Hiber Radio: አንድነት ፤ አንድነት ስንል ከአራባ ዓመታት በላይ አሳልፈናል—ፈቃደኛነት ካለ ለመተባበር ይቻላል( ሁሉም ሊያነበው የሚገባ)

DR Akelog_001

አክሎግ ቢራራ (ዶር)

እኛ ለኢትዮጵያና ለመላው ሕዝቧ ቆመናል የምንለው ሁሉ አንድነት፤ አንድነት፤ ህብረት፤ ህብረት ስንል ከአርባ ዓመታት በላይ አሳልፈናል። አንድም ውጤት አላስገኘነም። የፖለቲካ ባህላችን ድርጅትን ፈጥሮ መከፋፈል፤ ማጥፋት፤ መተካትና መጠላለፍ እየሆነ አንዱ ሌላውን በመተቸት ሁለት ትውልዶች አልፈው ሶስተኛውን ጀምረናል። ይህ በአንድ በኩል ተስፋ ሰጭ፤ በሌላ በኩል አድካሚ የፖለቲካ፤ የማህበረሰብና የመነፈስ ባህርይ የጀመረው በንጉሱ ዘመነ መንግሥት በተማሪዎች እንቅስቃሴ ነው። በዚያ ወቅት የነበረው ትውልድ ከራሱ በላይ ለአገሩና ለወገኖቹ የሚያስብ ነበር ለማለት እደፍራለሁ። የአሁኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ ይተቸው። የብሄረሰብ ፖለቲካም መሰረት የያዘው በዚያ በእኔ ትውልድ አካባቢ ነው። በተከታታይነቱ ሲታይ፤ የኢትዮጵያ ምሁራንና ልሂቃን ባህል ሁለት ወሳኝ የሆኑ ገጽታዎች አሉት።

አንድ፤ ሳይሰለቹ ስለ አገር ወይንም ስለ ቡድን ጉዳይ መነጋገር እና ሁለት፤ ተነጋግሮ በአንድነት ለመስራት አለመቻል/ቆርጦ ለመነሳት አለመድፈር።

የትንሽ የኪስ ዘውድ አበሳ

ሁለተኛውን ባህርይ በሚመለከት ሁለት ምሁራን ጓደኞቸ በተደጋጋሚ የሚጠቅሱት ብሂል አለ። “እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ምሁር፤ ልሂቅና ሌላ በኪሱ ትንሽ ዘውድ እየያዘ የሚዞር ይመስላል።” ይኼ እኔ ብቻ ልምራ፤ እኔ ብቻ የእውቀት ምንጭ ነኝ፤ እኔ ብቻ ያልኩት ይሁን፤ እኔ ብቻ፤ እኔ ብቻና የእኔ ብቻ የሚለውን ጎጂ ባህል ያካትተዋል። የኢትዮጵያ ሁኔታ በጣም እንደተለወጠ የማይቀበሉ ግለሰቦችና ስብስቦች “በእኔ ብቻ ዓለም ይኖራሉ” ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም። የፖለቲካ ሳይንቲስቱና ህይወቱን ለዲሞክራሲ፤ ለፍትህ፤ ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን እኩልነት ሲታገል የኖረውና አሁንም የሚታገለው ዶር መረራ ጉዲና ለብልሹው የፖለቲካ ባህላችን ባህርይ “የቡዳ ፖለቲካ” የሚል ስያሜ ስጥቶታል። እኔ እንደሚገባኝ ከሆነ “የቡዳ ፖለቲካ” ባህሪይ፤ ጊዜ ወስዶና አስቦ ራስን ከመመርመርና ከመተቸት ይልቅ ችግሮችን ሁሉ በሌላ ማመካኘት ነው። ለምሳሌ፤ ህወሓት ወደ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ሊገባ መንዝን ሲሻገር የአካባቢው የአማራ ሕዝብ “ህይወትና ኑሮ ከትግራይ ሕዝብ የማይለይ፤ በድህነትና በኋላ ቀርነት የተበከለ” መሆኑን አይቶ “ይኼን ሕዝብ እንዴት የትግራይ ሕዝብ ጠላት ነህ እንለዋለን” የሚል ውይይት እንደተደረገ አንድ ወዳጀ የዛሬ አስር ዓመት አጫውቶኝ ነበር። ሜጀር ጀኔራል አበበ ተክለሃይማኖት “የተገኘውን ሰላምና እድገት የሚንድ የአመራር ዘይቤ በአስቸኳይ ይቁም” በሚል አርእስት ያቀረበው ትንተና በብሄርተኝነት፤ ጎሰኝነት ወይንም ጎጠኝነት ዙሪያ ባለፉት ሰላሳና አርባ ዓመታት ተቋማዊ የሆነው “የቡዳ ፖለቲካ” ምን ያህል ስር ሰዶ አገሪቱን ለአደጋ፤ ሕዝቡን ለእርስ በርስ ግጭት እንዳጋለጣቸው ያሳያል። የአማራውን ሕዝብ አሰቃቂ ሁኔታ ጀኔራሉ እንዲህ በሚል አቅርቦታል። “የህወሓት ሠራዊት መንዝ ሸዋ በገባበት ጊዜ…ወደ ሠራዊቱ የተቀላቀሉት አዲስ ታጋዮች መንዝ ሲገቡ የሕዝቡ የኑሮ ሁኔታ ሊገባቸው አልቻለም። የሕዝቡ ኑሮ ከትግራይ ሕዝብ በምንም ሁኔታ የማይሻል ሆኖ ሲያገኙት አንዳንዶቹ ተዋከቡ። የአማራ ገዥ መደብንና የአማራን ሕዝብ መለየት አልቻሉም። “እንዴት ነው አማራ ጠላታችን ነው ያላችሁት፤ ተታልለን ነው የታገልነው” አሉ። በነባሮችና በአዲሶቹ መካከል የጦፈ ክርክር ተካሂዶ በመጨረሻ ተማመኑ። ህወሓት ሲያስተምራቸው የነበረው ግልጽ መሆኑ፤ እሱም፤ “የአማራ ገዥ መደቦች በአማራ ስም ሲነግዱም ለራሳቸው ካልሆነ ለአማራው ምንም እንዳልሰሩለትና አማራም እንደሌላው ሕዝብም እንደሚጨቆን” ተማመኑ።

ሁለት ማስታወሻዎች ግልጽ እንዲሆኑ እመኛለሁ። አንድ፤ የተማሪው እንቅስቃሴ የተከፋፈለው ከላይ በተጠቀሰው ምክንያት፤ ማለትም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ችግር የመደብ እንጂ የብሄር ጭቆና፤ ጥላቻና ልዩነት አይደለም በሚለው ዙሪያ፤ ሁለት፤ ተራው የአማራና የትግራይ ሕዝብ እንደሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጭቁን፤ ከቀዩ የሚሰደድ፤ ድሃና የገዢዎች ሰለባ መሆኑን የሚያስተጋባ ነበር። የህወሓት ነባሮች ይኼን ክርክር አያውቁትም ለማለት አይቻልም። “ሰፊው የአማራ ሕዝብ ለኋላቀርነት”፤ ለድህነት እና “ለብዝበዛ የተጋለጠ” መሆኑ፤ ልክ እንደ ትግራዩ፤ ኦሮሞውና ሌላው ሕዝብ ነጻነቱና “ዲሞክራሳዊ መብቱ የታፈነ” መሆኑ፤ ልክ እንደሌላው የኢትዮያ ድሃና የስራ እድል ያጣ ሕዝብ “የጦርነት ሰለባ” መሆኑ እና፤ ይኼ ሁሉ በመሬት የሚታይ ሁኔታ እየታወቀ የህወሓትና ሌሎች ነባሮች ለስልጣንና ለግል ጥቅም ሲሉ “ሌሎቹ ሕዝቦች በአማራ ሕዝብ ላይ ጥርጣሬ” ብቻ ሳይሆን የሚዘገንን ጥላቻ ተቋማዊ ማድረግ፤ የአማራን ብሄረሰብ ለይቶ ማጽዳትና ማጥቃት፤ ሆነ ብሎ ቁጥሩን መቀነስ፤ መሪዎች እንዳይኖሩት ተስፋ የሚሰጡትን ሲያብቡ ማሰር፤ እንዲሰወሩ ማድረግና በድብቅ መግደል፤ ከተፈጥሮ ኃብታቸው ማስወገድ እና በአማራው ሕዝብ ላይ በጅምላ “ጥርጣሬ” እንዲኖር ማድረጉ አሁንም ቀጥሏል። እንደዚህ ያለው የብሄር ጥላቻና አግላይነት ለሰላም፤ ለእርጋታ፤ ለአገር ሉዐላዊነትና ለሕዝብ አንድነት ጸር ነው። የአማራውን ሕዝብ የድህነትንና የኋላ ቀርነት ሁኔታ በቅርቡ አልጀዚራ በማስረጃ ተደግፎ ሲያቀርብ እንዲህ ብሏል። “የአማራው ሕዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያና የአፍሪካ ሕዝቦች በበለጠ ደረጃ ፍጹም ደሃ፤ ኋላ ቀርና በበሺታ የሚሰቃይ ሆኖ አግኝተነዋል” ብሏል። ይህ “የቡዳ ፖለቲካ” ሰለባ የሆነ ሕዝብ በአሁኑ መንግሥት ያገኘው ጥቅም ምን እንደሆነ ህወሓቶች መረጃ ማቅረብ ይኖርባቸዋል። በሌሎች ሃተታዎች እንዳቀርብኩት አብዛኛው የትግራይ ሕዝብም ያገኘው ጥቅም ፋይዳ የሌለው ነው። እንደ ብረት የተሳሰረ ሕዝብ ለመፍጠር ከተፈለገ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች በማንኛውም የኢትዮጵያ ክልፍ መብታቸው በሕግ የተጠበቀ መሆን ይኖርበታል።

ወደ አንድነቱና ወደ መተባበሩ ውጥንቅጥ ስለመለስ “ትንሽ ዘውድ በኪስ” ይዞ መዞር ሆነ “ቡዳው እኔ አይደለሁም፤ ሌላው ነው” የሚለው አገራችንንና ሕዝባችንን እንደጎዳ አያከራክርም። ጎጅነቱ በፖለቲካ ብቻ አይደለም። በመንፈሳዊ፤ በማህበረሰባዊና በሌሎች ስብስቦች ይንጸባረቃል። አብሮ ለመደራጀት፤ ለመስራትና ለዲሞክራሳዊ ባህል ምስረታ ማነቆ ሆኗል። እርስ በርስ መተማመን እንዳይኖር አግዶናል። አብሮ መስራት፤ መተባበርና አንድነት መሰረት የሚይዘው የዓላማ አንድነትና መተማመን ሲኖር ብቻ ነው። ሁለቱም ዓላማዎች መነጋገርን፤ መወያየትን፤ መናበብን፤ ልዩነቶችን መቀበልን፤ እኩልነትን፤ የሌላውን የግልና የቡድን ወይንም ሌላ መብት ማክበርን ወዘተ ይጠይቃሉ። በዚህ ዙሪያ እኛ ኢትዮጵያዊያን፤ በተለይ ምሁራንና ልሂቃን አልታደልንም። ትኩረት የሰጠነውና አሁንም የምንሰጠው ለአሉታዊው፤ ያውም ባለመነጋገር፤ ባለመወያየትና ባለመናበብ ለተከሰቱ ሁኔታዎች ነው። በእኔ ግምት፤ በሁሉም ብሄሮች የሚገኙ ለአገርና ለመላው ሕዝብ ኑሮ መሻሻል የሚጥሩ ግለሰቦችና ስብስቦች አሉ። ሆኖም፤ የአማራ፤ የኦሮሞ፤ የትግራይ፤ የአኟክ፤ የደቡብ፤ የጉራጌ ወዘተ ምሁራንና ልሂቃን አይገናኙም፤ አይነጋገሩም፤ አይወያዩም፤ መፍትሄዎችን በአንድ ላይ ሆነው ለሕዝብ አያቀርቡም፤ ወጣቱን ትውልድ አያስተምሩም፤ ነባሮችን የሚተኩ፤ አዲስ መሪዎች ለመፍጠር አልቻሉም። በቅርቡ በሰሜን ጎንደር፤ በኦሮሞያና ሌሎች ቦታዎች የተከሰቱት ሕዝባዊ አመፆች የማይገኝ እድል አቅርበውልን ይህም እድል እያመለጠን ነው። ጀኔራል አበበ ስለዚህ የተቸውን እቀበላለሁ።

“በኦሮሞያ የተቀሰቀሰው ተቃውሞና በአማራ ክልል አካባቢ የታየው ብጥብጥ የጠባብ ብሄርተኝነትና ትምክኅት እንደገና መጎልበትና በዚህ አገር ላይ አደጋ እንደሆነ መወያያ ሆኖ ሰንብቷል። ተገቢ ስጋት ነው። አንዳንዶች ፌደራል ስርዓቱ ያመጣው ጣጣ ነው ሲሉ፤ በአንዳዶቹ ዘንድ እጅግ መደናገጥ ይታያል። በእኔ አመለካከት ጠባብነት ይሁን ትምክህት በህብረተሰቡ ውስጥ የሚኖሩ የተወሰኑ ልሂቃን በቀጣይነት ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ የሚጠቀሙባቸው አመለካከቶች ናቸው። ….በኅብረተሰቡ ውስጥ ያሉ ኋላቀር አስተሳሰቦች ቢሆኑም አብዛኛውን የኅብረተሰብ ክፍል የሚጎዱ እንጂ አይጠቅሙም። ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበረሰባዊ ስጋትና ፍርኃት በኅብረተሰቡ ውስጥ በሚያይልበት ጊዜ የሚያጎለብቱ ክስተቶች ናቸው።”ይኼ አንዳለ ሆኖ፤ ገዥው ፓርቲ የችግሮቹን አደጋ ተቀብሎ “የኢትዮጵያ ጥንካሬ የሚመሰረተው በብሄር፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ብርታት” ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ነጻነት፤ ሰብአዊ መብት፤ እውነተኛ እኩልነት፤ ፍትህ፤ የሕግ የበላይነት እና ዲሞክራሳዊ መብቶች መከበር መሆኑን ደፍሮና ቆርጦ መቀበል ይኖርበታል። ችግሩን የፈጠረው ህወሓት/ኢህአዴግ ነው፤ ሕዝቡ አይደለም። በሌላ አነጋገር የውስጥና የውጭ አፍራሽ ኃይሎች መኖራቸው ቢታመንም፤ የችግሩ መንስኤ በብሄር መቃቃርና መከፋፈል ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ችግሮቹ መከሰታቸው አያስደንቅም። ብዙ ምሁራንና ተቋሞች ቀደም ሲል አደጋውን ጠቁመው ነበር። ይኼ እየተባባሰ የሄድ ሁኔታ የሚያስፈልገው ጥገናዊ ለውጥ ሳይሆን መሰረታዊ የስልጣን መጋራት ለውጥ ነው። ኢትዮጵያ ግዙፍ የሆነ ለአገሩ ሉዐላዊነትና ለመላው ሕዝብ ህይወት መሻሻል ሊሰራ የሚችል ትውልድ አጥታለች። በትውልድ ደረጃ፤ ያለፈውን ውጣ ውረድና ከፍተኛ መስዋእት ማስታወስ አሁን ለሚደረገው ጥረት ይጠቅማል የሚል እምነት አለኝ። የዝነኛው የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ጽንሰ ሃሳብና የትውልድ ውድመት ለዚህ ምሳሌ ነው።

ያ ወጣት ትውልድ የሰጠን ቅርስ

የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ በዓለም ደረጃ እውቅና የነበረው፤ የዚያ ጊዜ ትውልድ ለግል ወይንም ለቡድን ጥቅም ያልቆመና በህብረብሄር አስተሳሰብ የተሰበሰበ መሆኑን የሚያሳይ ነበር። ያ ትውልድ ራሱን የለየበት፤ አሁን ያጣነው መሰረት አለ። ትኩረት የሰጠውና ራሱን ያስከበረው ለአገሩና ለሕዝቡ ከፍተኛ የመሰብሰብ፤ የመደረጃት፤ የመወያየት፤ የመቀስቀስ፤ የማንቃት ወዘተ አስተዋፆ ማድረጉ ነው። የሚሰራ ስህተት መስራቱ የማይቀር ስለሆነ ብዙ ስህተቶች እንደተፈጸመ አይካድም። እኛ የምናስታውሰው ግድፈቱን ስለሆነ ገንቢውን አስተዋፆ ወደጎን እየተውነው አልፈናል። እኔ ለማስታወስና ላሰምርበት የምፈልገው ከስህተቱ በላይ ለአገሩ ዘላቂነትና ለሕዝቡ ሰብአዊ መብቶች መከበር መቆሙን ነው። ሆኖም፤ በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ ግብግብና መከፋፈል የተነሳ የግራው ክንፍና አገር ወዳዱ በአንድ ላይ ሆኖ የወደፊቷን ኢትዮጵያን አግባብ ባለው መንገድ፤ የሁሉንም ብሄሮች ጥቅም ቀደምትነት በሚሰጥ ደረጃና ሕዝቡ የስልጣኑ ባለቤት እንዲሆን አላደረገም። የከፈለው መስዋእት ግን ሊካድ አይችልም።

ካለፈው መማር ጥቅም አለው

የዚህ ትንተና ዋና ዓላማ ማንንም ለመውቀስ፤ ማንንም ለማወደስ አይደለም። ከአለፈው ተምረን አዲስ ቆራጥ ትውልድ እንዲተካ ምሳሌ እንሁን የሚል ነው። ይኼን የአሁኑ አንድ ግዙፍ የሆነ፤ ግን የባከነ ትውልድ አወንታዊ የፖለቲካ ቅርስ አለመረዳት በተደጋጋሚ ለምንሰራቸው ስህተቶች ግብአት ሆኗል። አንባቢን አስቀድሜ ልምከር። ይህን ሃተታ አይተው ትችት የሚሰጡ እንደሚኖሩ የማልጠራጠር መሆኔን ነው። እኔ እንደማስታውሰው አወንታዊውን አሉታዊ በሆነ ደረጃ ጨለማ ያደረገው ሁኔታ ለመነጋገር፤ ለመወያየት፤ ለመቻቻል፤ ለመናበብ፤ ልዩነቶችን በጋራ ለመፍታት ወዘተ ስላልተቻለ ነው። ግትርና “እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን” የሚል አመለካከት ስለበከለን ጭምር ነው። በስድሳዎቹና በሰባዎቹ የለውጥ ዓመታት ብዙ መጻፉና መነገሩ አይረሳም። ሆኖም፤ የችግሩ እምብርት በግልጽ ቀርቧል ለማለት አይቻልም። እኔ እንደማስታውሰው፤ ፊት ለፊት ተነጋግሮ ብሄራዊና ህዝባዊ ችግሮችን ለመፍታት አልተቻለም ነበር፡፡ ልክ አሁን ያለውን ሁኔታ ይመስላል። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ በርሊን ጀርመኒ ለመስማማት ተሞክሮ የከሸፈው የግራ ክንፎች ውይይት ነው። የተስፋፋውና ጥልቀት የያዘው፤ አሁንም እንደ ጅራት ሆኖ እየተከተለን ያለው የፖለቲካ ባህል ጠለፋ፤ መነቃቀፍ፤ ሽሙጥና ለግድያና ለስደት ያመቻቸ ስም ማጥፋትና እርስ በርስ መወነጃጀል ነበር። ዶር መረራ “የቡዳ ፖለቲካ” የሚለው መሰረቱ ይኼው ይመስለኛል።

አሁን ህወሓት/ኢህአዴግ እንደሚያደርገው ሁሉ፤ ደርግና ሌሎች ኃይሎች ይህን የአገር ወዳዶችና የተራማጆች መከፋፈልና ድክመት ተጠቅመውበታል። በተለይ የማስታውሰሰው፤ በዚያ ወቅት፤ በጀርባ ሆነው የብሄር ፖለቲካ ድርጅቶች ይህን ሰፊ ክፍተት ተጠቅመው፤ እኛን አናክስው፤ እኛ እርስ በርሳችን እንድንገዳደል መስጢረው የፖለቲካ ስልጣን ለመያዝ ችለዋል። በእኔ በአንድ ግለሰብ ላይ ብቻ ሶስት የግድያ ሙራዎች ተካሂደዋል። አንዴ ሹፈሬና የአጎቴ ልጅ አብረውኝ ወደ ንግድ ባንክ ሲሄዱ ቆስለዋል። የባንኩ መኪና አስራ ስድስት ጥይት በስቷታል። እኔ በሞያየ እንጅ ካድሬ አልነበርኩም። ኢላማ የሆንኩበት ዋና ምክንያት የመኤሶን አባል ስለንበርኩ ነው። ብንቀበልም ብንክድም ያ ወቅት፤ ጥበብና ብልሃት የጎደለበት አሳዛኝ የታሪክ ምእራፋችን ነው። እኔ “ቡዳ አልነበርኩም፤ ቡዳው አንተ ነበርክ” የሚለው ብሂል የትኛው ሃቀኝነትን መሰረት ያደረገ እና የትኛው ግድፈት ያለው እንደሆነ ሚዛናዊ በሆነ ደረጃ እስካሁን ለማቅረብና ከዚህ የፖለቲካ ውጥንቅጥ አልፈን ወደ አሁኑ ታሪካዊ ጥሪ እንድራመድ አግዶናል። በእኔ ግምት በደርግ አገዛዝ ለኢትዮጵያና ለመላው ሕዝቧ ዲሞክራሳዊ አገዛዝ ከፍተኛውን ሚና የተጫዎቱት መኤሶንና ኢህአፓ አብረውና ተባብረው ለመስራት ቢነጋገሩና ቢስማሙ ኖሮ የኢትዮጵያና የሕዝቧ የፖለቲካ ታሪክ የተለየ ይሆን ነበር። እርግጠኛ ነኝ አሁንም ይህን አመለካከት የምንተቸው ማን “ቡዳ” ነበር፤ ማን ገዳይ ነበር፤ ማን የደርግ ደጋፊ ወይንም ተቃዋሚ ነበር?” ወደሚለው ባህል በመዞር ነው። ከዚህ አንድ ትውልድ የወደመበት የፖለቲካ ታሪካችን ምን እንማራለን? ብየ ራሴን ስጠይቅ፤ ቢያንስ ቢያንስ፤ ያለፉትን ለማስታወስ ከጥሩውም፤ ከመጥፎውም ስራዎች ተምረን፤ ስህተቶች ካሉ ስህቶቹን አምነንና ተቀብለን ለጋራ አገራችንና በረሃብ፤ በስደት፤ በአፈና፤ በሙስና ወዘተ ለሚሰቃየው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንድረስለት ከሚል ድምዳሜ ላይ ደርሻለሁ። አለያ፤ ፖለቲካው ለሌሎች እንተወው፤ አዲሱን ትውልድ ተስፋ አናስቆርጠው።

ከላይ በጠቅስኳቸው ድርጅቶች ውስጥ ለአገራቸውና ለመላው ሕዝቧ የሚቆረቆሩና ህይወታቸው ያለፈ ብዙ ናቸው። ልዩነቶችም ቢኖሩ ኢትዮጵያን መአከል አድርገው ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ለማገናኘትና ለማስማማት፤ የብሄር ልዩነቶች ዲሞክራሳዊ በሆነ አገዛዝ ሊፈቱ የሚችሉ መሆናቸውን በጥናትና በምርምር ማሳየት የሞከሩ አገር ወዳዶችና ሶሻል ዲሞክራቶች ነበሩ። ብዙዎቹ መስዋእት ሆኑ። ያልታደለችው ኢትዮጵያ በልዩ ልዩ ኃይሎች መሪዎች አልባ የሆነችው በልዩነቶችና በስልጣን ሽሚያ ምክንያት ነው። አገራችንን ወደየት ለመውሰድ እንደምንመኝ ብናውቅ ኖሮ ትኩረታችን ከሕዝቡ ዲሞክራስዊ መብትና ከሕዝባዊ ስልጣን ላይ ይሆን ነበር። አንድ አዋቂ የሚለው አግባብ አለው። “ከየት እንደመጣ የማያውቅ፤ ወደየት እንደሚሄድ አያውቅም።” እኛ ትውልደ ኢትዮጵያ ከየት እንደመጣን እናውቃለን የሚል ግምት አለኝ። የቸገረን ይህችን የረጅም ታሪክና የስብጥር ሕዝብ ባለፀጋ አገር ወደየት ለመውሰድ እንደምንፈልግ የጋራ ግንዛቤ የሌለን መሆኑ ነው። ካለፈው የፖለቲካ ታሪካችን ተምረን ትኩረታችን በነገው ላይ ቢሆን የተሻለ ውጤት ልናበረክት እንችላለን የሚል እምነት አለኝ። የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ለሁሉም ይጠቅማል። ይኼ የሚቻለው ዲሞክራሳዊ በሆነች፤ የህግ የበላይነትን መሰረት አድርጋ የሁሉንም ዜጎቿን ነጻነነትና ሰብአዊ መብት፤ ክብር፤ እኩልነት፤ ፍላጎት ለማሟላት እንድትችል ብቁነት ያለውና ሃላፊነት የሚሰማው ዲሞክራሳዊ መንግሥት ለመመስረት ለሚደረገው ረዥም ጉዞ ህብረት፤ ቢቻል አንድነት ሲኖር ብቻ ነው።

የወደፊቱን ተስፋ የሚሰጥ አቅጣጫ ልዩ ልዩ ድርጅቶች በተለያዩ ወቅቶች እንዳቀረቡ ይታወቃል። በደርግ ዘመን፤ አንድ ተስፋ አድርጌበት የነበረ የአቅጣጫ ምሳሌ ብቻ ላቅርብ። በግንቦት 7, 1969, በሰፊው ሕዝብ ድምፅ ቁ. 55 ያነበብኩትን አንዳርጋቸው አሰግድ በጻፈው፤ በአጭር የተቀጨ ረጅም ጉዞ ግዙፍ መጽሃፍ ስላስታወሰኝ፤ ለአለንበት ሁኔታ ጠቃሚ ስለመሰለኝ እጠቅስዋለሁ። በነገራችን፤ እኔ ካድሬ ወይንም የአመራር አባል ባልሆንም የመኢሶን አባል እንደነበርኩ አሁንም ያለምንም ያዝ ለቀቅ እደግመዋለሁ። ጽሁፉን አንብቤው ነበር። እንዲህ ይላል “ መኢሶን የሚፈልገው እኩልነትና ነጻነት የሰፈነባት፤ የሕዝቦቿ አንድነት ከብረት የጠነከረባትና ብሄረሰቦቿ ሁሉ ያበቡባት፤ የማንም ተመጽዋች ያልሆነ፤ በራሱ የሚተማመን፤ በማንም ፊት የበታችነት ስሜት ሊኖረው የማይችል፤ በትግሉና በመስዋእትነቱ ውጤቶች የሚኮራ ፤ በዓለም ሕዝቦች ሸንጎ ተገቢ ቦታውን የያዘ ሕዝብ የሚኖርባት አዲስ ሕዝባዊ ኢትዮጵያ እንድትመሰረት ነው። የኢትዮጵያ አብዮት የፈለገውን ያ ህል ውስብስብ ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል የፈጀውን ጊዜ ቢፈጅምና የፈለገውን ያህል መሥዋእትነት ቢጠይቅም፤ ብዙ ችግሮችና መሰናክሎች ከፊታችን ቢደቀኑም፤ የዚች አይነቱ ኢትዮጵያ እንድትመሰረት እስከ መጨረሻው ለመታገል ቆርጠን ተነስተናል። ” ይ ህ ታ ሪ ካ ዊ መ ሰ ረ ተ ሃ ሳ ብ ነ ው ። ዛሬም ቢሆን የዲሞክራሲ ምስረታ ጥያቄ በቀላሉና በአጭር ጊዜ የሚሳካ አይደለም። እንኳን ተለያይተን ተባብረንም ቢሆን ስኬታማ ለማድረግ መፈላለግን፤ መተማመንን፤ ትእግስትን፤ መደማመጥን፤ መተሳሰብን፤ መነጋገርን፤ መናበብን፤ አብሮ መስራትን፤ ልዩነቶችን ተቀብሎ ለመቻቻል መሞረከርን፤ መስዋእትነትን፤ ብልሃትን ይጠይቃል። ከራስ በላይ ለአገር ዘላቂነትና ለሕዝብ ፍትህ ታግሎ ማለፍን ይጠይቃል። መስዋት ከሆኑት የምማረው ይኼን ነው። ቅርስ ማለትም ይኼው ነው። አብሮና ተባብሮ ከመስራት የበለጠ ቅርስ ሊኖር አይችልም። እንዳለፈው የፖለቲካ ታሪካችን ኢትዮጵያ አሁንም “የመሪ ያለህ፤ የአስተዋይ ያለህ፤ የሕዝብ እኩልነት ጠበቃ ያለህ” እያለች ልጆቿን እንድንስማማ ትጠይቃለች።

ከአገር ዘላቂነትና ከመላው ሕዝብ ፍትህ፤ እኩልነትና ነጻነት ሌላ ሊያስማማን የሚችል ምን አበይት ጉዳይ ሊኖር ይችላል? በንትርክና በጎሳ ጥላቻ ድባብ የሚሽከረከር ጎጅ ባህል ስር እንደስደደ መካድ አይቻልም። ይኼም ሆኖ አንድ የማህበረሰብ ክፍል በፓርቲዎች፤ በስብሰባዎች ብዛትና ስፋት የአገርን ሉዐላዊነት፤ ግዛታዊ አንድነት፤ ክብርና የሕዝብን ነጻነት፤ መብቶችንና የፍትህ ፍላጎትን ለማስከበር ቢችል ኖሮ እኛ በመላው ዓለም ተስደን የምንኖር ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለውጥ ለማምጣት እንችል ነበር። ከሌሎች አፍሪካዊያን ስደተኞች የበለጠ ስብሰባዎች እናዘወትራለን፤ እንጽፋለን፤ ቃለመጠይቆች እናካሂዳለን፤ በፓልቶኮች እንወያያለን ወዘተ። በቅንነት ስመለከተው ሁላችንም እንደጋገፍ፤ እንተባበር፤ በግለሰቦች ወቀሳና ትችት ላይ ትኩረት አናድርግ (Let us de-personalize and focus on issues rather than personalities) ፤ በፖሊሲ ላይ እንወያይና እንስማማ፤ አንድነት እንፍጠር እንላለን። ይህ መልካም ነው። መልካም ከሆነ አንድነትም ባይቻል ለመተባበር ማንና ምን ማነቆ ሆነ? ብየ ስጠይቅ አንዱ በሌላው ያመካኛል፤ ግልጽነትና ራስን መተቸት የሚባል ነገር የለም። ልክ በደርግ ዘመን እንደነበረው አሁንም ራሳችን ማነቆ ሆነን ሌላውን መተቸት ይቀድመናል።

አንድነት፤ መተባበር፤ አብሮና ተደጋግፎ መስራት የሚሉት የተቀደሱ እሴቶች ከቃላትነት አልፈው ውጤታማ አልሆኑም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሁሉም “ያጣ ጎመን” ሆኗል ለማለት ይቻላል። አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዙ ቢሊየን ብር ከሚቆጣጠረው መንግሥት የሚያገኘው ጭካኔ፤ አፈናና ሽንገላ ነው። ከተቃዋሚው የሚያገኘው የቃላቶች ሽንገላ ነው። ገዢው ፓርቲ ተቃዋሚውን “ቡዳ” ይላል፤ ተቃዋሚው ገዢውን ፓርቲ “ቡዳ” ይላል።” ቡዳ ሲደመር ቡዳ ውጤት ቡዳ አይደለም?

ኢህአዴግ የውስጥ የአስተዳደር ድክመቶች እንደበከሉት ቢያምንም ሕዝብን ለመሸንገል ከሚያወጣቸው መግለጫዎችና ተቃዋሚውን ከመወንጀል ባሻገር የፖሊስና የመዋቅር ችግሮቹን ስርዓቱ የፈጠራቸው መሆኑን አልተቀበለም። ለምን አይቀበልም? ከተቀበለ ስልጣኑን መልቀቅ አለበት የሚል ስሌት አለው፤ ቢያንስ ስልጣኑን ከሌሎች ጋር መጋራት። የማይካደው ሁኔታ አንድ ነው። ለአገሪቱ ህልውና አስጊ የሆነው ስርዓቱ ካልተለወጠ ችግሮቹ እየተባባሱ ይሄዳሉ የሚለው አበይት ጉዳይ ነው። ዛሬ የምናየው የኢትዮጵያ ህልውና ከአደጋ ጫፍ አልፎ እንደ ዩጎስላቪያና እንደ ሶሪያ ሊሆን እንደሚችል ነው። የታጠቀ ቡድን የጋምቤላን ድንብር ጥሶ ወገኖቻችን ሲገድል፤ ከመቶ በላይ ህጻንትና 2,000 መንጋ ከብት ማርኮ ሲወስድ ከዚህ የበለጠ ምን ውርደት አለ? ነገስ ከዚህ የባሰ ወንጀል ቢፈጸምስ? ድህነት፤ ረሃብና ስደት ጎሳና ኃይማኖት ሳይለይ ይባባሳል። የእርስ በርስ እልቂት የማይቀር ነው። የእርስ በርስ ግጭት ቢከሰት ማንንም አይምርም። ኃብት ያለው ኃብቱን ለማሸሽ መሸሸጊያ ይፈልጋል። “የፓናማ ወረቀተቾ” ተብሎ የሚጠራው ግዙፍ ጥናት የሚያሳው ሰርቆ የማሸሺ እድል እየጠበበ መሄዱን ነው። ዛሬ ፓናማ ነገ ካይመንና ሌላ መሆኑ የማይቀር ነው። ሙስና፤ አድልዎ፤ ኃብት ማሸሽ ወዘተ ስርዓት ወለድ ችግር ነው። ይኼን ስል አገዛዙ ጸረ-ኢዲሞክራሲ ነው ማለቴ ነው። ኢ-ዲሞክራሳዊ ስል በአገራቸው እድል የሚያገባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ አልሆኑም ማለቴ ነው። መቻቻል የለም ማለቴ ነው። ለዚህ መልሱ አንድነት፤ ቢያንስ መተባበር ነው።

አግልሎ መግዛትና መመዝበር ዘላቂነት የለውም

ታሪካችን ያሳየው የተገለሉና የታገቡ ክፍሎች በአገራቸውና በህዝባቸው የአሁንና የወደፊት እድል ተሳታፊ ካልሆኑ ሰላምና እርጋታ የማይቻል መሆኑን ነው። ተሳታፊ ስል የስልጣን መጋራት መኖር አለበት ማለቴ ነው። ኢህአዴግ በቅርቡ ከፈጸማቸው ግዙፍ ስህተቶች መካከል ሌሎችን አፍኖ፤ ጨፍልቆ፤ መሪዎቻቸውን አስሮና አሳዶ፤ ድርጅታዊ ህልውናቸውን አውድሞ ራሱን ለምርጫ ማቅረቡና 100 በመቶ አሸነፍኩ ማለቱ ነው። የኢትዮጵያን ሕዝብ መናቁን አሳይቶ ራሱንም አስንቋል። ይኼን አሳዛኝና አሳፋሪ የምርጫ ውጤት ሲናገር አስቀድሞ ያላሰበው ጉዳይ አለ። ይኼውም ገዢው ፓርቲ የሕዝብን ባጀት ተጠቅሞ በተከታታይ ምርጫዎችን አሸንፍኩ ሲል ሌሎችን አገብኩና የፖለቲካ ምህዳሩን አሳዛኝ በሆነ ደረጃ አጠበብኩ ማለቱን መርሳቱ ነው። “ የወጋ ቢረሳም የተወጋ አይረሳም” እንዲሉ ሕዝቡ አልረሳውም። የፖለቲካው ምህዳር በተከታታይ እየጠበበ ሲሄድ የታገዱትና የተገለሉት የፖለቲካና የማህበረሰብ ክፍሎች፤ ልክ እንደ ኢኮኖሚው፤ ምርጫዎችም እንደተማረኩ፤ እንደተሰረቁና የሕዝብ መብቶች ዋጋቢስ እንደሆኑ ይቆጥሩታል። በመንግሥት ላይ ያለው እምነት ዜሮ ስለሆነ ሕዝብ ያለው አማራጭ የራሱን መብት በመሰለው ዘዴ ማስከበር ይሆናል። ሜጀር ጀኔራል አበበ ተክለሃይማኖት ለሪፖተር ጋዜጣ በሰጠው ሰፊ ትንተና ኢትዮጵያ “መንታ መንገድ ላይ” እንደምትገኝ አስምሮበታል። ሌሎች ኢትዮጵያዊያንና አብዛኛው የምእራብ አገሮች ሕዝብ የተሳለቀበትን ምርጫ በሚመለከት እንዲህ ይላል። “የጠቅላላ ምርጫው ውጤት ከታወጀበት ስድስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መቶ በመቶ ያሸነፈው ኦህዴድ/ኢህአዴግ ትጥቅ የተቀላቀለበት ሕዝባዊ አመፅ ተቀሰቀሰበት።” መስዋእት የሆኑት፤ መድረሻቸው የማይታወቀው፤ የተሰደዱትና የታሰሩት ወጣቶች በኦሮምያ፤ በሰሜን ጎንደር፤ በጋምቤላ፤ በአዋሽ ሸለቆ፤ በኦጋዴንና ሌሎች ቦታዎች ስለታፈኑና መንቀሳቀሻ ስላጡ ነው እንጅ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ በኢህአዴግ አገዛዝ ላይ ማኩረፍና በልቡ መሸፈት የጀመረው ከምርጫው በፊት ነው። የዲሞክራሳዊ መብት ጭላንጭል ፈጽሞ ተዘጋ፤ የሕዝብ ዐመጽ ተከሰተ። አሁንም ጀኔራሉ እንዳስቀመጠው ሁኔታው “የተዳፈነ እሳት ነው።” ሁሉን የሚያሳትፍ መንግሥት ካልተቋቋም ችግሮቹ ሊፈቱ አይችሉም። “ሁሉም ሕዝቦች በዲሞክራሳዊ አስተዳደር እጦት እየተለበለቡ ነው።” እንዴት አድርጎ ነው መዓከላዊ መንግሥት አለ የሚባለው?

ብዙዎቻችን ስናሳስብ የነበረውን አደጋ የህወሓት አባልና ከፍተኛ ስልጣን የነበረው ሜጀር ጀኔራል አበበ ግልጽ በሆነ ደረጃ አስቀምጦታል። “የሕዝቦችንና ብሎም የአገራችንን ህልውና የሚፈታተኑት መሰረታዊ ችግሮችን በሚገባ ተጠንተው ሕዝባችንን በተሟላ መንገድ ባሳተፈ ግልጽነትና ተጠያቂነት በሰፈነበት፤ የሕግ የበላይነት በመከተልና ዲሞክራሳዊ ሕገ-መንግሥታዊ ተቋማትን በመገምገም አጠቃላይ ስርዓቱን መፈተሽ ይገባል።” መቶ አንድ ሚሊየን ሕዝብ በሚኖርባት “አገር አንድ ፖለቲካዊ ኃይል ሁሉንም ነገር ጠቅልሎ ከያዘ አደገኛ በሽታ መሆኑን መገንዘብ መቻል አለበት” ይላል። ኢትዮጵያ የደረሰባት አደጋ የውስጥ ብቻ አለመሆኑን ከዚህ በፊት አሳስቤኣለሁ። ዛሬ የኢትዮጵያ ጠላት መንግሥታት የውስጥ አክራሪዎችንና ተገንጣዮችን ከማባበል አልፈው ድጋፍ ይሰጣሉ። አገሪቱ እንድትፈራርስና ያላትን ግዙፍ የተፈጥሮ ኃብት (ወንዞች፤ ለም መሬቶች ወዘተ) ለራሷ ዘመናዊነትና ለሕዝብ ህይወትና ኑሮ መሻሻል እንዳትጠቀም እያደረጉ ነው። ግብጽ የተሃድሶ ግድብ ስኬታማ እንዳይሆን የምታደርገው ግፊትና ተንኮል ምሳሌ ነው። በብሄርና በኃይማኖት የተከፋፈለ ሕዝብ ለውጭ ጠላቶች ወንፊቶች እንደሚፈጥር ሊካድ አይችልም። ለዚህ መፍትሄው መሰረታዊ የአገዛዝ ችግሮችን አስወግዶ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አንድነት “ከብረት የጠነከረና” የተደጋገፈ የሕዝብ ግንኙነት መፍጠር ነው። የአሁኑ የጎሳ ፌደራል ስርዓት ይኼን ሊፈጥር አልቻለም። ለወደፊቱ የሚጠቅመውን የመንግሥት ስርዓት መወሰን የሚኖርበት የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ምሁራን፤ ልሂቃንና ባለሞያዎች ካለፈው ተምረው ጠቃሚና ለሕዝብ ስልጣን የበላይነት የሚያገለግል ሕገመንግስት ለሕዝቡ የማቅረብና ሕዝቡ እንዲወያይበትና እንዲያጸድቀው የማድረግ ሃላፊነት አለባቸው። ምርጫውና መብቱ የሕዝብ ነው።

ማንኛውም ዘመናዊ መንግሥት ራሱን ለማሻሻልና ለሕዝብ ተጠሪ ለመሆን ጥናትና ምርምር ያስፈልገዋል። ሆኖም፤ የማይሰራ ስርዓት በጥናትና በግምገማ ሊሻሻል አይችልም። ህወሓት/ኦህዴድ/ኢህአዴግ ብዙ ባጀት ፈሰስ አድርጎ ግዙፍ ጥናቶች አካሂዷል፤ ያልተጠና ነገር ብዙ የለም። የኦሮሞና ሌላ ሕዝብ ስርዓቱ አልበጀኝም ሲል የሚጠብቀው ጥናትና ግምገማ ሳይሆን የስርዓት ለውጥ ነው። ሕዝቡ በየቦታው ሕግን የጣሰ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር አይችልም እያለ ነው። ኪራይ ሰብሳቢና ሙሰኛ የሆነ የባለሥልጣንት ክበብ ሙስናን ጥናትና ምርምር ሊቀርፈው አይችልም። “የፌደራል መንግሥት በቢሊየን የሚገመት ሃብት የሚያንቀሳቅስ መንግሥት እንደመሆኑ መጠን በፌደራል ደረጃ የሚፈጸም ሙስና፤ እንዝህላልነትና አቅም ማነስ የሚያስከትለው አደጋ ከፍተኛ ነው።” ጥያቄው ለምን መፍትሄ አልተገኘም? የሚለው ነው። መልሱ በገዢው ፓርቲ፤ በተለይ፤ በህወሓትና በመንግሥት ተቋሞች መካከል ምንም ልዩነት የለም ነው። ኪራይ ሰብሳቢውን ኪራይ ሰብሳቢ ሊዳኘው አይችልም። ገዳዩን ራሱ ገዳይ ሊወነጅለውና ሊፈርድበት አይችልም። ተቋሞች የሚያገለግሉት የፓርቲውን ባለሥልጣናትና ቤተሰቦቻቸውን ነው። ስርዓቱ “ማፊያዊ ነው” የሚለው የመጣው ከዚህ ነው። የበላይ አመራሩ በሙስና የተዘፈቀ ስለሆነ ችግሩ “የአመራር ነው” የሚለውን እቀበላለሁ። ለዚህ አመራር የሚቀለው ደካማና ዝቅተኛ በሆኑ ሙሰኞች ላይ ጥብቅ እርምጃ መውሰድ መሆኑ በተደጋጋሚ ታይቷል። የበላይ ባለሥልጣናትንስ ማን ይዳኛቸዋል?

ኪራይ ሰብሳቢነት፤ ሙስና፤ ከአገር የሚሸሽ ግዙፍ ኃብት፤ ረሃብ፤ የስራ እድል እጦት፤ የአገር ውስጥና የውጭ ብድር እየጨመረ መሄድ ወዘተ ከቀጠለ የአገሪቱ እድገት፤ ጠቅላላና የነፍስ ወከፍ ገቢ ወደታች እየተሽከረከረ መሄዱ የማይቀር ነው። ድርብ አሃዝ እድገት የሚባለው በዚህ ዓመት ከግማሽ በላይ ዝቅ እንደሚል አይ ኤም ኤፍ ተናግሯል፡፡ የኑሮ ውድነት፤ የስራ እድል አለመኖር፤ ሙስና፤ ጎሳዊ አድልዎ፤ ጠባብ ዘረኝነት ወዘተ ለሰላማና ለእርጋታ ጸር ይሆናሉ። የውጭ ጠላቶች መግቢያ ቀዳዳ እየሰፋ ይሄዳል። አሁን ወደ ውጭ የሚጎርፈው ቢያንስ $35 ቢሌየን ደርሷል፤ የሚዘረፈው ኃብት እየተባባሰ ይሄዳል።

የሕግ የበላይነት ክፍተት ለሙስና አመች ሆኗል

የኢትዮጵያ ሕዝብ የሕግ የበላይነትን የሚያንጸባርቅ አገልግሎት አግኝቶ አያውቅም። በትንተናዎቸ በተደጋጋሚ እንዳቀረብኩት የሕግ የበላይነት ማለት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በሕግ ፊት እኩል ሲሆንና ተቋሞች ይኼን መብት ያለምንም አድልወና ያለምንም የፖለቲካ ተጽኖ ስራ ላይ ሲያውሉት ነው። ጎሳዊ አድልዎ ካለ የሕግ የበላይነት አይታሰብም። ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ኢህአዴግ በሕገመንግሥቱ እመራለሁ ሲል ቆይቷል። ሕጉን ያወጣው ራሱ፤ ሕጉን ተርጓሚውና አስፈጻሚው ራሱ ነው። ከንጉሱና ከደርግ በምን ይለያል? ከላይ በትርጉሙ እንዳሳየሁት፤ የሕግ የበላይነት ሕግን ሽፋን አድርጎ ሕዝብን ከመቅጣት ይለያል። እንዴት? በቅርቡ ገንዘብ በማሸሽ የተጋለጠው የአይስላንድ መሪ ጉድ ገጠመው። ሕዝቡ ሰላማዊ ሰልፍ ወጥቶ “አንተም ሆንክ ቤተሰብህ ከሕግ በላይ አይደላችሁም” ስላለው ራሱን ከስልጣኑ አውርዷል። ያለ አግባብ ያሸሸውና ያካበተው ኃብት እንደሚመለስ ይገመታል። እንግዲህ በተግባር ሲታይ፤ የሕግ የበላይነት ማለት ንጉስ ሆነ ፕሬዝደንት፤ ሚሊየኔር ሆነ ምስኪን፤ ሴት ሆነ ወንድ፤ ክርስቲያን ሆነ ሙስሊም በሕግ ፊት እኩል ናቸው ማለት ነው። የስልጣን ብልግና ተቋማዊ በሆነባት ኢትዮጵያ የሕግ የበላይነት አለመኖሩ አያከራክርም። እንዲያውም ከሕግ ውጭ መስራት እንደ ጀግንነት የሚታይባት አገር ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን አትቀርም።

ለማጠቃለል፤ ቁም ነገሩ ስለመተባበርና ስለአንድነት ስለሆነ ዶር መረራ ጉዲና የኢትዮጵያ የታሪክ ፈተናዎች እና ህልሞቻችን ሊታረቁ ወይንስ ኢትዮጵያን ሊያፈርሱ? በሚለው ጠቃሚ ትንተና እንዲህ በሚል ደምድሟል። “የተቃዋሚው ኃይል ከገባበት የፖለቲካ ቅርቃር (dead-end) ለመውጣት ራሱን እንደገና ማደራጀት አለበት፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ አዲስ የመሰባሰብ ስትራቴጂ መቀየስ አለበት፡፡ ነጻ የሆኑ የተቃዋሚ ድርጅቶች (ኢህአዴግ በቀጥታም ሆነ በሥውር የማይቆጣጠራቸው) በቁርጠኝነት የሀገሪቱ ችግሮች የሚፈቱበትን ዲሞክራሲያዊ ጨዋታ (democratic game) ውስጥ መግባት ዐለባቸው፡፡ የእንዲህ ዓይነቱ ጨዋታ ውጤት የሚያመጣው በአንድ ቡድን ወይም ሁለት ቡድኖች የተረጋጋች ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መፍጠር ይቻላል የሚለው ሕልም ሲቀር መሆኑን በውል መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በአንድ ቡደን ሥር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መገንባት ይቅርና፣ የተሻለ እድገት እንኳን ማምጣት እንዳልተቻለ የቅርብ ታሪካችን በቂ ምስክር ነው…. የኢህአዴግ መንግሥት ለ24 ዓመታት የአንድ ቡድንን ሕልም አሳካለሁ ብሎ ራሱም ታምሶ ሕዝብን ቢያምስም፣ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ስትፈጠር እያየን አይደለም፡፡” እድገት አለ ተብሎ የሚወራው ከእውነቱ የራቀ መሆኑን የአብዛኛው ሕዝብ ኑሮና ህይወት ሁኔታ በግልጽ ያሳያል። “ከሠሩት ሥራ የፕሮፓጋንዳ ጫጫታቸው እንደሚበልጥ የኢህአዴግ መሪዎችም ያውቁታል፡፡” በየቀኑ የሚለፈፈው ፕሮፓጋንዳ የኢትዮጵያን ሕዝብ ምግብ ሆኖ ከረሃብ አሮንቃ ነጻ አላወጣም። ወጣቱ ትውልድ በአገሩ ኮርቶ እንዲኖር አላደረገም። የሕዝብን ማህበራዊ ግንኙነቶች አላጠናከረም። ኢትዮጵያን ከጥገኝነት ነጻ አላወጣትም። ዶር መረራን ለመጥቀስ “ ወደ መቶ ሚሊዮን” የደረሰው “የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕልምና ፍላጐቱ ከኢህአዴግ መሪዎችና ካድሬዎቹ ሕልምና ፍላጐት በጣም ይሰፋል፡፡”

ነባር ሁኔታዎች ለእውነተኛ ዲሞክራሳዊ ለውጥ መመቻቸታቸው በግልጽ እየታየ ለምን ለመሰብሰብ፤ አብሮና ተባብሮ ለመስራት አልተቻለም? ለሚለው ጥያቄ ዶር መረራ የሚከተለውን ምክር አቅርቧል። “ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ሁኔታ የተቃዋሚው ኃይል እንደገና ራሱን ቢያደራጅ፣ የኢትዮጵያ የነፃነት ቀን ሩቅ አይመስለኝም፡፡ የማይታረቁ ሕልሞቹን ተሸክሞ በምኞች ፈረስ መጋለቡን ከቀጠለ ግን፤ ሕልሞቹ ሕልም ከመሆን አያልፉም፡፡ የቡዳ ፖለቲካችንን ተሸክመን ላለፉት አርባ ዓመታት ኳትነናል፣ ለሚቀጥሉት አርባ ዓመታትም በያዝነው መንገድ ብንኳትንም የትም አንደርስም፡፡ ስለሆነም፣ የተቃዋሚ ኃይል ነን የምንለው፤ እስካሁን ላለፉት አርባ ዓመታት የሠራናቸውን ስህተቶች ባረመ መልኩ በአዲስ መንፈስ፣ በጋራ ሕልም ዙሪያ እንደገና በሀገር ውስጥም፤ ውጭም መደረጀት የግድ ይመስለኛል፡፡ ውጤት አልባ ለሆነው የተበታተነ ትግል የሚባክነውን የሀገር ሀብት ወንዝ ሊያሻግር ለሚችል የጋራ ትግል ማዋልም የግድ ነው፡፡” ለዚህ ግን በግልጽ መነጋገር፤ የጋራ ብሄራዊ ዓላማ መመስረት አስፈላጊ ነው። ከየትኛውም አቅጣጫ ይምጣ የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ የሚፈልገው ግትርነትን፤ ቂም በቀልን፤ ጠባብ ብሄርተኝነትን አይመስለኝም።

ለማንኛውም፤ ይህ መልእክት ወደ ተግባር መለወጥ አለበት። በልሂቃንና ምሁራን መካከል ፈቃደኛነት ካለ ለጋራ አገር ህልውናና ዘላቂነት፤ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍትህ-ርተእ፤ ለነጻነትና ሰብአዊ ክብር፤ የኑሮና ህይወት መሻሻል፤ በሕግ ፊት ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እውነተኛ እኩልነት አብሮና ተባብሮ ለመስራት የሚቻልበት ወቅት አሁን ነው። ይህ ሊሆን የሚችለው የስልጣን ሽግግር ሲኖር ነው፤ ገዥውን ፓርቲ የሚጨምር። በዘላቂነት ሲታይ እውነተኛ ዘላቂነት ያለው ዲሞክራሳዊ ስርዓት ያለ መድብለ ፓርቲ ነጻና ፍትሃዊ ውድድር አይቻልም። የአገሪቱ ዘላቂነት የሚረጋገጠው፤ ሰላምና እርጋታ የሚቻለው፤ ዘላቅነትና ፍትሃዊነት ያለው እድገት መሰረት የሚጥለው ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ የማህበረሰብና ሌሎች ስብስቦች ለብሄራዊ መግባባት ሲዘጋጁና የስልጣን ሽግግር ስኬታማ ሲሆን ነው። የተቃዋሚ ፓርቲዎች የመደራደር አቅም ጠንካራ የሚሆነው ለመተባበር፤ ቢቻል ለአንድነት ቆርጠው ሲነሱ ብቻ ነው። ተባብረው ለአንድ ብሄራዊ ዓላማ ከቆሙ ገዢው ፓርቲ ለድርድር የማይስማማበት ምክንያት አይኖርም።

ህብር ሬድዮን በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ ከ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *