Hiber Radio: ዜግነት፣ ማንነት እና ብሔርኝነት በጦማሪ ናትናኤል ፈለቀ

በተለያዩ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ከተነሱ ፎቶዎች

የዜግነት ጉዳይ ከብሄር ማንነት ጋር አንዳንዴ እየተጣረሰ ሌላ ጊዜ እየተደበላለቀ መቅረብ የሰሞኑ የፖለቲካ አጀንዳ ሆኗል። ነገሩን አውቀው ለመተንተን ከሚፈልጉት ጀምሮ በራሳቸው አስተሳሰብ ዜግነትም የብሄር ጥያቄም ይሄው ነው ከዚህ ውጭ ዝውር የለም ማለት የሚዳዳቸውንም አስተውለናል። ጦማሪ ናትናኤል ፈለቀም የራሱን አስተያየት አስፍሯል። ቢያነቡት ብለን ወዲህ አምጥተነዋል።

እነዚህ ፅንሰ ሀሳቦች ሳናብራራ ውይይታችን ፍሬ ይይዛል ብዬ ስለማልገምት የኔን ሀሳብ ላስቀምጥ፡፡ ፅንሰ ሀሳቦቹን ስተነትን ከተሳሳትኩ ልታረም ዝግጁ ነኝ፡፡

ዜግነት ፖለቲካዊ ማንነት ነው፡፡ አንድ ሰው የኢትዮጵያ ዜጋ ናት ሲባል፣ አንድ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር (ሉዓላዊ ግዛት እና መንግስት ያላት) ውስጥ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ያላቸው መብቶች እና ያለባቸው ግዴታዎች በእኩል የሚሰጣት ሰው ማለት ነው፡፡ አንድ ሱዳናዊ እነዚህን መብቶች እና ግዴታዎች የምትኖረው የኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ እንኳን ቢሆን እንደተገቢነቱ ሊሰጣት እና ሊጣልባት ይችላል እንጂ በቀጥታ (Automatically) የሚመለከቷት አይሆንም፡፡ ስለዚህ ዜግነት ስንል አንድ ግለሰብ ከሀገረ መንግስት (state) ጋር የምትገባው ውል ማለት ነው፡፡ የዜግነት ውል ከሁለቱ ወገኖች አንዱ ግዴታውን ሳይወጣ ሲቀር (ወይንም አንዱ ወገን እንደዛ ሲሰማው) ሊቋረጥ ወይንም ሊቀየር የሚችል ነው፡፡ ግን በማኛውም ግዜ ዜግነት የሚባል ነገር ካለ ያንን ዜግነት የሚሰጥ ሉዓላዊ ሀገር አለ ማለት ነው፡፡

ማንነት ከዜግነት በተለየ የአንድ ሰው መገለጫ ነው፡፡ አንድ ሰው በአንድ ግዜ ብዙ ማንነቶች (እራሷን የምትገልጽበት ማነቶች) ሊኖሯት ይችላል፡፡ በቋንቋ፣ በባሕል (አመጋገብ እና አለባበስ)፣ በአኗኗር (ለምሳሌ ከተሜነት)፣ በምትከተለው ሃይማኖት፣ በተማረችው ትምሕርት ወይንም በተሰማራችበት የሙያ መስክ፣ ወዘተ፡፡ አንድ ሰው አንድ የማንነት መገለጫ ብቻ (exclusively) ሊኖራት አይችልም፡፡ እነዚህ ማንነቶች በግለሰብ ደረጃ በምናልፍባቸው ተሞክሮዎች እና መስተጋብሮች እየዳበሩ የሚሄዱ ናቸው፡፡ ማንነቶችን ከሚጋሩን ሌሎች ግለሰቦች ጋር ማኅበር መመስረት ይቻላል፡፡ እነዚህ ማኅበሮች በጋራ መብቶቻችንን ከሚያስከብሩ ስብስቦች እስከ ዜግነት የሚሰጥ ማኅበረሰብ (ሀገር) ድረስ ሆነው ሊቋቋሙ ይችላሉ (ቢያንሰ በንድፈ ሀሳብ ደረጃ)፡፡

ብሔርተኛነት ማንነት ላይ የተንጠለጠለ አራማጅነት ነው፡፡ አንድ ሰው ከማንነት መገለጫዎቿ መካከል በአንዱ የፖለቲካ ግብ አንግባ (ከመብት ማስከበር እስከ እራሱዋን የቻለች ሉዓላዊ ሀገር መመስረት ድረስ ሊደርስ የሚችል) የምታደርገው አራማጅነት ነው፡፡

 

*****

ኢትዮጵያዊ ዜግነት፣ ኢትዮጵያዊ ማንነት እና ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት

ኢትዮጵያዊ ዜግነት ኢትዮጵያ በምትባለው ሀገር ውስጥ በሕግ በተደነገገው መሰረት መብት እና ግዴታ ያለው ውል ነው፡፡ ፖለቲካችን በዚህ ዜግነት ላይ ይገንባ ስንል፣ ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል ናቸው፣ የሚከበር መብት እና የሚያከብሩት ግዴታ አለ፣ እንዲሁም ይህንን የሚከታተል እና የሚያስፈጽም በጋራ እና በመልካም ፈቃዳቸው የሚያቋቁሙት መንግስት ይኑራቸው እያለልን ነው ማለት ነው፡፡ ይሄ ሁላችንንም የሚያስማማ ሀሳብ ይመስለኛል፡፡

 

ኢትዮጵያዊ ማንነት ማለት ደግሞ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ተሰብስበው ያሉ የተለያዩ ማኅበረሰቦች ማንነት መገለጫ የነበሩ፣ ግን በማኅበረሰቦቹ መካከል በነበረ መስተጋብር የጋራችን የሆኑ መገለጫዎች እንዲሁም በጋራ ኢትዮጵያዊያን በታሪካችን ውስጥ የፈፀምናቸው ገድሎች (አድዋ) እና የደረሱብን ሰቆቃዎች (የ77ቱ ድርቅ) የሚያላብሱን መገለጫዎቻችን ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ማንነቶች ዘውግ ሳይለዩ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን የጋራ ማንነት መገለጫዎች ናቸው፡፡ ይህ ማለት ግን ሁሉም ኢትዮጵያዊያን አንድ ዓይነት ማንነት ነው ያላቸው ማለት አይደለም፡፡ እያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊያን በተለያየ መንገድ ያገኘናቸው ወይንም ያዳበርናቸው ማንነቶች አሉን፡፡ ከነዚህ ማንነቶች መኻከል የዘውግ ማንነት አንዱ ነው፡፡ የዘውግ ማንነት ለአንድ ኢትዮጵያዊ ከኢትዮጵያዊ ማንነቷ ጋር የሚመጋገብ እና ጎን ለጎን የሚሄድ ማንነት ነው፡፡ ከኢትዮጵያዊ ማንነት ጋር እየተወዳደረ በዚህ ያንሳል በዚህ ደግሞ ይሻላል የሚባል ዓይነት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊ ማንነት ከኢትዮጵያዊያን የዘውግ እና ሌሎች ማንነቶች መስተጋብር በማያቋርጥ ሂደት እየዳበረ የሚሄድ ማንነት ነው፡፡

ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ኢትዮጵያዊ ማንነተን ላይ የተመሰረተ አቀንቃኝነት ነው እንግዲህ፡፡

*****

ጤነኛ የዘውግም ሆነ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት የሚገፋፉ እና አንደኛው አንደኛውን ካልጣለ አብረው መኖር የማይችሉ አይደሉም፡፡ አንድ ነገር እውቅና መስጠት አለብኝ፤ ብሔርተኝነት፣ ለዛውም ደግሞ ዘውግ ላይ የተመሰረተ ሲሆን ሌሎች ማንነቶችን እነደጠላት በመፈረጅ እና ተጠቂነትን በመስበክ ብዙ ሰው ለማሰባሰብ ቀላል ይሆናል፡፡ የዘውግ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ማኅበረሰቦች ሀገረ መንግስት ለማቋቋም አስፈላጊው ማኅበረሰባዊ መዋቅር ስለሚኖራቸው (በሀብት እና በሥራ ክፍፍል) እራሳቸውን እንደ አንድ ሀገር ለማየት ስለማይቸገሩ የሀገር ግዛት አንድነት ላይ የስጋት አደጋ እንደሚጋርጡም እውነት ነው፡፡ ነገር ግን የዘውግ ብሔርተኞች የሚያነሷቸው የመብት ጥያቄዎች የሚስተናገዱበት መንገድ እና የማዕከላዊ መንግስቱ ስርዓተ-መንግስት (ዴሞክራሲያዊነት) የዘውግ ብሔርተኞች የሚጋርጡትን አደጋ እንዳይከሰት መከላከል ይችላሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ፖለቲካ መድረክ ላይ ከዘውግ ብሔርተኞች እና ከኢትዮጵያ ብሔርተኞች መካከል ገነው የሚሰሙት ድምፆች የጤነኛ ብሔርተኝነት ድምፆች አይመስሉኝም፡፡ ይህ እንዲሆን ምክንያታዊ መካከለኛ ድምፆችን (Moderates) በማሳደድ ወያኔ ወደር የለሽ አስተዋፅዎ አድርጓል፡፡ የእኔ ወቀሳ ግን የሚያተኩረው ኢትዮጵያ የምትባል ሀገርን ማቆየት እና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ እፈልጋለው የምንለው ላይ ነው፡፡ አሁን ኢትዮጵያ የደረሰችበትን የፖለቲካ ሁኔታ ከግንዛቤ ያስገባ የወደፊቷን ኢትዮጵያ ራዕይ አስቀምጠን ኃይል በዚያ ዙሪያ ማሰባሰብ ካልቻልን፣ የዘውግ ብሔርተኝነትን በማውገዝ እና በብሽሽቅ ሀገር ማቆየት አይቻልም፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *