን መንግስት ማውረድ ቢችልም ግባታዊው ትግል ቅልበሳን የሚከላከል ፕላን ስላማይኖረው አገሪቱን ወደ ነፃ ምርጫ እና ወደ ዲሞክራሲ ማሸጋገር ሊሳነው ይችላል። ህዝብን የድል ባለቤት ማድረግ አይችልም። አዲስ አምባገነን ወይንም ነባሩ አምባገነን ቡድን የድል ፍሬ ሰብሳቢ ሊሆን ይችላል።

(8) የሰላማዊ ትግላችን መሪዎች ደሞዝ የከፈለ ማዘዝ ይችላል የሚለው አባባል በፖለቲካም እንደሚሰራ ማስተዋል አለባቸው። ስለዚህ ሰላማዊ ትግሉን ከፍ በማድረግ በአገር ውስጥ ከንብረት ባለቤትነት፣ ከመሬት ባለቤትነት፣ ከንግድ፣ ከሰራተኛ ደሞዝ የሚያሰባስበውን ግብር እና በኢትዮጵያ ስም ከለጋሾች የሚፈስለትን የገንዘብ መጠን ከምንጩ ማድረቅ ያስፈልጋል። ይህ የኢኮኖሚ ትብብር መንፈግ የሚባለው ነው። ሰላማዊ ትግሉን ከፍ በማድረግ ከጅቡቲ፣ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሸቀጦችን ማቆም ይቻላል። መንገዶችን በተለያዩ ከተሞች ላይ በመዝጋት ከውጭ ወደ አዲስ አበባ እና ሊሎች ከተሞች የሚገባ ነዳጅ እና በርካታ ሸቀጦችን ማስተጓጎል ይቻላል። በዚህ አይነት የመንግስትን ኪስ መዳበስ ይቻላል። የኪሱ እብጠት ሲቀንስ እንደቀድሞው ደሞዝ የመክፈል አቅሙ ስለሚዳከም ሰላማዊ ተቃውሞ በማድረጋቸው ብቻ ህጻናትንን እና ወጣቶችን እንዲገድሉ የሚያዛቸውን ደህንነቶች እና ፖሊሶች እንደልቡ ማዘዝ ይሳነዋል። ሰራዊቱም ሰለማይከፈለው በተቃዋሚው ሁሉን አቀፍ ህብረት ለሚደረግለት “ለህገ-መንግስተ ተገዛ” እና “ሰላማዊውን ለውጥ ተቀላቀል” ጥሪ የሚሰጠው ምላሽ ከጊዜ ወደ ጊዜ አዎንታዊ እየሆነ እንደሚሄድ መጠራጠር የለብንም።

(9) የህዝቡ ጥያቄ በቅርቡ፥ “በ100% አሸናፊነት የተፈጠሩት መሳቂያ የፌዲራል እና የክልል ፓርላሞች ይፍረሱ፣ ጊዚያዊ መንግስት ይቋቋም፣ አዲስ ምርጫ ይደረግ” ከሚል ደረጃ እንደሚደርስ ጥርጥር የለኝም። ስለዚህ አርጅቶ በመበስበስ ላይ የሚገኘው የህውሃት/ኢህአዴግ መንግስት አንዴ “ስለ ይቅርታ” ሌላ ጊዜ “ስለመልካም አስተዳደር እጦት” በስውር ደግሞ “ስለ ወታደራዊ ዕዝ አስተዳደር“ ማውራቱን አቁሞ ከህዝብ ቢታረቅ እና የተጀመረውን የፖለቲካ ስርዓት ለውጥ ብሎም የነፃነት እና የዴሞክራሲ ሽግግር ሂደት ቢቀላቀል የሚሻለው ይመስለኛ። ቢያንስ በህወሃት/ኢህአዴግ ውስጥ የሚገኙ ተራማጅ ሰዎች ይህን አይነት እርምጃ ቢወስዱ ለራሳቸውም ለአገሪቱም ጠቃሚ ይመስለኛል። የአገር ሽማግሊዎች እና ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ሁሉን አቀፍ ጉባኤ መጥራት የሚያስችል ስራ መስራት መጀመር ያለባችሁ ይመስለኛል። እርግጥ ለውጥ ነገ ይመጣል ማለት አይደለም። ስራው ግን ቢጀመር ጥሩ ነው።

ሰላማዊ አቤቱታ እና ተቃውሞ በማንሳታቸው ብቻ ወጣት ልጆቿን የምትገድል፣ የምታስር፣ የምታዋክብ ኢትዮጵያ ማብቃት አለባት። ዜጎቿን በነፃነት እና በዴሞክራሲ ማስተዳደር ወደ ምትችል ኢትዮጵያ መሸጋገር አለብን። የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ተገቢውን ትብብር ካገኘ እንደሚሳካ ጥርጥር የለኝም።!

ከሰላምታ ጋር

ግርማ ሞገስ

ህብር ሬድዮን በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ ከ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *