Hiber Radio: የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ ፖርቲ አመራሮች ለፍርድ ተቀጠሩ -በመከላከያ ምስክርነት የተጠሩት ባለስልጣናት መቅረብ የለባቸውም በማለት ፍርድ ቤቱ ውሳኔ አስተላልፏል -ችሎት በመድፈር ጥፋተኛ ተብለው የስድስት ወር እስራት ተፈረደባቸው

በጌታቸው ሽፈራው

የእነ ጉርሜሳ አያኖ መዝገብ ለታህሳስ 27/2010 ከ1ኛ እስከ 4ኛ ያሉ ተከሳሾችን መከላከያ ምስክሮችን እና ማስረጃዎችን አቀራረብ እንዲሁም የቀሪ ተከሳሾችን መከላከያ ማስረጃዎች በተመለከተ ትእዛዝ ለመስጠት ተቀጥሮ ነበር። በመዝገቡ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ያሉት ተከሳሾች (አቶ ጉርሜሳ አያኖ፣ አቶ ደጀኔ ጣፋ፣ አቶ አዲሱ ቡላላ እና አቶ በቀለ ገርባ) ቀርበው ትእዛዙ አልደረሰልንም ተብለው ለዛሬ ጥር 3/2010 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸው ነበር።

በዛሬው ቀጠሮም ከማረሚያ ቤት የቀረቡት አራቱ ተከሳሾች ብቻ ናቸው ። የተቀሩት ተከሳሾች ለምን እንዳልቀረቡ ዳኛ ዘርዓይ ወ/ሰንበት ለቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ጉዳይ አስፈፃሚ ጥያቄ አቅርበው የነበረ ሲሆን፤ ጉዳይ አስፈፃሚውም የተሰጠው ቀጠሮ ለአራቱ ብቻ በመሆኑ እንደሆነ ገልፇል። ዳኛ ዘርዓይም አራቱ ብቻ እንዲቀርቡ እና ሌሎቹ ተለይተው እንዲቀሩ የታዘዘ ነገር አለመኖሩን እና የሚሰጠው ትእዛዝ በመዝገቡ የተካቱት የተቀሩት ተከሳሾችንም እንደሚመለከት ከተናገሩ እንዲሁም መቅረት እንዳልነበረባቸው ካስገነዘቡ በኋላ ትእዛዙን አንብበዋል።

ከ1ኛ እስከ 4ኛ ያሉ ተከሳሾች በጋራ የጠሯቸውን ባለስልጣናት በተመለከተ ፤ ከጠቅላይ ሚ/ር ፅ/ቤት በቀን 17/4/2010 በተፃፈ ደብዳቤ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ሃይለማርያም ደሳለኝ ስራ ስለሚበዛባቸው መጥተው መመስከር እንደማይችሉ ነገር ግን እሳቸው የሰጡት መግለጫ የሚፈለግ ከሆነ ግን በማንኛውም ጊዜ ፅ/ቤቱ ለፍርድ ቤቱ ሊያደርስ እንደሚችል በመግለፅ የተላከው ደብዳቤ፤ እንዲሁም ከኦህዴድ ፅ/ቤት የተከበሩ አቶ አባዱላ ገመዳ፣ የተከበሩ አቶ ለማ መገርሳ፣ የተከበሩ ዶ/ር አብይ አህመድ እና የተከበሩ ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ አስቸኳይ ሃገራዊ ስብሰባ ላይ እንደሚገኙ በመግለፅ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ፍርድ ቤቱ ትብብር እንዲያደርግላቸው በ18/4/2010 ደብዳቤ መላካቸው ተለዋጭ ቀጠሮ ሊያሰጥ የሚችል በቂ ምክንያት መሆኑን ትእዛዙ ይገልፃል። ሆኖም በቂ ምክንያት ስላለ ብቻ ምስክሮች እንዲቀርቡ ድጋሜ ትእዛዝ እንደማይሰጥ በመጥቀስ፤ ትክክለኛ ፍትህ ለመስጠት የሚረዳ መሆኑ ከታመነበት ግን ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠት እንደሚቻልም ይገልፃል። በመሆኑም ተከሳሾቹ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ያሉ ተከሳሾች እንዲከላከሉ የተባሉት ከሽብርተኛ ድርጅት ጋር ግንኙነት በመፍጠር በመሆኑ፤ 4ኛ ተከሳሽ የወንጀል ህጉን አንቀፅ 257(ሀ) በመሆኑ እንዲሁም ምስክሮቹን ለማቅረብ መንግስት የሚያወጣውን ወጩ ታሳቢ በማድረግ ምስክሮቹ ሊሰጡት የታሰበው ምስክርነት ጠቃሚ ሆኖ ስላልተገኘ ቀርበው እንዲመሰክሩ ትእዛዝ እንደማይወጣ በውሳኔው ተገልፇል።

ተከሳሾች ከብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት ኤጀንሲ በፅሁፍ በሪፖርት መልክ የቀረበባቸውን መረጃ በተመለከተ የስልክ ድምፅ ቅጂ እንዲደርሳቸው ለቴሌኮሚኒኬሽን እና ለብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት ኤጀንሲ እንዲታዘዝላቸው ያመለከቱት ጉዳይም ትእዛዝ ተሰጥቶበታል። ከብሄራዊ ደህንነት እና መረጃ ኤጀንሲ ተጠናቅሮ የመጣው ሪፖርት የተገኘው ከድምፅ ጠለፋ ይሁን አይሁን የሚገልፀው ነገር ባለመኖሩ እና በፀረ ሽብር ህጉ ደግሞ በማንኛውም መልኩ የተገኘ ማስረጃ ተቀባይነት ስለሚኖረው ከላይ ለተጠቀሱት መስሪያ ቤቶች የድምፅ ቅጂ እንዲያቀርቡ ትእዛዝ እንደማይሰጣቸው ዛሬ በተሰጠው ትእዛዝ ተገልፇል።

በሶስተኝነት ትእዛዝ የተሰጠበት ጉዳይ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ያሉ ተከሳሾች ከተለያየ የመንግስት መስሪያ ቤት እንዲቀርቡልን ያሏቸው የሰነድ ማስረጃዎች ጉዳይ ነው።

ተከሳሾቹ እንዲቀርቡላቸው የጠየቋቸው ሰነዶች የሚከተሉት ናቸው።

1ኛ ጠ/ሚ ሃይለማርያም ደሳለኝ ለተወካዮች ምክር ቤት በ15/4/2008 የ2008 የግማሽ መንፈቅ አመት የስራ ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት የተናገሩትን የድምፅ ከምስል ማስረጃ ከኢብኮ ወይም ከተወካዮች ምክር ቤት

2ኛ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በ15/9/2009 ከምሽቱ 2ሰአት ላይ በኦሮሚያ ቴሌቭዥን በአማርኛ የነበረው የዜና እወጃ ላይ ህገወጥ የመሬት ነጠቃን በሚመለከት የተነገረውን የድምፅ ከምስል ማስረጃ

3ኛ የተከበሩ ዶ/ር አብይ አህመድ በ27/10/2009 በኦሮሚያ ቴሌቭዢን በማታ የዜና እወጃ ላይ በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ብቻ ከ45 ሺህ ሄክታር በላይ ማስመለሳቸውን የተናገሩበት የድምፅ ከምስል ማስረጃ (ዜናው ከኦሮምኛ ወደ አማርኛ ተተርጉሞ)

4ኛ የተከበሩ አቶ ለማ መገርሳ ለጨፌ ኦሮሚያ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ በመልካም አስተዳደር ችግር ምክንያት በህገወጥ መንገድ የተያዙ ከ51ሺ ሄክታር በላይ ማስመለሳቸውን የተናገሩትና በበ8/11/2009 በኦሮሚያ ቴሌቪዥን በማታው የዜና እወጃ ሰአት የቀረበው የድምፅ ከምስል ማስረጃ (ዜናው ከኦሮምኛ ወደ አማርኛ ተተርጉሞ)

እነዚህ ማስረጃዎችም ተከሳሾቹ እንዲከላከሉ ከተባሉበት ጭብጥ አንፃር ጠቃሚ አይደሉም በሚል ማስረጃዎቹ እንዲቀርቡ እና በመከላከያ ማስረጃነት እንዲያዝልን የሚለው የተከሳሾቹ አቤቱታ ውድቅ ሆኗል።

በመጨረሻም ትእዛዝ የተሰጠው በ4ኛ ተከሳሽ (አቶ በቀለ ገርባ) የመከላከያ ምስክርነት የተጠራው እና በተደጋጋሚ ማረሚያ ቤት ያላቀረበው አቶ አንዷለም አራጌም ጉዳይ ነው። ፍርድቤቱ በተመሳሳይ አቶ አንዷለም እንዲቀርብ በተፈለገበት እና በሚሰጠው ምስክርነት አስፈላጊነት አለማመኑን በመግለፅ ለሱም መጥሪያ እንደማይወጣ ተገልፇል።

በተሰጠው ትእዛዝ ቅር በመሰኘት አስተያየት ለመስጠት ጠበቃ አቶ አመሃ መኮንንም ሆነ ተከሳሾቹ ቢጠይቁ፤ ዳኛው ትእዛዙ ላይ አስተያየት መስጠት እንደማይቻል ከተናገሩ በኋላ ተከሳሾቹ አስተያየት መስጠት እንዳለባቸው በመወትወታቸው ጠበቃው የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል። “እኛ ማስረጃዎቹን የቆጠርነው ጉዳዩ አግባብ መሆኑን ተነጋግረንበት ነው። ከጠ/ሚ/ሩ ውጪ ያሉ ምስክሮች ተለዋጭ ቀጠሮ ነው የጠየቁት። ፍርድ ቤቱም ከዚህ በፊት በመቅረባቸው አምኖ ሁለት ጊዜ ትእዛዝ ሰጥቷል።” ዳኛውም ፍርድ ቤቱ ፈቃደኛነታቸውን ሳይሆን ለጉዳዩ ያስፈልጋሉ አያስፈልጉም የሚለውን በማየት ትእዛዙ መሰጠቱን ተናግረዋል።

አራቱም ተከሳሾች አስተያየት እንዳላቸው እጃቸውን በማውጣታቸው ሃሳባቸውን ለጠበቃቸው እንዲናገሩ እና በጠበቃቸው በኩል ለፍርድ ቤቱ እንዲነገር ቢባሉም ሁሉም በራሳቸው ለራሳቸው መናገር እንደሚፈልጉ በመግለፅ የማይሰሟቸው ከሆነ እነሱም እንደማይሰሟቸው በብስጭት ተናግረዋል።

ደጀኔ ጣፋ፦ ” ታሪካዊ ውሳኔ ነው ዛሬ የሰማነው። ዛሬ ብቻ ሳይሆን በዚህ ሃገር ላይ ችግር ያመጣው ይህ አስተሳሰብ ነው። የ2008 ተቃውሞ እና አመፅ ኦነግ ነው? ሃገር ግልበጣ ነው? ወይስ የህዝቡ ጥያቄ? መግለጫውን ያወጡት የመልካም አስተዳደር ችግር ነው ነው ያሉት። ይቅርታ ጠይቀዋል እኮ በዚ ጉዳይ! ታዲያ ኦነግን ነው እንዴ ይቅርታ የጠየቁት? ነሃሴ 12/2009 በነበረው ቀጠሮ እና በባለፈው በነበረው ቀጠሮ ምስክሮቹ እንዲቀርቡ ችሎቱ አዟል። ታዲያ ፍርድ ቤቱ የራሱን ትእዛዝ እንዴት ይሽራል? ” የሚል አስተያየቱን አቅርቧል።

ዳኛ ዘርዓይም በምስክርነት የተጠሩት ባለስልጣናት ሃላፊነት ላይ ያሉ እና ስራ ያለባቸው በመሆኑ በሆነ ባልሆነ ለምስክርነት ስለተጠሩ ብቻ መቅረብ እንደሌለባቸው፤ አክለውም አንድ ሰው ባለስልጣንም ባይሆን ለምስክርነት ስለተጠራ ብቻ ቀርቦ ጊዜውን ማባከን እንደሌለበት ተናግረዋል።

2ኛ ተከሳሽ ደጀኔ ጣፋ፥ ” አቃቤ ህግ የወረዳ አስተዳደሮችን ፣ የዞን ሃላፊዎችን እና በተለያየ አመራር ላይ የሚገኙ ግለሰቦችን ጠርቶ አስመስክሯል። እኛ አመራሮችን ስንጠራ ለምን ትከለክሉናላችሁ? ለኛ አደጋ ነው።”

4ኛ ተከሳሽ በቀለ ገርባ፥ ” የኛን ጉዳይ የረባ ያልረባ እያላችሁ ስብእናችን እየተነካ ነው። ከእናንተ የማይጠበቅ ቃላት እየተናገራችሁ ነው። እኛ በሞት ላይ ነው የተረማመድነው። እዚህ ፍርድ ቤት ለ26 ዓመት ነው ኦሮሞ የተገደለው።”

1ኛ ተከሳሽ ጉርሜሳ አያኖ ፥ “እኛ ለመሞት ዝግጁ ነን ነገር ግን እኛ ላይ ይቆማል። የልጆቻችን ደም አይፈስም።”

3ኛ ተከሳሽ አዲሱ ቡላላ ፥ “ሁለት አመት የሰራችሁብንን ድራማ ተከታትለናል ወስኑብን!”

ከላይ የሰጡትን አስተያየቶች በችሎት ከተናገሩ በኋላ ተከሳሾቹ በችሎት ውስጥ ከዚህ ቀደም በነበሩነሁለት ችሎቶች ይዘምሩት የነበረውን መዝሙር ጮክ ብለው መዘመር ቀጥለዋል። ዳኞቹም ተከሳሾቹ እንዲወጡ ቢነገራቸውም አንወጣም በማለት መዘመራቸውን ቀጥለዋል። መዝሙሩ ካለቀ በኋላ ችሎቱ ስራውን በመቀጠል ሌላ አንድ መዝገብ ካስተናገደ በኋላ ዳኛው በእነ ጉርሜሳ አያኖ መዝገብ የቀረቡ አራት ተከሳሾች ችሎት በመድፈራቸው የተሰጣቸውን ውሳኔ በሚያነቡበት ወቅት ተከሳሾቹ አንሰማም በማለት አራቱም በብስጨት እና በሃይል ቃል የተለያየ ነገር ጮክ ብለው ሲናገሩ የነበረ ቢሆንም ውሳኔው ተነቧል። አራቱም ተከሳሾች ችሎት በመድፈር 6 ወር እስራት እንደተፈረደባቸው እንዲሁም አራቱም ለፍርድ ለጥር 10/2010 መቀጠራቸውን በውሳኔው ተገልፇል።

ውሳኔው ተነቦ እንዳለቀም ተከሳሾቹ አጨብጭበዋል። በሌላ መዝገብ ተከሰው መዝገባቸው ለመታየት ሲጠብቁ የነበሩ ሶስት ተከሳሾችም ከእነ ጉርሜሳ አያኖ ጋር አብረው በማጨብጨባቸው ችሎት ደፍረዋል ተብለው የሶስት ወር እስራት ተፈርዶባቸዋል

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *