Hiber Radio:ታዋቂዎቹን አርቲስቶች ጨምሮ የመብት ተሟጋቾችና ጋዜጠኞች ወደ አገር ሊገቡ መሆኑ ተገለጸ፣ደማቅ አቀባበል ይጠብቃቸዋል

በኢትዮጵያ በጠ/ሚ/ር አብይ አህመድ የተወሰዱ የለውጥ እርምጃዎችን መሰረት በማድረግ በረጅም እና ለአጭር ጊዜ በስደት ላይ የነበሩ ታዋቂዎቹን አርቲስቶች ዓለምጸሐይ ወዳጆ፣አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ፣ጋዜጠኛና አክቲቪስት የአዲስ ድምጽ ራዲዮ መስራችና ባለቤት አበበ በለው፣የሶማሌ ክልል የቀድሞ ፓርላማ ተወካይና የመብት ተሟጋች ጀማል ድርዬ፣ጋዜጠኛና አክቲቪስት ሙሉቀን ተስፋውና ለሶማሌ ሕዝብ መብት በመሟገት የአንዲ ኢሌን ውጀል በፊልም ጭምር በማጋለት የሚታወቀው አክቲቪስት አብዱላሂ ሐሰን ወደ አገር በቅርብ እንደሚገቡ ለማወቅ ተችሏል።

በነገው ዕለት ወደ አገር ቀድመው የሚገቡት ሁለቱ የሶማሌ ሕዝብ መብት ተሟጋቾች አቶ ጀማል ድርዬና አክቲቪስት አብዱላሂ ሐሰን መሆናቸውን ለህብር የደረሰን መረጃ ይጠቅሳል። ሁለቱ አክቲቪስቶች በወቅቱ በሶማሌ ክልል የተፈጠረውን የለውጥ ተስፋ በለጠ ሕዝባዊና ሕጋዊ መሰረት እንዲይዝ የበኩላቸውን ለማድረግና ከሕዝባቸው ጋር ለመነጋገር በነገው ዕለት አዲስ አበባ በጋርሚገቡ ሲሆን የመንግስት ተወካዮች ጭምር ከሌሎች የሶማሌ ሕዝብ በአገር ቤት የመብት ተሟጋቾች ጋር  አቀባበል ያደርጉላቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

እውቁዋ ዘርፈ ብዙ የጥበብ ሰው ዓለምጸሐይ ወዳጆ እና አክቲቪስትና ጋዜጠኛው አበበ በለው በመጪው ማክሰኞ አዲስ አበባ የሚገቡ ሲሆን ደማቅ አቀባበል ይጠብቃቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።ዓለምጸሐይ ወዳጆን ለመቀበል ከቦሌ እስከ ብሔራዊ ቴአትር የተዘጋጀ የአቀባበል ስነ ስርዓት እየተሰናዳ ሲሆን በመድረክ ከሕዝቡ ጋር ትገናኛለች ተብሎ ይጠበቃል።ለዓለም ጸሐይወዳጆ ተጨማሪ መድረኮችም ይዘጋጃሉ ተብሎ ተገልጿል።

አክቲቪስትና ጋዜጠኛ አበበ በለው በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የወያኔን የግፍ አገዛዝ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵአ ሕዝብ ለውጥ አመጣለሁ ያሉ ተቃዋሚዎች ጭምር መተቸት አለባቸው በሚል በጀመረው ጥረት ብዙ ውግዘትና የጅምላ ፍረጃ ደርሶበታል።ከተነሳበት የሕዝቡን የለውጥ ተስፋ ከመደገፍ ሳያፈገፍግ በአዲስ ድምጽ ሲታገል ቆጥቷል።

ታዋቂው አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ ባለፈው ዋሽንግተን ዲሲ በኮንቬሽን ሴንተር ተገኝቶ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሰጠው የአክብሮት ዝቅታ ድጋፍም ውዝግብም ቢያስነሳበትም ባለፉት 27 ዓመታት የሕወሓት የበላይነት የነገሰበትን አገዛዝ አሜሪካ ከመጣ ጀምሮ ጠንክሮ ሲታገል በመቆየቱ በአገር ውስጥባ በውጭ ሰፊ ድጋፍ እንዳለው ይታወቃል።የአማራ ክልል ቃል አቀባይ ታማኝና አክቲቪስትና ጋዜጠኛ ሙሉቀን ተስፋው እንደ ዓለምጸሐይ ወዳጆና አበበ በለው ሁሉ ወደ አገር እንደሚገቡና በአማራና በተለያዩ አካባቢዎች ደማቅ አቀባበል እንደሚጠብቃቸው ገልጸዋል።

ጋዜጠኛ ሙሉቀን ተስፋው በአማራ ላይ በስርዓቱ የተፈጸሙ ግፎችን በማጋለጥ እንደ ብዙ አክቲቪስቶች በማህበራዊ ሚዲያው ንቁ ተሳትፎ ከማድረግ አልፎ የጥፋት ዘመን በሚለው መጽሐፉ በአማራ ሕዝብ ላይ የተፈጸመውን ግፍ በማስረጃ የተደገፈ መጽሐፍ በማውጣት ላቅ ያለ ሙያዊ አስተዋጽዎ ማድረጉ አይዘነጋም።

ታዋቂው አክቲቪስትና አርቲስት ታማኝ በየነ በዋሽንግተኑ መድረክ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወገንን ለመርዳት የጀመሩትን ጥረት ለማገዝ መፈለጉን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትረስት ፈንድን እንዲመሩ ከመረጧቸው ታዋቂ ኢትዮጵያውያን መካከል መሆኑ አይዘነጋም።ታማኝ እና ሙሉቀን የሚገቡበት ቀን ለጊዜው ያልተገለጸ ሲሆን በርካታ ሕዝብ በየፊናቸው በትግሉ ያደረጉትን የላቀ አስተዋጽዎ በማየት ድጋፉን ያደርግላቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *