Hiber Radio: ኮማንድ ፖስቱ የአማራ ተፈናቃዮችን በባህር ዳር ቤተክርስትያን ግቢ ውስጥ እንዳያድሩ መከልከሉ ተገለጸ |፣”የተቸገረ ሰው ከእግዚያብሔር ቤት ውጣ አይባልም” አቡነ አብርሃም

በባህር ዳር አባይ ማዶ ከቤተ ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን እየተዘዋወሩ ሜዳ ላይ የሚአድሩት ከቤንሻንጉል የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች በሕወሓት የበላይነት በሚመራው ኮማንድ ፖስት አማካይነት አካባቢውን ለቀው እንዲሄዱ ማስጠንቀቂአ እንደተሰጣቸው መረጃዎቹን ጠቅሶ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ዘግቧል።ሙሉ ዘገባው ተከትሎ ቀርቧል።

ከጌታቸው ሽፈራው

ባህርዳር የሚገኙት ተፈናቃዮችን ወደ አማራ ክልል የመጡት ከታህሳስ ወር 2010 ዓም ጀምሮ ነው!

ለሶስት ቀን ያህል የኦሮሚያ ክልል መንግስት እገዛ አድርጎላቸዋል። የአማራ ክልል መንግስት ያደረገላቸው እገዛ እንዳልነበር ገልፀዋል። የተወሰኑ ሟቾችን አስከሬን ወደ ቤተሰቦቻቸው የላከው የኦሮሚያ ክልል መንግስት ነው።

ወደ ቤንሻንጉል ተመልሰው ለአንድ ወር ቆይተዋል። ለአንድ ወር ያህል ቀይ መስቀል እገዛ አድርጓል። በዚህ ወቅት ወደቀያቸው ይመለሳሉ ተብሎ ቢታሰብም የቤንሻንጉል ክልል መንግስት “ለቅቃችሁ ካልወጣችሁ ለህይወታችሁ ተጠያቂ አልሆንም” የሚል ማስፈራሪያ አደረሳቸው። ቀይ መስቀልም እገዛውን አቆመ

ወደ ባህርዳር እንደመጡ መግቢያ ሲያጡ ወደ ገብርኤል ቤተ ክርስትያን ነበር ያቀኑት። ሆኖም አንድ ቀን እንዳደሩ ኮማንድ ፖስቱ ቤተ ክርስትያን ውስጥ እንዳያድሩ ከልክሏል ተብለው ከቤተ ክርስትያን ተባርረዋል

ከገብርኤል ቤተ ክርስትያን ሲባረሩ ወደ ሚካኤል ቤተ ክርስትያን አቀኑ። ሁለት ቀን እንዳደሩ በተመሳሳይ ምክንያት ተባረሩ

አሁንም ወደ ሌላ ቤተ ክርስትያን ከመሄድ ውጭ አማራጭ አልነበራቸውም። ወደ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስትያን ሄደው አቡነ አብርሃም እግር ተደፉ። አቡነ አብርሃም እንዲነሱ ጠየቋቸው። ከየ ቤተክርስትያኑም “ውጡ” ሲባሉ የሰነበቱት ምስክኖች፣ አቡነ አብርሃምን ከጊዮርጊስ ቤተ ክርስትያን እንዲያስጠልሏቸው፣ “አስወጡ” ከተባሉም እንዳያስወጧቸውም ለመኗቸው። አቡነ አብርሃምም “ክፉ ሰርታችሁ መጥታችሁ ከሆነ እንዳታሳፍሩኝ፣ ተገፍታችሁ ከመጣችሁ ግን ቤተ ክርስትያን ለተገፉት መጠለያ ነች” ብለው አስገቧቸው። እራትም እንዲበሉ አደረጉ።

አንድ ቀን አድረው ግን ተመሳሳይ ጫና መጥቷል። አቡኑ ግን አላስወጧቸውም። “እኛ ከመንግስት አንበልጥም። ግን ይህ ቤተ ክርስትያን ነው። የእግዚያብሔር ቤት ነው። የተቸገረ ሰው ከእግዚያብሔር ቤት ውጣ አይባልም። ……” ብለው እንዳይወጡ እንዳደረጉ ተፈናቃዮቹ ገልፀውልኛል። አሁን በጊዮርጊስ ቤተ ክርስትያን ግቢ ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ!

ከቀያቸውም ተባርረው፣ ከእግዚያብሔር ቤትም እየተባረሩ ይገኛሉ! የቀጣይ እጣቸውም አስጊ ነው!

Hiber radio Las Vegas ይህ ህብር ሬድዮ _የወቅታዊ መረጃ ምንጭ ነው። ህብር ሬድዮ በአቤኔዘር ኮሙኒኬሽን ሴንተር እየተዘጋጀ  ከላስ ቬጋስ ከተማ፣ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 630 ሰዓት እስከሰዓት በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ  5639993994 ወይም 563999-3988 1641-793-8229 ወይም 1641-715-8596  በመረጡት ቁጥር መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ 01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *