ረሃቡ ህወሓት ሰራሽ ነው..!

Famine-in-Ethiopia-2015_tplf_made

አምዶም ገ/ስላሴ የህወሓት ባህሪ ልክ እንዳኮረፈ መስማት የተሳነው ሰው ነው። ያኮረፈ መስማት የተሳነው ሰው ሲጣላ ኣጋጥሟቹ ያውቃል?

ያኮረፈ መስማት የተሳነው ሰው ከተጣላ የምትናገረው፣ ካፍህ የሚወጣው ቃል ስድብ እየመሰለውና “ኣይተውም” በሚል እሳቤ ከመግባባት ይልቅ ሁሉ ዓይነት ስድብ ያዘንብብሃል፣ ዓቅም ካለውም ለድብድብ ይጋብዘሃል።

በይሆናል እሳቤው ገላጋይ፣ ሽማግሌና ኣስታራቂ ሲያስቸግር ይታያል። ያኮረፈው መስማት የተሳነው ሰው የሚያስቸግረው ለተጣላው ሰው ብቻ ሳይሆን ኣይደግፈኝ ይሆናል ላለው ገላጋይም ጭምር ነው።

ህወሓትም ልክ እንደ ኣኩራፊ መስማት የተሳነው ሰው የተለየ ሃሳብ ላለመስማት “በመቃብሬ” የሚል ኣቋም በማስቀደም የመጣ ጠቃሚ ሃሳብና ኣማራጭ ፖሊሲ ይምጣ ሳታዳምጥ በሃሳቡ ባለቤት ኣካል ከስም ማጥፋት እስከ ድራሹ ማጥፋት የደረሱ ኣብዮታዊ እርምጃዎች ትወስዳለች።

ለምሳሌ በ1969 ያጋጠማት ልዩነት ኣውራጃዊነት( ሕንፍሽፍሽ ) ኣወናባጆች ያለቻቸው ታጋዮች ድራሻቸው በማጥፋት ኣጠናቀቀች፤ በማሌሊት ምስረታ ወቅት የሃሳብ ልዩነት የፈጠሩና የኋላ ኋላ ሃሳባቸው ተቀባይነት ያገኘው እነ ዶክተር ኣረጋዊ በርሀ የስም መጥፋት ዕጣ ደረሳቸው፣ የነ ስየ መውጣት ተከትሎ ወዘተ የወሰደቻቸው እርምጃዎች ስንመለከት ነገረ ስራዋ እንደ ያኮረፈ መስማት የተሳነው ሰውየ ነው።

ዓረና_መድረክና ሌሎች በሰለማዊና ሕጋዊ መንገድ የሚታገሉ ፓርቲዎች ለሃገሪቱ ይጠቅማሉ ያሏቸው ኣማራጭ ፖሊሲዎችና ስትራተጂዎች ሲያቀርቡ ፀረ ህዝብ ሃይሎች ወይም የጥፋት ሃይሎች የሚል ቅጥያ ሰጥታ ጠቃሚ ሃሳባቸው ሳትመረምር በማውገዝ ያዙኝ ልቀቁኝ ትላለች ።

የወሰደችው መልካም ኣማራጭም የራስዋ ለማስመሰል ባለቤቱ ጥላሸት ትቀባለች። ለምሳሌ ኣባይ ገድቦ ለመብራት ብቻ ሳይሆን ለመስኖ ልማትም መዋል ኣለበት የሚል የመድረክ ፖሊሲ እንደመነሻ ወስደው ሲያበቁ እውቅና ለመስጠት የሚቸገሩበት ምክንያትም እንደ ያኮረፈው መስማት የተሳነው ሰው የበታችነት ስሜት የመነጨ መሆኑ ይታወቃል።

ይሄ ኣጉል የህወሓት ስሜት የወለደው ችግር ዋነኛ ማሳያ በያዝነው ዓመት ኣጋጥሞ ያለው ድርቅና ድርቁን ተከትሎ ኣጋጥሞ ያለው 15 ሚልዮን ህዝብ ለረሃብ መዳረግ ነው።

“ባለ ራኢዩ መሪ” መለስ ዜናዊ በ1977 ዓ/ም ያጋጠመው ድርቀ ተከትሎ የተከሰተው ኣስከፊ ረሃብ መነሻ ምክንያት “ድርቅን ሊከላከል የሚችል ምርጥ ፖሊሲ ኣለመኖር ነው” ሲሉ እምባ እየተናነቃቸው ለBBC ገልፀው ነበር።

እውነታቸው ነበሩ ኣቶ መለስ በወቅቱ ህዝባችን ያጠቃው ረሃብ የደርግ መንግስት ድርቅ የሚቋቋም ፖሊሲ ባለማበጀቱ የተከሰተ መሆኑ በሳቸው “ራኢ” የሚመራው ኢህኣዴግ ቁጥር ኣንድ ምስክር ነው።

ሃይለስላሴ፣ ደርግ፣ ህወሓት ድርቅ የሚከላከል ፖሊሲ ባለ ማዘጋጀት፤ ህዝብ በረሃብ ሲያልቅ ለስርዓታቸው ሚልዮን ብር ኣውጥተው በመደገስ፤ ረሃቡ ለመደበቅ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ የባህሪ ኣንድነት ኣላቸው። ኣንድም ሶስትም፣ ሶስትም አንድም ናቸው ምንም የሚለያዩበት መስፈርት የለባቸውም።

ኣዎ … ! ድርቁ በኢልኒኖ ምክንያት የተከሰተ ቢሆንም 15 ሚልዮን ህዝብዋ ድርቁ ባስከተለው ረሃብ ምክንያት በሞትና ሂወት መሃል ሁኖ ኣስቸኳይ እርዳታ የሚያስፈልጋት ሃገር ግን በ”መለስ ራኢ” የምትመራዋ ኢትዮጵያ ብቻ ናት። ድርቅ የመታቸው ሃገሮች በርካቶች ሁኖው ሳለ ኣደጋው ወደ ረሃብ የተሸጋገረባት ሃገር ኢትዮጵያ ከሆነች ፖሊሶችዋ መፈተሽ ኣለባቸው።

ህወሓት ህዝብ ከድርቅና ረሃብ ያላቅቅልኛል ብሎ የቀረፀው “ግብርና መር ኢንዳስትርያላዊ እድገት” የሚል የኢኮኖሚ ፖሊሲው በሃገራችን ተጨባጭ ውጤት ማምጣት ሳይችል ቀርቶ 15 ሚልዮን ለረሃብ ተዳርጓል። ፖሊሲው ኢንዳስትሪ መፍጠሩ ቀርቶ ልመናና ስደት ለማፍራት የበቃው የተሳሳተ እንደነበር ኩልል ብሎ እንዲጋለጥ ኣስችለዋል።

** የህወሓት ፖሊሲ ከወደቀ ሃገራችን ከዚህ ችግር የሚገላግላት ሌላ ኣማራጭ ፖሊሲ የት ኣለ?

ዓረና_መድረክ የህወሓት ፖሊሲ ያገራችን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ ያላስገባ፣ ጠለቅ ያለና የሰከነ ጥናት ያልተደረገበት መሆኑ ኣስቀድሞ ተገንዝቦ ያስረዳና በሌላ ኣዋጭ ፖሊሲ መተካት እንዳለበት በመግለፅ ኣማራጭ ፖሊሲው ኣስቀምጦ ያለፈ ድርጅት ነው።

ዓረና_መድረክ ከሃገራችን ተጨባጭ ተፈጥሮኣዊና ሰብኣዊ ሃብት ይዘት መሰረት ኣድርጎ ለኣካባቢዎችና ዘርፎች የሚመች ኣስፈላጊና ተመጣጣኝ ትኩረት በመስጠት ሚዛኑ የጠበቀ ኣስተማማኝ እድገት ማምጣት የሚያስችል ፖሊሲና ስትራተጂ በግልፅ ኣስቀምጠዋል።

እንደ ዓረና_መድረክ ኣማራጭ ሃሳብ የሃገሪቱ ክልሎች ተፈጥሮኣዊ ሃብት የተለያየ እንደመሆኑ መጠን የዘርፎች ትኩረትም ከክልል ክልል ሊለያይ እንደሚችል በማስቀመጥ እያንዳንዳቸው ኣንፃራዊ የበለጠ ተፈጥሮኣዊና ሰብኣዊ ሃብታቸው በማተኮር እንዲሰሩ በማድረግ የሃገሪቱ ምርታማነት ሚዛናዊ እንዲሆን ይረዳል የሚል እምነት ኣለው።

በዘርፎቹ የሚሰጠው ትኩረት እንደ ኣከባቢው ተፈጥሮኣዊና ሰብኣዊ ሃብት መሆን ኣለበት ሲባል በተሰጠው ትኩረትና በሚሰራው ስራ ሲወዳደር በቀላሉ ኣመርቂ ውጤት ሊገኝለት የሚችል ዘርፍ ለይቶ የበለጠ ጥረት በማከናወን የሚመጣ ለውጥ ኣስተማማኝ፣ የማይናጋና ተደጋጋፊ እድገት እንዲመዘገብ ይረዳል።

የሚሰራው ስራ በእርሻ፣ መዓድን፣ ቱሪዝም፣ ኢንዳስትሪ፣ ማህበራዊ ኣገልግሎት፣ ትራንስፖርት ወዘተ በተጨባጭ የኣከባቢው ሃብት መሰረት ያደረገ ይሆናል።

ለምሳሌ ዓረና_መድረክ ለትግራይ ክልል ያለው ምልከታ ማሳያ የሚሆን ባጭሩ እንደሚከተለው ይመስላል።

1) ግብርና:_ ።።።።።።።።።።

የትግራይ መሬት ከ3000 ዓመት በላይ የታረሰ፣ በርካታ ሰብኣዊ እንቅስቃሴ የተካሄደበት፣ የእርስ በርስና ከውጭ ወራሪ ሃይሎች ጦርነቶች የተካሄደበት በመሆኑ ለዘመናት ለፀሓይ፣ ዝናብና ንፋስ ተጋልጦ ስለ ነበር ኣምራችነቱ በምግብ ራስ ከመቻል ኣልፎ ኢንዳስትሪርያላዊ ኣብዮት ለማስመዝገብ የሚያስችል ተጨባጭ ኣቅም ያንሰዋል። በተነፃፃሪ ደህና ለም ናቸው ተብለው የሚታወቁ የሑመራና ራያ ኣከባቢዎች የሚመረተውም ከምግብነት ኣልፎ ያን ያህል ወደ ኣግሮ ፕሮሶሲግ ገብቶ ኢንዳስትርያላዊ ኣብዮት የሚያመጣ ኣይደለም።

ይህ ግምት ውስጥ ኣስገብቶ ዓረና_መድረክ ግብርና በትግራይ ክልል በዋናነት በምግብ ራስን ለመቻል የሚያስችል ጥረት ያደርጋል። እንደ ማስፈፀምያ ኣግባብም ጠባብ የእርሻ ቦታዎች በመስኖ ለማልማት መካከለኛና ትላልቅ ግድቦች በመገንባት ድርቅ የሚቋቋም ግብርና ይፈጥራል። ያሉት የእርሻ መሬቶች በመስኖ በማልማት ህዝቡ በምግብ ራሱ እንዲችል ከፍተኛ ኣስተዋፅኦ ያደርጋል። ገበሬው መሬቱ ከፍተኛ ጥረት ኣድርጎ እንዳያለማው ስጋት የሚፈጥርበት የባለቤትነት መብቱ በማረጋገጥ በዘላቂነት እንዲያለማው ያደርጋል።

ህወሓት የቀረፀው ፖሊሲ ያለ ዝናብ ሁለት ሳምንት መቆየት የማይችሉ የውሃ ማቆርያ ዘዴዎች ሆረየ፣ ዒላ(ጉድጓድ)፣ ውሃ ባንክ የእርሻ ቦታ በመስኖ ሊያለሙ ቀርተው ለመጠጥ እንኳ ሊጠቅሙ ኣልቻሉም። ለ 25 ዓመታት የፎከረበት ስራው በኣንዲት ጀምበር ድርቅ ድምጥማጡ መውጣቱ የከሸፈ ፖሊሲው ዋነኛ ማሳያ ነው።

ህወሓት እንደ ድርጅት እንደ ያኮረፈ መስማት የተሳነው ሰው የሌሎች ፖርታዎች፣ ሙሁራን ወዘተ የተሻለ ኣማራጭ ሃሳብ የማታዳምጥና የማትቀበል ደንቃራ ድርጅት ኣድርጓታል።

ይሄ “በመቃብሬ” የሚለው የቆየ ዛርዋ ጦሱ ደርሶ ለህዝባች በኣንዲት ኣመት ድርቅ በተፈጠረው ረሃብ መቃብር እያስገባው ይገኛል።

2) መዓድን:_ ።።።።።።።።።።

ትግራይ ለበርካታ ሺ ዓመታት ንቁ ሰብዓዊ እንቅስቂሴ የተካሄደባት ጥንታዊት ምድር እንደመሆንዋ መሬትዋ ለዝናብና ንፋስ እንዲጋለጥ ያስገደደው ሲሆን ይሄ ታራካዊ ኣጋጣሚ ለግብርናው ዘርፍ ከምግብነት የዘለለ ትርፍ ምርት እንዳይሰጥ የሚዳግተው ሲሆን ለመዓድን ሴክተር ግን በተቃራኒው ፀጋ ሆኖለታል። ምክንያቱም በመዓድን ዘርፍ ቅድመ ጥናት ለማካሄድና ፍለጋ ለማድረግ የመዓድኑ ምልክቶች ከላይ ስለሚገኙ ብዙ ጥረት ሳይጠይቅና ምልክቶች በተገኙባቸው ቦታዎች ኣሰሳ እንዲደረግ ይረዳል። ብያንስ የመዓድን ሃብቱ ጥናት ለማካሄድ የሚጠቁሙ ምልክቶች ለማግኘት ቀላል ያደርገዋል። የዚህ ማሳያ በትግራይ ለኢንዳስትሪላዊ ልማት መሰረት የሆኑ እንደ የብረት፣ ወርቅና ሌሎች በርካታ መዓድናት እንዳሉ ተረጋግጠዋል።

ለዚህ ዘርፉ ተገቢው ትኩረት በመስጠት ኢንዳስትሪ ለማስፋፋት፤ ከቁፋሮ እስከ ኣሴት ጨምሮ ለምርት ዝግጁ ማድረግና ወደ ምርት በመቀየር ሂደት ላይ በርካታ ኣዳዲስ የስራ እድል በመፍጠር የስራ ፈላጊ ሃይላችን እንዲረጋጋ፣ የውጭ ምንዛሬ በማስገባት ትልቅ ሚና እንዲጫወት ያደርጋል።

በሃገራችን እንደ ዘንድሮ ዓይነት ድርቅ ሲያጋጥም፣ በኢኮኖሚው ትልቅ ድርሻ ያለው ምርት(ምሳሌ ቡና ) ቀውስ ሲገጥመው ከውድቀትና ከድቀት እንዲያገግም፣ ሃገሪቱ የተረጋጋ ኢኮኖሚ እንዲኖራት ሚዛን እንዲጠብቅ ያግዛል።

3) ኢንዳስትሪ:_ ።።።።።።።።።።

የኢንዳስትሪ ዘርፍ ራሱ የቻለና በራሱ ህልውና እግር የተከለ ሴክተር በማድረግ በሃገሪቱ ኢኮኖሚ የማይተካ ሚና ኖሮት ለዘላቂ ልማት ከፍተኛ ድርሻ እንዲኖረው የሚያስችል ኣቅጣጫ ይይዛል። ይህ ማለት ህወሓት ዕድሜ ልኩ በከንቱ የለፋበትና በምግብ ራሳችን ማስቻል ያቃተውና በዝናብ መዝነብና መቋረጥ ተንጠልጥሎ ካለው የግብርና ዘርፍ ጥገኝነት በማላቀቅ ባገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ኣወንታዊ ኣስተዋፅኦ ማድረግ እንዲችል ማድረግ ግድ ይላል። ኢንዳስትሪ ከግብርና ተረፈ ምርት ተተከል የምንለው ሳይሆን ራሱን ችሎ በመንቀሳቀስ በግብርና ምርታማነትም የራሱ ኣወንታዊ ሚና የሚጫወት ዘርፍ ማድረግ ይጠይቃል።

እንደ የመዳበርያና የተለያዩ የእርሻ መሳርያዎች በማምረት ህብረተሰቡ በቀላል ዋጋ ገዝቶ እንዲጠቀምና ከዕዳ ነፃ እንዲሆን ያግዛል። ግብርና መር ኢንዳስትርያላዊ ዕድገት ኣዋጪነት ባለፉት 25 ዓመታት ተሞክሮ የወደቀ ከመሆኑ በላይ ዋና መገለጫው ረሃብ፣ ልመናና ስደት ሆነዋል።

4) ቱሪዝም:_ ።።።።።።።።።

ሃገራችን ኢትዮጵያ በርካታ የስልጣኔ ውጤት የሆኑ ቅርሶች፣ የሃይማኖት ስፍራዎች፣ የሰው ዘር መፍለቅያነታችን ያረጋገጡ የቅሪት ኣካላት መገኛ ቦታዎች፣ ውብ ተፈጥሮኣዊ የመሬት ኣቀማመጥ፣ የእንስሳ ማቀፍያ ፓርኮች፣ የብሄር ብሄረሰቦች ኣናኗርና ባህሎች፣ ታሪካዊ የጦርነት ቦታዎች ወዘተ ያላት ሃገር እንደመሆናዋ መጠን ትኩረት ሰጥተን ካለማነው በኢኮኖሚው ላይ የማይተካ ሚና መጫወት ይችላል። ቱሪዝም ወደ ትግራይ ክልል ብናመጣው ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖሮዋል ቢቻ ሲሆን በኢኮኖሚው ከፍተኛ ኣስተዋፅኦ ይኖረዋል።

5) ኣገልግሎት( ሰርቪስ)ና ትራንስፓርት :_ ።።።።።።።።።።።።

ሃገራችን ያላት እምቅ ሃብት በኣግባቡ መጠቀም ስትችል ከፍተኛ የሆነ የሰው እንቅስቃሴ መፈጠሩ ግድ ይሆናል። ይህ ፈጣን የሰዎች እንቅስቃሴም በጠንካራ ብቁ ኣገልግሎት ሰጪና የትራንስፖርት ተቋማት ሊደገፍ ይገባል። እነዚ ዘርፎችም በኣገሪቱ ልማት የራሳቸው ኣወንታዊ ኣስተዋፅኦ በማበርከት ጤነኛ ኢኮኖሚ እንዲኖር ያግዛሉ።

እነዚህና ሌሎች በርካታ ኣዋጪ ኣማራጭ ፖሊሲዎች ወደ ትግበራ የሚለወጡት እንደየ ኣከባቢው ሃብተ ገነት መሰረት ያደረገ ኣፈፃፀም ይኖራቸዋል።

ለምሳሌ የፖሊሲ ኣቅጣጫው በትግራይ ክልልና ኦሮምያ ሊለያይ ይችላል። በትግራይ ከግብርና ይልቅ በቱሪዝም ትኩረት ሰጥቶ መስራት በንፅፅር የተሻለ ውጤታማ ሲሆን በኦሮምያ ደግሞ ከቱሪዝም ይልቅ በግብርና የበለጠ ቱክረት ቢደረግ ኣዋጪ ሊሆን ይችላል። ይህ ሲባል ሌሎች ዘርፎች ኣይሰራባቸውም ማለት ኣይደለም።

ኣንድ ሃገር ስር ሁነን የተለያየ የፖሊሲ ኣቅጣጫና ትኩረት ማድረግ ያለው ጠቀሜታ ያለው የሃገሪቱ የካፒታል ሃብት በተገቢ ስራ እንዲውል፤ በተገቢው ጥረት በማድረግ ተመጣጣኝ ውጤት እንድናስመዘግብ ያስችለናል። የዚህ ኣፈፃፀም በማይሰማህ ታቦት በመፀለይ የሚባክን ግዜ፣ ገንዘብና ጉልበት እንዳይባክን ይረዳል።

ይሄ ተመጣጣኝ የፖሊሲ ኣቅጣጫ የተረጋጋ ማህበረ ኢኮኖሚና እንዲኖረን ያግዛል። በኣሁኑ ግዜ ከተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች ወደ ኣዲስ ኣበባ እንደሚደረገው ፍልሰትና መሰል ችግሮች በማስቀረት ተመጣጣኝ የኣገልግሎት ስርጭት ኢንዲኖር ያግዛል።

እነዚ ፖሊሲዎች ከነፃ የገበያ ስርዓት፣ ተመጣጣኝ የሃብት ክፍፍልና ማፍራት መብት፣ ዲሞክራስያዊና ሰብኣዊ መብቶች መከበር፣ የመሬት ባለቤትነት መብት፣ ነፃ ሲቪክ ማህበራት መኖር፣ የሕግ የበላይነትና የዳይነት ነፃነት መኖር፣ ሃሳብክን በነፃነት የመግለፅ መብት፣ የሚድያ ነፃነት ወዘተ ከማረጋገጥ ጋር ሲቀናጅ ሃገራችን ከፍ ወዳለ የብልፅግና ስፍራ ትጓዛለች፤ ዜጎቻችን የተረጋጉና ደስተኞች ይሆናሉ፤ ሁሉም ሰው ሃላፊነት የሚሰማውና ትጉ ዜጋ ይሆናል፤ ዜጎች ራስ በራሳቸው የሚከባበሩና የሚዋደዱ ደጋጎች ይወጣቸዋል፤ ኣገራቸው በእኩል ደረጃ የሚወዱና የሚጠብቁ ይሆናሉ፤ ህዝቦች ጠላት ድምበራችን ጥሶ ሲመጣባቸው ብቻ ሳይሆን በሰላማቸው ግዜም በኣንድነት የሚቆሙ የፍቅር ተምሳሌት ይሆናሉ ።

ህወሓት በ25 ዓመታት የስልጣን ዘመኑ ያስገኘልን ብቸኛው ለውጡ 15 ሚልዮን በረሃብ ተይዞ እጆቹ ለለጋሾች የሚጠብቅ ህዝብ ነው።

እነዚህ ኣማራጮች ከዓረና_የተወሰኑት ተቀንጭበው የቀረቡ ናቸው። ሃሳቦቻቹ እንጠብቃለን።

ነፃነታችን በእጃችን ነው።

IT IS SO……!

የህብር ሬዲዮን ዘገባ ህብር ሬዲዮን ከድህረ ገጻችን በተጨማሪ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው። በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 እና በአውስትራሊያ 0280725172 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን ወይም ከgoogel store Hiber radio አፕሊኬሽንን ዳውን ሎድ በማድረግና  ከዘሐበሻም ማዳመጥ ይቻላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *