የመምህር ግርማ ዋስትና መከልከልና አዲስ ክስ ብቅ ማለቱ እስራቸው ፖለቲካዊ ውሳኔ መሆኑን ኢትዮጵያውያን በመግለጽ ላይ ናቸው ፣የማታለል ክስ የቀረበባቸው መምህሩ “ሴራ ነው – ከሳሹን አይቼው አላውቅም” ብለዋል

memehir_girma_04

መምህር ግርማ ወንድሞ በአዲስ አበባ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደዋሉ በአገዛዙ የፓሪቲ ሚዲአ ያለ ፈቃድ በማጭበርበር ሲያስተምሩ መያዛቸውን ፖሊስን ጠቅሶ በዘገቡ ማግስት በፍርድ ቤት ፖሊስ ይዞ የቀረበው አዲስ የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ክስ ግለሰብን ማጭበርበር ወደሚል መቀየሩ አስቀድሞ በጉዳዩ ላይ ጥርጣሬ ለፈጠረባቸው ወገኖች የበለጠ ማረጋገጫ ሲሆን ራሳቸው መምህር ግርማ አጭበረበሩት የተባለውን ግለሰብ አይቼ አላውቅም ብለዋል።

ፖሊስ ዛሬ መምህር ግርማን ፍርድ ቤት አቁሞ ጠርጥሮ ያሰረበትን ምክንያት አስረድቷል:: የፌደራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ የወንጀል ችሎት በመምህር ግርማ ላይ ፖሊስ የፈጸመውን ክስ ከሰማ በኋላ ፖሊስ አቶ ግርማ ቢፈቱብኝ መረጃና ሰነዶችን ሊያሸሹ ይችላሉና 14 ቀን ይፈቀድልኝ ሲል ጠይቋል:: የመምህር ግርማ ጠበቃ የተጠረጠሩበት ክስ ዋስትና የሚያስከለክል አይደለም ሲል ሲል በዋስ እንዲለቀቁ ጠይቆ ነበር:: ሆኖም ፍርድ ቤቱ ፖሊስ አብዛኛውን ምርመራ በማጠናቀቁ የጠየቀውን 14 የምርመራ ቀን ሰርዞ በ7 ቀን ውስጥ አሉኝ የሚላቸውን ማስረጃዎች አሰባስቦ እንዲጨርስ ፈቅዶ ውጤቱን ለመስማትም ጥቅምት 25 2008 ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል። መምህር ግርማ ወደ ማረፊያ ቤት ሄደዋል:: በመምህር ግርማ ወንድሙ ላይ በፖሊስ ለጊዜ መጠየቂያ የቀረበው ክስ ላኢ ብዙዎች ጥርጣሬ ያላቸው ሲሆን በአገዛዙ ሚዲአ የቀረበው የፖሊስ ክስ እንደሚለው የወንጀሉ ዝርዝር ፖሊስ መምህር ግርማ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ምክንያት የሆነው ወንጀል የተፈፀመው መስከረም 2006 ዓ.ም ነው ብሏል። በየካ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ወሰን ግሮሰሪ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚኖሩት አቶ በላይነህ ከበደ በመምህር ግርማ የማታለል ወንጀል የተፈጸመባቸው ግለሰብ ናቸው። እንደ ፖሊስ የምርመራ መዝገብ እኚህ ግለሰብ ከትዳር አጋራቸው ጋር 400 ካሬ ሜትር ላይ ባረፈ መኖሪያ ቤታቸው ይኖሩ ነበር። እንደ ምርመራ መዝገቡ መምህር ግርማ የግል ተበዳይን እምነት በመጠቀም የምትኖርበትን መኖሪያ ቤት እስከ ጥር 30 2006 ሽጠህ ካልወጣህ አስከሬንህ ይወጣል ይሏቸዋል። የፖሊስ የምርመራ መዝገብ እንደሚለው ልጅ ያልወለዱት ባልና ሚስት ከመሞት መሰንበት በማለት ይህንን ቤት በጣም በዝቅተኛ ዋጋ በ800 ሺህ ብር ይሸጡታል። ቤቱ በዚህ ዋጋ እንዲሸጥ መምህር ግርማ በራሳቸው ሰዎች አማካኝነት ብዙ ያልተገባ ስራ ሰርተዋል ነው የሚለው የምርመራ መዝገቡ። ከዚያም መምህር ግርማ በዚህ ብቻ ሳይመለሱ የግል ተበዳዩን ቦሌ አካባቢ በራዕይ ያየሁት ቦታ አለ እዚያ ነው ገዝተህ የምትኖረው ይሏቸውና ሌላ የማታለያ ዘዴ ቀየሱ ይላል ምርመራው። ቤቱ የተሸጠበትን 800 ሺህ ብር አምጣና እንዲበረክትልህ ልፀልይበት ብለው በመውሰድ በዚያው ውለው አደሩ፤ የግል ተበዳዩም በእርሳቸው ላይ ያላቸው እምነት ባለመጥፋቱ በትዕግስት ስልክ ቢደውሉላቸውም ስልካቸው ዝግ ሆነባቸው፤ ይባስ ብሎ ከሀገር ወጡ ተባለ የሚለውም ተጠቅሷል። የግል ተበዳይ ሁኔታው ማታለል መሆኑን ስለተረዱ 2007 መጋቢት ወር ገደማ ለፖሊስ ያመለከቱ ሲሆን፥ እርሳቸው ከሄዱበት እስኪመለሱ ፖሊስ የግል ተበዳዩን እና የምስክሮችን ቃል ተቀብሎ ቆይቶ ተጠርጣሪው መምህር ግርማ ወንድሙን ትናንት በቁጥጥር ስር አውሏቸው ነው ዛሬ ፍርድ ቤት ያቀረባቸው። ተጠርጣሪው መምህር ግርማ እኔ የተባለውን ሰው ቀይ ይሁን ጥቁር አይቼው አላውቅም፤ ሆን ተብሎ ከጀርባ የተጠነሰሰብኝ ሴራ አለ በማለት ለችሎቱ አስረድተዋል።

ፖሊስ ከዓመት በላይ የጠበቀበት ክስ ከሆነ በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ ምስክሮችንም ሆነ ሰነዶችን በፈለገው መንገድ መሰብሰብ እየቻለ በተለመደው የአገዛዙ ስልት በመጀመሪአ በፈጠራ አስሮ የመሰለውን ወንጀል ለጥፎ ማስረጃ እንሰብስብ በማለት በሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ላይ እና በሌሎችም ንጹሃን ጋዜጠኞች፣ጦማሪአን፣ፖሌካ መሪዎች ያደረጉትን በሌላ መልክ እየደገሙ ነው የሚል ተቃውሞ መደመት ጀምሯል። <<መምህር ግርማ ይፈቱ!>> የሚሉ ድምጾች መሰማት የጀመሩ ሲሆን አንዳንዶች ሰዎችን እአሰረ ዘላለም ፍታ ከማለት ለወሳኝ ለውጥ የሁሉም የዕምነት፣የህይወት፣የፍትህም ሆነ ንብረት መብቶችና መናገርና መጻፍ መብቶች እንዲከበሩ ኢትዮጵያን የወያኔን የግፍ እስር ሁለተና ጉዳይ አድርገው እስር የሚቀርበትን ለውጥ ለማምጣት መተባበር አለባቸው የሚሉ ጥቂት ድምጾችም መሰማት ጀምረዋል።

የህብር ሬዲዮን ዘገባ ህብር ሬዲዮን ከድህረ ገጻችን በተጨማሪ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን ወይም ከgoogel store Hiber radio አፕሊኬሽንን ዳውን ሎድ በማድረግና  ከዘሐበሻም ማዳመጥ ይቻላል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *