Hiber Radio: በአቶ በቀለ ገርባ ላይ የቀረበው የሀሰት ክስ በሽብርተኝነት አያስከስስም በወንጀል ሕጉ ይታይ ተባለ ፣ፍርድ ቤቱ በእነ ጉርሜሳ አያና መዝገብ ላይ ብይን ሰጠ

  • 5 ተከሳሾችን በነፃ አሰናብቷል
  • አቶ በቀለ ገርባ በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ ተከላከል ተብሏል

(በጌታቸው ሺፈራው) የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ሀምሌ 6/2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት በእነ ጉርሜሳ አያና መዝገብ በተከሰሱት 22 ተከሳሾች ላይ ብይን ሰጥቷል፡፡ ተከሳሾቹ ሁለት ክስ ቀርቦባቸው የነበር ሲሆን ከ1ኛ እስከ 13ኛ ያሉት ተከሳሾች ኦሮሚያ ውስጥ ተከስቶ በነበረው ህዝባዊ አመፅ ‹‹በቀጥታ በመሳተፍ፣ ከውጤቱም ተካፋይ ለመሆን›› የሽብርተኝነት ወንጀል ፈፅመዋል በሚል በፀረ ሽብር አዋጁ አንቀጽ 3 ስር የተደነገገውን ተላልፈዋል ተብለው ክስ ቀርቦባቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡ በተመሳሳይ በሁለተኛ ክስ ከ14ኛ እስከ 22ኛ ያሉት ተከሳሾች በማንኛውም መልኩ በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ ተሳትፎ በማድረግ በሚል በፀረ ሽብር አዋጁ አንቀፅ 7(1) ስር ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ዛሬ በዋለው ችሎት በቀጥታ በሽብር ወንጀል ተሳትፈዋል ተብለው ተከሰው ከነበሩት መካከል 1ኛ ተከሳሽ ጉርሜሳ አያና፣ 2ኛ ተከሳሽ ደጀኔ ጣፋ፣ 3ኛ ተከሳሽ አዲሱ ቡላላ፣ 5ኛ ተከሳሽ አብደታ ነጋሳ፣ 6ኛ ተከሳሽ ገላና ነገራ፣ 8ኛ ተከሳሽ ጌቱ ግርማ፣ 11ኛ ተከሳሽ በየነ ሩዳ እና 12ኛ ተከሳሽ ተስፋዬ ሊበን ተመስርቶባቸው ከነበረው በቀጥታ የሽብር ወንጀል መፈፀም በሽብርተኝነት ድርጅት ውስጥ መሳተፍ ወደሚል ተቀይሮ ከፀረ ሽብር አዋጁ አንቀፅ 3 በዚሁ አዋጅ አንቀፅ 7(1) ስር ተቀይሮ ይከላከሉ ሲል ክሳቸውን አሻሽሏል፡፡ በተመሳሳይ አቶ በቀለ ገርባ ላይ የቀረበው ማስረጃ የሽብር ወንጀልን የሚያቋቁም ስላልሆነ ከፀረ ሽብር አዋጁ ወጥቶ በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ አንቀፅ 257 (ሀ) ስር የተደነገገውን ግዙፍ ያልሆነ መሰናዳትና መገፋፋት ክስ ተቀይሮ እንዲከላከል በይኗል፡፡ በሌላ በኩል በ1ኛ ክስ በጸረ ሽብር አዋጁ አንቀጽ 3 ስር ተከሰው ከነበሩት መካከል 7ኛ ተከሳሽ ጭምሳ አብደሳ፣ 9ኛ ተከሳሽ ፍራኦል ቶላ፣ 10ኛ ተከሳሽ ጌታቸው ደረጀ እና በማንኛውም መልኩ በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ በመሳተፍ ክስ ተመስርቶበት የነበረውና በዜግነት ኬንያዊ የሆነው 22ኛ ተከሳሽ አልካኖ ቆንጨራ የቀረበባቸውን ክስ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ወስኗል፡፡

በዚሁ መዝገብ በማንኛውም መልኩ በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ በመሳተፍ ክስ ቀርቦባቸው የነበሩት 14ኛ ተከሳሽ ደረጀ መርጋ፣ 15ኛ ተከሳሽ የሱፍ አለማየሁ፣ 16ኛ ተከሳሽ ኢካ ተክሉ፣ 17ኛ ተከሳሽ ገመቹ ሻንቆ፣ 18ኛ ተከሳሽ መገርሳ አስፋው፣ 19ኛ ተከሳሽ ለሚ ኢዴቶ፣ 20ኛ ተከሳሽ አብዲ ታምራት እና 21ኛ ተከሳሽ አብዲ ኩምሳ ተከሰውበት የነበረውን አንቀጽ 7(1) ስር የተጠቀሰውን እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል፡፡ አቶ በቀለ ገርባ ተከላከል የተባለበት አንቀፅ ዋስትና የሚያስፈቅድ በመሆኑ ዋስትና እንዲፈቀድለት በጠበቆቹ በኩል ጥያቄ አቅርቦ የነበር ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ‹‹በፅሁፍ አስገቡ›› ሲል ለጥያቄው ውሳኔ ሳይሰጥ አልፎታል፡፡ ፍርድ ቤቱ የተከሳሾቹን የመከላከያ ምስክር ለመስማት ከነሃሴ 8-12/2009 ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Hiber radio Las Vegas ይህ ህብር ሬድዮ _የወቅታዊ መረጃ ምንጭ ነው። ህብር ሬድዮ በአቤኔዘር ኮሙኒኬሽን ሴንተር እየተዘጋጀ  ከላስ ቬጋስ ከተማ፣ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 630 ሰዓት እስከ 8 ሰዓት በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ 5639993994 ወይም 563999-3988 ወይም 712-432-8451 በመረጡት ቁጥር መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ 01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *