Hiber Radio:መደመር መጨፍለቅን አይጨምርም!

የዶ/ር አብይን ለፍቅር፣ ለሰላም፣ ለዲሞክራሲ፣ ለፍትህ እና ለልማት ያደረጉትን የመደመር ጥሪ ከደጋፊ አንስቶ እስከ ተቃዋሚ፣ ከምሁር አንስቶ እስከ ተማሪ፣ በአራቱም ማዕዘናት ያሉ ኢትዮጵያዊያን እና ከአገር ውጭ በመላው አለም የሚገኙ ወገኖች ድጋፋቸው ሰጥጠዋል። ብዙዎቻችን ተደምረናል። እንዲህ ያለ አገራዊ መግባባት እና የአንድነት መንፈስ በአጨር ጊዜ ማምጣት እንኳን በጎሳ ፖለቲካ ስትናጥ በኖረች አገር አይደለም ዲሞክራሲ በሰፈነበትና የተረጋጋ በሚባለ ማህበረሰብም ውስጥ የሚታሰብ አይደለም።

ይህ እውነታ ሁለት ነገሮችን ያሳያል። አንደኛው የፍቅር ጥሪ አድራጊው አካል ቀናነት እና የሕዝብን ልብና ቀልብ የመግዛት ቻሎታን በደንብ ያሳያል። ብዙዎች በጉልበት፣ በዛቻ፣ በጉርሻና በጸሎት ያላገኙትን ተቀባይነት እና አክብሮት ማግኘት ቀላል ነገር አይደለም። ሁለተኛው ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ያህል ጨዋ እንደሆነ፣ አስተሳስረው እና አዋህደው ለዘመናት ያቆዩት የፍቅር ገመዶች እንዲህ በቀላሉ ተበጣጥሰው የማይጠፉ እና ጊዜ እና ሁኔታ ሲያገኙ እንደሚጠባቁ እና የተበጣጠሱትም ሰንሰለቶች እየተቋጠሩ ፍቅርን ሲሰጡት በመቶ አባዝቶ ፍቅርን መመለስ የሚችል ሕዝብ መሆኑን ነው። የሰኔ 16ቱ የአደባባይ የድጋፍ ሰልፍ የዚሁ ስሜት መገለጫ ነው። ዶ/ር አብይ ወደፊት ሊያደርጉ ያሰቡትን ተናገሩ እንጂ ገና ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ እንኳ አልገቡም። የሕዝቡ የፍቅር ምላሽ ግን ልክ ጥያቄዎቹ ሁሉ ተመልሶለት በደስታ የሰከረ ሰው አይነት ነበር። እንዲህ ያለ ፍቅር ማግኘት ለሳቸው እዳም፣ ብርታትም ነው።

እንዲህ እየተደመርን ባለንበት ወቅት አንዳንድ የአይን ቁስል፣ የህሊና ጠባሳ እና አሳፋሪ የሆኑ ድርጊቶች እዚም እዛም ማየታችን አልቀረም። የእናት ሆድ ዥንጉርጉር እንዲሉ ይች አገር የመቶ ሚሊዮኖች ነች። ልደምርህ ሲሉት ልቀነስ የሚል፣ ላፍቅርህ ሲሉት ጥላቻን የሚመርጥ፣ ሰላም ሲሉት ለጸብ የሚዳዳው፣ አንድነት ሲሉት ጎጠኝነት የሚያምረው አይጠፋም። ይች አገር የእነሱም ስለሆነች ሁሉንም ደምራ መሄዷ ግን ግድ ይላል። በዚህ ታላቅ የፍቅር ቀን ያንን የመሰለ እኩይ ተግባር የፈጸሙት ወገኖችም ልጇቿ ናቸው። እንዚህ ሰዎች ለፍርድ ቀርበው የእጃቸውን ማግኘታቸው ባይቀርም ያው የዚህ አገር እዳዎች ናቸው። አንድ ዜጋ ምንም አይነት ወንጀል ቢሰራ እና ሴጣናዊ ተግባር ቢፈጽምም ይቀጣል እንጂ የትም አይጣልም። እስር ቤትም ሆኖ ያው የሕዝብ እዳ ነው። ቀለቡ የሚሰፈርለት ከግብር ከፋዩና በዚያ ሰው የወንጀል አድራጎት ከተጎዳው ሰው ተወስዶ ነው።

የመደመርን ነገር ሲነሳ ሰሞኑን ሁለት ነገሮችን ታዘብኩ። አንደኛው ግርግር ለሌባ ይመቻል እንደሚባለው ዶ/ር አብይ ስለ ቀን ጅቦች የተናገሩትን ነገር ከመሰረታዊ ሃሳቡ አርቆ በመተርጎም አንዳንድ ግለሰቦች በማህበራዊ ሚዲያዎች ሳይቀር የዘር ጥላቻ ማራገቢያ ሲያደርጉት አስተውያለሁ። ይህ እጅግ አሳፋሪ እና በሕግም የሚያስጠይቅ የነውር ተግባር ነው። አንዳንዶች ሳይገባቸውም ሊሆን ይችላል ይህን አባባል ለህውሃት አመራሮች እና አባላት በጠቅላላ በመስጠት ሃሳቡን ሲያራግቡት ይስተዋላል። ሌሎች ደግሞ ሆነ ብለው የጎሳ ጥላቻን ለማራጋቢያ እና ለእኩይ የፖለቲካ ተልዕኳቸው ሲጠቀሙበት ይስተዋላል። ይህ አይነቱ አስተሳሰብ ወደ መደመር ሊያመጣን አይችልም። በውስጡ ጨፍላቂነት አለው። አንድን የህብረተሰብ ክፍል እየጨፈለቁና ጅብ እያሉ መደመር ሊመጣ አይችልም። ዶ/ር አብይ የጠቀሷቸው የቀን ጅቦች በሁሉም የህብረተሰብ ክፍል፣ በሁሉም ኃይማኖት፣ በሁሉም ጎሳ፣ በሁሉም ክልል ውስጥ አሉ። ስያሜዊ ለመጥፎ ድርጊት እንዲ ለማንነት አይደለም። ሌላው ቀርቶ በድጋፍ ያልተሳተፉ ሰዎችን በዚህ መልኩ ለመግለጽም የዳዳቸው ሰዎች አይቻለሁ። መዘንጋት የሌለብት ዶ/ር አብይን አለመደገፍም ሆነ መቃወም መብት መሆኑን እና የመደመሩ ሂሳብ እነሱንም የሚያካትት መሆኑን ነው። ዋናው ተቃውሟቸውን በሕግ አግባብ እና የሌሎችን ሰዎች መብት በማይነካ መልኩ ይሁን እንጂ። አብይን የተቃወመ ሁሉ የቀን ጅብ ከተባለ ዲሞክራሲ ገና በጊዜ በአፍጢሟ ተደፋች ማለት ነው።

ሌላው የመደመር ፖለቲካ በጥንቃቄ ካልተያዘ እና በሕግ፣ በሞራል እና በዴሞክራሲያዊ እሴቶች ያልታነጸ ከሆነ ወደ ጨፍላቂነት ይቀየራል። እኔ የወደድኩትን ካልወደድክ፣ እኔ ያለምኩትን እና የቃዠሁትን ካላለምክ እና ካልቃዠህ፣ እኔ የዘመርኩትን ካለዘመርክ ማለትና ከቅጥ በላይ በራስ መታበይ ይመጣል። ያ ደግሞ እጅግ አደገኛ የሆነ ባህሪን ይፈጥራል። በፍቅር እና በመደመር ካባ የተሸፈነ አንባገነናዊነት ይሆናል። እንዲህ ያለው አዝማሚያ ከወዲሁ ሃይ ሊባል የገባዋል። ከቦንብ ፍንዳታ ተጠርጣሪዎች አንስቶ ሰሞኑን በተለያዩ ሥፍራዎች በተመሳሳይ የጥቃት መሰናዶ ተጠርጥረው እየተያዙ ያሉ ሰዎች የአያያዛቸው ነገር አልፎ አፍሎ በማህበራዊ ሚዲያዎች እንደሚታየው ከሆነ ከሕግ እና ከሰብአዊ መርሆዎች የራቀ ነው። ይች ባቄላ ካደረች አጉል ነው፤ እሷን የሚቆረጥም ጥርስ ፍለጋ ልንሄድ ነው ደግሞ። ዛሬ በወንጀል ተጠርጣሪዎች የተጀመረው የመብት እረገጣ ነገ ወደ ሰላማዊው ሰው ላለመዞሩ ዋስትና የለንም። ዋስትና የሚሆነው ከወዲሁ ሁሉም ሰው ለሕግ እና ለሞራል ተገዢ ሲሆን ነው። በዋሽንግተን አንዳንድ ግለሰቦች በዶ/ር ፍሰሐ ላይ የፈጸሙትም ተግባር እጅግ አግባብ ያልሆነ እና ከመደመር መርህ ውጪ ነው።

እንደ እኔ መደመር ማለት ሁላችንም በአንድ አመለካከት እና በአንድ ገዢ አሳብ ተጨፍልቀን አንድ መሆን አይደለም። ድምር የብዙ ልዩነቶች ውጤት ነው። ስንደመር ከነ ልዩነታችን ነው። የመቶ ሚሊዮን አገር በድምሯ ውስጥ መቶ ሚሊዮን ልዩነቶችን ታቅፋለች። የመደመር ውበቱም ሆነ ቁልፍ ሚስጥሩ ልዩነቶችን ማቀፉ ነው። ያለ ልዩነት ድምር አይታሰብም። ጭፍለቃ ግን ልዩነትን ያጠፋል፤ በመደመርም ፋንታ መዋዋጥን ያመጣል። ሁሉንም ሰልቅጦ መዋጥ የቻለው ኃይል ገዢ ይሆናል። ይህ ደግሞ የኖርንበት፣ የቆረብንበት ፖለቲካችን ነው። አዲሱ ፖለቲካ መዋጥን ሳይሆን መደመርን፣ መጨፍለቅን ሳይሆን መተባበርን ነው የሚሻው። ሁሉም ነገር እየተስተዋለ ቢሆን ጥሩ ነው።

በቸር እንሰንብት

Hiber radio Las Vegas ይህ ህብር ሬድዮ _የወቅታዊ መረጃ ምንጭ ነው። ህብር ሬድዮ በአቤኔዘር ኮሙኒኬሽን ሴንተር እየተዘጋጀ  ከላስ ቬጋስ ከተማ፣ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 630 ሰዓት እስከሰዓት በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ  5639993994 ወይም 563999-3988 1641-793-8229 ወይም 1641-715-8596  በመረጡት ቁጥር መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ 01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *