Hiber Radio: የፈይሳ ለሊሳ እጆች~ ከ1968 ወዲህ በኦሎምፒክ መድረክ የታየ የመጀመሪያው ተቃውሞ!

athelet-Feyissa-Lelissa-1968-tom-protest

አዲስ አበባ ሰሞኑን የጦርነት ቀጠና ሆናለች።በተለይ ዛሬ ስርዓቱ ቀዩዋን ያ ሲል ውሎዋል።ተደናብሮ ተደናግሮ ፈርቶ ሕዝቡን አስፈራራሉ ብሎ ውሎ አምሽቷል። ይሄ ሰላማዊ ሰልፉን አድርጎ ቀይ ካርድ የማሳየትን ያክል አይሳካ እንጂ በራሱ የሌላ ታላቅ ተቃውሞ ድል ዋዜማ ነው።ይሄ ሁሉ ሰራዊት ይሄ ሁሉ ወከባ ይሄ ሁሉ ፍርሃት ስልጣን ላይ ያሉት ሰዎች ስጋት ምን ደረጃ እንደደረሰ ማሳያ ነው። ቀሪው ኳሱዋን በመሬት ላይ የሚጫወቱት የለውጥ ሀይሎች ቀጣይ ስትራቴጂ ነው። የዛሬውን የአዲስ አባባ የጦር አውድማ ያስመሰለው የቀይ ካርድ ተቃውሞ ቢከሽፍም አትሌት ፈይሳ ለሊሳ በሪዮ ኦሎምፒክ ሁለት ሰዓት ከዘጠኝ ደቂቃ ከ54 ሰኮንድ በመግባት የብር ሜዳሊያ አስገኝቷል።   ድርብ ድል እንዲሉ የሕዝብ አጋርም ሆኗል።ተቃውሞን በተገኘው ሁሉ መድረክ ላይ ማሰማት ጊዜው የጠየቀው ነው። በኦሎምፒክ አደባባይ አጋዚ ማይደርስበት ወያኔን አንገት ያስደፋ እርምጃ ወስዷል። ለሞቱ ወገኖቹ በድሉ ሳይኮራ አጋርነቱን አሳይቷል። አሁን የቀረው የነ ጌታቸው ቅርሻት ብቻ ነው <ኦሎምፒክ ላይ ምንትሴ..> ያበደ ስርዓት ያበደ ቃል አቀባይ።ለሁሉም የኦሎምፒክ መድረክ ከዚህ ቀደም ያስተናገደውን ጨምሮ የትነበርክ በገጹ የከተበውን ያንብቡት።

(የትነበርክ ታደለ)

በዝያ አመት በሜክሲኮ በተካሄደው የኦሎምፒክ ውድድር ቶሚ ስሚዝ እና ጆን ካርሎስ የተባሉ ሁለት ጥቁር አሜሪካውያን ወርቅና ነሀስ በማግኘት ለሽልማት መድረክ ላይ ቆመዋል። የሽልማቱ ስነ-ስርአት ተጀመረ። የአሜሪካ ብሄራዊ መዝሙር ተከፍቶ በስታዲየሙ የሚገኙ አሜሪካውያን ሁሉ ከመቀመጫቸው ተነስተው እጆቻቸውን በደረታቸው ላይ ጭነው ከፍ ባለ የብሄራዊ ስሜት መዝሙሩን ያስተጋቡ ጀመር….

ነገር ግን ሜዳሊያዎቹን በወዛቸው ያገኙት ሁለቱ አትሌቶች ቶምና ጆን አንገታቸውን ደፉ፣ እጆቻቸውን ወደ ላይ ሰቀሉ፣ በዝምታም ብሄራዊ መዝሙሩን ሳይዘምሩ ጸጥ ረጭ አሉ!!

በወቅቱ በጥቁር አሜሪካውያን ላይ ለሚደርሰው በደል እና የዘር መድልዎ እነዚህ ሁለት ወጣቶች በዚህ መድረክ በኩራት ደረታቸውን ሊያስነፋቸው በደስታ ሊያስቦርቃቸው አልቻለምና አንገታቸውን በመድፋት ለአለም ህዝብ ተቃውሞዋቸውን አሰሙ። ይህም ለብዙ የነጻነት ታጋዮች ዳግም የመነቃቃት ስሜትን ፈጠረ።….

ቶም ስሚዝና ጆን ካርሎስ ከዝግጅቱ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይም “ዛሬ ምን አይነት ታላቅ ስራ እንደሰራን አሜሪካውያን ሁሉ ያውቃሉ!” ሲሉ በኩራት ተናግረዋል። “ድላችን የህዝባችንን ድምጽ ለአለም ህዝብ ማሰማት መቻላችን ነው” ብለዋል።

ዛሬ ከ46 አመታት በኋላ ደግሞ የኛው የማራቶን ጀግና በሪዮ ኦሎምፒክ የህዝብ ልጅነቱን ደገመው። ዛሬ ኢትዮጵያውያን ከዳር ዳር የነጻነትና የእኩልነት ጥያቄ እያቀረቡ ባለበት ወቅት፣ ለጥያቄያቸውም ምላሹ የጥይት ባሩድ በሆነበት በዚህ ወቅት፣ መንግስት የተባለው የጥቂቶች ስብስብ ነገሮችን አረጋግቶ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው ውሳኔ ከመወሰን ይልቅ ህዝብን ከመጤፍ ሳይቆጥር ቀንና ማታ እያሸበረ ባለበት በዚህ ወቅት…….

….ፈይሳ ለሊሳ ኢትዮጵያ አይታው የማታውቀውን ታሪክ ሰርቷል። ማሸነፍ ሩጫን ብቻ አይደለም፣ ማሸነፍ አንድ የተሰለፉበትን የሙያ መድረክ ብቻ አይደለም፣ ማሸነፍ ማለት የሀገርና የወገንን ጥቅም ማስቀደም ማለት ነው።

እናም ፈይሳ በሪዮ ዴጄኔሮ የኦሎምፒክ የሽልማት አውድ ላይ ሲቆም ታሪክ የሚዘክረው ባስገኘው የብር ሜዳሊያ ብቻ አይሆንም። የብዙዎችን ዝምታ መስበር የቻለበት እና ለአለም ህዝብ ድምጻችንን ያሰማበት እጆቹም እንዲሁ ይዘከራሉ። ታሪክ ለመስራት ሁሉም ጊዜ አመቺ ነው!! ረዥም እድሜ ለፈይሳ ለሊሳ!!!

ህብር ሬድዮን በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ በ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ ከ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *