Hiber Radio: በሕወሃት ደህነቶች የታፈኑት የሕጋዊው መኢአድ ፕሬዝዳንት አቶ ማሙሸት አማረና ወንድማቸው በማዕከላዊ መሆናቸው ታወቀ

አቶ ማሙሸት አማራ ከእስር በፊትና ከአራት ወሩ እስር በሁዋላ ሲወጡ ከዚህ ቀደም የተነሱት ፎቶ ከፋይል

የሕጋዊው መኢአድ ፕሬዝዳንት አቶ ማሙሸት አማረ ባለፈው ረቡዕ መጋቢት 20 ቀን 2009 ዓ.ም. ከወንድማቸው ከአቶ ግዛቸው አማረ ጋር በወያኔ ደኅንነቶች ታፍነው የታሰሩ ሲሆን ቀሪ ቤተሰብ ለቀናት ያሉበትን ቦታ ለማጣራት በተለያዩ ጣቢያዎች የተንከራተቱ ሲሆን ዛሬ ማምሻውን ለማየትና ለማናገር ባይችሉም እነ አቶ ማሙሸት አማረ ማዕከላዊ አሉ ተብለው ስንቅ መስጠታቸውን ለማወቅ ተችሏል።ጠበቃም እንዲያገኛቸው አልተፈቀደም።

ከመዐሕድ ጀምሮ በቆራጥነት ሙሉ እድሜያቸውን ለሰለላማዊ ትግል የሰጡ ጀግና ሲሆኑ በተለያዩ ጊዜያት በጠቅላላው ለ11 ዓመታት በወያኔ እስር ቤቶች አሳልፈዋል፡፡

በ2006 ዓ.ም በመኢአድ ጠቅላላ ጉባኤ ከፍተኛ ድምጽ አግኝተው የፓርቲው ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡ ቢሆንም የሕወሓት ምርጫ ቦርድ ውጤቱን አልቀበልም በማለቱ ዳግም ጉባዔ አካሂደው ዳግም በመመረታቸው ቦርዱ ውጤቱን አልቀበልም ብሎ ለእነ አቶ አበባው መሐሪ መኢአድን ሰጥቶ ተለታፊ ማቋቋሙ ይታወሳል።

አቶ ማሙሸት አማረ የመኢአድን ህጋዊነት የተጋፋውን ምርጫ ቦርድን በከሰሱበትና የሕወሓት አገዛዝ መቶ በመቶ ምርጫውን አሸነፍኩ ያለበት ምርጫ 2007 ጥቂት ሲቀር ግንቦት 5 ቀን 2007 ከመንገድ ታፍነው በማዕከላዊ ለአራት ወራት የስቃይ እስር ማሳለፋቸው ይታወሳል።

አቶ ማሙሸት አማረ ከአራት ወራቱ እስር በሁዋላ ሲወጡ ከዚህ በሁዋላ አንተን አናስርም እንገድልሃለን የሚል ዛቻና ማስፈራሪያ እንደተሰጣቸው ከተፈቱም በሁዋላ ክትትል እንደነበረባቸው ከእስር በሁዋላ ለህብር ሬዲዮ በሰጡት ቃለ መጠይቅ መግለጻቸው ይታወሳል።

አቶ ማሙሸት አማረ የተቃውሞ ትግሉን የተቀላቀሉት በመላው አገሪቱ የዐማራ ተወላጆች የሚደርስባቸውን እልቂት ለመታደግ የዩንቨርሲቲ ትምህርታቸውን አቋርጠው በ1984 በሚያዚያ ወር ሲሆን ከፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ጋር ለ8 ዓመታት ታስረው ተፈተዋል፡፡ አቶ ማሙሸት እስካሁን ድረስ ለዐሥር ጊዜ ያክል በድምሩ 11 ዓመት ያክል የሚሆነው ዘመናቸውን ያሳለፉት በወያኔ እስር ቤቶች ሲሆን አሁንም ለዐሥራ አንደኛ ጊዜ በወያኔ ደኅንነቶች መጋቢት 20 ቀን 2009 ዓ.ም ታፍነው መታሰራቸውን ጋዜጠና ሙሉቀን ተስፋ የአቶ ማሙሰትን የሁዋላ ታሪክ አስታውሶ በበኩሉ ጽፏል፡፡ አይበገሬው ታጋይ አቶ ማሙሸት የወጣነት ጊዜያቸውን በወያኔ ማጎሪያ ቤቶች ቢያልፍም ከጸና አቋማቸው ወደ ኋላ ብለው አያውቁም፡፡

አቶ ማሙሸት አማራ በግንቦት ወር 2007 ከመንገድ ታፍነው በታሰሩበት ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በማታው ትምህርት ክፍል ለሚከታተሉት ትምህርት ለፈተና ዝግጅ ያደርጉ በነበረበት ወቅት መሆኑን ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል።

የአቶ ማሙሸት አማረ ወንድም ባለፈው ረቡዕ በጸበል ቦታ አብሯቸው እንደነበር በደህነቶች መታፈኑን ያገኘነው ተጨማሪ መረጃ ይገልጻል።

የወያኔ አገዛዝ የመኢአድ ዐማራ የሆኑ አባላትን በከፍተኛ ሁኔታ እያሳደደ ሲሆን በቅርቡ እንኳ አቶ ዘመነ ጌጤን፣ አቶ ለገሠ ወልደሃናንና ወጣት ክንዱ ዱቤን አስረው ከፍተኛ ስቅይት እየፈጸሙባቸው ነው፡፡ አቶ ዘመነ ምሕረት ላይ ደግሞ የግድያ አዋጅ ማውጣቱ ይታወቃል፡፡የሕጋዊው መኢአድ ም/ል ፕሬዝዳንት የነበረው አቶ ዘመነ ምህረት ከዚህ ቀደም በታሰረበት ወቅት በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ የሕወሃት አባላት የሆኑ የትግራይ ተወላጅ መርማሪዎች አስረው ከሚያደርሱበት ማሰቃየት በተጨማሪ ሽንታም አማራ በሚል እላዩ ላይ ሽንታቸውን ጭምር መሽናታቸውን ከእስር በሑዋላ ምስክርነት መስጠቱ ይታወሳል።

Hiber radio Las Vegas ይህ ህብር ሬድዮ _የወቅታዊ መረጃ ምንጭ ነው። ህብር ሬድዮ በአቤኔዘር ኮሙኒኬሽን ሴንተር እየተዘጋጀ  ከላስ ቬጋስ ከተማ፣ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 630 ሰዓት እስከ 8 ሰዓት በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ 5639993994 ወይም 563999-3988 ወይም 712-432-8451 በመረጡት ቁጥር መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ 01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *