Hiber Radio: ፈተናን መስረቅ ለስብሃት ነጋ ትግል ለሌላው ወንጀል ያደረገው ማነው ? ግልጽ ደብዳቤ ለክቡር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር

oromo-protest-fetena-001

የአገራችን የሰሞኑ አብይ ፖለቲካ መነጋገሪያ <<የ12ተኛ ብሔራዊ ፈተና አስቀድሞ ተሰርቆ መውጣት>> እና ተያይዞ የመጣው የስርዓቱ የተለመደ አስቂኝ መግለጫ ነው። <<ፈተና አልተሰረቀም ፣ፈተናው ተሰርቋል>> የሚሉት መግለጫዎች በእርግጥም አገሪቱን የሚመሯትን ሰዎች አቅም ጭምር ያጋለጠ ነው። የፈተናውን መሰረቅ የትግል አካል አድርገው ላልቆጠሩ የሚያቀርቡት መከራከሪያ የተምታታ ነው። ፈተናውን መስረቅ እንደ ትግል ስትራቴጂ ለቆጠሩት ብቻ ሳይሆን ውለው አድረው ለገባቸውም ድርጊቱ ውጤታማ አንዱ የሰላማዊ ትግል ስልት አካል ነው። አገር ተጎዳ የአገር ሀብት ወደመ የሚሉት ይሄ በጥቅል የሚቀርቡ ጉንጭ አልፋ መከራከሪያዎች ለሞኑ የአገር ሀብት የሚባክነው በነማን ነው የሚል ጥያቄ ራሳቸውን እንዲጠይቁ የሚያስገድድ ነው።። ስብሃት ነጋ በአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ታጋይነታቸውን ሲዘክሩ በረሃ ከመውረዳቸው በፊት የትምህርት ቤት ዳይሬክተር እያሉ የ12ተኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ሰርቀው፤ መልስ ተዘጋጅቶ የትግራይ ተማሪዎችን መጥቀማቸውን የተናገሩትን አንረሳም። ያኔ ስብሃትን ሲያሞግሱ የነበሩ የስርዓቱ ደጋፊዎች ዛሬ ስድስት ወር ሙሉ መከራቸውን ሲያዩና በባዶ እጃቸው ስለተቃወሙ ፍዳ ሲበሉ ለነበሩ የኦሮሞ ተማሪዎች ፈተና ስላልተራዘመ ለጉልበት ውሳኔ የተሰጠውን የአጸፋ ምላሽ ከትግል አለመቁጠር ያስተዛዝባል።ቤተሰብ ይጎዳል፣የተማሪዎች ሞራል እና የመሳሰለው ጉዳይ ማንሳቱ ባይከፋም የዚህ ሁሉ መዘዝ ግን ስልጣን በጠመንጃ ይዘው እኛ ያልነው ካልሆነ ለሚሉት እምቢኝ በቃን ማለት የታየበት ግልጽ እርምጃ ነው። ዛሬም ሲደናበሩ የተሰረቀውን ፈተና በሮመዳን ጾም ፍቺ ወቅት ማድረግ ያው የተለመደው እብሪት ነው። በጨዋ ቋንቋ የቀረበላቸው ግልጽ ደብዳቤ ነገ ሌላ ጫጫታ ከማምጣቱ በፊት ቆም ብለው እንዲያስቡ ይጠይቃል። የኦሮሞ ሰላማዊ ተቃውሞ አራማጆች ተከታዩን ግልጽ ደብዳቤ ጽፈዋል። ልብ ያለው ልብ ይበል ነው። እነ ለአገር ተቆርቋሪዎች አሁን ለመንግስታችሁ ጮክ ብላጭሁ ይህቺን ደብዳቤ አንብቡለት።

ለክቡር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር

ጉዳዩ: የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ፈተና (EUEE) በተመለከተ ፍትሃዊ የሆነ የመርሃግብር ምክረ ሃሳብ (program proposal) ስለማቅረብ ይመለከታል።

የተሰረዘውን ፈተና በተመለከተ መስሪያ ቤትዎ ያወጣውን መርሀ ግብር ተመልክተነዋል። ሆኖም ግን መርሃግብሩ ከታች በተገለጹት ምክኒያቶች ሊሻሻል ይገባዋል ብለን ስለምናምን የሚከትለውን ምክረ-ሀሳብ ልናቀርብ እንወዳለን። በደንብ ሊጤን የሚገባው ነጥብ ይህንን ምክረ-ሀሳብ በማጥናቀር ሂደት ውስጥ ከ5000 በላይ ተማሪዎች በግልጽ በሶሻል ሚዲያ ሀሰባቸውን ሰጥውበታል። 123 መምህራንን ከሁሉም የኦሮሚያ ዞኖች በቀጥታ አማክረናል። ተማሪዎቹም ሆኑ መምህራን በዋናው ጉዳይ ተመሳሳይ አቋም አንጸባርቀዋል። የተማሪዎቹም ሆነ የመምህራኑ ሀሳብ የሚያመለክተው በመስሪያ ቤትዎ ለድጋሚ ፈተናው የተሰጠው የአንድ ወር ጊዜ በቂ አለመሆኑንና ጊዜውን ማራዘሙ ግዴታ ነው የሚል ነው። አብዛኛዎቹ የኦሮሚያ ተማሪዎች (80%) ያመለጥንን የ6 ወራት ትምህርት ለማካካስ እና ለፈተናው ለመዘጋጀት ቢያንስ 12 ሳምንታት ወይም 3 ወራት ያስፈልግናል ብለዋል።

እንደአዲስ የወጣው የፈተና መርሀ ግብር ከጊዜ ማጠር በተጨማሪም ሌላ ግድፈት እንደለው ከተማሪዎች እና መምህራኖች ጋር ባደርግነው ምክክር ተገንዝበናል። ይሄውም መርሃግብሩ በረሞዳን ጾም ወር መጨረሻ ላይ መሆኑ በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ትክክል አንዳልሆነ ተረድተና።

1) ሳይንሱም እንደሚያረጋግጠው የሰው ጭንቅላት (brain) በፈተና ጊዜ በደንብ ለማሰብ ከፍተኛ የምግብ ሃይል አቅርቦት (high energy supply) ይጠቀማል። የጾም ወቅት ደግሞ የጿሚዎቹ ጭንቅላት ባንጻራዊ መልኩ ሃይል-አጠር (hypo) ስለሚሆን ጿሚ ተማሪዎችን በእንደዚህ ዓይነት ወቅቶች ለዛውም ሙሉ ቀን ረጃጅም ፈተናዎች ላይ እንዲቀመጡ ማድረግ አይመከርም። በተለይ ደግሞ ጉዳዩ ሃይማኖታዊ ሆኖ የሚጾሙና የማይጾሙ ተማሪዎች የሚወስዷቸውን ፈተናዎች በእንደዚህ ዓይነት ወቅቶች መስጠት ትክክል አይደለም ። ግልጽ የሆነ መድሎ (clear discrimination) የማድረግ ያህልም ሊቆጠር የሚችል፤ ማህበራዊ መተሳሰብን ብሎም ህገ-መንግስቱን የሚጥስ ነው።

2) በድጋሚ ባወጠችሁት መግለጫም ፈተናው የኢድ አልፈጥርን ቀን እንደሚዘል ገልጻችኋል። ይህ ማለት በኢድ ዋዜማ እና በማግስቱ ፈተና ይኖራል ማለት ነው። በማህበረሰባችን የበዓላት ሰሞን በግርግርና ለፈተና ትኩረት ፍጹም በማይመቹ (exam mood eroding) ማህበራዊና ቤተሰባዊ መስተጋብሮችና ፌሽታዎች የተሞላ መሆኑን ሁላችንም የምናውቀው ሃቅ ነው። ይህ ደግሞ ተረጋግቶ ለማጥናት የሚያስቸግር ከባባዊ ሁኔታ (distractive environment) በመፍጠር ተማሪዎች ለፈተናው ሙሉ ትኩረት እንዳይሰጡ ያደርጋቸዋል። እናም ፈተናን በእንደዚህ ዓይነት ትልቅ ዓመት በዓል ወቅት ማድረግ ለሃይማኖቱ ተከታይ ተማሪዎች ከፍተኛ ጉዳት እንደሚኖረው ግልጽ ግልፅ ነው።

የምናቀርበው ምክረ-ሃሳብ በተማሪዎቹ ምቾትና አስተያየት ላይ ብቻ በመመርኮዝ እንዳይሆን ሌሎች ባለ ድርሻዎችንም አማክረናል። አዲሱ ፈተና ተዘጋጅቶ፣ ታርሞ ውጤቱ እስኪታወቅ ድረስ ያለውን ሂደት ከግንዛቤ በማስገባት፣ ከዚህ በፊትና አሁንም በትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ በፈተና ጉዳዮች ላይ የሰሩ ባለሟያዎችን አማክረናል። እንዲሁም ፈተናው የዩኒቨርሲቲዎችን የሚቀጥለውን አመት መርሀግብር ሊያውክ ስለሚችል ፕረዚደንቶችን ጨምሮ የተለያዩ የዩኒቨርሲቲ መምህራንና የአስተዳደር ዘርፍ ሰራተኞችን አማክረናል።

ስለሆነም ከዚህ በላይ ከገለጽናቸው ምክኒያቶችና ባሰባሰብናችው ሙያዊ አስተያየቶች ላይ ተመርኩዘን ከዚህ ቀጥሎ የተዘረዘሩትን የመረሃግብር ምክረ ሃሳቦችን እናቀርባለን። ለተፈጻሚነታቸውም ከእርሶ መስሪያ ቤት በኩል በጎ ምላሽ እንደሚኖር ተስፋ እናደርጋለን:

1) ለተማሪዎቹ ሁለት ወር ቢሰጣቸው እና ፈተናው ከሃምሌ 25 እስከ 28 ወይም ከዚህ ጊዜ በኋላ በሚመቻቹ ወቅት ቢሆን ፍትሃዊ ይሆናል።

2) ባሉት ሁለት ወራት ውስጥ ተማሪዎች በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ ከዚህ ቀደም ያስረከቧቸው መጽሃፍትና ሌሎች የጥናት መርጃ መሳሪያዎች ቢመለስላቸው ጥሩ ይሆናል።

 

3) በተለይም በኦሮሚያ ተማሪዎች ላልተማሯቸው ክፍለጊዜዎች መምህራኑ ማካካሻ (make up classes) እንዲሰጧቸው ማድረግ ያስፈልጋል። ክረምቱ የእረፍት ጊዜያቸው መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባት ለመምህራኑ ማበረታቻ (incentives) የሚደረግበት መንገድ ቢዘጋጅ።

4) ጊዜው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለእረፍት ወደ ቤታቸው የሚመለሱበት በመሆኑ እነዚ ተማሪዎችም የየኣካባቢዎቻቸውን ተፈታኝ ተማሪዎች በቱቶር ማስጠናት ወይም በሌሎች መንገዶች ለፈተናው ዝግጅት ይረዷቸው ዘንድ የማበረታቻ መንገዶች ቢመቻቹ።

5) ለክረምቱ ወደየትውልድ ቦታቸው የሚመልሱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለተፈታኞቹ የማስጠናት (tutorial) ድጋፍ እንዲሰጡ ትምህርት ቤቶች እና የአስተዳደር ክፍሎች ሁኔታዎችን እንዲያመቻቹ ማድረግ።

6 ) በተለይም በኦሮሚያ አካባቢ በፖሊስና በመከላከያ ሃይሎች በተማሪዎች ላይ የሚደረገው ወከባና ተጽዕኖ እንዲቆም፣ እነዚ የታጠቁ አካላት ከትምህርት ቤቶች አካባቢ እንዲርቁ፣ የታሰሩ ተማሪዎችም ተለቀው ከላይ በተጠለተው መልኩ ለፈተናው ዝግጅት እንዲጀምሩ ቢደረግ።

በመጨረሻም፣ ከዚህ በፊት የወሰድናቸው እርምጃዎችም ሆኑ አሁን ያቀረብነው ምክረሃሳብ መነሻነቱ ፍትሃዊነት፣ የእኩል እድል ተጠቃሚነት እንዲሁም የተወዳዳሪነት መርህን የተከተለ የፈተና ስርዓት በሃገሪቱ እንዲረጋገጥ ማድረግ እንደሆነም ደግመን መግለጽ እንወዳለን። ለዚህም ከኛ በኩል ያለውን መልካም ፈቃድ (good faith) ይበልጥ ለማረጋገጥ በእጃችን ያሉትን ሌሎቹን የፈተና ቡክሌቶች ሚስጥራዊነት እንደምንጥብቅና አዲስ ለምታዘጋጁት ፈተናዎች ሚስጥራዊነት መጠበቅም የበኩላችንን አስተዋጽዕ እንደምናደርግ ቃል እንገባለን። ያቀረብነውን ምክረሀሰብ በሚገባ አጢናችሁ በበኩላችሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ባለጉዳዮች አማክራችሁ ፍትሃዊ ውሳኔ ላይ እንደምትደርሱ ተስፋ እናደርጋለን። ነገር ግን አሁን ያቀረብነው ምክረሀሳብ ወደጎን ተትቶ፣ እንደክዚህ በፊቱ የኦሮሚያ ተማሪዎች እሮሮ ጆሮ ዳባ ልበስ ተብሎ ፍርደገምድል በሆነ መልኩ አሁን የተቀመጠውን የፈተና መርሃ ግብር ወደ ማስፈጸም የምትሄዱ ከሆነ በእርግጥኝነት ለሚደርሰው ዳግም ሀገርዊ ኪሳራ ተጠያቂነቱ የትምህርት ሚኒስቴር መሆኑን ከወዲሁ ልናስጠነቅቅ እንወዳለን።

ከሰላምታ ጋር!

#‎OromoProtests

 

ግልባጭ፡

-ለኢፌድሪ ፕረዚደንት ጽ/ቤት

– ለኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት

– ለኢፌድሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ጽ/ቤት

– ለኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ፕረዚደንት ጽ/ቤት

– ለጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ጽ/ቤት

– ለሁሉም ክልሎች ትምህርት ቢሮዎች

– ለመላው የኢትዮጲያ ህዝብ

-ለሁሉም የ 12ኛ ክፍል ተፈጣኝ ተማሪዎች

– ለሁሉም ኢትዮጵያ ተኮር ሚዲያዎች

ህብር ሬድዮን በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ ከ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *