Hiber Radio: ዶ/ር አብይ አህመድ እና የኢትዮጵያ ህልውና! (ዳዊት ከበደ ወየሳ)

ትንታኔ

በአጼ ምኒልክ ዘመን ነው። የራስ ደረሶ ጦር አባይን ተሻግሮ፤ የራስ ጎበና ጦር  ደግሞ ጊቤን አልፎ መሃል መንገድ ላይ ይጋጭ ጀመር። የግጭቱ ምክንያት… አንደኛው ጦር ሌላውን፤ “ድንበር አልፈህ የኦሮሞን ህዝብ የሚያስቀይም ስራ ሰርተሃል።” የሚል ነው። ሁለቱም እርስ በርሳቸው መወቃቀሳቸው ሳያንስ፤ ጉዳዩ ወደሁለቱም አለቆች ዘንድ ደረሰና፤ የጎጃሙ ንጉሥ ተክለሃይማኖት እና የሸዋ ንጉሥ የነበሩት ንጉሥ ምኒልክ ተቀያየሙ። ከዚያም በግንቦት ወር 1874 ዓ.ም የእምባቦ ጦርነት ተከፈተ። በጦርነቱም ንጉሥ ምኒልክ አሸንፈው፤ የጎጃሙ ንጉሥ ተማርከው አዲስ አበባ መጡ። ታሪኩ ረዘም ያለ ስለሆነ፤ እዚህ ድረስ ያወራነውን በልቦናቹህ ያዙልን። ይህን ታሪክ ከአዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ጋር የምናያይዝበት የታሪክ ገመድ ይኖረናል። እናም ይህንን ሰው መደገፍ ማለት ኢህአዴግን መደገፍ ማለት እንዳልሆነ ታሳቢ በማድረግ፤ በአብይ ጾም ስለአብይ ትንሽ ቁምነገር እንጨዋወታለን።

ዶ/ር አብይ አህመድ እና የኢትዮጵያ ህልውና! (ዳዊት ከበደ ወየሳ)

ወደድንም ጠላን ዶ/ር አብይ በኢህአዴግ አብላጫ ድምጽ ተመርጧል። ኢህአዴግነቱን እሱም ሆነ እኛ የምንክደው ጉዳይ አይደለም። ኢህአዴግ ማለት ደግሞ  በስርቆት የጠገበ፤ በማጭበርበር የደለበ የፖለቲካ ድርጅት ነው። ይህን ለአንድ አፍታም ቢሆን መዘንጋት የለብንም። ይህን መዘንጋት ማለት፤ በሚሊዮን የሚቆጠርን የኢትዮጵያ ህዝብ ብሶትና ለቅሶ መዘንጋት ማለት ነው። የኢህአዴግን ግፍ መዘንጋት ማለት… ብዙዎች የሞቱላትን፣ የተጎዱባትን፣ የታሰሩላትን፣ የተሰደዱላትን ኢትዮጵያን መዘንጋት ማለት ይሆንብናል። ስለሆነም ስለዶ/ር አብይ አህመድ መልካም ነገር ስናወራ፤ ድርጅቱ በህዝብ ላይ የፈጸመውን ግፍ እና በደል ሳንዘነጋ ሊሆን ይገባል።

ልብ በሉ። ይህ ሰው እንዲመረጥ የፈለግነው፤ ኢትዮጵያ መዳን ስላለባት እንጂ ኢህአዴግ ስለታመመ አይደለም። ኢትዮጵያ በህወሃት የግፍ አገዛዝ ስር ሆና… በአጣብቂኝና መንታ መንገድ ላይ ባለችበት በአሁኑ ወቅት፤ እንደ ለማ መገርሳና ዶ/ር አብይ አህመድ አይነት ሰዎች ባልተጠበቀ ሁኔታ አንገታቸውን ቀና አድርገው፤ የህወሃት ሰዎችን መቃወም እና መገሰጽ መጀመራቸው – ሰፊ ህዝባዊ ድጋፍ አስገኝቶላቸዋል። በሌላ አባባል፤ “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው!” እንደሚሉት አይነት ሆነና ሳንወድ በግድ፤ ስለኢትዮጵያ ህልውና ንል… የወደፊት እጣ ፈንታችንን ከነለማ መገርሳ እና አብይ አህመድ መንገድ ላይ አድርገናል።

አሁን በተደረገው አዲስ ምርጫ መሰረት ደግሞ ዶ/ር አብይ አህመድ የኢህአዴግ መሪ እና ተጠሪ ሆኖ ይቀጥላል። የኢትዮጵያም አዲስ ጠቅላይ ሚንስትር በመሆን፤ በተለይ እራሱን ሰማይ ለማድረስ ከሚጣጣረው የህወሃት ድርጅት ነጻ በማድረግ “ኢትዮጵያን ለሚቀጥሉት አመታት በተሻለ መንገድ ይመራታል” ብለን ስለምንጠብቅ ከደብረ ሰይጣናት ሰይጣን መርጠን፤ ሳንወድ በግድ ወደን፤  ዶ/ር አብይን ደግፈነዋል። እርግጥ ነው። ከኢህአዴግ ውጪ ከዶ/ር አብይ የተሻለ ወይም የተስተካከለ ሰው ማግኘት ቢቻልም፤ በኢህአዴግ ድርጅት ውስጥ ግን እንዲህ አይነት ተራማጅ አስተሳሰብ ያለው ሰው ማግኘት እጅግ በጣም አስቸጋሪ እና ፈታኝ ጉዳይ ነው።

ሰውየው ሌሎች እንዳደረጉት… ኢትዮጵያን አሳንሶ ብሄሩን እላይ ልስቀል የሚል አይነት ሰው አይደለም። ይልቁንም ከኢትዮጵያዊነቱም በላይ የምስራቅ አፍሪቃ አገራትን ወደአንድ ለማምጣት እና በቀጣናው መረጋጋትን ለመፍጠር የሚቻልበትን ጥናታዊ ስራዎችን የሰራ ሰው ነው። ገና በለጋ እድሜው ብረት ጨብጦ ለነጻነቱ የተወጋ ሰው ቢሆንም፤ እንደህወሃት ታጋዮች የቀድሞውን ሰራዊት፤ “የደርግ ወታደር… የጠላት ጦር” ሲል ተደምጦ አያውቅም። ከሌሎች የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በሚያለያየው ነገር ላይ ከመከራከር ይልቅ፤ አንድ በሚያደርገው ጉዳይ ላይ ሲያተኩር እንሰማዋለን። እነዚህ ሁሉ ነገሮች ተጠራቅመው ለዶ/ር አብይ አህመድ አክብሮት ቢኖረንም፤ ለአንድ አፍታም ቢሆን የዚያ የመጥፎ ነገር ምሳሌ የሆነው የኢህአዴግ ድርጅት አባል መሆኑን ግን አንዘነጋም።

ዶ/ር አብይ አህመድ… በአባቱ ሙስሊም፣ በእናቱ ኦርቶዶክስ… በራሱ ደግሞ የጴንጤ እምነት ተከታይ ነው። ትውልዱ ጅማ፣ ብሄሩ ኦሮሞ፣ ዜግነቱ ኢትዮጵያዊ ነው። ዶ/ር አብይ እድገቱ ከአርሶ አደር ሆኖ፤ ለትምህርቱ ከፍተኛ ዋጋ በመስጠት የልጅነት ዘመኑን በትምህርት አሳልፎ፤ ከዚያም የኦሮሞ ነጻ አውጪ በወለጋ በኩል ሲመጣ፤ ገና በ14 አመቱ ሰራዊቱን ተቀላቅሎ፤ አብሮ ተዋግቶ በኢትዮጵያ መከላከያ ውስጥ እስከ ኮሎኔልነት ማዕረግ ደርሷል። ትምህርቱን እንደገና ተከታትሎ በኮምፒዩተር፣ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ፤ ብሎም በሰላም እና ደህንነት የዶክትሬት ዲግሪውን ወስዷል። እራሱን ከውትድርና አግልሎ፣ ትምህርቱ ላይ ትኩረት ሰጥቶ፤ በኮምፒዩተር ሳይንስ እንዲሁም በሰላም እና ደህንነት ጥልቅ የሆነ እውቀትን በመገብየት ረዥም መንገድ ባይሄድ ኖሮ፤ ወታደራዊ እድገቱን ጠብቆ የ“ጄነራል”ነትን እርከን የሚከለክለው አይኖርም።

ነገር ግን ጀግንነት የሚለካው ህዝብን በመበጥበጥ ወይም ብረት በመጨበጥ አይደለም። ጀግንነት የሚለካው በገደሉት የሰው መጠን እና ብዛት ሳይሆን፤ በህይወት ዘመን ውስጥ በሚተገበር ቁምነገር ነው። ይህን አባባል ይዘን ከላይ በመግቢያችን ላይ በአጼ ዮሃንስ ዘመን… ንጉሥ ምኒልክ እና ንጉሥ ተክለሃይማኖት በኦሮሞ ግዛት እና በህዝቡ በደል ተቀየይመው ጦርነት እስካማስነሳት የደረሱበትን ታሪክ እንጨዋወታለን። እንግዲህ “ጀግና ማለት ምን ማለት ነው?” የሚለውን በማሰብ ወደቁምነገራችን እናምራ።

ከጦርነቱ በኋላ ንጉሥ ምኒልክ አዲስ አበባ ሲገቡ ታላቅ የድል አቀባበል ተደረገላቸው። ፉከራና ሽለላው በርክቶ ቤተ መንግስቱ ቀውጢ ሆነ።ይሄ ሁሉ ሲሆን ግን ንጉሥ ምኒልክ የማረኳቸውን የጎጃም ንጉሥ ሳያስሩና ሳያዋርዱ አክብረው አስቀመጡ። ይልቁንም ምሽት ላይ እራት ሲቀርብ፤ የጎጃሙን ንጉሥ በክብር አስጠርተው በአንድ ማዕድ እንዲቆርሱ አደረጓቸው። እራት ተበላ፤ ጠጅ ተጠጣ። ጨዋታም ተጀመረ። መኳንንቱም ሰብሰብ ብለው ይሄንን ጨዋታ እየሰሙ ነው። እምዬ ምንሊክ – ንጉሥ ተክለሃይማኖትን ጠየቁ…

“ኧረ የሆነስ ሆነና… ምርኮኛው እኔ ብሆን ኖሮ ምን ታደርገኝ ነበር?” ብለው ጠየቁ ንጉሥ ተክለሃይማኖትን።

የጎጃሙም ንጉሥ፤ “አልዋሽም። እጅና እግርህን ቆራርጬ አንተን ለአሞራ ሲሳይ እሰጥህ ነበር።” አሉ።

“ምህረት ማድረግ እያለ በአሰቃቂ ሁኔታ መግደልን ምን አመጣው?” ምኒልክ ጠየቁ።

“ማራኪ ተማራኪውን መቅጣቱማ ከጥንት ጀምሮ የነበረ የጀግንነት ልማዳችን ነው።” አሉ ንጉሥ ተክለሃይማኖት።

በዚህን ግዜ ንጉሥ ምኒልክ ወደሁሉም ዘወር ዘወር ብለው አዩና፤ “እንግዲህ መልስ ከናንተ እፈልጋለሁ። ለመሆኑ ጀግና ማለት ምንድነው?” ብለው ጠየቁ፤ የተሰበሰበውን የጦር አበጋዝና መኳንንት። በዚህን ግዜ ጨዋታው እንደገና ደራ። ሁሉም የየበኩሉን መልስ ሰጠ። በመጨረሻ ግን ምኒልክ እንዲህ አሉ።

“ወንድሞቼ ሆይ! አንዱ ሌላውን መግደል ጀግንነት አይደለም። ግዜ ስለሰጠህ የገዛ ወገንህን መግደል ጀግና አያሰኝም። ይልቁንም ጀግና ማለት… ጀግና ማለት መሸነፉን ሲያውቅ ይቅርታ የሚጠይቅ ነው!” አሉና ፊታቸውን ወደ ንጉሥ ተክለሃይማኖት አዞሩ። ይህ አባባል የተማረኩትን ንጉሥ ከፍ በማድረግ የጀግና ያህል እንዲቆጠሩ የሚያደርግ ነበር።

በእምዬ ምኒልክ ንግግር የተገረሙት ንጉሥ ተክለሃይማኖት ብቻ አይደሉም። በእምባቦ ጦርነት ላይ የተካፈሉት ጀግኖች ጭምር በምኒልክ ምላሽ ተገርመዋል። ከዚህ በኋላ ንጉሥ ተክለሃይማኖትም እንዲህ አሉ። “አይይ… ጀግና ማለትስ የማረከውን አክብሮ ምህረት የሚያደርግ ነው!” በማለት ምህረት ያደረጉላቸውን የምኒልክ ሰዎች አመሰገኑ። ይህንን ታሪክ ለማጠቃለል ያህል… በኋላ ላይ ምኒልክ የንጉሥ ተክለሃይማኖትን፤ ለበላያቸው ለአጼ ዮሃንስ አስረከቡ። በመቻቻልና ይቅር በመባባል ላይ የተመሰረተው፤ የንጉሥ ተክለሃይማኖት እና የአጼ ምኒልክ ፍቅርም፤ እስከሞታቸው ፍጻሜ ድረስ አብሯቸው ዘለቀ።

 

ከመቶ ሰላሳ አመት በፊት ንጉሥ ምኒልክ እና ንጉሥ ተክለሃይማኖት ጦርነት አድርገው፤ ብዙ ሰው ሞቶ… እርስ በርስ ይቅር ተባብለው ከአንድ ገበታ ቀርበው መብላት ከቻሉ፤ የአሁኑ ትውልድ ይህን ለማድረግ ምን ይገደዋል? ጀግና ማለት መሸነፉን ሲያውቅ ይቅርታ የሚጠይቅ ከሆነ፤ ኢህአዴግ ደግሞ ደጋግሞ ይቅርታ ሊጠይቅ እና የበደለውን ህዝብ ሊክስ ይገባዋል። የጥላቻን ግንብ አፍርሶ በፍቅር ላይ የተመሰረተች ኢትዮጵያን መገንባት አለበት። ይህን ለማድረግ ግን ኢህአዴግ እጁ ላይ ደም ስላለ፤ በቅድሚያ እራሱን ማጥራት ይኖርበታል። በዚህም መሰረት አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር፦

1ኛ – መሰረቱን ብሄር ሳይሆን፤ ኢትዮጵያዊነትና እውቀትን ያደረገ አዲስ የጠቅላይ ሚንስትር ካቢኔ ማቋቋም ይኖርበታል።

2ኛ – የአንድ ዘር የበላይነትን ለማረጋገጥ ተብሎ ህዝብን ለመጨፍለቅ የተዘጋጀውን የአጋዚ ጦር ከከተማ አውጥቶ በድንበር ማስጠበቅ ስራ ላይ ማሰማራት አለበት።

3ኛ – በጄነራል ሳሞራ የኑስ የሚመሩ “የትግራይ ህዝብ ማለት፤ ህወሃት ማለት ነው” የሚል ጠባብ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች፤ ለሌላው ህዝብ ጥላቻ እንጂ አክብሮት የሌላቸው ግለሰቦች፤ ሌላውን ህዝብ ከህወሃት ጋር ሳይሆን፤ ከትግራይ ህዝብ ጋር እንዲጋጭ እኩይ ፕሮፓጋንዳ የሚነዙ ሰዎች፤ ከወታደራዊ ስልጣናቸው መነሳት አለባቸው።

4ኛ – በህገ ወጥ መንገድ የተደረገው እና እየተደረገ ያለው የቡድን ዘረፋ መቆም ብቻ ሳይሆን፤ የዚህ ተዋንያን ለፍርድ መቅረብ አለባቸው።

5ኛ – ተቃዋሚውንና ህዝቡን ለማፈን የተዘረጋውን የአፈና መረብ ከላይም ከታችም በማፈራረስ፤ ተቋሙ ለአገር በሚጠቅሙ የደኅንነት ስራዎች ላይ ትኩረት ሊያደርግ ይገባዋል።

ይህ ኢህአዴግ በራሱ ውስጥ ሊያደርገው የሚገባ አበይት የጽዳት ዘመቻ ሲሆን፤ ከህዝቡ ጋር አብሮ ለመስራት ደግሞ የሚከተሉት ጉዳዮች ትኩረት ሊያገኙ ይገባቸዋል።

1ኛ – ከምንም በላይ ሁሉንም እኩል የሚያይ የህግ የበላይነት መከበርና መረጋገጥ አለበት።

2ኛ – በህዝቡ ላይ የደረሰው በደል እና ግፍ በቀላሉ የሚካስ አይደለም። ሆኖም ኢህአዴግ በግልጽ ወጥቶ ይህንን ህዝብ ይቅርታ በመጠየቅ፤ እራሱን በህግ ለሚቋቋም ብሔራዊ እርቅ ማዘጋጀት ይኖርበታል።

3ኛ – የፖለቲካ ምህዳሩ ሰፍቶ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ያለምንም መሳቀቅ እና ሰቆቃ፤ በማይጨበረበር ህዝባዊ ምርጫ ተሳታፊ የሚሆንበት መንገድ ሊመቻች ይገባል።

4ኛ – የሰብአዊ መብት አያያዝ እንዲረጋገጥ ከተፈለገ፤ የግል እና የወል መብቶችን ሲጥሱ የነበሩ የኢህአዴግ ባለስልጣኖች ላይ ግልጽ የሆነ እርምጃ መወሰድ ይኖርበታል።

5ኛ – ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ዳግም መረጋገጥ ብቻ ሳይሆን ለጋዜጠኞች ዘላቂ ዋስትና የሚሰጥበት ሁኔታ ሊመቻች ይገባል። በዚያው መጠን ኢህአዴግ እንደግል ንብረቱ የሚጠቀምባቸው የሚዲያ ተቋማት፤ ከድርጅታዊ የፕሮፓጋንዳ  ስራ ወጥተው ህዝባዊ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ የግድ ነው።

6ኛ – የኢትዮጵያን ህዝብ በብሄር በመከፋፈል፤ እርስ በርስ እየተጋጨ እንዲኖር፤ ግልጽ እቅድ ወጥቶ እየተሰራበት ለመሆኑ፤ በኦሮሚያ ውስጥ ብሄራዊ ቋንቋ በትምህርት ቤት ውስጥ እንዳይሰጥ መደረጉ አንደኛው ምሳሌ ነው። ይህ ትውልድ ገዳይ መሰሪ ተንኮል፤ የኦሮሞ ህዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር በቋንቋም ሆነ በፊደል እንዳይገናኝ ሆን ተብሎ በህወሃት የተቀመመ ትውልድ ገዳይ መርዝ መሆኑ ታውቆ፤ ህዝቡ ከአፍ መፍቻው ቋንቋ በተጨማሪ ብሄራዊ ቋንቋንም በአማራጭ እንዲማር መደረግ ይኖርበታል።

ቢያንስ እነዚህን ጥቂት ነገሮች ማድረግ የማይችል ኢህአዴግ፤ እስካሁን በሄደበት መንገድ ላይ እንደውሃ ወቃጭ “እዛው እዘጭ እዘጭ” ከማለት ውጪ ምንም አይፈይድም። ዶ/ር አብይ አህመድ የዚህ ድርጅት እና የአገሪቱ መሪ ነው። ይህ ድርጅት እስካሁን የሄደበት መንገድ ስህተት መሆኑን አውቆ ለማስተካከል የማይጥር ከሆነ፤ እንደፔንዱለም ባለበት የሚወዛወዝ ግዑዝ ነው የሚሆን።

ንጉሥ ምኒልክ፤ “ጀግና ማለት መሸነፉን ሲያውቅ ይቅርታ የሚል ነው።” ባሉት መሰረት፤ ኢህአዴግ በህዝብ ንቅናቄ ተሸንፎ እራሱን ለመበወዝ ተገዷል። በቅድሚያ ይህንን ሽንፈት መቀበል ያስፈልጋል። ይህንን ተቀብሎ ህዝብን ይቅርታ ሲል፤ ህዝብ እንደጀግና ይቀበለው ይሆናል። ከዚያ ውጪ ግን… ገድሎ እና አስሮ “ጀግና ነን!” እያሉ መዘባበት መቆም ይኖርበታል።

ንጉሥ ተክለሃይማኖት፤ “ጀግና ማለት የማረከውን አክብሮ ምህረት የሚያደርግ ነው!” እንዳሉት፤ የዚህ ህዝብ ጀግንነት የሚለካው ሌላውን በማዋረድ ሳይሆን፤ ለተሸነፉት ጭምር ክብር እና ዋጋ የሚሰጥ በመሆኑ ነው። ይህንንም ለቀድሞ የሰራዊት አባላት በሰጠው ፍቅር አሳይቷል። የደርግ ዘመን ወታደር ከሰሜን እስከደቡብ ድረስ ሲበተን፤ ሰራዊቱን ተሸናፊ አድርጎ አልተበቀለም፤ ዛሬም ድረስ ኢህአዴግ እንደሚያደርገው አልተአለቀባቸውም። ይልቁንም የኢትዮጵያ ህዝብ በሁሉም አቅጣጫ የተራቡትን እያበላ፤ የተጠሙትን እያጠጣ፤ የታረዙትን እያለበሰ ነው ወደየመንደራቸው የሸኘው። የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲህ አይነት ይቅርታ አድራጊ ህዝብ ነው። ይቅርታ ለማድረግ ግን፤ ተሸናፊው አካል ይቅርታ የሚጠይቅ ሆኖ ሊገኝ ይገባዋል።

ለማጠቃለል ያህል… በዶ/ር አብይ የሚመራው አዲስ ስርአት፤ ይቅር መባባልን ካወቀበት፤ ከህዝብ እና ከአለማችን ስልጣኔ ጋር አብሮ መሄድ ካለበት፤ በቅድሚያ ተቃዋሚ ከሚባሉት ሰዎችና ድርጅቶች ጋር በቅን መንፈስ ቁጭ ብሎ ሊነጋገር ይገባዋል። በዚያን ግዜ እኛ ከገለጽነው ዝርዝር በላይ፤ ጠቃሚ ሃሳቦች በጠረጴዛው ዙሪያ ሊቀርቡ ይችላሉና… ታላቋን ኢትዮጵያ ለመገንባት በቅድሚያ የህዝቡን አንድነት በፍቅር ላይ ለመገንባት እንዘጋጅ።

በመጨረሻም… ዶ/ር አብይ አህመድ እንደሌሎቹ፤ “የኢትዮጵያ ታሪክ ፈርሶ የኛ ታሪክ ብቻ ይደመጥልን” ሲል ሰምተነው አናውቅም። ስለሆነም የሚቀጥለው የአድዋ በአል ሲከበር ከአጼ ምኒልክ ሃውልት ስር የአበባ ጉንጉን እንደሚያኖር እንገምታለን። በዚህ ታላቅ ሃውልት ስር የተጻፈ አንድ ትልቅ ቁም ነገርም አለ። የአጼ ምኒልክ አባባል ነው፤ “ከትልቅ ሰው መወለድ ሳይሆን እራስን ለትልቅ ቁም ነገር መውለድ፤ ታላቅነት ነው።” ይላል ከሃውልቱ ስር የተጻፈው ኩራፒታ።  ዶ/ር አብይም… አጼ ምኒልክ እንዳሉት ለተወለደበት ሳይሆን፤ እራሱን ለወለደበት ኢትዮጵያዊነት፤ ስለድርጅት ሳይሆን ስለኢትዮጵያ ህልውና ሲል፤ አንድ ቁምነገር ይሰራ ዘንድ የሁላችንም ምኞት ነው።

Hiber radio Las Vegas ይህ ህብር ሬድዮ _የወቅታዊ መረጃ ምንጭ ነው። ህብር ሬድዮ በአቤኔዘር ኮሙኒኬሽን ሴንተር እየተዘጋጀ  ከላስ ቬጋስ ከተማ፣ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 630 ሰዓት እስከሰዓት በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ  5639993994 ወይም 563999-3988 1641-793-8229 ወይም 1641-715-8596  በመረጡት ቁጥር መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ 01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *