Hiber Radio: እዚህም እዚያም የወገን ለቅሶ ይጨንቃል ያስፈራል በይድነቃቸው ከበደ

በቆሼ አደጋ የሞቱት ወገኖቻችን ቁጥር ዛሬም እንዳሻቀበ ነው።የዚህ ሁሉ ጥፋት መንስዔ ሆን ተብሎ የተቀነባበረ አካባቢውን ወደ ሜዳነት ለመለወጥ ታቀደ ስራ ውጤት መሆኑን እማኞች መግለጽ ጀምረዋል። ሀይለና ፍንዳታ ተሰምቷል ያን ለዘመናት ወደ ተራራነት የተቀየረ ቋጥኝ ማነው በድማሚት ለመናድ የሞከረው? ለተጎጂዎች ለምን ፈጥኖ መድረስ አልተጫለም? የአዲስ አበባን መሬት ለመቀራመት ገበያ ላይ በተቀነባበረ ሁኔታ እሳት እየለቀቁ የዜጎችን ንብረትና ሕይወጥ ሲያጠፉ የነበሩ ገዚዎች በተለይም የሕወሃት አጥፊ ቡድን ለዚህ ቀውስ ጉልህ ሚና አይኖረውም ብሎ መናገር አይቻልም። ለዚህ የነሱን አጣሪ ኮሚስን ዌኢስ የዲፕሎማቶችን ምስጢራዊ መረጃ ያጋለጠውን ዊክሊክስን እንጠብቅ? የወገኖቻችን ስቃይ እዚህም እዚያም ዋይታ ያሰቅቃል። ዛሬም የሚፈለጉና የደረሱበት ያልታወቀ ንጹሃን እተፈለጉ ነው። አስጨናቂውን ሁኔታ ይድነቃቸው ከበደ ያየውና የታዘበውን ከትቧል። እነሆ አንብቡት።

ይጨንቃል ፣ያስፈራል …

እዚህም እዚያም ለቀስተኛው ያለቅሳል ፣ ገሚሶቹ በቁጭት እና በንዴት ፊታቸውን አጨልመው የሆነ ነገር አድርጉ አድርጉ የሚላቸው ስሜት እየተፈታተናቸው ግን እንዴት ማድረግ እንዳለባቸው ግራ መጋባታቸው ሁኔታቸው ያሳብቃል፣ እናቶች ነጠላቸውን አዘቅዝቀው ወገባቸው ላይ ፎጣ አሸርጠው ፣ በደከመ ድምፃቸው እያለቀሱ፣ ወዲህ ወዲያ ይላሉ።

-አርብ እለተ በአንድ ክፍል፣ በአንድ ላይ ሆነው ሲማሩ የነበሩ ፣ በት/ቤት ቅጥር ጊቢ በእረፍት ሰዓት ሲጫወቱ የነበሩ ጓደኞች፣ በድንግት መቼም ላይገናኙ በሞት የተለዮቸውን ጓደኞቻቸውን ፣በማሰብ ሐዘናቸውን ለመግለፅ እና ለማጽናናት ቁጥራቸው የበዛ ተማሪዎች በየዱንኳን እየገቡ ሲያለቅሱ ፣ የሆነ ነገር ሰውነትን ውርር ያደርጋል። ” ልጄ ፣ሙሽራዬ፣ ” በማለት አንድ ጎልማሳ አባት ፣እጅግ በጣም ልብ በሚነካ ሁኔታ ሲያለቅሱ፣ ሰውነት ሽብርክ ይላል። የፈጣሪ ያለ! እኔ ነኝ ያለ ጨካኝ ሰው እኚህን አባት ሲያለቅሱ አይቶ የት እንደ-ሚገባ ግራ ይሆንበታል።

-የፌደራል ፖሊሲ ብዛቱ ፣ እዚያ አካባቢ ከፍተኛ የሆነ አድማ እና እረብሻ የተፈጠረ ነው የሚመስለው። የእሳት አደጋ እና የድንገተኛ አምቡላንስ መኪናዎች ይሄዳሉ ይመጣሉ፣ ገልባጭ መኪናዎች ይመላለሳሉ፣ እናቶች ፣አባቶች እንዲሁም ወጣቶች ፣ፊታቸውን በሐዘን አጨግገው ከታች ወደ ላይ ይሄዳሉ፣ በመሐል ቆም ብለው፣ በቁጭትና በሐዘን አንዱ ለሌላው ፣ የሆነ ነገር ያወራዋል ሌላኛው በተመስጦ ያዳምጣል ። ድንገት በመሃል፣ በቁፋሮ የተገኘ አስከሬን በሦስት አምቡላንስ ተጭኖ ሲያልፍ ፣ ሁሉም በያለበት ግራና ቀኙን ይዞ፣ ግማሹ ያለቅሳል፣ የተቀረው ሐዘን እና ብስጭት ቅጥል አድርጎት ፣ የሚለው እና የሚያደርገው ግራ ገብቶት ባለበት ይቆማል። ወዲያውኑ ፖሊሲ ይመጣና “ተንቀሳቀሱ” በማለት አካባቢውን ጭር ለማድረግ ይሞክራል ግን አይሆንም ።

-ወደ ዋና ቦታ መድረስ አይቻልም። ከዋናው ቦታ በቅርብ እርቀት ፣ የተራራ ክምር የሚያህል ቆሻሻ በደንብ ይታያል። በላስቲክ የተወጠሩ መጠለያ ቤቶች ቆሻሻውን ተገን አድርገው በግራና በቀኝ ቦክል አሁን ድረስ ይታያሉ፣ በውስጣቸው የነበሩ (የቤቱ ባለቤቶች) እንዲወጡ ተደርገዋል ። የተራራ ክምር የሚያህል የቆሻሻ የሚገኝበት መሃከለኛው ተንዶ ግማሹ ለዓይን ህይታ ከርቀት ሲታይ ተሰዉሯል።

-ከሩቅ ሲታይ የጠፋው የተራራ ክምር የሚያህል ቆሻሻ ፣ እሱን ተገን አድርገው በላስቲክ ወጥረው፣ መጠለያ “ቤታቸውን” ቤቴ ብለዉ ፣ ወገባቸውን አሳርፈው እንቅልፋቸውን ከመተኛታቸው በፊት፤ ህይወታቸውን የነጠቀ ላካስ እሱ የመሃከለኛዉ የቆሻሻ ክምር ተራራ ነው። ይሄ የመሃከለኛዉ የቆሻሻ ክምር ተራራ ፣ እሱን ከለላ አድርገው የኖሩትን ብቻ አይደለም ፣ ይዞ የተናደው። ከእሱ በቅርብ እርቀት በተለያየ ቦታ በልማት ስም የተነሱ ፣ በተለይ በንፋስ ስልክ ቤታቸው የፈረሰባቸው፣ እንዲሁም ቦታ ተመርተው የቁጠባ ቤት ገንብተው ፣ የሚኖሩ እነሱ ላይ ነው፣ የመሃከለኛዉ የቆሻሻ ክምር ተራራ የተናደው።

-አዎ ! አካባቢው ከ120 ሰወ የማያንስ ህይወቱን በአንድ ጊዜ በአንድ ቦታ የሞተበት ሥፍራ ነው። እናም ይጨንቃል ፣ ያስፈራል … ግን ለዚህ ሁሉ የሰው ህይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት መድረስ ተጠያቂው ፣ ከመንግስት ውጪ ማንም የለም። መጋቢት 6 ቀን 2009 ዓ.ም በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከጠዋቱ 4 ሰዓት እስከ 6 ሰዓት ቆይቼ ነበር። የሟች ቤተሰቦችን እግዚአብሔር ያጽናችሁ ለማለት፣ እንዲሁም በጉልበት የምችለውን ለመርዳት። ይሁን እንጂ በቦታው ላይ እኔን ጨምሮ ሌሎች ብዙ ወጣቶች በጉልበት ለመርዳት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። ፖሊሲ ወደ ዋናው ቦታ ሰዎች እንዳይደርሱ ክልከላ አድርጓል ። የነበረኝ ቆይታ ከብዙ በጢቂቱ ይሄን ይመስላል ። ህይወታቸውን ላጡ ፈጣሪ ነፍሳቸውን ይማር ፤ለቤተሰቡና ለወዳጅ ዘመድ መጸናናት ፈጣሪ ይስጥልን ፤ አሜን !!!

(ይድነቃቸው ከበደ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *