Hiber Radio: አንጋፋው ጋዜጠኛ አበራ ወጊ በአሜሪካን አገር በሳዲያጎ በመኪና አደጋ ሕይወቱ አለፈ /የኢነጋማ ፎረም የጋዜጠኛው ሞትን አስመልክቶ መግለጫ አወጣ

abera-wegi-hiber-radio

በሳንዲያጎ ከተማ የኮሚኒቲ ሊቀመንበር የነበረው የቀድሞ የማዕበል ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አንጋፋው ጋዜጠኛ አበራ ወጊ ከትላንት በስቲያ አርብ ምሽት በሳንዲያጎ ከተማ ትራፊክ በሚበዛበትን ኖርዝ ፓርክ ጎዳና በመኪና ተገጭቶ ሕይወቱ አልፏል።በሳንዲያጎ የሚገኙ የኢትዮጵያውያን የማህበረሰብ አባላት በከተማው በሚገኘው ደብረ ሳህል ቅዱስ ገብርኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በመሰባሰብ ሐዘን ተቀምጠዋል።

ጋዜጠኛ አበራ ወጊ በማህበረሰቡ ተወዳጅ ፣ለሰዎች ደራሽና ሩህሩህ እንደነበር በዝግጅቱ ላይ የተገኙ ገልጸዋል።በስደት የሚገኙ የኢትዮጵያ የነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች በበኩላቸው የጋዜጠና አበራ ወጊን ዜና ዕረፍት እንዳስደነገጣቸው ባወጡት የጋራ መግለጫ ገልጸው፣ አንጋፋው ጋዜጠኛ አበራ ወጊ ለሙያው የደከመ፣በአገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለአገሩና ለወገኑ ተቆርቋሪ በሙያው ሳቢያ እስርና እንግልት የተፈጸመበት ለተጨማሪ እስር ሲፈለግ ለስደት መዳረጉን ጠቅሰዋል።

የኢነጋማ ፎረም አንጋፋውን ጋዜጠኛ አበራ ወጊን በተመለከተ ያወጡትን መግለጫ አስከትሎ እናቀርባለን።የህብርሬዲዮም በሙያ አጋራችን በጋዜጠኛ አበራ ወጊ ሞት የተሰማውን ሐዘን ገልጻል። ለቤሰሰቦቹ፣ለሙያ አጋሮቹ፣ ለሳንዲያጎ የኢትዮጵያውያን ኮሚኒቲ ማህበረሰብ አባላት እና ወዳጅ ዘመዶች መጽናናትን እንመኛለን።

የጋዜጠኛ አበራ ወጊ ድንገተኛ ሞትን አስመልክቶ በስደት የሚገኙ የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች ማህበር አባላት በኢነጋማ ፎረም አማካይነት መግለጫ አውጥተዋል።የመግለጫው ሙሉ ቃል ተከትሎ ቀርቧል።

በሳዲያጎ ከተማ ነዋሪ የነበረው እና ለረዥም ግዜ በነጻ ፕሬስ ጋዜጠኝነት ያገለገለው፤ ጋዜጠኛ አበራ ወጊ በድንገተኛ የመኪና አደጋ ከዚህ አለም በሞት መለየቱን የሰማነው፤ በጥልቅ የሃዘን ስሜት ውስጥ ሆነን ነው። ጋዜጠኛ አበራ ወጊ… ዛሬ በእስር ከሚገኘው ከጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ጋር አብሮ ሰርቷል። በተለይም ማዕበል በተሰኘው ጋዜጣ ላይ ዋና አዘጋጅ በመሆን ለብዙ አመታት አገልግሏል።

አቶ አበራ ወጊ የማዕበል ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በነበረበት ወቅት፤ በበሳል ብዕሩ ወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ጽፏል። በተለይም በዚሁ የማዕበል ጋዜጣ የፊት ገጽ ላይ፤ “ኢትዮጵያዊነት የቃል ኪዳን ማተማችን ነው” የሚለውን መሪ ቃል ያመነጨው፤ አቶ አበራ ወጊ ነበር።ከዚሁ የጋዜጠኝነት ስራው ጋር በተያያዘ፤ የታሰረበት እና ለብዙ ስቃይ የተዳረገበት የክስ መዝገብ፤ አነጋጋሪ እና አስገራሚ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን፤ በህግ ስም የተስራውን ግፍ ስለሚያሳይ፤ በዚህ አጋጣሚ ለመጥቀስ እንወዳለን።

ወቅቱ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጦርነት ውስጥ ውስጡን እየተካሄደ የነበረበት ግዜ ነው። እናም ጋዜጠኛ አበራ በድንበር አካባቢ ይደረግ የነበረውን የተኩስ ልውውጥ በዜና መልክ አቀረበ። ዜናውን ተከትሎ… በወቅቱ የትግራይ ፕሬዘዳንት የነበሩት አቶ ገብሩ አስራት፤ “በትግራይና ኤርትራ ድንበር፤ እንኳንስ ጦርነት ተነስቶ ክባድ የተኩስ ድምፅ ሊሰማ ቀርቶ፤ የባረቀም ጥይት የለም።” ሲሉ፤ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ደግሞ፤ “በኤርትራ እና ኢትዮጵያ ድንበር፤ እንኳንስ ጥይት ጅራፍም አልጮኸም።” በማለት ፓርላማውን ፈገግ አደረጉት። ተከታዮቻቸውም የጦርነት ሰበር ዜና አቅራቢውን፤ ጋዜጠኛ አበራ ወጊን “ህዝብን ከህዝብ ጋር ለማጣላት፤ የሃሰት ዜና አቀረብክ” ብለው አሰሩት።

ጋዜጠኛ አበራ ወጊ፤ በዚህ ዜና ምክንያት እስር ቤት እያለ፤ ውስጥ ውስጡን ሲደረግ የነበረው ጦርነት ተጋግሎ ሊደበቅ የማይችልበት ደረጃ ላይ ደረሰ። እንደ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ግንቦት 4 ቀን፤ 1990 ዓ.ም. በፓርላማ ደረጃ ጦርነቱ ታወጀ። ምንም እንኳን ጦርነቱ ገሃድ ቢወጣም ለአቶ አበራ ወጊ ግን ምህረት አልተደረገለትም፤ ወይም “ለካስ ያቀረብከው ዜና እውነት ነበር።” ተብሎ ይቅርታ አልተጠየቀም። ጦርነቱ ተፋፍሞ እያለ፤ የጠቅላይ ሚንስትሩ መግለጫ እንደ መረጃ ቀርቦም ጭምር፤ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ 2ኛ ችሎት ዳኛ ሃጎስ ወልዱ፤ በአቶ አበራ ላይ የአንድ አመት ተኩል እስራት ፈረደበት።

አቶ አበራ ወጊ ከላይ በተጠቀሰው “የኢትዮጵያ ኤርትራ ጦርነት ”ለአንድ አመት ከስድስት ወር ከታሰረ በኋላ ሲፈታ፤ “በሌላ ክስ ይፈለጋል” ብለው፤ ከእስር ቤቱ ውጪ የማዕከላዊ ምርመራ ፖሊሶች እየጠበቁት ነበር። ከ’ነዚህ ፖሊሶች በማምለጡ ምክንያት፤ ደህንነቶች ጭምር ጋዜጠኛ አበራ ወጊን ማደን የጀመሩበት አጋጣሚ ተፈጠረ። በዚህ መሃል ነው የሚወዳት አገሩን፤ ኢትዮጵያን ለቅቆ ለመሰደድ የበቃው።

ጋዜጠኛ አበራ በሳንዲያጎ ከተማ ነዋሪ በነበረበት ወቅት፤ በሃዘን እና በደስታ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን አልተለየም። ከኢትዮጵያ ወጥተው በስደት ላይ የነበሩ ጋዜጠኞችን ለመርዳት ይደረግ በነበረው እንቅስቃሴ፤ ግንባር ቀደም ተባባሪ፤ ለተቸገሩ ደራሽ እና አጽናኝ ወንድማችን ነበር። ከጋዜጠኝነቱ በተጨማሪ ለኢትዮጵያ አንድነት ለቆሙ የሲቪክ እና የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ልባዊ ድጋፍ በመስጠት ይታወቃል።

በመጨረሻም በህይወት በነበረበት ወቅት በቁጭት ከሚናገራቸው ነገሮች ፤ እስር ቤት ውስጥ እያለ አስፈላጊ ህክምና ባለማግኘቱ ለተባባሰ የስኳር ህመም መዳረጉን ሁሌም በቁጭት ከሚያነሳቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ነው። በኋላ ላይ ህመሙ እየባሰበት ሲመጣ፤ ወደ ሆስፒታል ከወሰዱት በኋላ፤ ያልተገባ በሽታ በመርፌ እንደተሰጠው፤ ይህንንም ከእስር ቤት ከወጣ በኋላ በህክምና ማወቁን በቁጭት ይገልጽልን ነበር።

የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዘዳንት የነበሩት፤ አቶ ክፍሌ ሙላት ተጨማሪ ምስርነታቸውን ሲሰጡ፤ “በአቶ አበራ ወጊ ላይ የተደረገበትን በደል ይህ ብቻ አይደለም። ከእስር ቤት ከወጣ በኋላ የነገረኝ አንድ ጉዳይ አለ። ‘አንድ ቀን ለኢትዮጵያ ህዝብ ምስክርነትህን ትሰጥልኛለህ።’ በማለት፤ በእስር ላይ ሳለ ዘር እንዳያፈራ ለማድረግ አሰቃቂ ድብደባ ያደረጉበት መሆኑን ገልጾልኛል።” በማለት ምስክርነቱን ሰጥቷል። በማያያዝም፤ “ሃሳብን በነጻነት በመግለጻቸው፤ ብዙ ግፍ ከተሰራባቸው የነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች መካከል አንዱ ነበር።” በማለት አቶ ክፍሌ ሙላት የተሰማውን ሃዘን ገልጿል።

ሌሎች በስደት ላይ የሚገኙ የቀድሞ የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች፤ አቶ አበራ ወጊ በኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ታሪክ ውስጥ ያበረከተውን መስዋዕትነት በማክበር፤ “ስምህ ከመቃብር በላይ ይኖራል” ለማለት፤ ይህን ወቅታዊ መግለጫ አውጥተናል። ለወዳጅ እና ዘመዶቹ አምላክ መጽናናትን ይሰጥልን ዘንድ እንማጸናለን።

በህይወት በነበረበት ወቅት ራሱ ጋዜጠኛ አበራ እንዳለው… “ኢትዮጵያዊነት የቃል ኪዳን ማተማችን ነው”!

በስደት የሚገኙ የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች።

ህብር ሬድዮን በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ ከ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *