Hiber Radio: የሀብታሙ አያሌው ጤንነት አልተሻሻለም፣ ሰማያዊ ፓርቲ ከአገር ወጥቶ እንዲታከም መንግስት የጣለውን እግድ እንዲያነሳ ጠየቀ

Habtamu-Ayalew-hospital-protest

የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ሀላፊ ሀብታሙ አያሌው ጤንነቱ ያልተሻሻለ ሲሆን ዛሬም ራሱን እንደማያውቅና መናገር እንደማይችል በቅርብ የጎበኙት የገለጹ ሲሆን አመሻሽ ላይ ገርጂ ካዲስኮ ሆስፒታል ጠይቀነው ሲመለሱ እንደገለጹት ባይነቃም አልፎ አልፎ አንገቱን ነቅነቅ፣ አይኖቹንም በትንሹ ገለጥ ከማድረግ ውጭ የጤናው ሁኔታ ዛሬም አሳሳቢ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ እንደጻፈው ባለቤቱ ወ/ሮ ቤተልሄም አዛናው እንደነገረችው ከሆነ፣ ሀብታሙ በየ8 ሰዓት ልዩነት የሚወሰድ ህመም ማስታገሻ እየተሰጠው ነው። “ዶ/ሩም ሀብታሙ ከባድ የህመም ስቃይ ውስጥ ስለሚገኝ እስከፊታችን አርብ ድረስ ምንም የሚጀምረው ህክምና የለም።” ብሎኛል ስትል መግለጿን ጽፋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰማያዊ ፓርቲ ዛሬ ባወጣው መግለጫ የሀብታሙ ዐያሌው የጤንነት ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑንና አገዛዙ በሀብታሙ ላይ በፍርድ ቤት ስም የጣለውን እግድ አንስቶ ከአገር ወጥቶ እንዲታከም እንዲፈቀድለት ጠይቋል። ፓርቲው በሀብታሙ ላይ ለሚደርሰው አደጋ መንግስት ሀላፊነቱን የመወስድ መሆኑን ጭምር ገልጿል።

በስልታን ላይ ያለው አገዛዝ በእስር ቤት ሀብታሙን ጨምሮ በህሊና እስረኞች ላይ በእስር ወቅት በሚያደርሰው ስቃይ ለተደጋጋሚ ጤና መታወክ ሲጋለጡ ህክምና ሲጠይቁ እንደ ፕ/ር አስራት ሬሳችሁ ነው ከእስር ቤት የሚወጣው ጭምር እያሉ በጥላቻ እንደሚዝቱ ተደጋግሞ መዘገቡ ይታወሳል።

ሀብታሙ አያሌው በእስር ቤት በደረሰበት ተደጋጋሚ ማሰቃየት ለከፍተና የኩላሊትና የሂሞራይድ በሽታ በተጋለጠበት ወቅት ከእስር ቤት በጊዜው ሆስፒታል ካለመወሰዱም ሌላ ሆስፒታልም ሲሆድ በተደጋጋሚ ካርዱ ጠፍቷል እየተባለ ለረጅም ተደጋጋሚ ቀጠሮ ይዳረግ እንደነበር ገልጿል።

ሀብታሙ በእስር ቤት የደረሰበትን ስቃይ ከእስር ከተፈታ በሁዋላ ለመጀመሪአ ጊዜ ለህብር ሬዲዮ በሰጠው ቃለ መጠይቅ መግለጹ አይዘነጋም። የሰማያዊ ፓርቲ መግለቻ ግርጌ የሀብታሙን ቃለ መጠይቅ አያይዘነዋል።ሰማያዊ ፓርቲ አወጣው መግለጫ የሚከተለው ነው።

በግለሰቡ ሕይወት ላይ ለሚደረስው አደጋ መንግሥት ኃላፊነቱን የሚወስድ መሆኑን ጭምር ፓርቲው አክሎ ገልጾአል

መንግስት የዜጎችን ደህንነትና ጤንነት የመጠበቅ ኃላፊነት ያለበት ቢሆንም በሀገራችን በሕግ ከለላ ስር ያሉ ዜጎች ተገቢውን ሕክምና ባለማግኘታቸው ሕይወታቸው አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ በእስር ቤት እያሉ ተገቢውን ሕክምና ማግኘት ባለመቻላቸው ለሞት የተዳረጉ እንዳሉ የሚታወቅ ነው፡፡

አቶ ሀብታሙ አያሌው በተለምዶ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ በመባል በሚታወቀው ተቋም በምርመራ ወቅት በደረሰባቸው ህመም ሕክምናውን በሀገር ውስጥ ባሉ የጤና ተቋማት መታከም እንደማይችሉና ወደውጭ ሀገር ሄዶ ህክምና ማግኘት እንዳለባቸው የተገለፀ ቢሆንም ከሀገር እንዳይወጡ በፍ/ቤት ታግደዋል፡፡

በመሆኑም አቶ ሀብታሙ አያሌው በፍ/ቤት የተጣለባቸው ዕግድ ተነስቶ ወደ ውጭ ሀገር ሂደው እንዲታከሙ አስፈላጊው ሁሉ እንዲደረግ እየጠየቅን ይህ ባይሆንና ህክምና ባለማግኘቱ በግለሰቡ ሕይወት ላይ ለሚደረስው አደጋ መንግሥት ኃላፊነቱን የሚወስድ መሆኑን እናሳስባለን።

ግልባጭ፣

ለኢፊዲሪ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት

፨ለሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ለፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *