Hiber Radio: የአገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጥሪ ከቅዳሜው ሰልፍ በፊት -ንቅናቄ በጥንቃቄ-ለሰልፉ አስተባባሪዎች-ለሰልፈኞች እና አገራችሁን ለምትወዱ ዜጎችና የሰራዊቱ አባላት በሙሉ

የአገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጥሪ ከቅዳሜው ሰልፍ በፊት -ንቅናቄ በጥንቃቄ-ለሰልፉ አስተባባሪዎች-ለሰልፈኞች እና አገራችሁን ለምትወዱ ዜጎችና የሰራዊቱ አባላት በሙሉ

የቅዳሜው ሰልፍ መነሻ ባለፉት ጥቂት ወራት ዶ/ር አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በሁዋላ የታዩ ለውጦች አደጋ ላይ መውደቃቸው ዜጎችን ስላስደነገጠ የተጠራ የድጋፍ ሰልፍ ነው።በኢህአዴግ ውስጥ ሕግና ሕገ መንግስቱን መሰረት አድርጎ ለውጡን ማስቀጠል የሚፈልገው በዶ/ር አብይ የሚመራው ሀይልና  ሕግን ለራሱ ጥቅም ካልሆነ ለይስሙላ ቢያወራም ሕግ ማክበር የማይፈልገው የሕወሓት አመራር ጋር ፍጥጫ ውስጥ ገብተዋል። ሕወሓት አስቀድሞ ባወጣው የስራ አስፈጻሚው መግለጫ ዶ/ር አብይ የጀመሩትን የለውጥ ሒደት ለማደናቀፍ ማሰቡ ዜጎችን አስቆጥቷል።የጠ/ሚ/ሩ በፓርላማ ተገኝተው ለአባላቱ ባደረጉት ማብራሪያ አስከትሎ እየወሰዷቸው ያሉ እርምጃዎች መጪው ጊዜ ብሩህ ከኤርትራ ጋር የቆየው ሰላም የሌለበት ግንኙነት ትልቅ ተስፋ አጭሯል።ይሄ 27 ዓመት አገሪቱን ሲዘርፍ ዜጎችን ሲያሸብር ለቆየው ሕወሓት አልተመቸውም።በዚህም ሳቢያ የቅዳሜውን ሰልፍ ዶ/ር አብይ የጀመሩት ጥረት እንዳይቀለበስ ድጋፍ ሰልፍ መሆኑን እያወቀ ጸረ ትግራይ ነው የሚል ቅስቀሳ ላይ ተጠምዷል።የትግራይ ሕዝብን ለተቃውሞ ሰልፍ ጠርቷል።የትግራይ ልሂቃንና የተለያዩ ተቃዋሚዎች በአደባባይ ይህን ፈጥነው በማውገዝ የሕወሓትን የስልጣን ጥም የወለደውን ሀሰተኛ ቅስቀሳ መቃወም አለባቸው።

ለቅዳሜው ሰልፍ አስተባባሪዎች ጥሪ

የሰልፉ ዋና ዋና አስተባባሪዎች ሕወሃት በበላይነት 27 ዓመት ሲመራው በነበረው ስርዓት በየደረጃው ግፍ የተፈጸመባቸው ዜጎች ናቸው።እነዚህ ግፍ የተፈጸመባቸው ዜጎች  አብነት የሚሆኑ አላግባብ ሀሳባቸውን በነጻ በመግለጻቸው እና ሕገ መንግስቱ የሰጠውን መብት ተግባራዊ ለማድረግ በመንቀሳቀሳቸው ታስረው ፍዳቸውን ያዩ ዜጎች መሆናቸው ግልጽ ነው። የሰልፉ አስተባባሪዎች ዛሬ የተጀመረው የጠ/ሚ/ር ዶ/ር አብይ የሚመሩት የሰላም ጥረትና ኢትዮጵያን ከገባችበት ማጥ ለማውጣት የሚደረግ እንቃስቃሴ እንዳይቀለበስ እና ጉዞው እንዳይገታ ለመጠየቅ እና ለእስካሁኑ ጥሩ ጅምር ለማመስገን ነው።ዜጎች ብሄር ሳይለዩ በጥሪው ተደስተው በየራሳቸው የተለያዩ ፈጠራቸውን ተጠቅመው ሰለፉን ለማድመቅ እየተንቀሳቀሱ ነው። ከሰልፉ አስተባባሪዎች ኣላማ ውጭ ሰልፉን ለኢህአዴግ የተጠራ የድጋፍ ሰልፍ አድርጎ ለማሳየት ከተደረገው የፈቃድ ምላሽ  ጀምሮ እስከ ጸረ የትግራይ ሕዝብ ሰልፍ አድርጎ ለማሳየት የሚደረገውን የሕወሓት ጥረት በአግባቡ መረዳትና ከፍተኛ የጥንቃቄ እርምጃ መውሰድ ይገባል።ለትንኮሳ ሊወሰዱ የሚችሉ የህወሃት ሴራዎችን አስቀድሞ መገመት ይቻላል። እነዚህም

  1. ሰልፈኛው ውስጥ ሆን ብሎ አስርጎ ጸረ ትግራይ የሆኑ ቅስቀሳ አድራጊዎችን በማስገባት መፈክር በማሲያዝ እና እነዚሁ ሰዎች የዶ/ር አብይ ምስል አለበት ካናቴራ በማልበስ ሊያንቀሳቅሱ ይችላሉ። በዚህ ሳቢያ በሰልፈኛው ውስጥ ግጭት ሊቀሰቅሱና ሁኔታውን አስቸጋሪ ለማድረግ ይሞክሩ ይሆናል።

2.አስቀድሞ በሰልፉ ላይ የህወሓትን የሰሞኑ ቅስቀሳ የሚያጠናክሩ ተልዕኮ የተሰጣቸውን ያሰማሯቸው ቪዲዮ ቀራጮች እና የሕወሃት ተልዕኮ የተሰጣቸው <<ጋዜጠኞች>.> እና ብሎገሮች ይሄንኑ በከፍተኛ ደረጃ በማራገብ ብዙሃኑ የተሰለፈበትን ዓላማ ለማጠልሸትና ህወሓት ለጀመረው ጸረ በዶ/ር አብይ ቅስቀሳ ማጠናከሪያ ለማግኘትና አስከትሎ በአገሪቱ የተጀመረውን መልካም ሒደት ለመቀልበስ ወደ ግልጽ ጦርነት ሊገቡ ይችላሉ።

3.ሰልፈኛውን የሚያስቆጡ የተለያዩ መፈክሮች ፖስተርና ሌላምድርጊት ሊፈጸምና አስቀድሞ ተልእኮ የወሰዱ ይህን በሽፋን ተጠቅመው ሰልፉን ሊያውኩ ይሞክሩ ይሆናል።

የሰልፉ አስተባባሪዎች ይህንና ሌሎች የጥፋት ጥሪዎችን ለመከላከል ቢቻል መግለጫ ሰጥቶ በግልጽ የትግራይ ሕዝብን ማረጋጋትና የሕወሃት ቅስቀሳ ሀሰተኛ መሆኑን መግለጽ። ጊዜው አጭር በመሆኑ ካልተቻለ በየትኛውም መድረክ በሰልፉ ላይ ችምር ይህንኑ አስረግጦ መግለጽ። ይህን በአገሪቱ የተጀመረውን የዶ/ር አብይ ጥረት ለማደናቀፍ መሞከር በሕዝብ ላይ ተጨማሪ መከራ ለመጫን መሞከር መሆኑን ገልጾ ማውገዝ።ሕዝቡ ለለውጡ ተስፋ ያለውን ድጋፍ ጠንካራ መሆኑን በዕለቱ በተግባር እንዲያሳይ የህዝቡን አጋርነት የሚገልጹ መፈክሮችን መርጦ ማደራጀት።ተናጋሪዎችን፣ለመገናኛ ብዙሀን መግለቻ ሰጪዎችን ሆነ ከጸጥታ አካላት ጋር የሚነጋገሩትን ለይቶ መመደብና ግርግር ማስወገድ።ሰርገው የሚገቡ ተልዕኮ የተሰጣቸው በሕወሓት የታዘዙ አባላቱ መድረኩን እንዳይቆጣጠሩት መጠንቀቅ።

አገራችሁን ለምትወዱ የጸጥታ ሰዎች

አገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት 27 ዓመታት በሕወሓት የበላይነት በዜጎቿ ላይ ሲፈጸም የነበረው የሽብር ድርጊት እንዲያበቃ ተስፋ የሰነቀችበት ታሪካዊ ወቅት ላይ እንገኛለን። ሕወሃት የአገሪቱን ሕገ መንግስት ጥሶ ከኢህአዴግ ደንብና መመሪያ ውጭ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።በጉልበት አገሪቱን በሁሉም አቅጣጫ ዜጎችን በዘርና በጎሳ እያጋጨ ትርምስ ውስጥ ለመክተት የጥቅም ተጋሪዎቹን ይዞ በመራወጥ ላይ ነው። በመቀሌ የጠራው በዶ/ር አብይ ላይ የተቃውሞ ሰልፍ ለዚህ አብይ ማሳያ ይሆናል።ማንኛውም መሳሪያ ያነገበ ሀይል በቅድሚያ  የሕወሓትን የሁከት ጥሪ ወደ ጎን አድርጎ ለሕዝቡና ለአገሩ ታማኝ መሆን አለበት።በጸጥታ ክፍሉ ሆነ በመከላከያ ሰራዊቱ ሕወሃት የአመራሩን ቦታ የተቆጣጠሩ አባላቱን ተማምኖ እያደረገው ያለውን እንቅስቃሴ መገንዘብ ይገባል። የዚህ የህወሓት እንቅስቃሴ ዓላማ ባለፉት 27 ዓመታት እንዳደረገው ዜጎችን እየገደለ እያሰረ የአገር ሀብትና ንብረት እንደልቡ እየዘረፈ በትግራይ ሕዝብ ስም እየነገደ መቀጠል ነው። በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ ጥረት ማደናቀፍ ነው።ለዚህም የተለያዩ በዘር ላይ የተመሰረቱ ግጭቶችን ከግብረ አበሮቹ ጋር ሆኖ በደቡብ፣በኦሮሚያ፣በሀረሪ፣በቤንሻንጉል አስቀድሞ የነበረውን መዋቅርና ተሰሚነት ታሳቢ አድርጎ በዜጎች ሕይወት ላይ እየተጫወተ ይገኛል።በዚህ ሳቢያ አሰቃቂ ጭፍጨፋ መፈናቀል ሞትና አካል መጉደል እየደረሰ ዜጎችን በገዛ አገራቸው እያሸበረ ይገኛል። ስለዚህም የዚህ ድርጊት አካል እንዳትሆኑ በየትኛውም ደረጃ ዶ/ር አብይ የጀመሩትን ጥረት ለመደገፍና ይሄው እንዳይቀለበስ ለመጠየቅ የተጠራው ሰልፍ ሰላማዊ እንዲሆን የበኩላችሁን አስተዋጽዎ እንድታደርጉ።ይህን ለማደፍረስ በሕዝብ ላይ ብጥብጥ ለመፍጠር የሚሞክሩ የሕወሓት አባላት መሳሪያ አንጋቾች ሆኑ አመራሮችን ተባባሪ እንዳትሆኑ ያስፈልጋል።ይህ ሰልፍ የኢትዮጵያ ሰላም እንዲረጋገጥ የተጀመረው ሰላማዊ ዲሞክራሲያዊ የለውጥ ተስፋ እውን እንዲሆንና ሁሉም ዜጎች የአገራቸው እኩል ባለቤት የሚሆኑበት ስርዓት ለማምጣት ነው።ስለዚህም የአገራችሁ እንጂ የፓርቲ ተቀጣሪ አለመሆናችሁን ተገንዝባችሁ የከዚህ በፊቱን የ27 ዓመት ድርጊት እንዳትደግሙ ትጠየቃላችሁ።ግዴታችሁ አገርና ሕዝብን መጠበቅ ነው እንጂ የአንድ የሕወሓት ፓርቲ አገልጋይነት አይደለም።

ጥሪ በአገር ውስጥ በሰልፉ ላይ ተሳታፊ ለምትሆኑ ሁሉ

ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን

ቅዳሚው የመስቀል አደባባይ ሰልፍ ዋና ዓላማ የተጀመረውን የዶ/ር አብይና አጋሮቻቸው የለውጥ ተስፋ ለማበረታታትና እንዳይቀለበስ ለመጠየቅ እንጂ ቁጭትና የቁርሾ አይደለም። ባለፉት 27 ዓመታት የታፈነ፣የተረገጠ ፣የተዋረደ፣የታመቀ ቁጭትና እልህ በገዢዎቹ ላይ ያለው ሕዝብ በዚህ መሰሉ የሰላም መድረክ ብልህ ሆኖ ሀላፊነቱን መወታት አለበት።ይህ የሕዝብ ሰልፍ ነው።አስተባባሪዎም ተሳታፊዎም ሕዝቡ ራሱ ነው።ሰልፉ የነገዋን አገርና የዶ/ር አብይን ብዙሃኑ ሕዝብ የደገፈውን የመደመር ዓላማ በፍቅር ለማሳካት በመሆኑ እያንዳንዱ ሰልፈኛ ሀላፊነት አለበት።በሰልፉ ላይ በዘር ላይ ያነጣጠረ ቅስቀሳ ለማድረግ ሰርገው ለገቡት ተባባሪ አለመሆን ፣የሰልፉን ዋነኛ ዓላማ ማክበር፣ሰልፉን የኢህአዴግ የድጋፍ ሰልፍ አስመስለው መፈክር ይዘው ሌላው ቀርቶ የመለስን ፎቶ ለብሰው ለትንኮሳ የሚመጡ ቢኖሩ እንኳን ተልኮ ያነገቡ በጥባጮች ቢሆኑም ዲሚክራሲያዊ መብታቸው ነውና በትዕግስት አልፎ ማጋለጥ።ሰልፉ ሚያዚያ 30/1997 በመስቀል አደባባይ እንደተደረገው ሌላው ቀርቶ ለትንኮሳ መብራት ሲያጠፉ እንኳ በትዕግስት ሚሊዮኖች አደባባይ ወጥተው በሰላም ኮሸ ሳይል አንድም ሞባይል ሳይጠፋ እንዳጠናቀቁት ቅዳሜም ሚሊዮኖች በሰላም ወጥተው በሰላም ሀሳባቸውን ገልጸው በተሳካ ሁኔታ እንዲገቡ እያንዳንዱ ሰልፈኛ ሀላፊነቱን ይወጣ።በፍቅር ይደመር።

የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች

በሰልፉ የሚገኙ የአገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በርካታ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።በአገሪቱ ባለፉት 27 ዓመታት በአንድ የህወሓት የበላይነት ቁጥጥር ስር የነበረ ስርዓት መገናኛ ብዙሃን ዛሬም ከዚያ ወጥቷል ለማለት አያስደፍርም።ሕወሓት ባለው መዋቅር ሰልፉን ለማጠልሸት አስቀድሞ በመገናና ብዙሃኑ ያሉትን ሰዎች ሊጠቀም ይችላል።በምርጫ 97 በታሪካዊው ሚያዚያ 30 በመስቀል አደባባይ ሚሊዮኖች ቅንጅት እያሉ ስለ ሰላምና ዲሞክራሲ የዘመሩበትን ሰልፍ አንድ አላሙዲን የተቃወመ ህጻን ብቻ አብይ እርእስ አድርጎ ለማሳየት የተሞከረበት አሳፋሪዎ የኢቲቪ ታሪክ አይረሳም። ዛሬም አስቀድሞ በግል ስም ፈቃዱ በታማኝነታቸው የተሰጣቸውን እነ ስብሃት ነጋ ኢ.ኤን.ኤን ፣የእነ ሚሚ ስብሃቱ ዛሚን ጨምሮ በመንግስትና በፓርቲ መገናኛ ብዙሃን የሚሰሩ አንዳንዶች የተለመደ ተልእኮ ሊኖራቸው እንደሚችል መገመት ይቻላል።ስለዚህ አብዛኛው ባለሙያ እውነቱን በመዘገብ የህወሓትን ሴራ ማክሸፍ ይቻላል።

አስቀድሞ ከተዘረዘሩት ይሆናሎች ውጭ ሌሎችም ሴራዎች ሎኖሩ ይችላሉ። ሰልፉ በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲያልቅ ሁሉም አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የበኩሉን አስተዋጽዎ በማድረግ ሰልፉን የጠሩት ዜጎች ህልም በሰላም የተሳካ እንዲሆን ከጎናቸው ልንቆም ይገባል። ይህን ሰልፍ ባለፉት ጥቂት ወራት ዶ/ር አብይ ጀመሩትን ጥረት አብራዋቸው ለውጡን ተግባራዊ ለሚያደርጉ በርቱ ከማለት ጎን ለጎን የተደቀነባቸውም አደጋ የማይታያቸው ዜጎች ሊኖሩ ይችላሉ። አንዳንዶቹ የመንግስት ተቀላቢ ተቃዋሚዎች ብቻ ሳይሆኑ የእውነተኞቹም ሊሆኑ ይችላሉ። መቃወም መብት በመሆኑ ሰልፉን ዲሞክራሲአዊ በሆነ መንገድ በያሉበት ማህበራዊ ሚዲያ ገጽ ሆነ በሌላ መቃወም መብታቸውን በማክበር ከአላስፈላጊ የጎንዮሽ ልፊያ መውጣት ያስፈልጋል።ትኩት ዶ/ር አብይና በውስጥና በውጭ ያሉ የለውጥ አጋሮቻቸው የጀመሩት አገራዊ የሰላምና የለውጥ ሒደት የተሳካ እንዲሆን ማገዝና ማበረታታት ብሎም መደመር ላይ ብቻ ይሁን።

የሰልፉ ደጋፊዎች አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን

Hiber radio Las Vegas ይህ ህብር ሬድዮ _የወቅታዊ መረጃ ምንጭ ነው። ህብር ሬድዮ በአቤኔዘር ኮሙኒኬሽን ሴንተር እየተዘጋጀ  ከላስ ቬጋስ ከተማ፣ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 630 ሰዓት እስከሰዓት በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ  5639993994 ወይም 563999-3988 1641-793-8229 ወይም 1641-715-8596  በመረጡት ቁጥር መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ 01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *