መነሻ ደሞዝ እንዲጨምር የሚደረገው ድርድር የስራ ስምሪቱን እንዳዘገየው መንግስት ገለፀ (ኢ.ፕ.ድ)

በሳውዲ አረቢያ ለስራ የሚሄዱ ዜጎች የሚከፈላቸው ዝቅተኛ መነሻ ደሞዝ እንዲጨምር ከሀገሪቱ መንግስት ጋር ድርድር እየተደረገ በመሆኑ የስራ ስምሪቱ ሊዘገይ መቻሉን የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በኳታርና ጆርዳን የስራ ስምሪት ጉዞ ያልተጀመረው በሀገራቱ የሚሰሩ የጉዞ ወኪሎች ፍቃድ ባለማግኘታቸው መሆኑንም ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡
ከባለፈው መስከረም 30 ጀምሮ ወደ ኳታር፣ ዮርዳኖስና ሳውዲ አረቢያ የሚደረጉ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት መከፈታቸውን መንግስት መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ወደ እነዚህ ሀገራት የሚደረጉ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት እስካሁን እንዳልተጀመረ ነው ከውጭ ሀገራት የጉዞ ኤንሲዎች የተገኘው መረጃ የሚያመለክተው፡፡

በኳታርና ዮርዳኖስ የውጭ የስራ ስምሪት ጉዞ ያልተጀመረው በሀገራቱ የሚሰሩ የጉዞ ወኪሎች ፍቃድ ባለማግኘታቸው መሆኑን በሰራተኛና ማህበራዊ ሚኒስቴር የውጭ ሀገር ስምሪት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ብርሃኑ አበራ ተናግረዋል፡፡

ይህንንም ችግር ለመፍታት መንግስት ከሀገራቱ ጋር ስምምነት በመድረሱ የጉዞ ኤጀንሲዎቹ ፍቃዱን እንደሚያገኙ ገልፀዋል፡፡
ሆኖም በሳውዲ አረቢያ በውጭ ሀገር የስራ ስምሪት የሚሰሩ የጉዞ ወኪሎች ፍቃድ እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡

የሳውዲ አረቢያ የስራ ስምሪት ሊዘገይ የቻለው መንግስት ለስራ ለሚሄዱ ዜጎች የሚከፈላቸው ዝቅተኛ መነሻ ደሞዝ እንዲጨምር ከሀገሪቱ መንግስት ጋር እየተደራደረ በመሆኑ ነው ብለዋል አቶ ብርሃኑ፡፡

ፍቃድ ባገኙ የውጭ ሀገር የጉዞ ወኪሎች ወደ እነዚህ ሶስት ሀገሮች የሚደረጉ ጉዞዎች በህጋዊ መንገድ የሚደረጉ በመሆናቸው ዜጎች የአውሮፕላን ትኬትን ጨምሮ ለምንም ዓይነት ተጨማሪ ወጪ አይዳረጉም ተብሏል፡፡

ይህ ህጋዊ ጉዞ መስተጓጎሉን ተከትሎ ህገወጥ ደላሎች ዜጎችን እያባበሉ በአጎራባች ሀገራት በኩል ወደ እነዚህ ሀገራት የመላክ አዝማያሚያ እንደሚታይም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጠቁሟል፡፡

እናም ዜጎች አስፈላጊ ላልሆነ እንግልትና ወጪ ከሚዳረጉ ህጋዊው ጉዞው እስከሚጀመር በትዕግስት እንዲጠባበቁ ሚኒስቴሩ ጠይቋል፡፡
በውጭ ሀገር ስምሪት የሁለትዮሽ ስምምነት ካልተደረሰባቸው ሀገራት ጋር ያለውን ድርድር ለማፋጠን እየተሰራ መሆኑንም ዳይሬክተር ጀነራሉ ተናግረዋል፡፡

በዚህም ከዱባይ፣ ከኦማን፣ ኩዌት፣ቤሩትና ከባህሬን ጋር በዘርፉ ስምምነት ላይ ለመድረስ በድርድር ሂደት ላይ እንደሚገኝም አመልክተዋል፡፡
ስምምነቱም የዜጎችን መብት ለማስጠበቅ የሰራተኛ ላኪና የተቀባይ ሀገራትን መብትና ግዴታ ያስቀምጣል ማለታቸውን የዘገበው ኢቢሲ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *