Hiber Radio: ‹‹ጥያቄን በመፍራት፣ ጠያቂዎችን ማሸሽ!›› ዳንኤል ሺበሺ ከእስር ቤት

አቶ ዳንኤል ሺበሺ ከመጀመሪያው እስር በፊት በአደባባይ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ንግግር ሲያደርግ

በሁለተኛ ዙር እስር ላይ የሚገኘው ዳንኤል ሺበሺ በአንድ በኩል ቀድሞ ከእነ ሀብታሙ አያሌው ጋር በተከሰሰበት ከደህነት የተላከልኝ ሰነድ ከፋይሌ ጠፋ ጭምር እያለ ቀጠሮ ሲያራዝም የነበረው ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኮማንድ ፖስቱ አስሮት በሌለበት ተከላከል ብሎታል። ዳንኤልን ሲይዙት የሕወሃት ኮማንድ ፖስት የደህነት አባላት ክፉና ደብድበውታል።ድብደባውን ተከትሎ በደረሰበት ጉዳት ዳንኤል የግራ ጆሮው ክፉኛ ተጎድቶ ህክምና ተከልክሏል።ዳንኤል ሲደበደብ ይሄ የመጀመሪያ አይደለም ቀድሞ በታሰረበትም ወቅት ማዕከላዊ ደጋግመው ደብድበውታል። የቀድሞው የሕጋዊው አንድነት ፓርቲ ም/የድርጅት ጉዳይ ሀላፊ ዳንኤል ሺበሺ ዛሬም ከእስር ቤት ሀሳቡን ገልጿል።አንብቡለት።

የኮማንድ ፖስቱ አጣሪ ኮሚቴ ነን ያሉ አምስት ሰዎች ታኅሣስ 4 ቀን 2009ዓ.ም በቦሌ ክ/ከተማ ኮከብ ህንጻ ጀርባ በተለምዶ (አምቼ) አካባቢ ያለው ፖሊስ መምሪያ (እኛ ወደ ታሰርንበት) መጥተው ነበር፡፡ በእዚህ ፖሊስ መምሪያ እኛን ጨምሮ ከ180 ያላነሱ እስረኞች ይገኛሉ፡፡ ሁሉም ማለት ይቻላል በኮማንድ ፖስቱ የተያዙ ናቸው፡፡ በዕለቱ ጧት የእስረኞቹ ኃላፊ ኢንስፔክተር እኛ ወደታሰርንበት ክፍል መጥቶ ‹‹ምን ችግር አለባችሁ?›› ብሎ ጠይቆን ነበር፡፡ ኢንሰፔክተሩ ካነሳናቸው ነጥቦች ውስጥ አንዱ ‹‹ዛሬ የኮማንድ ፖስቱ አባላት ሊመጡ ይችላሉ፣ ሲመጡ ከእስረኞች ጋር የተያያዙ ነገሮች ማንሳት ትችላላችሁ፡፡›› ብሎ ተመልሶ ሄደ ኢንሴፔክተሩ በነገረን መሰረት ወደ ምሣ ሰዓት ገደማ የመጡ ሲሆን እነርሱ ከመምጣታቸው በፊት እኔን (ዳንኤል ሺበሺ) እና ኤልያስ ገብሩን ጠርተው አስወጡንና ወደ ቢሮ ወስደው በአንድ ክፍል ውስጥ አስቀመጡን፡፡

በተቀመጥንበት ቢሮ ቆይታችን ስለበዛ ለምን እንዳቆዩን ጠየቅናቸው ‹‹ኮማንድ ፖስቱ እየመጣ ነው፡፡ ሲመጣ እስረኞቹን ወክላችሁ ጥያቄ እንድታቀርቡ ነው!›› አሉን፡፡ እኛም ‹‹እሺ እንጠብቃለን›› ብለን ብንጠብቅም ጊዜው እየገፋ ሄደ፡፡ በድጋሚ ስንጠይቃቸው ምላሽ በማጣታችን ‹‹ወደ ክፍላችን መለሱን›› ብለን ጠየቅንና ጠባቂው ዋ/ሳጅን ቢንያም የተባለ ለአለቃቸው ስልክ ደውሎ ጠየቀ፡፡ ‹‹በቃ! አስገቧቸው›› አለ፡፡ ‹‹ ተነሱ! ወደ ውስጥ ግቡ›› ብለው ወደ ማደሪያ ክፍላችን ስንገባ ቅድም እኛን እንዳስወጡን የመጡ የኮማንድ ፖስቱ አባላቶች በጎን ከተቀሩት እሥረኞች ጋር ከማደሪያችን ፊት ለፊት ባለው አዳራሽ ተሰብስበው ስብሰባውን አጠናቀው ጠበቁን፡፡ የተሠራብንን ፊልም እንደሆነ ገባን፡፡ በስብሰባው ላይ እኛ እንዳንገኝ ስላልፈለጉም እንደሆነ ተረዳን፡፡ ደግነቱ እኛ ባንገኝም አናንያ ሶሪ በእስረኞች ‹‹ይሳተፍ!›› ቢሉም የኮማንድ ፖስቱ አባላት ‹‹አይሆንም!›› ሌላ ወክሉ ሲሉ ታሳሪዎቹ ባለመቀበላቸው በብዙ ጭቅጭቅ በስብሰባው ላይ ተገኝቶ ነበር፡፡

በእኛ ላይ የተደረገውም ሆነ በእስረኞች አጠቃላይ ጉዳዩ ላይ ሰፊ ንግግር እንዳደረገና በጥያቄም ትንፋሽ እንዳሳጣቸው በቦታው የተገኙ ሌሎች እስረኞች ነገሩን፡፡ በእኔ ላይ የደረሰውን ድብደባንም በተመለከተ በሰብዓዊ መብት ላይ የተፈፀመ ወንጀል መሆኑን በመጥቀስ የገለፀ ሲሆን መልስ መስጠትም አልቻሉም፡፡ ሀሳብንና እውነትን እንደ ጦር የሚፈሩ መሆናቸውን ተረዳን፡፡

ይህ ድርጊት ሲያጋጥመኝ ለ2ኛ ጊዜ ነው፡፡ ሰኔ 9 ቀን 2007ዓ.ም በቂሊንጦ እስር ቤት እያለን የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ባለሥልጣናት እና ሌሎቹችንም ኃላፊዎች ለጉብኝተው መጥተው ነበር፡፡ በዕለቱ በእኛ መዝገብ ተከሰው ከነበሩት ውስጥ እኔ (ዳንኤል ሺበሺ) ሀብታሙ አያሌው፣ አብርሃ ደስታ፣ የሺዋስ አሰፋንና ……….. እና ሌሎቹንም ስብሰባው ወደ ማረሚያ ቤት ኃላፊ (ኢንስፔርክተር ህቡዕ……?) ቢሮ ለስብሰባ ብለው ወሰዱን ከእዛ የተደረገውን እና የተሰራብንን ደባ ዝርዝር ከአቶ ሀብታሙ አያሌው መስማት ይቻላል፡፡ በመጨረሻም ነጮቹና ባለሥልጣናቱ ጉብኝታቸውን ጨርሰው ከወጡ በኃላ ነበር የተለቀቅነው፡፡

በአሁኑ ስብሰባ ላይ እኔ ዳንኤል ሺበሺ እና ኤልያስ ገብሩ እንዳንገኝ የተደረገው ቀደም ሲል ተደርጎ በነበረው ስብሰባ ላይ በተደጋጋሚ ህጋዊነትን የሚሸት ጥያቄዎቻችን በተለይም ከሰብዓዊ መብት (ይዞታ) ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ስናነሳ ስለነበረን ቂም ተይዞብን ነው! የሚል እምነት አለን፡፡

‹‹በጊዜውም አለጊዜውም ትግሉ ይቀጥላል!››

አቶ ዳንኤል ሺበሺ

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *