Hiber Radio በምርጫ ቦርድ ላይ ክስ የመሰረቱት የመኢአድ ሕጋዊው ፕሬዝዳንት አቶ ማሙሸት አማረ በደህንነቶች ታፍነው ተወሰዱ

አቶ ማሙሸት አማረ

      መኢአድን ለመምራት በሕጋዊ መንገድ ተመርጠው አመራሩን በያዙ በጥቂት ቀናት በምርጫ ቦርድ ሕገ ወጥ ውሳኔ በፌዴራል ፖሊስ ከቢሮ          ተባረውየነበሩት ህጋዊው የመኢአድ ፕሬዝዳንት አቶ ማሙሸት አማረ ረቡዕ ማለዳ አዲስ አበባ ቦሌ ሚካኤል አካባቢ ቴዲ ባር አቅራቢያ ከቤታቸው እንደወጡ በደህንነቶች ታፍነው መወሰዳቸውን አንድ የፓርቲው የቀድሞ አመራር ለህብር ሬዲዮ ገለጹ።

አቶ ማሙሸት አማረ ዛሬ ማለዳ ከጠዋቱ 2 ሰዓት ቦሌ ሚካኤል ቴዲ ባር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከቤታቸው እንደወጡ ሲጠብቋቸው በነበሩ የደህንነት አባላት ታፍነው የተወሰዱ ሲሁን ከቆይታ በሁዋላ ሲ.ኤም.ሲ አካባቢ ከሚገኝ ፍርድ ቤት ወስደው መልሰው ፖሊሶችና የደህንነት አባላት ቤታቸውን መበርበራቸውን ያገኘነው መረጃ አስረዳል።

አቶ ለገሰ ወልደሃና የቀድሞው በምርጫ ቦርድ እንዲፈርስ የተደረገው መኢአድ ም/የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የአቶ ማሙሸት ከቤት ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ማታ ለሚከታተሉት የፖለቲካል ሳይንስ ትምህርት ፈተና ስላለባቸው ላይብረሪ ለመግባት በወጡበት ወቅት በቤታቸው አካባቢ ሲጠብቋቸው በነበሩ የደህንነት አባላት በያዙት መኪና አፍነው እንደወሰዷቸው ለህብር ሬድዮ ገልጸዋል።

አቶ ማሙሸት አማረ በሁለት ጊዜ በቀናት ልዩነት በተደረገ ጉባዔ መኢአድን ለመምራት ከመላው አገሪቱ በመጡ የፓርቲው የማዕከላዊ ም/ቤት አመራሮች ቢመረጡም ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ባለመቀበል ስልጣኔን በፈቃዴ ለቅቄያለሁ ያሉትን የፓርቲውን የቀድሞ ፕሬዝዳንት አቶ አበባው መሐሪን ከቤታቸው አምጥቶ ስልጣን ላይ ማስቀመጡን ተከትሎ ውሳኔውን በመቃወም በፍርድ ቤት በቦርዱ ላይ ክስ መመስረታቸው ይታወሳል። ክሱ በሂደት ላይ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የፓርቲውን ሕጋዊነት ለማረጋገጥ ከመንቀሳቀስ ውጭ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እያደረጉ እንዳልነበር አቶ ለገሰ ጠቅሰዋል።

አቶ ማሙሸት በተለይ የመኢአድን አመራር ቦርዱ አልቀበልም ባለው ከጥቅምት 28-30 በተደረገ ጉባዔ መኢአድን ለመምራት በተመረጡበት ሕጋዊ ምርጫ ስልጣን ከመያዛቸው በፊትና በሁዋላ ማስፈራሪያና ዛቻ ብቻ ሳይሆን ሰፊ ክትትል ይደረግባቸው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።

አቶ ማሙሸት አማረ አገዛዙን በሰላማዊ መንገድ ታግሎ መጣል ይቻላል ብለው በማመን በምርጫ ቦርድ የተወሰደውን ውሳኔ በመቃወም ወደ ፍርድ ቤት ሄደው የፓርቲውን ሕጋዊ ስልጣን ለማስመለስና ትግሉን ለማስቀጠል ሲንቀሳቀሱ ነበር።

(ህብር ሬዲዮን ከድህረ ገጻችንና ከዘ-ሐበሻ በተጨማሪ ዘወትር በ7124328451 ማዳመጥ ይቻላል)

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *