Hiber Radio: አንዳንድ ተቃዋሚዎች ላይ የሚታየው <<ስቶክሆልም ሲንድሮም>> የተሰኘው በሽታና የወቅቱ ፖለቲካ

አቻምየለህ ታምሩ

«ስቶክሆልም ሲንድሮም» ታጋቾች ከአጋቾቻቸው ጋር ከመላመዳቸው የተነሳ አጋቾቻቸውን አዳኝና ተከላካይ [savior and defender] አድርገው በመውሰድ ስለነሱ ያላቸው ኃዘኔታና ርህራሔ እንዲሁም አወንታዊ ስሜት በጣም ከፍ ወዳለ ፍቅር ያድግና ከአጋቾቻቸው መለየት እጅግ በጣም ከባድ የሚሆንባቸው ደረጃ ላይ የደረሱ ታጋቾችን የሚገልጽ የስነልቦና ክስተት ነው።

የታገተው የኢትዮጵያ ሕዝብም በመንግሥትነት ከተሰየሙት አጋቾቹ የትግራይ ወያኔዎች ጋር እጅግ በጣም ከመላመዱ የተነሳ አጋቾቹን በግፍ ያጎሯቸውን የህሊና ሰዎች በጭካኔ ከሚመትሩበት ከጠባቡ የሰው መታረጃ ቄራ ወደሰፊው የማሰቃያ እስር ቤት ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲዘዋወሩ ስለፈቀዱላቸው በታጋቾቹ ወገን ያሉ ተቃዋሚ ነን የሚሉ ፖለቲከኞች አጋቾቹን ፋሽስት ወያኔዎች አዳኝና ተከላካይ አድርገው በመውሰድ መቼም ሊለቃቸው በማይችለው የአጋች ፍቅር ተለክፈው የአበሻ ሲንድሮም ውስጥ የወደቁ ይመስለኛል። ይህንን ለማየት ሰሞንን ፋሽስት ወያኔ በግፍ ያጎራቸውን የህሊና ሰዎች በጭካኔ ከሚመትርበት ከጠባቡ የሰው መታረጃ ቄራ ወደሰፊው የማሰቃያ እስር ቤት ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲዘዋወሩ እፈቅዳለሁ ስላለ ብቻ ወያኔ በጎ እርምጃ እንደወሰደ አድርገው የሚያመሰግኑና ውጭ አገርም ያሉት ሻንጣቸውን እየሸከፉ ያሉ ፖለቲከኞቻችንን እያየን ነው።

ይህም በመሆኑ ፋሽስት ወያኔ መናኛ ስራ ስለሰራ ሳይሆን ከአፍንጫቸው አርቀው ማሰብ በማይችሉ «ስቶክሆልም ሲንድሮም» በሚባለው የህሊና በሽታ በተጠቁ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ወለፈንዲነት ምክንያት ኢትዮጵያውያን ስንት መስዕዋትነት እየከፈሉበት ያለው ሕዝባዊ ትግል ፋሽስት ወያኔ ነጥብ እያስቆጠረበት እየተንገዳገደ ይገኛል።

የትግላችን አላማ ምንድን ነው? እየታገልን ያለነው በግፍ የታጎሩ እስረኞች እንዲለቀሱ ብቻ ነው? በግፍ የታሰሩ ሰዎች በግፍ የእግር ብረት ውስጥ ሆነው በጠባቡ ማሰቃያ ቤት ታጉረው ከሚመተሩት death chamber ወጥተው በረጅሙ ታስረው ወደ ሰፊው እስር ቤት መለቀቃቸው የወያኔን በጎ እርምጃ ያሳያል? ይህስ በጎ ጅምር ነው? ትግላችን መስዕዋትነት እየከፈልን እስረኛ ለማስፈታት ብቻ ነው ማለት ነው? እስረኛ መፈታቱ የወያኔን ወንጀለኛነት ይለውጠዋል?

አንዳንድ ፖለቲከኛ ነን ባዮችማ ባለም አቀፍ ሜዲያዎች ሁሉ ሳይቀር እየወጡ ወያኔ የህሊና ሰዎች አጉሮ በጭካኔ ከሚመትርበት ከጠባቡ የሰው መታረጃ ቄራ አስወጥቶ ተሃድሶ የሚሉትን የአርፋችሁ ተቀመጡ የቅጣት ትምህርት ሰጥቶ «አይደገመንም» በማስባል ወደሰፊው የማሰቃያ እስር ቤት እንዲዘዋወሩ ስላደረጋቸው በጎ ጅምር እንደሆነ፣ ፍትህ እንደተገኘ፣ ሰላም እንደመጣ፣ ነጻነት እንደተጎናጸፍን አድርገው ወያኔን ስለ «መልካም እርምጃው» ያመሰግኑታል። በነዚህ ወለፈንዲ ሰዎች አማካኝነት ስንት መስዕዋትነት የተከፈለበት ሕዝባዊ ትግል ወንጀለኛው ወያኔ በኛ ላይ ግፍ ስለፈጸመ እያመሰገኑት በፖለቲካው ሜዳ ነጥቡን ግን እያስቆጠረ ይገኛል። ያሳዝናል!

Hiber radio Las Vegas ይህ ህብር ሬድዮ _የወቅታዊ መረጃ ምንጭ ነው። ህብር ሬድዮ በአቤኔዘር ኮሙኒኬሽን ሴንተር እየተዘጋጀ  ከላስ ቬጋስ ከተማ፣ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 630 ሰዓት እስከሰዓት በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ  5639993994 ወይም 563999-3988 ወይም 712-432-8451 በመረጡት ቁጥር መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ 01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *