Hiber Radio: በጥቂቶች የተማረከው የኢትዮጵያ “አስደናቂ” እድገት – አክሎግ ቢራራ (ዶር)

dr akelog with kelem kened -hiber radio

(ከቀለም ቀንድ ጋዜጣ ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ)

የቀለም ቀንድ

  1. ኢትዮጵያ ላለፉት ዐሥርት ተከታታይ ዓመታት ባለሁለት አሃዝ እድገት ማስመዝገቧ በመንግሥት በኩል ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ በመንግሥት በሚገለጸው አሃዝ ባይስማሙም ዓለም አቀፍ ተቋማትም እድገት መኖሩን ሲናገሩ ቆይተዋል፡፡ እነዚህ ተቋሞች መረጃውን ከየት ያገኛሉ፤ እንዴት ያረጋግጣሉ፤ ተመሳሳይ የሆኑ አገሮች አሉ፤ ማለትም በመረጃ በኩል በመሬት በሚ ታየውና  አበዳሪዎችና ደጋፊዎች በሚሉት መካከል?

ዶር/አክሎግ

ይኼን ቁልፍ ጥያቄ ለመመለስ መጀመሪያ ሕዝብ የእድገቱ ውጤት ተጠቃሚ ሊሆን የሚችለው መብነቱና ነጻነቱ በሕግ

አስተማማኝ ሲሆን ብቻ ነው በሚለው እንስማማ። በተደጋጋሚ በማስረጃ እንዳሳየሁት፤ በነጻነትና በፍትሃዊ እድገት

መካከል ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት አለ። ነጻነት የሌለው ሕዝብ የንብረቱ ብቻ ሳይሆን የህይወቱ ባለቤት ሊሆን

አይችልም። ነጻነት የሌለው ሕዝብ በቀላሉ ለኪራይ ሰብሳቢዎች፤ ለጉቦኞች፤ ለሙሰኞች፤ ከሃገር በገፍ ኃብት ሰርቀው

ለሚያሸሹ ክፍሎች ሰለባ የሚሆነው ድምጽና ነጻነት ስለሌለው ነው። በሌላ አነጋገር ሕዝቡ በራሱ የተፈጥሮ ኃብት

ተገዥ እንጅ አዛዥ አይደለም። የመሬት ነጠቃ ይኼን ሃቅ በየቦታው ያሳያል። ወደ ጥያቄው ስመለስ፤ ስለ እድገታዊ

መንግሥት ሚና በአጭሩ ለማቅረብ እገደዳለሁ። ለእኔ፤ ዘላቂነትና ፍትሃዊነት ያለው እድገት ማለት የጋራ አገርን

የተፈጥሮ፤ የሰውና ሌሎች ጥሪቶችንና ኃብቶችን ኃላፊነትና ዘላቂነት ባለው መልክ ተጠቅሞ የጋራ ህይወትን (የሁሉምን

ዜጎች)፤ የግልና የጋራ ኑሮን ማሻሻል ማለት ነው። የአገር ጥቅላላ ገቢ አድጓል የሚለው ብቻውን የኑሮን መሻሻል

አያሳይም። ለምሳሌ፤ ድርብ አሃዝ እድገት አለ የሚለው ለኦሞ ሸለቆ ወይንም ለጋምቤላ ሕዝብ ትርጉም የለውም።

ምክንያቱም፤ በአብዛኛው ይህ ሕዝብ የራሱ የተፈጥሮ ኃብት እድገት ውጤት ተጠቃሚ አልሆነም። በኢትዮጵያ ሕዝብን

ያማከለአና ዋና ኢላማ ያደረገ እድገት የለም። በሌላ አነጋገር፤ ፍትሃዊ የእድገት ውጤት ስርጭት የሚባል ነገር

ኢትዮጵያ የለም። ነጻነት ከሌለ ምንም አይታሰብም። የእድገቱ ውጤት ስርጭት ፍትሃዊ ነው ሊባል የሚችለው በተቻለ

መጠን ሁሉም ዜጎች መብታቸውና ነጻነታቸው ተከብሮ የእድገቱ ተጠቃሚ ሲሆኑ ብቻ ነው። እድገት ዘላቂነት

የሚኖረውም ሕዝብን በሙሉ ለማሳተፍና አቅሙን ለማጎልመስ ሲቻል ነው፤ ነጻነትና ሙሉ ተሳትፎ ለፍትሃዊ እድገት

መሰረት ነው የምለው ለዚህ ነው። የፍትሃዊነትና የዘላቂነት መሰረት ያለው እድገት በተፈጥሮና በሌላ ችግር ወቅት

(ለምሳሌ የተፈጥሮ ርሃብ) በራሱ ሊተማመንና ተመልሶ ሊያንሰራራ ይችላል (Resliency) ይኖረዋል። ራስን በራስ

የመጠገንና የማሻሻል አቅም ይኖረዋል። አለያ፤ እድገቱን ለመቀጠል መበደር አስፈላጊ ይሆናል። ተበድሮ መክፈል

የሚባል ነገርም አለ።

 

ዓለም ባንክ ለሰላሳ ዓመታት ስሰራ “የእድገት መስፈርቶች?” ምንድን ናቸው የሚለው ጥያቄ ተደጋግሞ ይነሳ ነበር።

እድገት የአገርን የተፈጥሮና የሰው ኃብትን በሃላፊነት፤ በጥንቃቄ፤ በስልትና በእቅድ ተጠቅሞ ዘላቂነትና ፍትሃዊነት

ያለው፤ በተቻለ መጠን አገር ተከል የሆነ የልማት መሰረት መጣል ነው። ለዚህ ቁልፍ ሚና የሚጫወተው ጥሩ ሕዝብን

መአከል ያደረገ አገዛዝና ጥበባዊ አመራር ነው። በሊቃውንት አነጋገር፤ የስራ እድል ፈጥሮና የምህርት ኃይሎችን አሳድጎ

ጠቅላላ የአገርንና የነፍስ ወከፍ ገቢን በተከታታይ በመጨመር የአብዛኛውን ሕዝብ ህይወት ማሻሻል የሚለው እድገትን

ያጠቃልለዋል። ሗላ ቀር እና ድሃ የሆነው የገጠር ኢኮኖሚ ዘመናዊ ሆኖ ከከተማው ኢኮኖሚ ጋር ጠንካራ ግንኙነት

ይኖረዋል። ገጠሬው የፍጆት እቃዎች መግዛት ይጀምራል፤ ልጆቹን ያስተምራል፤ ጤናው ይሻሻላል። ቀደም ሲል እንደ

መሰረታዊ የእድገት መስፈርት ይጠቀሱ የነበሩ ሞዴሎች አሉ። በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ የነበረው የእድገት ሞዴል

ከታች ወደላይ የሆነ ወደጎን ያልተያያዘ የእዝ ሞዴል ነበር። በ1970ዎቹና በ1980ዎቹ ዓመታት በዓለም ባንክ እና

በአይኤም ኤፍ ይገፋ የነበረው የመዋቅራዊ ለውጥ ሞዴል ብዙ ማህበረሰባዊ ችግሮችን እንዳስከተለ ይነገራል።

በ1990ዎቹ ዓመታት ዋናው መርህ ከዓለም ትሥስር ጋር በተያያዘ መልኩ ንግድ፤ የውጭ ኢንቬስትመንትና የውጭ

እርዳታ አስፈላጊነት መርህ ይታይ ነበር። የዓለም ትሥስር (Globalization) ለታዳጊ አገሮች መድህን ነው የሚለው

ገበያ ደርቶ ቆይቷል። ለእኔ የዓለም ገበያና ልቅ የሆነ የውጭ ኢንቬስትመንት አከራካሪ ስልሆነ ሞዴሉ ይሰራል የሚል

እምነት የለኝም። አሁንም በያዝነው በ2000ዎቹ “የነጻ ገበያ (free market and economic liberalism) እና ለይስሙላ

የሚነገረው የመልካም አገዛዝ” አስፈላጊነት አከራካሪ የሆነ ተቀባይነት አግኝተዋል። በአጭሩ የእድገት ጎዳናዎች የተለያዩ

ናቸው።

የምስራቅ ኤዢያና ፓሲፊክ አገሮች–ሲንጋፖር፤ ሆንግኮንግ፤ ታይዋን፤ ደቡብ ኮሪያ፤ ታይላንድ፤ ቀደም ሲል ጃፓን

ወዘተ ተዓምራዊ እድገት ከውጭ ንግድ ጋር በተያያዘ ሁኔታ አሳይተዋል። የአፍሪካና የላቲን አሜሪካ አገሮች ወደኋላ

ቀርተዋል የሚለው ብሂል በእድገት ሊቃውንት ዘንድ አነጋጋሪ ሆኖ ነበር። አንዳንድ ተመልካቾች የቻይኒስ ቋንቋ

ተናጋሪዎች እና የኮንፉሼየስ እመንት ያላቸው አገሮች የስነምግባራቸው፤ ባህላቸው፤ ታሪካቸው፤ የስራ ልምዳቸው፤

ለክፉ ቀን የሚሆን የቁጠባ፤ የመረዳዳትና የመደጋገፍ ልምዳቸው፤ አገር ወዳድነታቸው፤ የራሳቸውን ባህል አስከብረው

የውጩን የእድገት፤ ለምሳሌ የሳይንስና ቴክኖሎጅ ባህል መቀበላቸው፤ ብድርን ለኢንዱስትሪና ለእርሻ ዘመናዊነት

መጠቀማቸው፤ የአገር ውስጡን የገበያ ፍላጎት አሟልተው ለውጭ አቅርቦት የተለያዩ ምርቶች ማቅረባቸው ወዘተ

ይለያቸዋል ይባል ነበር። ቻይኒሶች ረጅም ታሪክ፤ የታወቀ ስልጣኔ፤ የንግድ፤ የኢንዱስትሪና ሌላ ልምድ አላቸው።

ደቡብ ኮሪያስ? ታይላንድስ? አሁን ደግሞ ቬትናምስ? ኢንዶኔዢያስ? ሞሪሺየስ፤ ቦትስዋና፤ ደቡብ አፍሪካና ሌሎችስ?

በላቲን አሜሪካ ችሌስ? ኮስታ ሪካስ? ብራዚልስ? ወዘተ።

እነዚህ አገሮች ባህላቸው፤ ታሪካቸውና የእድገት ጉዟቸው የተለያየ ነው። በእድገት በኩል ያስገኙት ውጤት አስደናቂ

ነው። ይህ ሲባል የስራ እድል ለአብዛኛው ሕዝባቸው መፍጠራቸው፤ ለሴቶች ወጣቶች የትምህርት እድል ከፍተው ወደ

ዘመናዊው ኢኮኖሚ እንዲሻገሩ ማድረጋቸው፤ አገር ተከል ኢንዱስትሪዎች አስፋፍተው ለገጠሩ ሕዝብ በከተማው የስራ

እድል ማስገኘታቸው፤ የገጠሩን ኢኮኖሚ ግብዓቶች እያቀረቡ ዘመናዊ ማድረጋቸው፤ የምርት ኃይሎችን፤ በተለይ

የእርሻንና የኢንዱስትሪን ምርቶች ከፍ እያደረጉ ለሕዝብ የሚቀርበውን ቁሳቁስ ዋጋ እንዲቀነስ ማድረጋቸው፤ የአገር

ውስጥ ቁጠባን ማጠናከራቸው፤ የግል ክፍሉን ማጎልመሳቸው፤ አንዳንዶቹ ጉቦንና ሙስናን መቅረፋቸው፤ ከውጩ

 

ዓለም ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለራሳቸው ጥቅም እንዲረዳ መደራደራቸውና ጥገኝነትን መቀነሳቸው ይታያሉ። ይኼን

ሁሉ ሲያደርጉ የአገራቸውን ሉዐላዊነት፤ ማንነትና የሕዝባቸውን ባለቤትነት አስከብረው ነው። በእድገት በኩል

ስኬታማ የሆኑበት ዋና ምክንያቶችና ቅድመ ሁኔታዎች በአብዛኛው ተመሳሳይ ናቸው።

አንድ፤ አገር ወዳድ መንግሥታት፤ ትጉህ የመንግሥት ሰራተኞች፤ አገር አቀፍ ተቋሞች፤ መልካም አስተዳደር

ሁለት፤ አግባብ ያላቸው ፖሲሲዎች፤ የኢኮኖሚ መርሆዎች ግልጽነትና አመቻችነት

ሶስት፤ የመንግሥትና የግሉ ክፍሉ ተደጋጋፊነት፤ የማህበረሰቡ ትሥስርና ተሳትፎ

አራት፤ የውጭ ኢንቬስትመንት ሚና ከአገር ተከል የኢኮኖሚ እድገት ጋር መያያዝ፤ የቴክኖሎጂ ስርጭት መሰረት

መጣል

አምስት፤ የገጠሩና የከተማው እድገት ተደጋጋፊነት

ስድስት፤ የትምህርት ጥራትና የተማሩት ስራ መያዝ፤ ማምረት፤ መፍጠር፤ በአገራቸው እድገት ፖሊሲ መሳተፍ

ሰባት፤ የመሰረተ ልማት ኢንቬስትመንት ከምርት ኃይሎችና ከስራ እድል መፍጠር ጋር መያያዝ፤

ስምንት፤ በግልጽነት፤ በሃላፊነት፤ በሕግ የበላይነት የሚመራ የኢንቬስትመንት መርህ ይገኙበታል።

የደቡብ ኮሪያን አስደናቂ እድገት በሚመለከት ብዙ ተጽፏል። ከኢትዮጵያ በባሰ ሁኔታ የመጨረሻ ድህና ኋላቀር፤

በጦርነት የደቀቀች፤ አስተማማኝ የሆነ የተፈጥሮ ኃብት የሌላት አገር እንዴት በ1960ወቹና በ1980ዎቹ (ኢህአዴግ

ስልጣን የያዘበትን ዓመታት የሚመጣጠን ጊዜ ማለት ነው) መካከል አስደናቂ እድገት አሳየች? ይኼን ጥያቄ ሚዛናዊ

በሆነ ደረጃ የመለሰው የደቡብ ኮሪያ ተወላጅ፤ በሞያው የታወቀው ኢኮኖሚስት ሃ ጁን ቻንግ ነው። እንዲህ ይላል፤

“የደቡብ ኮሪያ ተዓምራዊ እድገት የውጭ ፈጠራ አይደለም፤ ደቡብ ኮሪያ የሊበራል ኢኮኖሚ መርህ ስለተከተለችም

አይደለም፤ የውጭ እርዳታም ብቻ አይደለም። ውጤቱ የተገኘው በመእከላዊ መንግሥት ጥበባዊ፤ ውጤት ተኮር፤ አገር

ተከል እና አግባብ ባለው የገበያ አመራር ቅይጥ ኢኮኖሚ ነው”። የኢትዮጵያ ገዢዎች የ“እድገታዊ/ልማታው መንግሥት”

መርህ እንከተላለን ይላሉ። ልማታዊ መንግሥት የሚባለውን መርህ የፈጠሩት የምስራቅ ኤዢያና ፓሲፊክ አገሮች፤

በተለይ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ናቸው። የኢትዮጵያው ኢኮኖሚ የአንድ ጠባብ ብሄርተኛ ቡድን እና የአንድ ፓርቲን

የኢኮኖሚ የበላይነትና የጥቂት ቤተሰቦችን ኪስ የሞላና በኪራይ ሰብሳቢነት የተበከለ ነው። ግዙፍ የሆነውን የውጭ

ብድር የሚበደረው የመንግሥትና የገዢው ፓርቲ ተቋማት፤ በተለይ የህወሓትግ ተቋማትና አጋሮች ናቸው። ብድሩን

የሚከፍለው ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ተጠቃሚው የበላዩ ፓርቲ እዳ ከፋዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ መሆኑ

አያከራክርም። ስለዚህ የእድገቱ ውጤት ዘላቂነትና ፍትሃዊነት ያለው ሊሆን አልቻለም። የፖለቲካው አመራር የጋራ

ካልሆነ የፈለገው ብድር ቢገኝ ዘላቂነትና ፍትሃዊነት ያለው እድገት አይኖርም። ገዢው ፓርቲ እጁን ያላስገባበት

የኢኮኖሚ፤ የፋይናንስ፤ የመገናኛ፤ የተፈጥሮ ኃብትና ሌላ ክፍል የለም። ገበያው ከቁጥጥር ውጭ ነው። አቅርቦት

ሲጨምር ገበያውም አብሮ የሚጨምርበት ኢኮኖሚ ነው። የውጭ እርዳታ ሲጨምር ሙስናና ከአገር የሚሸሽ ኃብት

 

የጨመረበት ኢኮኖሚ ነው። የውጭ እርዳትና የውጭ ኢንቬስትመንት በገፍ እየተለገሰ ሕዝቡ በልቶ ለማደር

የማይችልባት አገር ኢትዮጵያ ናት። የኢትዮጵያ የግል ክፍል ጫጩት የሆነበትና ሃያ ሚሊየን ሕዝብ የተራበበት መሰረት

ይህ የተዛባ የእድገት መርህ ነው። የተዛባ የኢኮኖሚ መርህ የተዛባ ውጤት ይኖረዋል የሚባለው ለዚህ ነው። የተዛባ

የእድገት መርህ የውጭ የምግብ እርድታ ያስፈልገዋል። ለምን?

ለተመልካቾች ህሊና የሚቀፈው፤ ህወሓት/ኢህአዴግ የሚቆጣጠረው መገናኛ ብዙሃን በየቀኑ በቴሌቪዢን፤ በሬዲዮ፤

በጋዜጣ፤ በመጽሄትና ሌላ “አገሪቱ” ታይቶ የምይታወቅ እድገት ስለምታሳይ ሁሉም ደልቶት ይኖራል የሚለው በመረጃ

ያልተደገፈ ፕሮፓጋንዳ ነው። በነገራችን ላይ የአፓርታይዱ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት “አስደናቂ እድገት” እያሳየሁ ይል

ነበር። ኬፕ ታውን፤ ጆሃንስበርግና ሌሎች ከተሞች “ከምእራብ ከተሞች ጋር ይወዳደራሉ” ይል ነበር። ከተሞቹ ዘመናዊ

መሆናቸው፤ መንገድና ሌላ መሰረተ ልማት መሰራቱ አያከራክርም። ሆኖሞ አብዛኛው የደቡብ አፍርካ ጥቁር ሕዝብ

ይኖርበት የነበረው ሁኔታ አሳፋሪና ዘረኛነትን የሚያንጸባርቅ ነበር። ለእነ ኔልሰን ማንዴላ፤ ለእነ ስቲቭን ቢኮና ለመላው

ጥቁር ሕዝብ እድገቱ በእነሱ ትክሻና ጉልበት፤ በአገራቸው የተፈጥሮ ኃብት የተገኘ መሆኑን በሚገባ ተረዱት። ይህ

ሁኔታ ሊለወጥ የሚችለው ጥቁሮች ለነጻነታቸው ታግለው ዘረኞችን ለማንበርከክ ሲችሉ መሆኑን አመኑበት፤ አምነው

ለነጻነታቸው በአንድነት ተነሱ፤ ተነስተው መስዋእት ሆኑ። ነጻነታቸውን ስኬታማ አደረጉ። የአፓርታይድ እድገት

ውጤት ዋና ጥቅሙ ለነጮች ብቻ ነበር። ሆኖም፤ የዓለምን ሕዝብ ለማታለልና ለማሳመን አፓርታይድ “የደቡብ አፍሪካ

ጥቁሮች ከሌሎች የአፍሪካ ጥቁሮች የተሻለ ኑሮ ይኖራሉ” ይል ነበር፤ ደጋፊዎችም ነበሩት። ስለዚህ መንገድ፤ ፎቅ፤ ቤት፤

ሃዲድ ወዘተ መሰራቱ ብቻ የአብዛኛውን ሕዝብ ኑሮ ሊያሻሽለው አይችልም። ነጻነትና ፍትህ ከሌለ እድገት

የሚያገለግለው ለፖለቲካ ልሂቃን ነው። ነጻነት የሌለው ሕዝብ በራሱ አገርና በራሱ የተፈጥሮ ኃብት እነደ “ባሪያ ሆኖ”

ይገዛል የሚባለው ለዚህ ነው። በኢትዮጵያ ተገኘ የሚባለው እድገት የአብዛኛውን የኢትዮጵያ ድሃ ሕዝብ ህይወት

አልለወጠውም፤ ሊለውጠውም አይችልም። በአፓርታይዷ ደቡብ አፍርካ ይነገር የነበረው ሃስት (ፍትሃዊ እድገት አለ

የሚለው) “በጥቁሯ ኢትዮጵያ” ሲቸረቸር ቆይቷል፤ አሁንም አደገኛ የሆነ የውሸት መረጃ እየቀረበ ነው።

ህወሓቶች/ኢህአዴጎች ከምኒልክ ቤተ መንግሥት ወጣ ብለው የተራውን የአዲስ አበባን፤ ከቪላዎች ወጣ ብለው

የመቀሌን፤ የአዋሳን፤ የጎንደርን ሕዝብ ኑሮ አመኔታን በሚያሳይ መልኩ ጥሩውንም መጥፎውንም ቢያሳዩ ሕዝብ

ይገባውና ያምናቸው ነበር። ዛሬ እውነት ተቀብሯል፤ ውሸት ዳብሯል። አንድ መስፈርት ብቻ ላቅርብ። በዚህ ዓመት

የጋና የነፍስ ወከፍ ገቢ በአመት $4,000 ነው። የኢትዮጵያ ከ $470-$490 አደገ ቢባል ከ$500 አላለፈም። የዋጋ

ግሽበት መር እንደለቀቀ ሕዝብ ይነጋገርበታል። ልዩነቱን አንባቢ ይፍረደው። የጋና ሕዝብ በልቶ ያድራል። ኢትዮጵያ

ብዙ የአዲሱ ስርዓት ፈጠር ሚሊየኔሮች አሏት፤ ጀኔራልቾ ኃብታም ሆነዋል። አብዛኛው ሕዝብ ድሃ ነው።

አጭሩ መልስ የፓርቲና የመንግሥት ባለሥልጣናት ሃላፊነታቸው ለሕዝብ አልሆነም ነው። የሚሰሩት ለራሳቸው፤

ለቤተሰቦቻቸው፤ ለወዳጆቸውና ለደጋፊዎቻቸው ነው። ስሙን ቢዋስም፤ የኢትዮጵያ ልማታዊ/እድገታዊ መንግሥት

እንደ ጃፓን ሞዴል አይሰራም። ባለሥልጣናት ለሕዝብ ታዛዢና ታማኝ ቢሆኑ ኖሮ ልማታዊ/እድገታዊ መንግሥት

ሊባል ይችል ነበር። ቻንግ እንዲህ ይላል። “የኮሪያ መንግሥት ልማታዊ/እድገታዊ ሆኖ ወሳኝ ሚና ቢጫወትም

የኮሙኒስት አገሮች እንዳደረጉት የገበያውን ሚና አልቀበልም አላለም፤ እንዲያውም ተቀብሏል፤ የውጭ ኢንቬስትመንት

ቢጋብዝም ለነሱ ተገዢ አልሆነም….ገበያውን በሚመለከት አይነስውር ሆኖ ነጻ ገበያው ይሰራል አላለም። The Korean

 

strategy recognized that markets often need to be corrected through policy intervention.. የመንግሥት

ጣልቃገብነት አስፈላጊ ነው…..የእድገትን ታሪክ ስንመረምር…ዓለም ባንክና አይኤምኤፍ እንደሚሉት አይደለም።

የአሜሪካም ሆነ የእንግሊዝ መንግሥታት” በኢኮኖሚውና በገበያው ከፍተኛ ሚና ነበራቸው። “The records of

today’s rich countries on policies regarding foreign investment, state-owned enterprises,

macroeconomic management and political institutions show significant deviations from today’s

orthodoxy (World Bank, IMF and others) regarding these matters. Why then don’t the rich countries

recommend to today’s developing countries the strategies that served them so well? Why do they

instead hand out a fiction about the history of capitalism, and a bad one at that?” Ha-Joon Chang,

Bad Samaritans፡ the myth of free trade and the history of capitalism.”

ባጭሩ፤ “የበለጸጉ አገሮች ስለ ኢንቬስትመንት፤ ስለ መንግሥት የሆኑ ድርጅቶች ሚና፤ ስለ አጠቃላይ ኢኮኖሚ መርህ

እና ስለ ፖለቲካ ተቋሞች ሚናዎች ለታዳጊ አገሮች የሚመክሩት ፖሊሲ ከራሳቸው የእድገት ታሪክ የተለየ ነው። እነሱ

ተጠቃሚዎች ከሆኑ ለምንድን ነው ለታዳጊ አገሮች ስለመንግሥት ሚናና ስለ ካፒታሊዝም ከእውነቱ የራቀ ሰው ሰራሽ

ታሪክ የሚያወሩት?” ይኼን የሚቀበል ተባባሪና ራስ ወዳድ መንግሥት ስለሚያገኙ ነው። ለምሳሌ መለስ ዜናዊ

በ1990ዎቹ አመታት በዓለም ባንክና በአይኤመኤፍ ጫና ብዙ መቶ የሕዝብ የነበሩ ድርጅቶችን ምንም ግልጽነትና

ውድድር በሌለው፤ ሃላፊነት በማያሳይ መልኩ በዝቅተኛ ዋጋ የግል አድርጓል። ኤፈርት፤ ሌሎች የህወሓት ድርጅቶችና

ደጋፊዎች፤ ተቋሞችና ቤተሰቦች፤ አላሙዲ ወዘተ የኢትዮጵያን ሕዝብ ኃብት ለመውረስ ችለዋል። ይህ ስጦታ አገሪቱን

ጎድቷታል። ይኼ በአሜሪካ፤ በእንግሊዝ፤ በምስራቅ ኤዢያና ፓሲፊክ አገሮች፤ በቦትስዋናና ሌሎች አልተደረገም።

በሳውዲ አረባያ አልተደረገም። በአንዳንድ የኢኮኖሚ ክፍሎች ቢደረግም በውድድር፤ በግልጽነት፤ በጥሩ ዋጋ፤ የግል

ክፍሉን ቁልፍነት በሚያስተጋባ መልካቸው ነው የተካሄዱት። የቻይና ኢኮኖሚን ከፍተኛ ድርሻ የያዘው በቻይና ሕዝብ

አማካይነት መንግሥት ከፍተኛ ብሄራዊና ሚዛናዊ ሚና ስለሚጫወት ነው። ቻይና የአገሯን የግል ክፍል ለማጠናክረ

የቻለችው እንክብካቤና ድጎማ በመስጠት ነው። ህወሓት/ኢህአዴግ ቻይናን አደነቀ ቢባልም ከቻይናም ከደቡብ ኮሪያም

የኢኮኖሚ እድገት ልምድ አልተማረም። ከቻይና የተማረው ቁጥጥርን ብቻ ነው። ድጎማ የሚሰጠው የአገር ውስጡን

ኢንቬስተር ለሚጫኑት ለውጭ ኢንቬስተሮች ነው። ይህ መንግሥት በኢትዮጵያዊያን የመፍጠር፤ የማምረትና

የመወዳደር አቅም አያምንም።

ወደ ጥያቄው ለመመለስ የኢትዮጵያ እድገት የተደገፈው በውጭ እርዳታ፤ ስደተኛው በሚልከው ገንዘብ፤ በውጭ

ኢንቬስተሮችና በውጭ ብድር ነው። በያመቱ 60 በመቶ የሚሆነውን የልማት ባጀት የሚሸፍነው የውጭ እርዳታ

ነው። ለእድገት የተሰጠው እርዳታ እስካለፈው ዓመት $40 ቢሊየን ነበር፤ በዓመት $4 ቢሊየን አልፏል። የውጭ ብድር

እዳ ከ$35 ቢሊየን በላይ ነው። ከዚህ ውስጥና ከንግድ ወዘተ ጋር ተጨማምሮ በዝቅተኛ ሂሳብ $35 ቢሊየን ከአገር

ተሰርቆ ወደ ውጭ መደበቂያዎች እንደተላከ መረጃዎች አሉ። ይህ ከአገር ተሰርቆ የሚሸሽ ግዙፍ ኃብት ስንት

ፋብሪካዎች ሰርቶ ለስንት ኢትዮጵያዊያን የስራ እድል እንደሚያስገኝ ለመገመት አያዳግትም፤ ስንት የተሃድሶና የመስኖ

ግድቦች ሊሰራ እንደሚችል ለማሰብ ቀላል ነው። ስንት አምራች ገበሬዎችን ለማጎልመስና እርሻቸውን ዘመናዊ

ለማድረግ፤ የመስኖ እርሻን ለማስፋፋት እንደሚረዳ እናስብ። እውነት ነው ብለን ለመቀበል ብንገደድም እንኳን፤

 

በተከታታይ “ባለሁለት አሃዝ” እድገት አለ የሚለው እድገት ያለውጭ እርዳታ፤ ያለስደተኛው የውጭ ምንዛሬና የውጭ

ኢንቬስተሮችና የውጭ ብድር አይታሰብም። የእድገት አሃዝ ይታመናል አይታመንም? በእኔ ግምት አይታመንም።

ማንንም ተቃዋሚ ግለሰብ በፈጠራ ወሬ “ሽብርተኛ ነህ/ነሽ” ብሎ የሚከስ መንግሥት “ባለሁለት አሃዝ” እድገት አለ

ብሎ ቢናገር ማን ያምነዋል። ከዚህ ላይ ነጻነት ባለመኖሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ እውነቱን ከውሸቱ ለመለየት አልቻለም።

በመሬት የሚታየው እና ገዢው ፓርቲ የሜልው የተለያዩ ናቸው። አራት ምሳሌዎች ልስጥ።

አንድ፤ እኔ ዓለም ባንክ በነበርኩበት ጊዜ ለመሆኑ የሚለገሰው ግዙፍ ገንዘብ የት ላይ እንደዋለ እንዴት ታውቃላችሁ?

የሚል ጥያቄ አቅርቤ ነበር። በተደጋጋሚ የተሰጠኝ መልስ መረጃውን የምንሰበስበው ከመንግሥት መስሪያ ቤቶች ነው

የሚል ነው። አንዳዶቹ የሚታወቁበት ውጤት አለ፤ ለምሳሌ የተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ መሄዱ። በእርሻ ምርት

ውጤት በኩልስ? መሰረተ ልማት ተስፋፍቷል፤ የአብዛኛው የገጠር ሕዝብ የኑሮ ሁኔታ ግን አልተሻሽለም የሚል መልስ

ይሰጠኝ ነበር። ታዲያ ለምን የኢትዮጵያን መንግሥት እድገት አሃዝ ትቀበላላችሁ ለሚለው ጥያቄ አጥጋቢ መልስ ሰምቸ

አላውቅም። ግዙፍ ድጋፍ እየሰጡ እድገት የለም ለማለት አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል። ምክንያቱም፤ ለለጋስ አገሮች ሕዝብ

የሚነገረው እድገት አለ የሚል ነው። በዚህ ምክንያት ነው የሚሰጠው ገንዘብ የሚቀጥለው ወይንም እየጨመረ

የሚሄደው። የውጭ ኢንቬስተሮች የሚመጡት። የእርሻው እድገት ከሕዝቡ ፍላጎትና እየጨረ ከሄደው የሕዝብ ቁጥር

ጋር የማይመጣጠን መሆኑን ዓለም ባንክ ባደረገው ሰፊ ጥናትና መረጃ ለማየት ይቻላል። The World Bank,

Wellbeing and Poverty in Ethiopia: the role of Agriculture and Agency, 2005. ጥናቱ “ምንም እንኳን

የእርሻ ፖሊሲ (አመራር) ለውጥ ተደርጓል፤ መንግሥት ግብዓቶች አቅርቧል ቢልም፤ የኢትዮጵያ የእርሻ ምርት ውጤት

ከሕዝቡ ፍላጎትና ጭማሬ ጋር አልተመጣጠነም” በሚል ደምድሟል። የእርሻው ምርት ውጤት “ዜሮ ወይንም ባዶ

ነው” ይላል። “Despite agricultural policy reforms in the 1990s, and substantial investments in

extension services afterwards, agriculture has failed to keep up with population growth, resulting in

zero growth in agricultural GDP per capita.” የድርቅ ርሃብ ሲከሰት ወደ ምግብ ልመና የሚኬድበት ዋና

ምክንያት ይኼው ነው። ይህ የሚያሳየው መንግሥት የሚናገረውና በመሬት ላይ የሚታየው ምንም ግንኙነት የሌላቸው

መሆኑን ነው። በቀን ሶስት ምግብ ለመብላት ያልቻለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቢጠየቅ ተመሳሳይ መልስ እንደሚሰጥ

እገምታለሁ። እኔን የሚያሳስበኝ ዓለም ባንክ የሚያምንበት፤ የሚጽፈውና በገሃድ የሚታየው ምንም ግንኙነት የሌላቸው

መሆኑና ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የተለገሰው የብድርና የድጎማ እርዳታ ውጤት ዝቅተኛ መሆኑን አለመቀበላቸው

ነው። ይህ የመጀመሪያ አይደለም።

በሰሜን አፍሪካና ሌሎች የአረብ አገሮች የጸደይ አብዮት በተካሄደበት ጊዜ ዓለም ባንክና አይኤምኤፍ በግብጽና

በቱኒዢያ “የሚያስመሰግን እድገት” አለ ብለው ነበር። አብዮቱ የተካሄደው ይኼን ዘገባ ባቀረቡ በዓመቱ ነው። የምግብ

ዋጋ ግሽበት፤ የስራ እድል መጥፋት፤ ስደት፤ የሰብአዊ መብቶች መታፈን፤ ሙስና፤ የአስተዳደር በደል ወዘተ ከዘገባው

ውስጥ አልገቡም። እድገት አለ ብለው የደመደሙት የባለሥልጣናትን መረጃ ተጠቅመው ነው። የመንግሥት

ባለሥልጣናት እንደሚዋሹ ያውቃሉ። ስራቸው ማበደርና ለኢንቬስተሮች ማመቻቸት ስለሆነ ባለሥልጥናትን

ለማስቀየም የፈለጉበትን ጊዜ ተመራምሮ ለማግኘት አይቻልም። የኢትዮጵያን መንግሥት የፈጠራ መረጃ የሚቀበሉበት

ዋናው ምክንያት የፖለቲካና የዲፖማሲ ውሳኔ ነው።

 

ሁለት፤ በአብዛኛው እድገት የሚመለከተው የአሁኑንና የወደፊቱን ትውልድ ህይወት መሻሻል ነው። ድርብ አሃዝ እድገት

አለ ሲባል የስራ እድል ተስፋፋና የመካከለኛም መደብ እየጨመረ ሄደና የአገር ውስጥ ቁጠባ ጨመረ ማለት ነው።

ጥራትም ባይኖረው የትምህርት እድል ተስፋፍቷል። መንገድ ተሰርቷል። ሆኖም፤ ዛሬ ኢትዮጵያ ከምትታወቅባቸው

መካከል በግዙፍ የሚሰደደው ወጣት ትውልድ ነው። ሌላው ስር የሰደደ ርሃብ ነው። በተጨማሪ የሕብረተሰቡን ሰቆቃ

የሚያሳየው በተከታታይ በጋምቤላ፤ በኦሞ ሸለቆ፤ በኦጋዴን፤ በኦሮሞያና በአማራ፤ በተለይ በጎንደር የሚካሄድው

ሕዝብዊ አመጽና ግጭት ነው። Freedom House, Ethiopia: Attack on Civil Society Escalates as Dissent

Spreads, July 23, 2016. የድገቱ፤ የተፈጥሮ ኃብቱ፤ የማንነቱ፤ የነጻነቱና የመብቱ ባለቤት እንዳይሆን ስርዓቱ

ያስገደደውን ሕዝብ በመሳሪያ ኃይል እቆጣጠራለሁ ማለት በሳት ላይ ቤንዚን እንደመርጨት ይሆናል።

የርሃቡን ጉዳይ በሌላ ቦታ አነሳዋለሁ። ወጣቶች ለምን ይሰደዳሉ? የሚለውን የኢትዮጵያ አናቶችና አባቶች ያውቁታል።

ወጣቶች በሊቢያ አድርገው ወደ አውⶂፓ ለመግባት ሲሞክሩ በሺብርተኞች ሲሰየፉ ማየት ለአገራችን ውርደት ነው።

በ2013 ብቻ ከሳውዲ አረቢያ 160,000 ኢትዮጵያዊያን የቀን ሰራተኞች ከአገር እንዲወጡ ተደርጓል። የየመን መንግሥት

ከ400,000 በላይ ኢትዮጵያዊ ስደተኞች በየመን እንደሚኖሩ ለ International Office for Migration (IOM)

አስታውቋል። በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ስደተኞች ተገድለዋል፤ በማላዊና በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ታስረዋል።

ከኢትዮጵያ ተነስተው ቢያንስ ስድስት አገሮች አልፈው፤ በሜክሲኮ ገብተው ወደ አሜሪካ ሲሄዱ በማያሚና ሌሎች

ከተሞች የታሰሩትን ስደተኞች ቁጥር ለማወቅ አይቻልም። በደቡብና ሰሜን ሱዳን የተሰደዱት ኢትዮጵያዊያን ቁጥር

አስተማማኝ በሆነ መረጃ አይታወቅም። በዝቅተኛ ግምት አንድ ሚሊየን ይሆናል ይባላል። በሰሜን አሜሪካ ከአንድ

ሚሊየን በላይ ትውልደ ኢትዮጵያ ይኖራሉ። እንግዲህ ተምሮ ለስደት ከሆነ ድርብ አሃዝ እድገት ፈጠራ መሆኑ

አይደለም? ወይንም የእድገቱ ውጤት በጥቂቶች ይማረካል ማለት ነው። ውጤቱ ተመሳሳይ ነው።

ሶስት፤ ድርብ አሃዝ እድገት አለ ሲባል ምርቶች አድገዋል፤ ሰው ሶስት ምግብ በልቶ ያድራል፤ የስራ እድል ይጨምራል

ወዘተ ማለት ነው። የዛሬ 21 አመት፤ አንድ ታዋቂ ስደተኛ ከመለስ ዜናዊ ጋር ቃለ ምልልስ ሲያያደርግ “ለኢትዮጵያ

ያለህ ራእይ ምንድን ነው?” አለው። “የዛሬ አስር ዓመት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በልቶ ማደር ብቻ ሳይሆን፤ የሚበላውን

ምግብ ለመምረጥ እንዲችል ማድረግ” የሚል መልስ ስጥቶት ነበር። ይህ ራእይ፤ ከቃላትነት ውጭ ስኬታማ

አልሆነም። ሃብታሞች ካልሆኑ በስተቀር የምግብ አይነት መምረጥ ይቻላል የሚለው በሬ ወለደ እንደማለት ነው። ዛሬ

ከጥቂት ኃብታሞች ውጭ በቀን ሶስት ምግብ የሚበላ ኢትዮጵያዊ ፈልጎ ለማግኘት አይቻልም። ይኼን በገሃድ የሚታይ

አሰቃቂ የእድገት እንቆቅልሽ አብዛኛው ሕዝብ ሲተቸው ቆይቷል፤ ሰሚ አላገኘም። ከዚህ በላይ ግን የእድገቱን መጠን

ከጥያቄ ውስጥ ያስገባው በአለፉት አምሳ ዓመታት ታይቶ የማይታወቀው የድርቅ ርሃብ ነው። የተባበሩት መንግሥታት

የምግብ ድርጅት፤ የአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት፤ ኢፍፕሬና ሌሎች ያቀረቡት በድርቅ ርሃብ የሚሰቃይ ሕዝብ ቁጥር ከ15

ሚሊየን እስከ 20 ሚሊየን ይሆናል። በተጨማሪ የወደመውን ኃብት–ቤቶች፤ ሰብል፤ እንስሳዎች ወዘተ ለመተካት ምን

ያህል የገንዘብ ፈሰስ ያወጣል የሚለውን ከስሌቱ ማስገባት አስፈላጊ ነው። በአፋር የወደመውን ግመል፤ ከብት፤ በግ

ወዘተ ለመተካት ለአንድ እንስሳ ብቻ ከሰባት እስከ አስራ አራት ጊዜ ዋጋው የሚጨምር ወጭ ያስፈልጋል። ለምሳሌ

አንድ ግመል ዛሬ 500 ብር የሚያወጣ ከሆነ ለመተካት 3,500 ብር ያስፈልጋል። አንድን በርሃብ የተጎዳ ግለሰብ

 

በዝቅተኛ ደረጃ ለመደጎም በቀን ቢያንስ 150 ብር ወጭ ማድረግ ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ይኼን ሸክም

አይችለውም። ይኼን ወጭ ማን ይችለዋል?

አሰቃቂውን የኢኮኖሚ ሁኔታ በሚገባ ለማጤን መጠነኛ ድርቅ ባለበት ጊዜ እንኳን ኢትዮጵያ አስቀድማ በመከላከል

ፋንታ በድርቅ ሁኔታዎች ብቻ ከ1997-2007 ባለው ጊዜ በያመቱ $1.1 ቢሊየን አጥታለች። በዚህ ጊዜ ለልማት ከውጭ

የተገኘው እርዳታ በአማካይ በዓመት $1.3 ቢሊየን ነበር። በድርቅ ምክንያት የጠፋው ገንዘብ ለእርሻ ልማት ከተደረገው

ኢንቬስትመንት ይበልጣል። በያመቱ የእርሻ እድገት አለ የሚለው መንግሥት ተከታታይ ድርቅን መሰረታዊ በሆነ ደረጃ

አስቀድሞ ለመከላከል አልቻለም። ይኼ ስላልሆነ ካድሬዎች በያመቱ የፈጠራ ስታትስቲክስ እንዲያቀርቡ ይገደዳሉ።

በቅርቡ በተከሰተው የድርቅ ቸነፈር ዙሪያ መንግሥት ችግሩን ቀላል አድርጎ ያቀረበበት ምክንያት ፖለቲካዊ ነው።

የችግሩን መሰረቶች ለመቅረፍ የማይቻለው መንግሥት ችግሩን አልቀበልም የሚል መርህ ስለሚከተል ነው።

ከመንግሥት አንጻር ሳየው፤ የርሃብን አሃዞች ለመቀበል ካልተቻለ የእድገቱን አከራካሪ ድርብ አሃዝ ለመቀበል

አይቻልም። የእድገቱን አሃዝ ቀጥታ በሆነ ደረጃ ለመተቸት የሚችለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። በእኔ ግምት፤ ድርብ

አሃዝ እድገት አለ ከተባለ ከድርቅ የሚከሰትን ርሃብ ለመቋቋም ይቻል ነበር። ኢትዮጵያ የርሃብ ችግሯን በውጭ የምግብ

እርዳታ ልትወጣ አልቻለችም፤ አትችልም። የምግብ እርዳታ የሰው ህይወት ማትረፉ አይካድም። የምግብ ድጎማ

መሰረታዊና መዋቅራዊ ችግሩን ሊፈታ አይችልም። ችግሩን ለመፍታት ከተፈለገ የፖሊሲና ሌሎችን መሰናክሎች

መፍታት አስፈላጊ ነው። በተለይ የኢትዮጵያን ዝቅተኛ አምራቾች አቅም ከመቸውም በበለጠ ደረጃ ማጠናከር

ያስፈልጋል። ይህም የነጻነት ጥያቄ ነው።

እርግጥ ነው፤ ርሃቡን በሚመለከት የኢህአዴግ መንግሥት የተቻለውን እያደረገ ነው፤ በዚህ ሊመሰገን ይገባል። ሆኖም፤

ይህን ተከታታይ ችግር ለመቅረፍ የመሬት ይዞታና አጠቃቀም ፖሊሲ መለወጥ አለበት። ኢትዮጵያ ተደጋጋሚ የሆነ

የተፈጥሮ ርሃብ ደርሶባታል። ይህ ሊወገድ የሚችል ርሃብ በዘላቂነት ሊፈታ የሚችለው አካባቢውንና የአካባቢውን

ሕዝብ ለጥቃት እንዳይጋለጥ አማራጮችን መፈለግና በእነዚህ አማራጮች ላይ ኢንቬስት ማድረግ ነው። አንዱ

አማራጭ የውሓ ቋቶች መስራት፤ የመስኖ እርሻን ማሻሻል፤ ለክፉ ጊዜ የሚሆኑ ጎተራዎችን መሙላት፤ ለተፈጥሮ አደጋ

የተጋለጡ አካባቢዎች ከአምራች አካባቢዎች ጋር ቀጥታ የሆነ ማህበረሰባቢና የገበያ ግንኙነት እንዲኖራቸው ማድረግ

ወዘተ ይገኙበታል። ይህ ሁሉ ግዙፍ ኢንቬስትመንትና የአምራቹን ሕዝብ አቅም ማጎልመስ፤ የመሬት ባለቤትነት

ይጠይቃል። የወንዞች ባለኃብት በሆነችው ኢትዮጵያ የመስኖ እርሻና ከእርሻ ጋር የተያያዘ የኢንዱስትሪ ልማት

መስፋፋት ወሳኝ ነው። በክልሎች መካከል ያለውን የገበያ ግንኙነት ማስተካከል ወሳኝ ነው። የመሬት ስሪትን

ማስተካከል ወሳኝ ነው። የኪራይ ሰብሳቢዎችንና የነጋዴወዎች ስግብግብነት ማቆም ወሳኝ ነው። ብዙ ሚሊየን ሕዝብ

እየተራበ ኪራይ ሰብሳቢነት አሁንም ሲቀጥል ማየት አሳፋሪና ለህሊና የሚቀፍ ነው። በድሃ፤ የምግብ ጥገኛና ኋላ ቀር

አገር ኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና ወንጀል መሆን አለባቸው። ይህ በሽታ ሊወገድ የሚችለው ከቁንጮው ላይ የሚገኙት

የፓርቲና የመንግሥት ባለሥልጣናት የጥቅም ነጋዴዎች በሕግ ፊት በሃላፊነት ሲጠየቁና ሲቀጡ ብቻ ነው። ይህ ረዥም

ጊዜ ይወስዳል። በአጭር ጊዜ የምግብ እጥረት በግልጽ እየተታየ ወደ ውጭ የሚላከው ጥራ ጥሬ መቆም አለበት።

በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍለ ሃገር ወይንም ክልል ሰርቶ መኖር ወንጀል መሆኑ መቆም አለበት። የክልል ባለሥልጣናት

 

ይህን መብት እንዲያስከብሩ የሚያስገድድ ህግ መኖር አለበት። ዜጎች በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል አርሰው እንዲኖሩ

የፌደራል መንግሥቱ የማያሻማ ሚና መጫወት አለበት። ይህ ሁሉ ሰብአዊ መብቶችን ማክበርንና ነጻነትን ይጠይቃል።

አራት፤ ድርብ አሃዝ ከሰብአዊ እድገት ጋር ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት አለው። ባለፉት ዓምስት ዓመታት በተባበሩት

መንግሥታት የልማት ድርጂት ዓመታዊ መስፈርት ኢትዮጱያ በአማካይ ከ 187 አገሮች ከ 177ኛነት በላይ እድገት

አሳይታ አታውቅም። በአፍሪካ አገሮች ድሃ ከሆኑት መካከል አንዷ ናት፤ በዓመት የነፍስ ወከፍ ገቢያዋ ከአፍሪካ አገሮች

አንድ ሶስተኛ ነው። የመካከለኛ መደቧ ዝቅተኛ ከሆኑት መካከል አንዷ ናት። ስለሆነም ዓለም ባንክና ሌሎች

የተቀበሉት የእድገት አሃዝ የመንግሥትን ነው እንጅ የሕዝቡ ኑሮ መሻሻልን መሰረት አድርገው አይደለም። እድገቱ

ከሕዝቡ ኑሮና ህይወት ጋር ግንኙነት የለውም። ለምሳሌ፤ ባለፉት አምሳ አመታት ታይቶ የማይታወቅ ርሃብ ተከስቷል

ከተባለ እድገቱ ለማን ጠቅሟል፤ ፍትሃዊ ነው ወይንስ በጥቂት ኪራይ ሰብሳቢዎች የተማረከ? ብለው ራሳቸውን

አልጠየቁም፤ አይጠይቁም። እድገቱ መዋቅራዊ ለውጥ አላስየም የሚለውን ተቀብለው ለምን እንደ ምስራቅ ኤዥያና

ፓሲፊክ አገሮች መዋቅራዊ ለውጥ ስኬታማ አልሆነም ብለው መፍትሄ አላቀረቡም። ሕዝብን ምን አይነት ድጋፍ

ቢሰጥህ በተደጋጋሚ የሚከሰተውን የተፈጥሮ አደጋ ለመከላከል ትችላለህ ብለው አያውቁም። የሕዝቡን የኑሮ ሁኔታ

መረጃ ያገኙት ከመንግሥት ነው። አደገኛ ርሃብ ተከስቶ አሁንም ያተኮሩት ብልጭልጭ ከሆኑት የእድገት መስፈርቶች

ላይ ነው–የውጭ ኢንቬስትመንት ፈሰስ እያደገ መሄድ፤ ብድር እየጨመረ መሄድ፤ አዲስ አበባ የብዙ ፈረንጆች አገር

መሆን፤ የቪላዎች፤ መንገድዶች፤ መኪናዎች ሆቴሎች መስፋፋትና መብዛት። እኔ እስከማውቀው ድረስ፤ የኢትዮጵያ

እድገት ዘላቂነትና ፍትሃዊነት ያለውና ሕዝቡ ሶስት ምግብ በልቶ የሚያድር ቢሆን ማንም ኢትዮጵያዊ ይደሰታል እንጅ

በሚገዛው መንግሥት አያፍርም ነበር።

ይቀጥላል

ህብር ሬድዮን በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ ከ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *