Hiber Radio: የ ዶ/ር አብይ ‘መደመር ‘ ‘ ደ ‘ ን ጠበቅ… በሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ እይታ

ጠቅላይ ሚኒስትር  አብይ አህመድ ብዙ ንግግራቸው ላይ  በአፅንኦት<< መደመር >> የሚለውን ቃል ይጠቀማሉ :: ባጠቃላይ ሚኒስትሩ ንግግራቸው ሁሉ የሚያሰባስብ፣ የሚያፋቅር ፣ አንድነትን የሚያስተጋባ:፣ተስፋ የሚሰጥ በመሆኑ ኢትዮጵያን እየለወጡዋት ነው:: ከንንግግራቸው ጋር በተግባር የሚያሳዩት ሁሉ ከጨለማና ሕዝብን ከለያየ ከከፋፈለ  በጥቂቶች ተገዝቶ ተዋርዶ ከኖረበት ዘመን ወደ ብርሀንና የተስፋ ዘመን እያሸጋገሩት ነው:: አንዱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መርሆ <<መደመር >> ነው’::

ኢትዮጵያን ታላቅ አድርጓት እስከዛሬ በማንም በምንም ሳትደፈር እዚህ ያደረሳት መደመር ነው:: ኢትዮጵያውያን በባህል፣  በቋንቋ፣ በሀይማኖት ያሸበረቀ የድልና የትግል ታሪክ ተጎናጽፈው የደፈራቸውን ሁሉ ያሸነፉት በመደመራቸው ነው:: እንደሰው በውስጣቸው ልዩነት ኖሮ አልፎ አልፎ ቢጋጩም  እንደ አንድ ሕዝብ  አንድ አገር   ተደምረው አሸንፈው ኢትዮጵያ የምትባል አገር አቆዩን :: በመደመር ያላመኑትና ይህንን እድል ያላገኙት ብዙ የአፍሪካ አገሮች ቅኝ ገዢዎች በሰጧቸው ድንበር ውስጥ ተከፋፍለው ለአገራቸውም ስም ሰጥተው በዚያ ስም ብሔራዊ ስሜት ለመገንባት የሞከሩት ባለፉት ሰባ ዓመታት ውስጥ ነው:: ኢትዮጵያ ግን ኢትዮጵያ ተብላ የኖረችው ከሁለት ሺህ አመታት በላይ ነው:: እንደ ዘመኑ ኢትዮጵያዊነት የተለየ ትርጉም የተለየ አስተዳደር ይኑረው እንጂ ኢትዮጵያዊነት የኖረ የነበረ  ስሜትና ዜግነት ነው ::ይህም የሆነው በመደመራችን ነው :: ዛሬ አዲሱ ትውልድ በተለያዩ ርዕዮተ ዓለሞች ተደናግሮ ጥቂቶች ባራመዱት የግራ አስተሳሰብ አገርና ብሔርን ለያይቶ በመመልከት ሕዝብን ለመከፋፈል ሲሞከር በመደመር ፋንታ ተቀነስን ::

በእኔ የውትድርና ዘመን የምናውቀው መደመር ብቻ ነበር :: ቁዋንቃ ባህል ሀይማኖት ሳይከፋፍለን እንደ ሰው ባህርይ ጉድለቶች ብናሳይም በአገር ጉዳይ ላይ ግን ሁል ጊዜ እንደተደመርን ነበር ::

የኤርትራ መገንጠል እንቅስቃሴ ሲወለድ መቀነስ ጀመርን :: በመቀነሳችን ምክንያት ብዙ ሕዝብ አለቀ። ሰላም አጣን። ኢትዮጵያ አካሏ ጎደለ:: መደመርን አውግዘው መቀነስን ለመረጡ ለነሱም አልበጀም። የመደመርን አስተሳሰብ በጥሞናና በሰላም ያላራመደ ህዝብ ወደጦርነት ይሄዳል:: የሚደመረው በሀይል ሳይሆን በፍቅር በውይይት በመቻቻል መሆኑን መረዳት የተሳነው የደርግ መንግሥት ኢትዮጵያ እንድትቀነስ ሁኔታውን አመቻቸ:: በመደመር የማያምነው እንደውም መቀነስን ዓላማው አድርጎ የመጣው የወያኔ መንግስት አገርን ከማስገንጠል አልፎ ሌላው ኢትዮጵያ ከድምር በታች ሆኖ ተከፋፍሎ እንዲኖር የአገዛዙ ፖሊሲ አደረገ :: ኢትዮጵያ በደቡባዊ እፍሪካ ሀገሮች  የቅኝ አገዛዝ አስተዳር  ያወጀው ( Bantustanization ) ባንቱስታናይዜሽን በውኃላም በደቡብ አፍሪካ የተተገበረው የአፓርታይድ  ፖሊሲ ዓይነት ኢትዮጵያ ታወጀባት:: ሕዝብ ተከለለ ::  ወያኔ እራሱን ከሌላው ኢትዮጵያ ቀነሰ:: መደመር ለአገዛዙ አደገኛ ስለሆነ ጥቂቶች እንዲገዙ ሌሎች ደግሞ ተከፋፍለው ተገዥ እንዲሆኑ 27 ዓመት የመቀነስ ፖሊሲ ሲያራምድ ኖረ :: ለመግዛት እንዲያመች የአገራችን ታሪክ ጎደፈ፣ተጣመመ ፣ አዲስ ታሪክ ተፈጠረ። ብዙ ሕዝብ ተሰቃየ፣ታሠረ፣  ተገደለ፣ ተለያየ። አገሩን ለቆ በምድረ ሰሀራ ፣በሜዲቴራኔያን ባህር፣ በቀይ ባህር ፣በየመን፣በአረብ አገሮች ምድረ በዳ እና  በሲናይ በረሀ አለቀ።  ታረደ፣ሰውነቱ እየተቀደደ  ኩላሊት መነገጃ ሆነ ::

መደመር ሲዋረድ መቀነስ ሲነግስ ማንንም አልጠቀመም ። ጥቂቶች የተጠቀሙ መስሏቸው ነበር:: መደመር ሲያሸንፍ ኢትዮጵያዊነት አሸነፈ :: በጠ/ሚ አብይ አማካኝነት የመደመር ታሪካችን እየታደሰ ነው :: ስንደመር የአድዋ ነብር፣  የመቅደላ አምበሳ ሆነን ዳር ድንበራችንንና አንድነታችንን ጠብቀን እንኖራለን:: ስንደመር እንፋቀራል። ስንደመር ያለንን እንካፈላለን፡፡ ስንደመር እንከባበራለን።  ስንደመር የቋንቋ፣ የሀይማኖት፣  የባህል ልዩነቶች የጥንካሬና የአንድነት ምንጮች እንጂ አይቀንሱንም :: ስለዚህ የጠ/ሚ አብይን መልዕክት በተግባር ለማዋል ለአመራሩም ድጋፍ ለመስጠት  መነጋገር  መወያየት እንጀምር :: መደመር ሀይል ነው ::  ሰሞኑን የሚወጣው ሕዝባዊ ሰልፍ የመደመር ተሀድሶ፣ የአንድነት ሀይል አሸናፊ መሆኑን የሚያበስር ታላቅ ሰልፍና መልዕክት ይሁን :: ስንደመር በማንም በምንም አንሸንፍም :: ሊቀንሱን ፣ ሊያደክሙን፣ ሊበታትኑን፣ሊያፋጁን የሚሞክሩ ሁሉ የታሪክ አተላዎች ሆነው ይቀራሉ :: መደመር ያሸንፋል ::

Hiber radio Las Vegas ይህ ህብር ሬድዮ _የወቅታዊ መረጃ ምንጭ ነው። ህብር ሬድዮ በአቤኔዘር ኮሙኒኬሽን ሴንተር እየተዘጋጀ  ከላስ ቬጋስ ከተማ፣ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 630 ሰዓት እስከሰዓት በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ  5639993994 ወይም 563999-3988 1641-793-8229 ወይም 1641-715-8596  በመረጡት ቁጥር መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ 01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *