Hiber Radio: ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የምስክርነት ቃሉን ሰጠ- ‹‹የህሊና እስረኛ ነኝ›› እስክንድር ነጋ

Esekender_Nega_pen_awareded_01

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርቧል ። የህሊና እስረኛ መሆኑን ደግሞ አስረግጦ ነግሯቸዋል። በመጻፉ፣ሀሳቡን በመግለጹ ያለ ወንጀሉ ወንጀል ተለጥፎለት እንደ ቀሩት የህሊና እስረኞች መስዋእትነት እየከፈለ ነው።ዛሬም እስክንድር ይፈታ ስንል ተመስገን፣የሱፍ፣ውብሸት፣አንዷለም፣ሀብታሙ፣እነ አቡበከርና ሌሎቹም የህሊና እስረኞች ይፈቱ ማለታችን ነው። የዛሬውን የፍርድ ቤት ውሎ ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቦታል።ይከታተሉት።

በሽብርተኝነት ወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ 18 አመት እስር ተፈርዶበት በእስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የመከላከያ ምስክርነት ቃሉን ሰጥቷል ሲል ነገረ ኢትዮጵያ ዘገበ። በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ አንደኛ ተከሳሽ ለሆነው አቶ ዘላለም ወርቃገኘሁ መከላከያ ምስክር ሆኖ ልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ከእስር ቤት የቀረበው ጋዜጠኛ እስክንድር ዛሬ ጥር 27/2008 ዓ.ም ምስክርነቱን ሊያሰማ ችሏል፡፡ ያለጠበቃ በግሉ የሚከራከረው ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ ጋዜጠኛ እስክንድር እንዲያስረዳለት የሚፈልገው ጭብጥ ጡመራ ምንድነው፣ ከወንጀል ጋርስ ግንኙነት አለው ወይ፣ እና ሰብዓዊ መብት እና ዴሞክራሲ ላይ ስልጠና ስለሚሰጡ ድርጅቶችና የስልጠናው ይዘትን በተመለከተ እንደሆነ ቢያስታውቅም በጭብጡ ላይ አቃቤ ህግ ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡ በዚህም አቃቤ ህግ ጡመራ ምንድነው፣ ወንጀልስ ነው ወይ የሚለው በምስክር ሳይሆን በህግ ድንጋጌዎች የሚረጋገጥ እንደሆነ በመግለጽ ተቃውሟል፡፡ ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን ከሰማ በኋላ ጡመራ ወንጀል ስለመሆን አለመሆኑ የተያዘውን ጭብጥ ውድቅ በማድረግ ስለ ስልጠናውና አሰልጣኝ ተቋማት የተመዘገበው ጭብጥ ላይ ምስክሩ እንዲመሰክሩ ብይን ሰጥቷል፡፡ ብይኑን ተከትሎ ምስክሩ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ችሎት ፊት የቀረበ ሲሆን በመጀመሪያ በፍርድ ቤቱ የቀረቡለትን ጥያቄዎች መልሷል፡፡ ምስክሩ ሙሉ ስሙን፣ እድሜውን፣ ስራውንና ለምን እንደመጣ፣ እንዲሁም ከተከሳሾች ጋር ስለመተዋወቁ ለቀረቡለት ጥያቄዎች መልስ ሰጥቷል፡፡ እስክንድር ‹‹ስራ›› ተብሎ ሲጠየቅ፣ ‹‹ጋዜጠኛ ነበርኩ›› ብሏል፡፡ ‹‹አሁንስ›› የሚል ጥያቄ ፍርድ ቤቱ አቅርቦለት፣ ‹‹አሁን የህሊና እስረኛ ነኝ›› ሲል መልሷል፡፡ ተከሳሹ ዘላለም ወርቃገኘሁ በዋና ጥያቄ ተከሳሹ ውጭ ሀገር ሊወስደው ነበር ተብሎ በክሱ ላይ ስለተጠቀሰው ስልጠና ምስክሩ እንዲያብራሩለት ጠይቋል፡፡ ምስክሩም ‹‹ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሀገራትንም የሚያሳትፍ ስልጠና በሰብዓዊ መብት፣ በሚዲያ ‹ኢቲክስ›፣ እና በዴሞክራሲ ላይ ይሰጣሉ፡፡ ድርጅቶቹ የተለያዩ ቢሆንም በሰብዓዊ መብት ጉዳይ ላይ መርሃቸው ተመሳሳይና ዓለም አቀፍ ነው›› በማለት መስክሯል፡፡ ድርጅቶቹን በስም መጥቀስና የሚገኙበትንም ሀገር ለፍርድ ቤቱ መግልጽ ይቻል እንደሆነ ምስክሩ ተጠይቆ ‹‹የተቋማቱ መገኛ ምዕራቡ ዓለም ነው፡፡ በዴሞክራሲ የዳበሩ ሀገራት ነው ዋና መቀመጫቸው፡፡ ሲ.ፒጄ፣ ፍሪደም ሀውስ፣ አምንስቲ ኢንተርናሽናል እና አርቲክል 19 የመሳሰሉትንም በስም መጥቀስ ይቻላል፡፡ እኔም ከነዚህ ተቋምት ውስጥ በአንዱ የተሰጠ ስልጠና አዲስ አበባ ላይ ተካፍየ ነበር፡፡ ስልጠናው ስለ ሰብዓዊ መብት፣ ስለ ሚዲያ፣ ስለ ዴሞክራሲ የሚያስተምር ነው፡፡ ስልጠናው ከሽብር ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፤ ይህ እንደማስረጃ መቅረቡ ኢትዮጵያን ትዝብት ውስጥ የሚከትና የሚያሳዝን ነው›› ሲል ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ መቼ እንደታሰረ በመስቀለኛ ጥያቄ ተጠይቆ ‹‹መስከረም 2004 የሀሰት ክስ ቀርቦብኝ፣ በግፍ ተፈርዶብኝ ታስሬ እገኛለሁ›› ሲል መልሷል፡፡ እስክንድር ነጋ ጥቁር ሱፍ በደብዛዛ ሸሚዝ ለብሶ፣ ሙሉ ጥቁር መነጸር አድርጎና ነጠላ ጫማ ተጫምቶ ችሎት ፊት ቀርቧል፡፡ አንደኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ ምስክሩ ምስክርነቱን ማጠቃለሉን ተከትሎ በመከላከያ ምስክርነት እንዲቀርቡለት የጠራቸው ሌላኛው ምስክር አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በተደጋጋሚ እንዲቀርቡለት ትዕዛዝ እንዲሰጥለት የጠየቀ ቢሆንም እስካሁን አለመቅረባቸው መንግስት ግለሰቡን ለማቅረብ ፍላጎት እንደሌለው ያሳያል ሲል ቅሬታውን አሰምቷል፡፡ ‹‹አሁን የተረዳሁት ነገር ከሳሼ የሆነው መንግስት አቶ አንዳርጋቸውን ከሚያቀርብ እኔን በነጻ መልቀቅ እንደሚቀለው ነው›› ብሏል ተከሳሹ፡፡ ተከሳሹ ከአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጋር በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች እንደተገናኜ አቃቤ ህግ መጥቀሱን በማስታወስ ምስክሩ መቅረባቸው ያለውን ተገቢነት አስረድቷል፡፡ ‹‹ምስክሩ እንዲቀርቡልኝ እፈልጋለሁ፡፡ ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ፍርድ ቤቱ ከምስክሩ ጋር በተገናኘ ያለውን የክሱ ፍሬ ነገር አውጥቶ በቀሪው ላይ ብይን ይስጥልኝ›› ብሏል ተከሳሹ አቶ ዘላለም፡፡ ፍርድ ቤቱም ምስክሩ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንዲቀርቡ ትዕዛዝ በመስጠት ምስክርነታቸውን ለመስማት በሚል ለየካቲት 16/2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ህብር ሬድዮን በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ 01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *