Hiber Radio : የመኢአድ ሕጋዊው ፕሬዝዳንት አቶ ማሙሸት አማረ የአሜሪካ ቪዛ ተከለከሉ

Mamushet_Amare_us_embassy_02

 

ህብር ሬዲዮ ( ላስ ቬጋስ) የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት(መኢአድ) ሕጋዊው ፕሬዝዳንትና በአገዛዩ ምርጫ ቦርድ ህገ ወጥ ውሳኔ ከቢሮ የተባረሩትና በቅርቡ ከእስር በነጻ የተፈቱት አቶ ማሙሸት አማረ በውጭ ከሚገኙ የፓርቲው ደጋፊዎች ጋር ለመነጋገር ወደ አሜሪካ አቅደውት የነበረው ጉዞ በዛሬው ዕለት ቪዛ በመከልከላቸው ሳይሳካ መቅረቱን ለህብር ሬዲዮ የፓርቲው ምንጮች የላኩልን መረጃ ያስረዳል።

አቶ ማሙሸት አማረ ግንቦት 5 ቀን 2008 ከመንገድ ላይ በአገዛዙ ደህነቶች ታፍነው ከአራት ወራት በላይ በተለያዩ እስር ቤቶች ሲንገላቱ የቆዩ ሲሆን በፓርቲው ውስጥ ከፕሮፌሰር አስራት ሊቀመንበርነት ጊዜ ጀምሮ ሲያገለግሉ የቆዩና በምርጫ 97 ከቅንጅት መሪዎች ጋር የታሰሩትን ጨምሮ በመረጡት ሰላማዊ ትግል ሳቢያ ለስምንት ጊዜያት ታስረዋል።

አገዛዙ መቶ በመቶ አሸነፍኩ ካለበት ምርጫ ዋዜማ መኢአድና አንድነት ያካሄዱትን ሕጋዊ ጉባዔ በምርጫ ቦርዱ አማካይነት ድጋሚ እንዲደረግ ሲያስገድድ ከመላው አገሪቱ የተሰባሰቡ የመኢአድ የጠቅላላ ጉባዔን በቀናት ልዩነት በድጋሚ የጠሩ ሲሆን ለሁለተኛ ጊዜ ፓርቲውን በፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ መመረጣቸው ይታወሳል። የአገዛዙ ምርጫ ቦርድ የፓርቲውን ጉባዔ ውሳኔ በመሻር ቢሮውን በፖሊስ ቁጥጥር ስር በማድረግ አቶ ማሙሸትና ዛሬ በእስር ቤት የሚገኙትን የፓርቲውን የውጭ ግንኙነት ሀላፊና ሌሎች አመራሮችንና ውሳኔውን ያልተቀበሉትን አባላት አባሮ በምትካቸው ስልጣኔን ለቅቄያለሁ ያሉትን የቀድሞ የፓርቲው ፕሬዝዳንት አቶ አበባው መሐሪን ከቤታቸው በማምጣት ቦርዱ ስልጣን ላይ በማስቀመጥ ግለሰቡ ከማን ጋር ሲሰሩ እንደቆዩ ችምር ያጋለጠ ውሳኔ ነው ሲሉ የፓርቲው ሰዎች መግለጻቸው አይዘነጋም።

አቶ ማሙሸት ቦርዱን ለፈጸመው ሕገ ወጥ ውሳኔ በፍርድ ቤት ክስ የመሰረቱ ቢሆንም ክሱ ዳር ሳይደርስ ግንቦት 5 ቀን 2008 ከቤታቸው አቅራቢያ በአገዛዙ ደህነቶች ታፍነው መጀመሪያ ቦሌ ምድብ ፖሊስ ጣቢያ መታሰራቸው እና በሊቢያ በኤይሲስ የተቀሉና የተገደሉ ኢትዮጵያውያን ሐዘናቸውን በገለጹበት ወቅት ተገኝተህ አመጽ ቀስቅሰሀል የሚል ክስ ቀርቦባቸው የደህነት አባላት ቀርበው በሀሰት መሰከሩ። ድርጊቱን መስቀል አደባባይ ተገኝተው ፈጽመዋል በተባሉበት ሚያዚያ 14 ቀን 2008 ዓ.ም በቦታው እንዳልነበሩ፣ በዕለቱ ምርጫ ቦርድን ከሰው ልደታ ፍርድ ቤት ክርክር ላይ እንደነበሩ ከፍርድ ቤት ማረጋገጫ አቅርበው፣በዕለቱ አብረዋቸው ፍርድ ቤት የነበሩ ጓዶቻቸውን አስመስክረው ፍርድ ቤቶ ክሱ ተቋርጦ በነጻ ይለቀቁ ቢላቸውም ሳይፈቱ ከእስር ቤት ወደ እስር ቤት መዛወራቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

አቶ ማሙሸት አማረ ከእስር ከተፈቱ በሁዋላ ለህብር ሬዲዮ በሰጡት ቃለ ምልልስ ከዚህ በሁዋላ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ብታደርግ እንገድልሃለን መባላቸውንና የደህነቶች ክትትል ከወጡም በሁዋላ እንዳልተቋረጠ ነገር ግን እስኪገሉኝ ሰላማዊ ትግሉን እቀጥላለሁ ማለታቸው ይታወሳል።

አቶ ማሙሸት አማረ የመኢአድ ሕጋዊው አመራር እና ብዙሃኑ አባላት በምርጫ ቦርድ ሕገ ወጥ ውሳኔ ቢራችን ቢነጠቅም ተመልሰን ትግሉን እንቀጥላለን ሲሉ ከዚህ ቀደም በሰጡት ቃለ ምልልስ የገለጹ ሲሆን የሰሞኑ የአሜሪካ ጉዞዋቸው ከፓርቲው ደጋፊዎች ጋር ለመነጋገር የታቀደ ሲሆን በኤምባሲው ቪዛ ክልከላ ሳቢያ ጉዟቸው ተስተጓጉሏል።

የህብር ሬዲዮን ዘገባ ህብር ሬዲዮን ከድህረ ገጻችን በተጨማሪ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን ወይም ከgoogel store Hiber radio አፕሊኬሽንን ዳውን ሎድ በማድረግና  ከዘሐበሻም ማዳመጥ ይቻላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *