Hiber Radio: ሕገ ወጡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲሰረዝ በውጭ የሚኖሩ የነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች ጠየቁ

በስደት በመላው ዓለም የሚኖሩ የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን ሕዝብ ሰላማዊና ሕጋዊ የለውጥ ትግል ለማኮላሸትና ሕዝቡን መልሶ ባሪያ ለማድረግ የታወጀውን ሕገ ወጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውግዘው በአስቸኳይ እንዲነሳ ጠየቁ። የሕዝቡን ትግል መደገፋቸውን እንደሚቀጥሉ በኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች ማህበር ፎረም አማካይነት ባወጡት መግለጫ ገለጹ።

የኢነጋማ ፎረም ሙሉ መግለጫ ተከትሎ ቀርቧል።

የወቅቱን የሃገራችንን ሁኔታ አስመልክቶ ከነጻ-ፕሬስ አባላት የተሰጠ መግለጫ

ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የህወሃት መራሹ መንግስት፤ በነጻው ፕሬስ ላይ ሲፈጽም የቆየው አፈና፣ እስር፣ እንግልትና ማሳደድ ሰለባ ሆነን፤ በተለያዩ የአለም ጥጋግ እንደ ጨው ዘር ተበትነን የምንገኝ የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ አባላት፣ አገዛዙ የህዝባችንን ሁለንተናዊ መብቶች በአፈ ሙዝ ስር ለማዋል ያጸደቀው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ በእጅጉ አሳስቦናል።

በሰለጠኑት አገሮ ተጠያቂነት እንዲጎለብት፣  የህዝብም ሆነ የግለሰብ መብት በአግባቡ እንዲከበር፣ ኢ-ፍትሃዊነት እንዳይነግስ፣  ሙስናና ሌሎችም የአሰራር ንቅዘቶች እንዳይስፋፉ በማድረግ ለአንድ ሃገር ሰላም፤ ዲሞክራሲና ብልጽግና ፕሬስ  የሚጫወተውን ቀጥተኛ ሚና ኖረንበት እያየነው ነው።

ያለመታደል ሆኖ በኢትዮጵያና በህዝቧ ላይ የተሰየመው መንግስት ግን መንበር ስልጣኑን ከተቆናጠጠበት ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ነጻውን ፕሬስ በጠላትነት በመፈረጅ ሲገዳደረው ቆይቶ በሂደት ህልውናውን አሳጥቶታል።  ይህ መሆኑ ደግሞ እንሆ አገዛዙ የሃገርን ሃብትና የህዝብን ንብረት ያለ ከልካይ እንዲመዘብርና ጥያቄ የሚያነሱትን ወገኖች እንዳሻው እንዲያሰቃይ አስችሎታል።

ምዝበራው፤ ግፍና እመቃው ከመጠን በማለፉ በተለይ ካለፉት ሁለት አመታት ወዲህ  የህዝብ ቁጣ ዳር እስከ ዳር ገንፍሎ ጥያቄውን ወደ ሥርዓት ለውጥ ከፍ አድርጎታል።

አሁንም ቢሆን አገዛዙ የህዝብን ጥያቄ በአግባቡ ከመመለስ የተሻለ ምንም አይነት አማራጭ እንደሌለው አልተረዳም። ከህዝብ የተነሳበትን ከፍተኛ ተቃውሞ ለማፈን በተደጋጋሚ የወሰዳቸው የኃይል እርምጃዎች ሁሉ አላዋጣ ሲሉት፤ለዘላቂ ሰላም እሰራለሁ ብሎ ቃል ከገባ ወር እንኳን ሳይሞላው እንሆ ተመልሶ የህዝብን ሁለንተናዊ መብትና ጥያቄ በጠመንጃ አፈሙዝ ስር የሚያውል አዋጅ አጽድቋል።

አዋጁ፤ የሙያ አጋሮቻችንና የፖለቲካ እስረኞች በመለቀቃቸው የተሰማንን ደስታ በቅጡም ሳናጣጥመው እንደ ጉም አብንኖታል። የእስረኞች መፈታት ለዘላቂው ሰላም መልካም ጅማሮ የመሆኑንም ተስፋ አጨልሞታል።

በመሆኑም እኛ በውጭ አገር የምንገኝ የኢትዮጵያ ነጻ-ፕሬስ አባላት የአገዛዙን ምክር ቤት ትዝብት ውስጥ በከተተው የተጭበረበረ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ጸደቀ የተባለውን የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ፤

  • የህዝብን የመናገር፣ የመንቀሳቀስ፣  ብሎም መሰረታዊ የሆኑ የግለሰብ መብቶችን በሙሉ የሚደፈጥጥ በመሆኑ በእጅጉ እናወግዘዋለን! እንቃወመዋለን።
  • የአገዛዙ ታጥቂዎች የህዝብን ልጅ እንዲያሰቃዩ፣ እንዲገድሉና እንዲመዘብሩ ፈቃድ የሚሰጥ የሞት አዋጅ በመሆኑ በጥብቅ እናወግዘዋለን! እንቃወመዋለን።
  • ከሁሉም በላይ ደግሞ ይህ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ፤ ለዘላቂ ሰላምና ለህዝቦች አብሮነት እንቅፋት በመሆኑ በጥብቅ እንቃወመዋለን! እናወግዘዋለን።

እኛ በስደት የምንገኝ የኢትዮጵያ የነጻ ፕሬስ አባላት፤    ከላይ የጠቀስናቸውን ምክንያቶች መሰረት በማድረግ፣  አገዛዙ በህገ ወጥ መንገድ ይፋ ያደረገውን የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን በመሰረዝ የህዝብን ጥያቄ በአግባቡ እንዲመልስ ስንል እናሳስባለን፡፡  ይህ ሳይሆን ቀርቶ፤ በህገ ወጥ መንገድ ለታወጀው አዋጅ እና ለዚህም ተፈጻሚነት ተባባሪ በመሆን የንጹሃን ደም እንዲፈስ የሚያደርጉ ወገኖች  ሁሉ ወደፊት በህግ መጠየቅ እንዳለባቸው እናምናለን። በመሆኑም ህልውናዋ አስጊ ምዕራፍ ላይ የምትገኘውን ሃገራችንን ለመታደግም ሆነ ቁጣው እንደ እቶን እሳት እየተቀጣጠለ ያለውን ህዝባችንን አብርዶ ወደ ሰላማዊ መንገድ ለመምራት፤ አገዛዙ ያለውን እድል ሳይረፍድ በፊት ይጠቀምበት ዘንድ እንመክራለን፡፡ በጥብቅ እናሳስባለን።

እኛ በውጭ አገር የምንገኝ የኢትዮጵያ የነጻ ፕሬስ አባላት፤ በአሁኑ ወቅት ድምፁን እንዳያሰማ የታፈነውን ህዝባችን፤ መብቱን ለማስከበር እያደረገ ባለው እልህ አስጨራሽ ትንንቅና ትግል ከጎኑ መቆማችንን እናረጋግጣለን። ሙያዊ ግዴታችንን በተገቢው በመወጣት ለድሉ እውንነት በጽናት እንደምንታገል ቃል እንገባለን።

ሕዝብ ሁሌም አሸናፊ ነው!

በውጭ አገር ከምንገኝ የኢትዮጵያ ነጻ-ፕሬስ አባላት

 Hiber radio Las Vegas ይህ ህብር ሬድዮ _የወቅታዊ መረጃ ምንጭ ነው። ህብር ሬድዮ በአቤኔዘር ኮሙኒኬሽን ሴንተር እየተዘጋጀ  ከላስ ቬጋስ ከተማ፣ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 630 ሰዓት እስከሰዓት በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ  5639993994 ወይም 563999-3988 1641-793-8229 ወይም 1641-715-8596  በመረጡት ቁጥር መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ 01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *