Hiber Radio: የአማራ ወጣቶችን ትግልና የከፈሉትን ዋጋ መካድ፣ ማሳነስና ማንኳሰስ አይገባም

እየሆነ ላለው ነገር የአማራ ወጣቶችም ተገድለዋል፣ ታስረዋል፣ ተሰደዋል፣ አሁንም በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ በየማጎሪያው አሉ።

በሀገሪቱ ውስጥ ባለፉት 3 ዓመታት ሕዝባዊ አመጽ ከተካሄደባቸው ክልሎች አንዱ የአማራ ክልል ነው። ኦሮሚያ ክልል ላይ ሁለተኛው ዙር አመጽ ጊንጪ ላይ ህዳር 2008 (November 2015)ተጀምሮ በመላው ኦሮሚያ እንደተቀጣጠለ ሁሉ ከ8 ወራት በኋላ የአማራ ክልል አመጽም በእነ ኮል ደመቀም ተጀምሮ ሐምሌ 2008 መጨረሻ ላይ (August 2016) ጎንደር ላይ በአደባባይ ሰልፍና ተቃውሞን አስከትሎ በመላው የአማራ ክልል ተስፋፋ።

በዚህም ሕዝባዊ አመጽ በሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ወጣቶች ተገድለዋል፣ ከ30 ሺህ በላይ በጅምላ ታፍሰው ታስረዋል፣ ብዙዎች ደብዛቸው ጠፍቷል፣ የአካል ጉዳት ደርሶባቸውል። አሁንም ድረስ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የአማራ ወጣቶች በየማግሪያው ይገኛሉ።

ኦሮሚያ ክልል ላይ እንደነበረው ሁሉ በአማራ ክልልም ከአደባባይ ሰልፍና ተቃውሞ በተጨማሪ የሥራ ማቆም አድማና ቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማዎች ውጤታማ በሆነ መልኩ ተካሂደዋል።

የአማራ ወጣት ከራሱም አልፎ በኦሮሚያ ክልል የሚካሄደውን ግድያ ያወገዘ “የሚፈሰው የኦሮሞ ሕዝብ ደም የእኔም ደም ነው” ብሎ አመጹን ያካሄደና ከማንም ቀድሞ አንድነትን የገለጸ ወጣት ነው።

ሌላ ምሳሌ ልጨምር ሀገር ውስጥ ሆኖ የግንቦት 7 መሪን ሥምና ፎቶ በአደባባይ ይዞ መውጣት አይደለም ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ፎቶውን post and share ማድረግ በሚያስፈራበት ወቅት የአማራ ወጣቶች ስሙንና ምስሉን ይዘው አደባባይ በመውጣት ከመከላከያና ፌደራል ጋር ተፋጠው አንዳርጋቸው ይፈታ ብለው ሲጠይቁ ነበር።

ኢህአዴግን አስጨናቂ ነገር ውስጥ ከቶ ጥቅምት 2009 ዓም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመላ ሀገሪቱ እንዲያውጅ ያስገደደው የኦሮሞና የአማራ ሕዝብ አመጽ ተደምሮ ነው።

ዛሬ እየሆነ ላለው ነገር ሁሉ ልክ እንደ ኦሮሞው ሁሉ የአማራ ሕዝብም በተለይም ወጣቱ ዋጋ ከፍሎበታል። ዕውነታው ይሄ ሆኖ ሳለ አሁን የሚታየው ነገር የፖለቲካ እስረኞች መፈታትም ሆነ ሌላው ነገር በሙሉ ሊመጣ የቻለው በኦሮሞ ወጣቶች/ ቄሮዎች/ ትግል ብቻ እንደሆነ ተደርጎ እየተዘገበና እየተነገረ ነው። ይሄ ሕይወታቸውንና አካላቸውን ላጡ በየማጎሪያው ለተሰቃዩትና እየተሰቃዩ ላሉት የአማራ ወጣቶች ስድብ ነው። ፍጹም ውሸት የሆነና ሊስተካከልም የሚገባው ነገር ነው።

በፎቶ፣ በቪዲዮ ወዘተ በተጨባጭ ማስረጃ ተመዝግቦ ያለን ክስተትና ሁሉም ሰው በዓይኑ ያየውን የአማራ ወጣቶች የከፈሉትን መስዋዕትነት መካድ ወይም ማሳነስ ራስን ግምት ውስጥ መጣል ነው። ይሄ የታሪክ ሽሚያና ፉክክር አይደለም።

 

የአማራ ሕዝብ በተለይም ወጣቱ እንደ ኦሮሞው ወጣት ሁሉ ለከፈለው መስዋዕትነት ተገቢውን ክብርና ዕውቅና መስጠት ይገባል። በዚህ ጉዳይ ላይ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪዎች፣ አክቲቪስቶች ወዘተ ጉዳዩን ስትዘግቡም ሆነ ስታነሱ በዚህ መልኩ ልታቀርቡት ይገባል።

* የቀን ስህተት ካለ ሊታረም ይችላል።

አቤኔዘር ቢ. ይስሐቅ

Hiber radio Las Vegas ይህ ህብር ሬድዮ _የወቅታዊ መረጃ ምንጭ ነው። ህብር ሬድዮ በአቤኔዘር ኮሙኒኬሽን ሴንተር እየተዘጋጀ  ከላስ ቬጋስ ከተማ፣ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 630 ሰዓት እስከሰዓት በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ  5639993994 ወይም 563999-3988 1641-793-8229 ወይም 1641-715-8596  በመረጡት ቁጥር መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ 01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *