ይፈቱ ተብሎ ያልተፈቱት የፖለቲካ እስረኞች ቁጥር እጨመረ ነው

እነ አብርሃ ደስታና አቶ ማሙሸት አማረ
እነ አብርሃ ደስታና አቶ ማሙሸት አማረ

በፖለቲካ ውሳኔ በፈጠራ የሽብር ወንጀል፣ከሽብርተኛ ድርጅት ጋር በማበር በሀሰት የተከሰሱት እና በፍርድ ቤት ውሳኔ ነጻ የተባሉት እነ ሀብታሙ አያሌው ዛሬም ድረስ ያልተፈቱ ሲሆን በዛሬው እለት ሕጋዊው የመኢአድ ፕሬዝዳንት አቶ ማሙሸት አማረ በፍርድ ቤት ኢፈቱ ቢባልም እስካሁን ሳይፈቱ ቀርተዋል።ይፈቱ እየተባለ ያልተፈቱት የፖለቲካ እስረኞች ቁጥር እየጨመረ ሄዷል።አቶ ማሙሸት አማረ ከዛሬው ጋር ለሶስተና ጊዜ በተለያዩ ፍርድ ቤቶች እንዲፈቱ የተወሰነላቸው ቢሆንም ከቤታቸው አቅራቢያ ከተያዙበት ግንቦት 5 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ በእስር ላይ ናቸው።

የዛሬውን የአቶ ማሙሸት የፍርድ ቤት ሂደት ነገረ ኢትዮጵያ እንደዘገበው የአራዳ ፍርድ ቤት አራተኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ነሃሴ 22/2007 ዓ.ም በዋለው ችሎት አይ ኤስ አይ ኤስን ለመቃወም መንግስት ከጠራው ሰልፍ አንድ ቀን ቀድሞ ከለቅሶ ቤት ወደ ቤተ መንግስት የተደረገውን ሰልፍ አደራጅቶ መርቷል እንዲሁም ለዋናው (ለሚያዝያ 14/2007 ዓ.ም) ሰልፍ አነሳስቷል በሚል ክስ የተመሰረተበት አቶ ማሙሸት አማረ በነፃ እንዲለቀቅ ወስኗል፡፡

አቃቤ ህግ ነሃሴ 20/2007 ዓ.ም አቶ ማሙሸት ገንዘብ ከፍሎ ወጣቶችን ሰልፍ እንዳስወጣቸው፣ ወጣቶችን እንዳደራጀ፣ በሰላማዊ ሰልፉ ወቅትም መንግስትን የሚተቹ መፈክሮችን በመሪነት ሲያሰማ እንደነበርና ለሚያዝያ 14 ሰልፍም ሲያደራጅ እንደነበር ያስረዱልኛል ያላቸውን ሶስት የሰው ምስክሮችን ማሰማቱ ይታወሳል፡፡ ይሁንና ፍርድ ቤቱ የአቃቤ ህግ ምስክሮች የግል ሰራተኛ እንደሆነ በምስክርነት ቃላቸው ቢሰጡም በመስቀለኛ ጥያቄ አንደኛው የመንግስት ሰራተኛ፣ ሁለተኛው የወጣቶች ሊግ ከዚህም አለፍ ሲል የኢህአዴግ አባል፣ ሶስተኛው ደግሞ የጥቃቅንና አነስተኛ ባልደረባ መሆናቸውን በማመናቸው የሰጡት ምስክርነት ትክክል አለመሆኑን ያስረዳል ብሏል፡፡ በተጨማሪም ምስክሮቹ ገዥው ፓርቲን የሚደግፉና የወጣት ሊግ አባል ሆነው ገዥው ፓርቲን የሚቃወም ግለሰብ ላይ የሰጡት ምስክርነት ገለልተኛ ነው ብሎ ለማመን ያስቸግራል ብሏል፡፡ ከዚህም ባሻገር ምስክሮቹ የገዥው ፓርቲ ደጋፊ ሆነው እያለ አቶ ማሙሸት አማረ በተደጋጋሚ ይደውልላቸው እና ይገናኙም እንደነበር የመሰከሩ ሲሆን አቶ ማሙሸት ቀንደኛ የገዥው ፓርቲ ተቃዋሚ ሆኖ እያለ ከመንግስት (ከገዥው ፓርቲ) ቀንደኛ ደጋፊዎች እንዲህ አይነት ግንኙነት ይኖረዋል ብሎ ለማመን እንደማይቻል አስረድቷል፡፡ በሌላ በኩል ከ4 አመት ጀምሮ እስከ 7 አመት አዲስ አበባ ውስጥ የኖሩት ምስክሮች ስለ ሰልፉ ባስረዱበት ወቅት ቤተ መንግስትን ጨምሮ ሰልፉ ያለፈባቸውን ቦታዎች አናውቃቸውም ማለታቸው ራሳቸውን ከመስቀለኛ ጥያቄ ለማዳን ያደረጉት እንደሆነ ፍርድ ቤቱ ገልጾአል፡፡ በመሆኑም የምስክሮቹ ቃል ታማኒነት ስለሌለው አቶ ማሙሸት አማረ መከላከል ሳያስፈልገው በዛሬው ዕለት በነፃ እንዲለቀቅ ሲል ፍርድ ቤቱ ወስኗል፡፡ አቶ ማሙሸት አማረ ሚያዝያ 14/2007 ዓ.ም በተካሄደው ሰልፍ ላይ ሁከትና ብጥብጥ ፈጥሯል በሚል ተከሶ የነበር ቢሆንም በወቅቱ ከምርጫ ቦርድ ጋር በነበረው ክርክር ሰልፉ ላይ አለመገኘቱን የሚያጋግጥ መረጃ በማምጣቱ በነፃ እንዲለቀቅ ተወስኖ ነበር፡፡ ነገር ግን ክሱ ወደማነሳሳት ተቀይሮ እስከዛሬ እስር ቤት እንዲቆይ ተደርጓል፡፡

የህብር ሬዲዮን ዘገባ ህብር ሬዲዮን ከድህረ ገጻችን በተጨማሪ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን ወይም ከgoogel store Hiber radio አፕሊኬሽንን ዳውን ሎድ በማድረግና  ከዘሐበሻም ማዳመጥ ይቻላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *