Hiber Radio: የአድዋን ድል ማጥላላት ከኤርትራዊው <ምሁር> እስከ … ይሆን ? ሊነበብ የሚገባው የማዕረጉ በዛብህ ጽሑፍ- ዕውነትን መፈለግና ምሁራዊነት

የአድዋ ድል 121ኛ በዓል ዋዜማ ላይ እንገኛለን።ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን የአድዋን ድል አከባበር ተከትሎ ብቅ ብቅ ሚሉ የማጥላላት ድርጊቶች፣የአደባባይ ንግግሮች የዘር ሐረጋቸው ራቅ ሲል ፋሺስት ኢታሊያ ራሱ ቀረብ ሲል የፋሺስት ጠበቃ ኤርትራውያን ምሁራን፣ ሻዕቢያና ወያኔ ብሎም የእነሱ ተላላኪዎች መሆናቸው ገሀድ እየወጣ ነው። በዚህ የሰሞኑ በማህበራዊ ሚዲያ የአድዋን ድል በተለያየ መንገድ ለማጣጣል የተወጠነ ሴራ ዛሬ ያልጀመረ፣ ስልቱን ቀይሮ የመጣ መሆኑን በተለይ የዕውቁ ጋዜጠኛ ማዕረጉ በዛብህ ወቅታዊ ጽሑፍ አገር ቤት በሰንደቅ ጋዜጣ ታትሞ ብሎም በጋዜጣው ድህረ ገጽ ወጥቷል።እኛም ወቅታዊነቱን አይተን ወዲህ አምጥተነዋል። የአድዋ ድል ጠላቶች ጋር ከመወዛገብ በፊት መሰረታቸውን ለማጥናት አቅጣጫ ጠቋሚ ይመስላል።አንብቡት አሰራጩት።

ዕውነትን መፈለግና ምሁራዊነት

በማዕረጉ በዛብህ

ከምሁራን ከሚጠበቁ አበይት መለያ ባህሪያት ዕውነትን መፈለግ፣ ማግኘትና በዕውነት መገዛት አንዱና ዋናው ነው። ዕውነት ከሌላ ሰው ይልቅ ከምሁራን ዘንድ ይበልጥ የሚጠበቀው ትምሕርት፣ በተለይ ከፍተኛ ትምሕርት፣ ዕውነትን ለማግኘት የሚያገለግልና የሚያስችል ፍቱን መሳሪያ በመሆኑ ነው። ስለዚህ ምሁራን የሚጠሉትንና የማይቀበሉተን ሃሣብም ሆነ ጉዳይ በሰሜት ሳይሆን ከዕውነት አንጻር አጥንተውና መርምረው ነው ብይን ሊሰጡበት የሚገባው።

ዶ/ር ፕሮፌሰር ተስፋጽዮን መድሐኔ የተባሉት ኤርትራዊ ምሁር “Towards Confederation in the Horn of Africa Focus on Ethiopia and Eritrea” (የአፍሪካ ቀንድ አገሮች ወደ ኮንፊደሬሽን ቢያመሩ፣ በተለይ ኢትዮጵያና ኤርትራ) ተብሎ ሊተረጎም በሚችለው መጽሐፋቸው (ትርጉም የኔ) ሁለቱ አገሮች በኮንፊደሬሽን የፓለቲካ ስርአት ቢቀላቀሉ የሚለውን ሃሣብ ስለሚደግፉና ስለሚቃወሙ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ምሁራን ውይይት በሰፊው አቅርበዋል። በዚህ ነጥብ ላይ ጉዳዩን ከሰሜት ውጭ የሆነ ምርምር አድርገው አቋማቸውን እንደገለጹ ምሁራን ሁሉ ከወገናዊ ስመት ተነስተው የራሳቸውን ማብይን የሰጡ እንዳሉ በመጽሐፉ በግልጽ ይታያል። መጽሐፉ የሁሉቱ አገሮች ምሁራን፣ መንግስታትም ሆኑ፣ ሕዝቦች በጉዳዩ እንዲወያዩበት የሚያሳስብ ቁምነገር የያዘ ታሪካዊ ሰነድ በመሆኑ ደራሲው ሊመሰገኑ ይገባል።

 

እላይ ከተጠቀሰው አጠቃላይ ጉዳይ ውጭ አንድ በአሉታዊ መልኩ እጅግ የሚያስቆጣና የሚያሳፍር ጉዳይም በመጽሐፉ ሰፍርዋል። ዶ/ር ፀጋዬ ይስሐቅ የተባለ ኤርትራዊ የፓለቲካል ሳይንስ ምሁር “Italy Not Yet in Its Finest Hour” በተባለው እ.አ.አ በ2001 ባቀረበው ጽሁፉ አንድ እስከዛሬ የማይታወቅ የታሪክ ግንዛቤ አለኝ ሲሉ ብቅ እንዳለ ዶ/ር ፕሮፌሰር ተስፋጽዮን መድኃኔ ይገልጹልናል። ይህ አዲስ “ታሪክ” የአድዋን ጦርነት ያሸነፈችው ኢጣልያ ነች እንጅ ኢትዮጵያ አይደለችም የሚል ነው። ኤርትራዊው ዶክተር ይህንን የገለጸው በምሁራን ስብሰባ ላይ ባቀረበው አስተያየት ሲሆነ እንደ ፕሮፌሰር ተስፋጽዮን አጻጻፍ፣ “ዶ/ር” ፀጋዬ፤

 

“ኢትዮጵያ የአድዋን ጦርነት ፈጽሞ አላሸነፈችም፣ ጦርነቱን ያሸነፈችው ኢጣልያ ስትሆን ይህንኑ ባለመግለጽዋ ኢጣልያ ትልቅ ስህተት ፈጽማለች። ኢጣልያ የአድዋን ጦርነት አሸንፊያለሁ ብላ ባለማስታወቋ ኢትዮጵያ ያላሸነፈችውን ጦርነት አሸንፊያለሁ እያለች በኩራት የጥቁር ሕዝብ ዘረኝነትን አፍሪካ ውስጥ ለመናኘት ችላለች። የኢጣልያ የአድዋን ጦርነት በኢትዮጵያ አሸናፊነት እንደተፈጸመ መቀበልና ኢትዮጵያም የድሉ ባለቤት መሆን በኢጣልያ ሕዝብ አስደናቂ ታሪክ ላይ አሳዛኝ ትዝብት ጥሏል። ይህ ኢትዮጵያ የአድዋን ጦርነት አሸነፈች የሚለው “ታሪክ” የብዙ ዕውቅ ጀኔራሎች፣ የድል አድራጊዎችና የነገሥታት አገር የሆነችውን ኢጣልያ እንዴት ኢትዮጵያ ልታሸንፍ ትችላለች? አፍቃሪ ሮማ የሆነው ኤርትራዊ “ምሁር” ኢጣልያውያን የአድዋን ጦርነት ያሸነፍነው እኛ ነን ብለው ባለመግለጻቸው የተነሳ የተፈጠረ ሃሰት ነው የሚል ክርክር ያለዕፍረት ማቅረቡ ሰውየው ኤርትራዊ ወይም አፍሪካዊ መሆኑን ጭምር የሚያጠራጥር የሚያደርገው ይመስላል። “በሌላ በኩል የአድዋ ጦርነት ለኢትዮጵያውያን የውሸት የድል አድራጊነት ኩራት ስላሳደረባቸው በአፍሪካ የጥቁሮችን ዘረኝነት እምነት ለማሰራጨትና ለመስበክ ተጠቅመውበታል። የአድዋው ድል ታሪክ አፍሪካውያኑ አንዲት አፍሪካዊት የሆነች አገር (ኢትዮጵያ) የአውሮፓ አገር በሆነችው በኢጣልያ ላይ ድል ተቀዳጅታለች ብለው በቅዥት ዕምነት ውስጥ እንዲሰምጡ አድርጓቸዋል። ኢትዮጵያውያኑ ለዓለም ሊገልጹት ያልፈለጉት ዕውነት ግን የኢጣልያ ድል አድዋ ላይ ወሳኝ ስለነበር ንጉሣቸው ምኒልክ ሽንፈቱን በመቀበል ለዚያ ካሣ ኤርትራን ለኢጣልያ አሳልፎ መስጠቱን ነው።” ሲል ሞግትዋል አዲስ “ታሪክ” ይዞ ብቅ ያለው ኤርትራዊ “ምሁር”

 

እንደዚህ ዓይነት ወደ ድንቁርናና ወደ ዕብደት የተጠጋ ተረት በአንድ ምሁር ነኝ በሚል ሰው ሲቀርብ ብዙ ምሑራንን የሚያስገርምና የሚያስቆጣ በመሆኑ ዶ/ር ገላውዴዎስ አርአያ የተባሉት ኢትዮጵያዊ ምሁር ዶ/ር ፀጋዬ ኢትዮጵያን ለማዋረድና ለማሳነስ ያቀረበውን የውሸት ጥብቅና እጅግ ሚዛናዊና ዕውነተኛ የሁነ ጽሁፍ በማውጣት ነበር ያጋለጡት። ዶ/ር ገላውዴዎስ ምሁራዊነቱ በደንብ በሚታይ ዕውነታዊ ትረካ ከ1894 እስከ 1896 በየጊዜው በኢትዮጵያና በኢጣልያ የተካሄድትን ጦርነቶች ከጠቃቀሱ በኋላ ኢትዮጵያ አድዋ ላይ የተጐናጸፈችው ታሪካዊ ድል ለመላው ዓለም ጥቁር ሕዝቦች የኩራት ምንጭ እንደሆነ በመግለጽ በዶ/ር ፀጋዬ አሰፋሪ የውሸት ታሪክ ላይ የሚከተለውን ሂስ አቅርበዋል።

 

“የዚህን የውሸት ድርሰት አቅራቢ ሰው ማንነትና ዘር ለማያውቅ ታዛቢ፣ ይህን ድርሰት ሊያቀርብ የሚችል በጥንታዊትዋ ሮም ታላቅነት ታሪክ የሰከረና በሙስሊኒ የፋሽስት ፓርቲ ውስጥ የስልጣን ፍርፋሪ የተቋደሰ እንጅ ሌላ ሰው ሊሆን ይችላል ብሉ ሊገምትም ሊያምንም አይችለም” ይላሉ ዶ/ር ገላውዲዎስ።

 

ዶ/ር ፕሮፌሰር ተስፋድዩን በበኩላቸው ስለ ዶ/ር ፀጋዬ ይስሐቅ አስተያየት ባቀረቡት ትችት ይህ የዶ/ር ፀጋዬ አስተያየት አንድ ግለሰብ ታሪክን በማስተባበል ጥላቻውን ለመግለጽ የቀረበ አስተያየት ወይም ታሪክን በሚገባ ካለማንበብና ካለመረዳት ከዚያም አልፎ ኢትዮጵያ በኢጣልያ ላይ ያገኘችውን ታሪካዊ ድል ካለመቀበል የተነሣ የተገለጸ የጥላቻ አቋም ነው ይላሉ።

 

ሌላው ኢትዮጵያዊ ምሁር ፕሮፌሰር ጳውሎስ ሚልክያስ በሰጠው አስተያየት “የአድዋ ጦርነት ዋናው ቁምነገር ድሉ የወራሪው ሳይሆን የተወራሪው/የተጠቂው ደግሞ ፍትሐዊው አቅዋም በጥጋበኛው ወንበዴ ላይ ያደረሱው ታሪካዊ ድል መሆኑ ነው” ልዩ የሚያደርጋቸው ብሏል።

 

  • ኢትዮጵያ አድዋ ላይ ለተጐናጸፈችው ታሪካዊ ድል የብዙ ኤርትራውያን እስከ ሕይወት መሰዋዕትነት የደረሰ አስተዋጽኦ አለበት። ለምሳሌ ደጃዝማች ባህታ ሐጐስ የተባሉት ጀግና በትግራይ ውስጥ የፀረ-ኢጣልያን ቅኝ አገዛዝ እንቅስቃሴ እንዲጀመር ከማነሳሳት በላይ ኢትዮጵያ በአድዋ ጦርነት ድል እንድትጐናጸፍም አስተዋጽኦ አድርገዋል። የሀማሴን ገዥ የነበሩት ራስ ወልደሚካኤል ሰለሞንም የአጼ ምኒልክ የጦር አዛዥና አማካሪ በመሆን በጦርነቱና በተገኘው ድል ተከፍተዋል።

 

  • ሌላው ተጨማሪ ምክንያት፣ የኢጣልያኖችና የኢትዮጵያ ሰላይ ነበሩ በማለት የሚታወቁት አቶ አውአሎም ለኢጣሊያኖቹ የተሳሳተ መረጃ በመስጠትና አንዱን የኢጣልያ ጦር ክፍል ከቦታው ተንቀሳቅሶ በኢትዮጵያውያን ወታደሮች እንዲታፈን በማድረግ የተጫወቱት ሚና ለድሉ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገ ነው።

 

  •  ብዙ ኤርትራውያን ከኢጣልያን ጦር እየከዱ ከኢትዮጵያውያን ወንድሞቻቸው ጐን በመሰለፍ የሠሩት የጀግነት ተግባርና የከፈሉት የሕይወት መስዋዕትነት ለአድዋውድል ተጨማሪ አስተዋጽኦ ማድረጉ የሚረሳ አይደለም።

 

  •  ዛሬም አፍሪካ ብቻ ሳትሆን መላው ዓለም የአድዋ ጦርነት አሸናፊ ኢትዮጵያ መሆኖን ማወቁና በዓለም ታሪክ ውስጥ የተመዘገበ ዕውነት ሲሆን የዶ/ር ፀጋዬ ግንዛቤ የአገርንና የጥቁር ሕዝቦችን ክብር ማዋረድ ብቻ ሳይሆን የሰውየውን የራሱን ጤና ትክክለኛነት አጠያያቂ የሚያደርግ ነው። ዶ/ር ፀጋዬ ታሪካዊውን የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ሳይሆን የኢጣልያ ነው የሚል አቅዋም በመያዝ የኤርትራን፣ የኢትዮጵያንና የአፍሪካን ታሪክ ለቅኝ ገዥዎች ለመሸጥ የፈለገ ቢመስልም ትዝብት እንጅ የሽያጭ ዋጋ ሊያገኝበት አልቻለም ምክንያቱም እርሱ በድፍረት እንዳለው ድሉ የኢጣልያ ነው የሚል እንኳንስ ሌላ ሰው ከኢጣልያም እስከዛሬ ያንን አይን ያወጣ የታሪክ ውሸት የተቀበለ ሰው አይገኝም።

ድል አድራጊዋ ኢትዮጵያ እንደሆነች መካድ የራስን ሕልውና እንደመካድ የሚቆጠር ዕብደት ነው። 1ኛ አጼ ምኒልክ አድዋ ላይ ስለተሸነፉ ኤርትራን ለኢጣልያ ሰጡ የሚለው ውሸት ነው ምክንያቱም ኢጣልያኖች ኤርትራን የያዝዋት እ.አ.አ በ1890 ሲሆን የአድዋ ድል የተገኘው በ1896 ነው ከስድስት ዓመት በኋላ መሆኑ ነው። 2ኛ ኢጣልያ መሸነፍዋን ተቀብላ ከአጼ ምኒልክ ጋር አዲስ አበባ ውስጥ የኢትዮጵያን ነፃ አገር መሆን ተቀብላየሰላም ስምምነት የተፈራረመችው በኦክቶበር 1896 ዓ.ም ነው። ዓ.ም ነው። ስለዚህ የዶ/ር ፀጋዬ የፌተኛውን የታሪክ ኩነት ወደ ኋላ፣ የሁዋላውን ወደ ፊት እያደረገ የማቅረብ ባህሪው የጤና ስላልሆነ የስነ አዕምሮን(ሳይኮሎጂ) ሐኪም እርዳታ የሚጠይቅ ይመስላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *