Hiber radio: አሁንም እስረኞች ነን – ከዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች የተሰጠ መግለጫ

zONE9_AFTER_PRISON_02

ከሚያዝያ 17 2006 ጀምሮ በፓሊስ ቁጥጥር ስርውለን የነበርነው 3 ጋዜጠኞችና እና 6 የዞን9 ጦማርያን ከአንድ አመት ከሁለት ወር እና ከአንድ አመት ከ5 ወር የእስር ቆይታ በኋላ ሁላችንም ከእስር አንደተፈታን ይታወሳል፡፡ በሃምሌ ወር መጀመሪያ ሶስት ጋዜጠኞች እና ሁለት ጦማርያን አቃቤ ህግ ክስ አቋርጦ፣ በማስከተል አራት ጦማርያን ደግሞ ነጻ ተብለው ከእስር መለቀቃችን የሚታወስ ሲሆን ጦማሪ በፍቃዱ ሃይሉ በዋስትና ላይ ሆኖ የቀረበበትን “አመጽ የማነሳሳት ክስ” እንዲከላከል መባሉም ይታወቃል፡፡

ይሁን አንጂ የዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች ከተፈታን ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ ነጻ አለመውጣታችንን የሚያሳዩ ተደጋጋሚ ተግዳሮቶች በመኖራቸው እና ሊቀየሩም ባለመቻላቸው ይህንን መግለጫ ለማውጣት ተገደናል፡፡

 

  1. የኢፌዲሪ ህገ መንግስት አንቀጽ32 በሚደነግገው መሰረት “ ማንኛውም ኢትዮጲያዊ … በፈለገው ጊዜ ከአገር መውጣት ነጻነትን” በሚጻረር መልኩ “የመንቀሳቀስ መብታችን”አሁንም ተገድቧል፡፡ ለምሳሌ ጦማሪ ዘላለም ክብረት ህዳር 7/2008 በፈረንሳይ አገር በሪፓርተርስ ሳንስ ፍሮንቲየርስ (ድንበርየለሽ ጋዜጠኞች ድርጅት) ለዞን 9 ጦማር የተበረከተውን 2015 የሲቲዝን ጆርናሊዝም ሽልማት የዞን9 ጦማርን ወክሎ ለመገኘት ህዳር 6/2008 ቦሌ አየር ማረፊያ ቢገኝም ባልታወቀ ምክንያት ከአገር መውጣት ተከልክሎ ፓስፓርቱንም ተቀምቷል፡፡ በዚህም የተነሳ የሚቀጥለው ሳምንት በሚከናወነው በአለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተከላካይ የሆነ የሲፒጄ የፕሬስ ነጻነት ሽልማት ላይ መገኘቱን እድልም በጣም አጥብቦታል ፡፡
  2. ጦማሪ አቤል ዋበላ (የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኢንጂነር) ፣ ጦማሪ ዘላለም ክብረት (የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር) ጦማሪት ማህሌት ፋንታሁን( የጤና ጥበቃሚኒስትር የዳታ ኦፌሰር) እና ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬ (በፕላን ኢንተርናሽናል የኮምኒኬሽን እና ኖውሌጅ ማኔጅመንት ሰራተኛ) ወደስራ ገበታችን መመለስ አልቻልንም ፡፡ ከእኛ ቁጥጥር ውጪ በሆነው መንገድ ተገደን ከአንድ አመት በላይ እስር ቤት መቆየታችን የእኛ ጥፋት አንደሆነ ተቆጥሮ ከስራ ተባረናል ፡፡ሌሎቻችንም በግል እንሰራቸው የነበሩ ስራዎችንም መቀጠል አልቻልንም ፡፡
  3. ከፍተኛው ፍርድ ቤት ከክሳችሁ ሙሉ ለሙሉ ነጻ ወጥታችኋል ብሎ የበየነልን ሶስት ጦማርያን ስንያዝ “ማአከላዊ” ምርመራ የተወሰደብን ፓስፓርታችን እና ሌሎች እቃዎቻችን እንዲመለሱልን ብንጠይቅም “ አቃቤ ህግ ይግባኝ ጠይቆባችኋል” በሚል ሰበብ እስካሁን አልተመለሱልንም፡፡
  4. ቢቢሲ አንደዘገበው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ አሁንም “ ታስረው የነበሩት ጋዜጠኞች እና ጦማርያን የእውነት ጋዜጠኞች አይደሉም ከሽብር ጋር ግንኙነት አላቸው” በማለታቸው እንዲሁም የተለያዬ የመንግስት ባለስልጣናት የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ላይ የሚሰጡት አስተያየት ፍርድቤቱ ያወጀልንን ነጻነታችንን ኢ- ህገመንግስታዊ በሆነ መንገድ እየናደው ነው ፡፡

በእነዚህእና በሌሎች ጫናዎች ምክንያት ራሳችንን ሳንሱር አንድናደርግ እና ሁሉም ጉዳያችን በእንጥልጥል ላይ ያለ የቁም እስረኞች የሆንን እንዲመስለን እየተደረገ ነው ፡፡ ስለሆነም

–     ህግ መንግስታዊ መብታችን የሆነው እና ምንም ህጋዊ ገደብ ያልተቀመጠበት በነጻነት የመንቀሳቀስ መብት መብታችን እንዲመለስልን

–     በኢግዚቢት ስም በማእከላዊ ምርምራ የሚገኙት እና ካለምንም ህጋዊ ምክንያት የተያዙት ፓስፓርት እና ሌሎች የግል እቃዎቻችን እንዲመለሱልን

–     መንግሰት የራሱን ፍርድ ቤት ውሳኔ አክብሮ አሁንም ወንጀለኛ ስያሜ የሚሰጠንን ስም ማጥፋት እና የእጅ አዙር ጫና አንዲያቆምልን

–     የፓለቲካ ታማኝነትን ለማሳየት ያለህግ አግባብ ወደስራ ገበታችን አንዳንመለስ ያደረጉን አካላት ውሳኔያቸውን መለስ ብለው እንዲያዩልን እንጠይቃለን፡፡

ሕገ መንግስቱ ይከበር

ዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች

የህብር ሬዲዮን ዘገባ ህብር ሬዲዮን ከድህረ ገጻችን በተጨማሪ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 እና በአውስትራሊያ 0280725172 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን ወይም ከgoogel store Hiber radio አፕሊኬሽንን ዳውን ሎድ በማድረግና  ከዘሐበሻም ማዳመጥ ይቻላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *