Hiber Radio: ጀግናው በላይ ዘለቀ – በአቻምየለህ ታምሩ

ከዚህ በታች ያለውን አነስተኛ ጽሁፍ ከስድስት ወር በፊት የጻፍሁት ነው። የፈጠራ ታሪኩ ከሰሞኑም ስለተደጋገመ ለፈጠራ ተረት ተረቱ የሰጠሁትን ጽሁፍ በድጋሜ አትሜዋለሁ።

–––––––––––––

ባለፈው ሰሞን «ጎጃም ቢወለድም በላይ ኦሮሞ ነው» የሚል ግጥም ያለው አዲስ ዘፈን ተለቆ ነበር። የግጥሙ «ኃሳብ» ባለቤት የእውቀት ጾመኛው ተስፋዬ ገብረዓብ ነው። ተስፋዬ ገብረዓብ ከሁለት ዓመታት በፊት በተካነበት የእባብ ልቡ እየተሳበ «በላይ ዘለቀ ኦሮሞ ነው፤ ሙሉ ስሙም በላይ ዘለቀ ላቀዉ ቂልጡ አያኖ ገልገሊ ይባላል» ሲል በሬ ወለደ ጻፈ። ተስፋዬን ተቀብለው የኦነግ «ዶክተሮች» የወዲ ገብረዓብን ፈጠራ በስፋት አስተጋቡ። እኔ ሁልጌዜ የሚገርመኝ የኦነግ «ዶክተሮች» ተስፋዬ ፈልስሞ እንካችሁ የሚላቸውን ሸቀጥ «ምንጭህ ከምን?» ብለው ሳይጠይቁ እንደወረደ መቀበላቸው ነው። ተስፋዬ የወያኔ ፕሮጀክቶች የሆኑትን «የቡርቃ ዝምታን» እና «ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድን» የጻፈው በዚህ መልክ በበሬ ወለደ ነበር። ለነገሩ ሳይመረምር የሚያስተጋባ ተቀባይ ስላለው ለምን ይጨነቃል። በዚህም የተነሳ በተስፋዬ ልብ ወለድ ኦሮሞ የሆነው በላይ ዘለቀ በኦነጋውያን ዘንድ ቅቡል ሆነ። ግጥምም ተጻፈና «ጎጃም ቢወለድም በላይ ኦሮሞ ነው» ተብሎ ተዘፈነለት።

በላይ ጎጃም የተወለደ ኦሮሞ ቢሆን እንኳ «ጎጃም ቢወለድም በላይ ኦሮሞ ነው» ተብሎ ግጥም ይጻፋል ወይ ብዬ የዘፈን ግጥም ሀያሲያንን ለመጠየቅ ሞክሬ ነበር። ሁሉም የዘፈን ግጥም ሀያሲያን «ትግራይ ቢወለድም እገሌ አማራ ነው»፤ «ሸዋ ቢወለድም እገሌ ትግሬ ነው»፤ «ሀረር ቢወለድም እገሌ ስሜን ነው» ፤ «ናዝሬት ቢወለድም እገሌ ጋሞ ነው»፤ «ጎጃም ቢወለድም በላይ ኦሮሞ ነው» ወዘተ የሚል ይዘት ያለው የዘፈን ግጥም በሞያ ዘመናቸው ውስጥ እንዳላጋጠማቸው፤ ያን አይነት ይዘት ያለው የዘፈን ግጥም በትምህርት ቤትም እንዳልተማሩ፤ ቢጻፍም የግጥሙ ጥራት በጣም ደካማና የወረደ እንደሆነ አጫውተውኛል።

ኦሮሞ የነበላይ የእድሜ አጋር የሆኑ እንደነ ጀኔራል ጃጋማ ኬሎ አይነት ጀግና ኢትዮጵያውያን አርበኞችን አፍርቷል። ዘፋኙ ወይንም ግጥሙን የጻፉት የተስፋዬ ተማሪዎች «ጎጃም ቢወለድም በላይ ኦሮሞ ነው» የሚል ደካማና ኃሳብ የሌለው ዘፈን ከሚጽፉ እንደ በላይ ዘለቀ ጀግና ለሆኑት ለእውነተኛው የኦሮሞ ጀግና ኢትዮጵያዊ ለጄኔራል ጃጋማ ኬሎ ትንሽ ዘፈኑን ቀየር አድርጎ ቢዘፍን ዘፈኑ የእውነት ማስታወሻ ይሆን ነበር ብለውኛል። ኦነጋውያን እነ ጀኔራል ጃጋማ ኬሎን፣ ራስ መስፍን ስለሽን፣ ገረሱ ዱኪን፣ በቀለ ወያን የመሰሉ ስመ ጥር የኦሮሞ ተወላጅ የኢትዮጵያ አርበኞች «ጎበናዎች» እያሉ እያሸማቀቁ ለምን የእነዚህ አርበኞች የእድሜና የዘመን ጓድ የሆነውን ደጃዝማችን በላይ ዘለቀን ኦሮሞ አድርጎ ማክበሩን ለምን ፈለጉት? ለነገሩ አገራችን ውስጥ ያለው የዘር ፖለቲካ ብሂል «የራስ» የሚሉትን እየጣሉና እያኮሰሱ «የሌላውን» ደግሞ ማንሳትና መንጠቅ፤እንዲሁም ለጠብ መጋበዝ ስለሆነ «ጎጃም ቢወለድም በላይ ኦሮሞ ነው» የሚል ኃሳብ የሌለውን ዘፈን መደረቱ የማይጠበቅ አይደለም።

በላይ ዘለቀ «አባ ኮስትር» በሚለው የአበራ ጀምበሬ ታሪካዊ ልቦለድ ላይ እንደሰፈረው ትውልዱ ጫቃታ አይደለም። በላይን ራሱን በአካል አግኝነተው አናግረ ታሪኩን ከስሩ የጻፉት ደጃዝማች ከበደ ተሰማ «የታሪክ ማስታወሻ» በተሰኘው የታሪክ መጽሀፋቸው ምዕራፍ ፩፯ ገጽ ፪፻፩፫ ላይ እንደጻፉት በላይ ዘለቀ የተወለደው እዚያው ጎጃም ምድር በቢቸና አውራጃ በእነማይ ወረዳ ልዩ ስሙ ለምጨን ከተባለው ቀበሌ ውስጥ ነው። ይህን የሚያውቀው ጎጃሜውም…

እንደ ቀትር እሳት የሚፋጀው ፊቱ፣ አባ ኮስትር በላይ ለምጨን ላይ ነው ቤቱ። ብሎለታል።

የበላይ አባትም ሙሉ ስማቸው ዘለቀ ላቀው ያስጨንቃል እንጂ ተስፋዬ ገብረዓብ ፈልስሞ ለኦነጎች እንዳስተማረው«ዘለቀ ላቀዉ ቂልጡ አያኖ ገልገሊ» አይደለም። ዘለቀ ላቀው ያስጨንቃል የንጉስ ተክለ ኃይማኖት የቢቸና ሹምና በኋላ የንጉስ ተክለ ኃይማኖት የልጅ ልጅ የሰብለ ወንጌል ኃይሉ ተክለኃይማኖት ባል የልጅ እያሱ አንጋች ሆነው ነበር። ኦሮሞነቴን «በህግ አስከብሬያለሁ» የሚለው ተስፋዬ ገብረዓብ የበላይን አስከሬን በሞገሳ ባህል መሰረት ኦሮሞ አድርጎት ካልሆነ በስተቀር በህይወት የነበረው በላይ ዘለቀ እውነተኛ ታሪክ ይህ ከላይ የቀረበው ነው።

በዚያ ላይ ማንነት ዋናው ባለቤቱ የሚወስነው መለያ እንጂ አንድ ሰው ከሞተ ከሰባ አንድ አመት በኋላ ማንም የተስፋዬ ተማሪ እየተነሳ «ጎጃም ቢወለድም በላይ ኦሮሞ ነው» በማለት የሚደርተው ጨርቅ አይደለም። ያገራችን ዘረኞች ግን አገር የመፍጠር ትግሉ አልሳካ ሲላቸው የታሪክና የማንነት ሽሚያ ላይ ተሰማርተው ዘፈኑን፣ ታሪኩንና ግጥሙን ሁሉ በብሽሽቅ አጨማልቀውት ፌስቡክ ላይ ታሪክ ለሚማረው የኔ ዘመን ትውልድ የታሪክን እውነትና ውሸት መለየት እንዳይችል አድርገው አወሳስበውበታል። የሆነው ሆኖ በላይ ዘለቀ የጎጃም ተወላጅ ኢትዮጵያዊ ጀግና አርበኛ ነው። በአርበኝነት ዘመኑ ድንቅ ኃሳብ የሰፈረበት ማህተም ነበረው። የበላይ ክብ ማህተም…

«በላይ ዘለቀ የኢትዮጵያ ደም መላሽ፤ እንባዋን አባሽ፤ ጣሊያንን ደምሳሽ» ይላል። እሱም ሲፈርም «በላይ ዘለቀ የኢትዮጵያ ደም መላሽ» ብሎ ነበር። የበላይ ማንነት ይህ ነው። ከዚህ የተለየ ማንነት የለውም። በላይ በዚህ መልክ ራሱን ስለገለጸ ዛሬ ሺህ ተስፋዬ የፈለገውን ቢደርት በላይን ሌላ ሊያደርገው አይችልም።

ከበላይ ጋር በጀግንነት አብሮ የተዋደቀው የጎጃም ሰውም… ጎጃም ባርበኝነት እንደምን ታወቀ፣ ያ በታች ዝቅ ሲል ያ በላይ ዘለቀ፤ *** ያ በላይ ዘለቀ የለምጨን በርበሬ፣ ጠላት ተሸበረ እየሰማ ወሬ፤ *** ጎጃም አይኑን ታሞ ሲደነባበር፣ የለምጨኑ አንበሳ ይመራው ጀመር፤ *** የለምጨኑ አንበሳ፣ መጣሉ እያገሳ፤ የሸበል ንጉስ፣ ገባሉ ማርቆስ። *** አባ ኮስትር በላይ የለምጨኑ አንበሳ እባክህ ተቆጣ፣ አንተም ራስ ተባል እኛም ጎጆ እንውጣ፤ *** ፈረንጅ ምድር ለቆ ቢሄድ በሰማይ፣ የጎጃሙ አንበሳ ዳመናውን አልፎ ዘለቀ በላይ። *** ጣሊያን ፍየል ሆኖ ቅጠል ቅጠል ሲያይ፣ የለምጨኑ አንበሳ ነብር ተመስሎ አረደው በላይ። ብሎለት ነበር። *** በኋላ ከአዲስ አበባ ከእስር አምልጦ ወደ ጎጃም ሲሄድ ሱሉሉታ ላይ መያዙን የሰማው የጎጃም ሰው ያ ጥይትና ጦር በያይነት የነበረው አርበኛው ጥይትና ሽመል አጥቶ ሳይዋጋ ለሚያሳድዱት እጁን መስጠቱን በተረዳ ጊዜ …

ጥይት አልቆብህ፣ ድንጋይ ተቸግረህ፣ ሽመል ተቸግረህ፣ አወይ ወንድም ወንድም አወይ አገር አገር አላለም ወይ ልብህ፤ በማለት በላይ ተዋግቶ እንዲያመልጥ በቦታው ተገኝቶ ጥይትና ሽመል ለጀግናው ባለማቅረቡ የተሰማውን ቁጭት ገልጿል።

በመጨረሻም የበላይ መሰቀል በጎጃም ሲሰማ…

ያ በላይ ዘለቀ ታላቁ ዝሆን፣ ጦር መጣልህ በሉት፣ ይነሳ እንደሆን፤ *** የሺፈራው እናት አይዞሽ አታልቅሺ፣ የልቡን ሰርቶ ነው የሞተው ልጅሺ፤ *** ተንግዲህ ወንድ አለ ብየም አላወራ፣ ጀግንነቱ አለቀ ካባኮስትር ጋራ። ብሎ ነበር!

በርግጥ በላይ ዘለቀ ጀግና ነበር። በርግጥም «የኢትዮጵያ ደም መላስ፤ እምባዋን አባሽ፤ ጣሊያንን ደምሳሽ»!!!!

ክብር ለጀግኖች አርበኞቻችን!

Hiber radio Las Vegas ይህ ህብር ሬድዮ _የወቅታዊ መረጃ ምንጭ ነው። ህብር ሬድዮ በአቤኔዘር ኮሙኒኬሽን ሴንተር እየተዘጋጀ  ከላስ ቬጋስ ከተማ፣ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 630 ሰዓት እስከ 8 ሰዓት በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ 5639993994 ወይም 563999-3988 ወይም 712-432-8451 በመረጡት ቁጥር መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ 01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *