Hiber Radio: መንግስት የሚወድቀው በህዝብ ስም ዜጎችን ሲገድል ነው | ጦማሪ ስዩም ተሾመ

መንግስት የሚወድቀው በህዝብ ስም ዜጎችን ሲገድል ነው | በስዩም ተሾመ

ባለፈው ሳምንት አንዳንድ አርቲስቶች እና ታዋቂ ሰዎች በቴሌቪዥን ቀርበው “በሀገራችን ሰላም እንዲኖር መንግስት የዜጎችን ጥያቄ በአግባቡ መስማትና ተገቢ ምላሽ መስጠት አለበት” የሚል ምክር ማስተላለፋቸው ይታወሳል። በእርግጥ የዜጎችን መብትና ነፃነት ማከበር እና የሀገሪቱን ሰላምና ደህንነት ማስከበር የመንግስት ድርሻና ኃላፊነት ነው። ከላይ የተጠቀሱት ታዋቂ ሰዎች ሚዲያ ላይ ቀርበው እንዲህ ያለ “ምክር አዘል መልዕክት” ለመንግስት ማስተላለፋቸው መልካም ነው። ነገር ግን፣ መልዕክቱ የተላለፈው በእውን በሌለና ለሌለ ነገር ስለሆነ የሰዎቹ ምክር በድንጋይ ላይ ውሃ እንደማፍሰሰ ነው። ምክንያቱም የኢትዮጲያ ዜጎች ሀገር ሆነ መንግስት የላቸውም።

ሰላምና ደህንነት እንዲረጋገጥ በቅድሚያ ዜጎች ሀገራቸውን መውደድና ለሕግ ተገዢ መሆን አለባቸው። ለዚህ ደግሞ ለሕግና ስርዓት ተገዢ የሆነና የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚያከብርና የሚያስከብር መንግስት ሊኖር ይገባል። መንግስት የዜጎችን መብትና ነፃነት የሚገድብና የሚጥስ ከሆነ ዜግነት በራሱ ትርጉም የለውም። በዜግነታቸው የሚከበር የተለየ መብት፥ ነፃነትና ተጠቃሚነት ከሌለ ዜጎች ለሀገራቸው ፍቅር አይኖራቸውም። በእንዲህ ያለ ሁኔታ “ሀገር” ማለት እንደ “Jean-Jacques Rousseau” አገላለፅ አስቀያሚና ቂላቂልነት ነው፡-

¨…how can [men] love their country, if it is nothing more to them than to strangers, and afford them nothing but what it can refuse nobody? It would be still worse, if their lives, liberties and property lay at the mercy of persons in power,… For in that case, being subjected to the duties of the state of civil society, without enjoying even the common privileges of the state of nature would be in the worst condition in which freemen could possibly find themselves, and the word country would mean for them something merely odious and ridiculous” The Social Contract and Discourses by Jean-Jacques Rousseau, translated with an Introduction by G.D. H. Cole. PP: 217

በአሁኗ ኢትዮጲያ የውጪ ሀገር ዜጎች ከኢትዮጲያዊያን የተሻለ መብትና ነፃነት አላቸው። ለምሳሌ በኢትዮጲያ የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ከኢትዮጲያዊያን የበለጠ ፖለቲካዊ መብትና ነፃነት አላቸው። የኤርትራ ስደተኞች በአዲስ አበባ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ ሲያደርጉ የኦሮሞ ተወላጆች በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ በወጡበት ወቅት በፀጥታ ኃይሎች የተወሰደባቸውን አስቀያሚ እርምጃ እንደ ማሳያ ሊጠቀስ ይቻላል።

Eritrean refugees and dissidents, some holding Eritrean flags, demonstrate outside the headquarters of the African Union in Addis Ababa, Ethiopia, Thursday, June 23, 2016. Hundreds of Eritrean refugees and dissidents in Ethiopia have demonstrated against alleged human rights abuses committed by Eritrea’s government, and supporting a new U.N. report that accuses it of crimes against humanity over the last 25 years. (AP Photo/Mulugeta Ayene)

የኤርትራ ስደተኞች የሀገራቸውን መንግስት ለመቃወም በአዲስ አበባ ከተማ የካሄዱት የተቃውሞ ሰልፍ

በመሠረቱ መንግስት የተመሰረተበት መሰረታዊ ፋይዳ የዜጎችን የሃሳብና የመንቀሳቀስ ነፃነት ለማስከበር ነው።  ይህን ግዴታና ኃላፊነት ከመወጣት ይልቅ በዜጎች ላይ የሕይወት፥ አካልና የንብረት ጉዳት የሚያደርስ ከሆነ የተመሰረተበትን መሰረታዊ ዓላማ ስቷል። ምክንያቱም መንግስት የሚመሰረተው በዜጎች ላይ የሕይወትና አካል ጉዳት፣ እንዲሁም የንብረት ውድመት እንዳይፈፀምባቸው ነው። ስለዚህ መንግስት መልሶ በዜጎች ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረስ የለበትም።

በእርግጥ አንዳንድ የፖለቲካ ልሂቃን መንግስት የሀገርና ሕዝብን ሰላምና ደህንነት የማስከበር ግዴታ እንዳለበት ይገልፃሉ። በዚህ መሰረት፣ “የግለሰቦች ሕይወትና ንብረት የጠፋው የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ሲባል ነው” የሚል ማስተባበያ ያቀርባሉ። ነገር ግን፣ የአንድ ግለሰብ ሕይወትና ደህንነት ከጠቅላላው ሕዝብ ሰላምና ደህንነት የተለየ አይደለም። በመሆኑም የሕዝብን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ሲባል የአንድን ግለሰብ ሕይወትና ንብረት ማጥፋት በማንኛውም አግባብ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም። በድጋሜ “Jean-Jacques Rousseau” እንዲህ ያለው ማስተባበያ ፍፁም ሊወገዝ የሚገባ በውሸት ላይ የተመሰረተ የጨቋኞች ፈጠራ እንደሆነ ይገልፃል፡-

“… if we are to understand by it, that it is lawful for the government to sacrifice an innocent man for the good of the multitude, I look upon it as one of the most execrable rules tyranny ever invented, the greatest falsehood that can be advanced, the most dangerous admission that can be made, and a direct contradiction of the fundamental laws of society. …all have pledged their lives and properties for the defence of each, in order that the weakness of individuals may always be protected by the strength of the public, and each member by the whole State.”  The Social Contract and Discourses by Jean-Jacques Rousseau, translated with an Introduction by G.D. H. Cole. PP: 218

ከላይ በተገለፀው መሰረት፣ “የሕዝብን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር” በሚል ሰበብ የግለሰብን ሕይወትና ንብረት ማጥፋት ከሕብረተሰቡ መሰረታዊ ሕግ ጋር ይጋጫል። የመንግስት ኃይል ከእያንዳንዱ ዜጋ ራስን በራስ የማስተዳደርና የመምራት መብትና ስልጣን ላይ ተቀንሶ የተወሰደ ነው። ይህ ከሁሉም ዜጎች የተወጣጣ ኃይልና ስልጣን የእያንዳንዱንና የሁሉንም ዜጎች መብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚውል ነው።

“የህዝብን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር” በሚል ሰበብ የአንድን ግለሰብ ሕይወት ማጥፋት መንግስት የተመሰረተበትን ማህበራዊ ውል (Social Contract) የሚያፈርስ ነው። ምክንያቱም የመንግስት ስልጣንና ኃላፊነት ከሁሉም ዜጎች ወይም ከሕዝብ የተሰበሰበን ኃይል ተጠቅሞ የእያንዳንዱን ግለሰብ የሕይወትና ንብረት ከማንኛውም ዓይነት ጥቃት እንዲከላከል ነው። በዚህ መልኩ የእያንዳንዱን ግለሰብ መብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ሲያረጋግጥ የሕዝብ ሰላምና ደህንነት ይከበራል።

በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ለተቃውሞ ሰልፍ የወጡ የኦሮሞ ተወላጆች እና የፀጥታ ኃይሎች የወሰዱት እርምጃ

በአንፃሩ የሕዝብን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር በሚል ሰበብ የአንድን ግለሰብ ሕይወትና ንብረት ካጠፋ ሰላምና ደህንነቱን የሚያጣው ግለሰቡ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የሀገሪቱ ሕዝብ ነው። ምክንያቱም መንግስት የእያንዳንዱን ግለሰብ ሕይወትና ንብረት እንዲያስከብር ከሕዝብ የተሰጠውን ስልጣን፥ ኃይል የእያንዳንዱን ግለሰብ ሕይወትና ንብረት ለማጥፋት ተጠቅሞበታል። በመሆኑም እያንዳንዱ ዜጋ ከሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች ጋር በውስጥ ታዋቂነት የገባው ማህበራዊ ውል ተጥሷል። ይህ ሲሆን መንግስት የተፈጠረበትን መሰረታዊ ዓላማ ይስታል። መሰረታዊ ዓላማውን የሳተ መንግስት ፋይዳ-ቢስ ነው።

ህወሓት/ኢህአዴግ ባለፉት ሦስት አመታት ብቻ፤ ከ1200 በላይ ግለሰቦችን ገድሏል፤ በሺህዎች ላይ የአካል ጉዳት አድርሷል፣ ከ700 ሺህ በላይ ደግሞ ከመኖሪያ ቤታቸው አፈናቅሏል። አሁንም ቢሆን በዜጎች ሕይወት፥ አካልና ንብረት ላይ የሚደርሰው ጉዳትና ጥቃት ቀጥሏል። ይሄን ሁሉ ግፍና በደል በዜጎች ላይ የፈጸሙ፣ እንዲሁም ሲፈፀም ዳር ቆመው ሲመለከቱ የነበሩ የመንግስት ኃላፊዎች፥ የፀጥታና ደህንነት ኃላፊዎች፣ የጦር ጄኔራሎች፣ ወታደሮች፥ ፖሊሶች፥ ታጣቂዎች፥…ወዘተ ዛሬም ድረስ ዜጎችን ይገድላሉ፥ ያቆስላሉ፥ ያስራሉ፥ ያሰቃያሉ። እንደ ከዚህ ቀደሙ አሁንም “የሕዝብን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር” የሚል ሰበብ ያቀርባሉ።

ዛሬም “መንግስት” እንደሆኑ፣ ሕዝብና ሀገር እንደሚመሩ ያስባሉ፥ ይናገራሉ፥ ይሰብካሉ። የኢትዮጲያ ሕዝብ ሰላምና ደህንነቱን ያጣው የመጀመሪያውን ንፁህ ዜጋ በግፍ የገደሉ ዕለት ነው። መንግስት የወደቀው በሕዝብ ስም ዜጎችን የገደለ ዕለት ነው! ኢትዮጲያዊያን ሀገር-አልባ የሆኑት ከዚያን ዕለት ጀምሮ ነው!

Hiber radio Las Vegas ይህ ህብር ሬድዮ _የወቅታዊ መረጃ ምንጭ ነው። ህብር ሬድዮ በአቤኔዘር ኮሙኒኬሽን ሴንተር እየተዘጋጀ  ከላስ ቬጋስ ከተማ፣ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 630 ሰዓት እስከሰዓት በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ  5639993994 ወይም 563999-3988 ወይም 712-432-8451 በመረጡት ቁጥር መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ 01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *