Hiber Radio: ሀብታሙ አያሌው በእስር ቤት ደረሰበት ስቃይ ለደረሰበት የጤና መቃወስ ሕክምናውን ለመከታተል አሜሪካ ገባ

ሀብታሙ አያሌው እና ባለቤቱ ወ/ሮ ቤተልሔም ዳላስ ኤርፖርት፣ዋሽንግተን

(ህብር ሬዲዮ) በእስር ቤት በደረሰበት ስቃይ ለከባድ የጤና እክል የተዳረገው የተቃዋሚው ፖለቲከኛ ሀብታሙ አያሌው ለረጅም በስልታን ላይ ያለው አገዛዝ በወቅቱ ከአገር እንዳይወጣ ፍርድ ቤትን ተገን አድርጎ ሲከለክል ቆይቶ በመጨረሻ ለህክምና ዛሬ ማምሻውን ሰሜን አሜሪካ ዋሽንግተን በሰላም ገብቷል።

ሀብታሙ አያሌው የጤናው መቃወስ በተደጋጋሚ እየተባባሰ መሄድን መሰረት አድርገው የሐኪሞች ቦርድ ሕክምናውን በአገር ቤት ማድረግ ስላማይችል ከአገር እንዲወታ የወሰነው አስቀድሞ ቢሆንም ፍርድ ቤትን አንዱ የአፈና መዋቅሩ ዱላ አድርጎ የቀተለው አገዛዝ በእስር ፍርድ ቤት በቀረበባቸው የሽብርተኝነት ክስ ከሳሹ ዐቃቤ ሕግ በቂ ማስረጃ አላቀረበም ተብሎ ከሁለት ኣመት በላይ ታስሮ ቢፈታም ዐቃቤ ሕግ ይግባኝ አለ በሚል ሀባታሙ በጊዜው ከአገር ወጥቶ ሕክምና ሳያገኝ ቆይቷል።የዛሬው ወደ አሜሪካ የሀብታሙ ለጤናው ምርመራና ዘላቂ ሕክምና መምጣት በቀጣዩ የሕክምና ሒደት ይጠበቃል።

ሀብታሙ አያሌውን ጨምሮ አገዛዙን በሰላማዊ መንገድ የሚቃወሙ ወገኖች በተደጋጋሚ በእስር ቤት በሚደርስባቸው ችግር ሳቢያ ለከፋ የጤና አደጋ አንዳንዶችም ለሞት መዳረጋቸው ይታወሳል። አገዛዙ ሙሉ ለሙሉ የተቃውሞ ድምጾችን በአፈነበት በአሁኑ ወቅት ከሀብታሙ ጋር ታስሮ ከሁለት ዓመት እስር በሁዋላ ከእስር ወጥቶ የነበረው አቶ ዳንኤል ሺበሺን ጨምሮ በርካታ የተቃዋሚ መሪ መሪዎች እና ነጻ አሳቢ ዜጎች በገፍ ታስረው እየተሰቃዩ መሆኑ አይዘነጋም።

አገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ ለሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ ለጋዜጠኞች፣ ለብሎገሮችና ለሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ሲኦል እንደሆነች ነው።ብዙዎች ለአገራቸውና ለሕዝባቸው ሲሉ ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ ነው። የሕግ ስርዓቱ የበሰብሰ ነው። በአሥር ሺሆች ከሚቆጠሩ ከራሳችው ትቅም ይልቅ የአገርን ጥቅም ካስቀደሙ ታጋዮች መካከል አቶ ሃብታሙ አያሌው አንዱ ነው።

አቶ ሃብታሙ በሕወሃት ሕግ ወጥ በሆነ መንገድ የታገደው፣ አንጋፋ የነበረው የአንድነት ለዲሞክራሲ ለፍትህ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊ የነበረ ሲሆን ፣ ከጥቂት አመታት በፊት በመላው ኢትዮጵያ ሰላማዊ ሰልፎች በማድረግ ህዝብን ማንቀሳቀስ የቻለው የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት እንቅስቃሴ ግብረ ኃይል ሰብሳቢም ነበር።በሚሊዮኖች ድምጽ እንቅስቃሴ ወቅትም ነበር ሕወሃት “ሽብርተኛ ነህ” በሚል ሐምሌ ወር 2006 ዓ.ም አቶ ሃብታሙን ወደ ማእከላዊ የቶርቸር ቻምበር አፍኖ የወሰደው።

በማእከላዊ በደረሰበት ኢሰብዓዊ ግፍና ቶርቸር ለከፍተኛ ሕመም ተዳረገ። ከሰላሳ ጊዜ በላይ የፍርድ ቤት ምልልስ በኋላ፣ ፍርድ ቤቱ ፣ ወደ ዉጭ እንዳይወጣ እገዳ አድርጎ፣ ከወህኒ ዉጭ ሆኖ እንዲከራከር ወሰነ። ሆኖም እስር ቤት እያለ በሕወሃት መርማሪ ነን ባዮች ወንበዴዎች በደረሰበት ትልቅ ጉዳት ለከፍተኛ ሕመም የተዳረገው አቶ ሃብታሙ፣ ራሱን እስኪሰት ድረስ ታሞ ለሆስፒታል ተዳረገ። ሐኪሞች “ከአቅማችን በላይ ነው” በሚል ወደ ዉጭ ሄዶ እንዲታከም ገለጹ። ፍርድ ቤቱ እገዳዉን እንዲያነሳ ጥያቄ ቀረበለት። ሆኖም ፍርድ ቤቱ እገዳዉን አላነሳም አለ። አቶ ሃብታሙ ሕመሙን ተሸክሞ፣ በእግዚአብሄር እርዳታ፣ አገር ዉስጥ ባሉ ሐኪሞች ክትትልና በማስታገሻዎች እስከአሁን ቆይቶ፣ በመጨረሻ ፍርድ ቤቱ የቀረበበትን ክስ ዉድቅ በማድረጉ ለሕክምና ዛሬ ጃኑዋሪ 12 ቀን ወደ አሜሪካ ሊመጣ ችሏል።

አቶ ሃብታሙ ወደ ዉጭ ሄዶ እንዳይታከም ተደረጎ በነበረበት ወቅት “እነአቦይ ስብሃት ከዘጠና በላይ ዓመታቸው የክብር ዶክትሬት ሲሰጣቸው እኔ በዚህ ዕድሜዬ የሞት ደብዳቤ ተጽፎልኛል። በእኔ ላይየሚፈርደው ግን እግዚአብሔር ነው። ዝም ብዬ የእግዚአብሔርን ማዳን እጠብቃለሁ” ነበር ያለው። ሀብታሙ እንዳለውም በፈጣሪው እርዳታ ለዛሬዋ ቀን በቃ እንጂ ያ ሁሉ የአገዛዙ ደማ ነገሮችን ከዚህ ተቃራኒ ለመውሰድ እንደነበር መረዳት አይከብድም።

ለአቶ ሃብታሙ የአሜሪካ ቆይታዉ መልካም እንዲሆን እየተመኘን፣ ፈጣሪ በቶሎ እንዲፈወሰው እንጸልያለን። ኢትዮጵያዊያንም ከዚህ በፊት ከአቶ ሃብታሙ ጎን እንደነበርን፣ ከዚህም በኋላ ከጎኑ መሆናችንን እንድንቀጥልም ጥሪ እናቀርባለን።

ሀብታሙ አያሌው ከእስር ቤት ከወጣ በሁዋላ ስለጤናውና የእስሩ ሁኔታ ለህብር ሬዲዮ ከዚህ ቀደም የሰጠው ቃለ መጠይቅ ለትውስታ አያይዘነዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *