Hiber Radio: ኢህአዴግ “ሕዝብን ለአመፅ በማነሳሳት” በሚለው ይከሰስልን! ጦማሪ ስዩም ተሾመ

ትላንት ማታ ሰፈር ካለች አንዲት ግሮሰሪ ቁጭ ብዬ ሞባይሌን እየጎረጎርኩ ሳለ ባለቤቷ መጥታ “ስዬ ዛሬ በግዜ ግባ” አለችኝ። እኔም ነገሩ ገርሞኝ “ምነው? ምን ችግር ተፈጠረ?” አልኳት። “አይ..ነገ ለተቃውሞ እየተዘጋጁ ስለሆነ ማምሸቱ ለአንተ ጥሩ አይደለም” ብላኝ ዕቃዎቿን ማስገባት ጀመረች። ላለፉት ዘጠኝ ወራት በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ተጠፍሮ የከረመ ማህብረሰብ በአስረኛው ወር ላይ ለአመፅና ተቃውሞ አደባባይ ይወጣል ብዬ አልጠበቅኩም ነበር። ጠዋት ላይ የተመለከትኩትን ነገር ማመን ነው፡፡

ዛሬ ጠዋት ከእንቅልፌ የቀሰቀሰኝ ከአዲስ አበባ ወደ ጅማ በሚሄዱ መኪኖች ላይ የሚያርፈው የድንጋይ ውርጅብኝ ነበር። ሮጬ ወደ አስፋልት ስወጣ ለወትሮ በባጃጆችና በመኪናዎች ይጨናነቅ የነበረው በፈረሶች ተሞልቷል። የሕዝብ ትራንስፖርት የለም። የንግድ ቤቶች በሙሉ ተዘግተዋል። ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ የኦሮሚያ አድማ በታኝ ፖሊስ እና የወሊሶ ከተማ ፖሊሶች ሁኔታውን ለመቆጣጠር ጥረት ማድረግ ጀመሩ። ከሰፈር እስከ መሃል ከተማ ድረስ በእግሬ ተጓዝኩ። በዚያውም የተቃውሞ እንቅስቃሴውን በጥሞና ለማጤን ሞከርኩ። የዛሬው ተቃውሞ ከዚህ ቀድም ሲካሄዱ ከነበሩት የተለየ ነው።

የግብር የጭማሪን በመቃወም በወሊሶ ከተማ የነበረው የህዝብ ትራንስፖርት አድማ

በዋናው መንገድ ላይ በእግር የሚጓዘውን ሕዝብ ለተመለከተ “ይሄ ሁሉ ሕዝብ ወሊሶ ውስጥ አለ እንዴ?” ብሎ መጠየቁ አይቀርም። ግራና ቀኝ መስመሩን ይዞ የሚተመው ሕዝብ ለተቃውሞ አደባባይ የወጣ መሆኑን የምታውቀው ከአዲስ አበባ ወደ ጅማ የሚሄዱ መኪኖች አጠገባቸው ሲደርሱ ነው። በድንገት ከግራና ቀኝ የድንጋይ ውርጅብኝ ሲወርድባቸው ስታይ የት እንዳለህ ይገባሃል። ለካስ አብዛኛው መንገደኛ በኪሱ ድንጋይ ይዞ ኖሯል።

በዋናው መንገድ ላይ በዝምታ እየተመመ ያለው ህዝብ ወደ ሥራ ቦታ ወይም ወደ መኖሪያ ቤቱ እየሄደ አይደለም። ሕዝቡ ከቤቱ ወጥቷ፣ ከስራ ቀርቷል። የትራንስፖርት ሆነ የንግድ እንቅስቃሴው ላይ አድማ መትቷል። ነገር ግን፣ መንገድ ላይ ዝም ብሎ ይሄዳል። እንደ ቀድሞ ግዜ አንድ ቦታ ላይ ተሰብስቦ መፈክር አያሰማም። ነገር ግን፣ ለተቃውሞ አደባባይ ወጥቷል። በመንገዱ ግራና ቀኝ በዝምታ እየሄደ ተቃውሞውን ያሰማል። ድምፅ ሳያሰማ “ግብር በዛብኝ!” እያለ ብሶትና ምሬቱን ይገልፃል።

አዲስ በወጣው የግብር ተመን ላይ ተቃውሞውን እያሰማ ያለው የንግዱ ማህብረሰብ ብቻ አይደለም። ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ነው። እኔ እንደታዘብኩት በዝምታ ለመቃወም አደባባይ የወጣው ሕዝብ ነው። የሚቃወመው የኢህአዴግ መንግስትን ነው። ህዝቡን ለአመፅና ተቃውሞ የቀሰቀሰው ደግሞ የኢህአዴግ መንግስት ራሱ ነው።

እስከ ባለፈው አመት ድረስ ሲከፍል ከነበረው የግብር መጠን 20ና 30 እጥፍ ያለ ምንም ማስጠንቀቂያ በድንገት ክፈል ሲባል ነጋዴው ራሱን ስቶ ያልወደቀው ወይም ጨርቄን-ማቄን ሳይል ከሀገር ብንን…ብሎ ያልጠፋው ነገሩ “ቀልድ” ስለ መሰለው ነው። ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በአመፅና ተቃውሞ ሲናጥ የነበረ፣ በአስቸኳይ ግዜ አዋጅና በኮማንድ ፖስት የፊጥኝ ታስሮ የከረመ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ የ20ና 30 እጥፍ ግብር ጭማሪ በመጀመሪያ እንደ እብድ ለብቻ ያስቃል። ከዚያ መንግስት ከምሩ “ክፈል” እያለህ እንደሆነ ስታውቅ “በፍፁም አልከፍልም!” ብለህ ለተቃውሞ አደባባይ ትወጣለህ። በእርግጥ ሕዝቡ “የምከፍለው የግብር መጠን አይጨመር” እያለ አይደለም። ይሁን እንጂ፣ በአንዴ ተነስቶ 20ና 30 እጥፍ ግብር መጨመር እንኳን ለግብር ከፋዩ ለመንግስት አካላትም ግራ የሚያጋባ ነው።

በመሰረቱ፣ ጭማሪው ምንም ያህል ቢሆን በቅድሚያ መሰራት ያለባቸው ስራዎች አሉ። ለግብር ከፋዩ ማህብረሰብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መሰራት አለባቸው። ግብር ከፋዩ የሚመጣበትን የግብር ዕዳ ቀድሞ አውቆ ራሱን ማዘጋጀት አለበት። ይህም ሆኖ ግን፣ አምና ሲከፍል ከነበረው 20ና 30 እጥፍ ጭማሪ ክፈል ማለት ሕዝብን “ለአመፅና ተቃውሞ ተነስ! ሁከትና ብጥብጥ አስነሳ!” እያሉ ጥሪ እንደማቅረብ ይቆጠራል።

በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ እንደተመለከትኩት እንደ አምቦ፥ ጊንጪ፣ እንዲሁም በአንዳንድ የአርሲና ሐረርጌ አከባቢዎች ተመሳሳይ የአመፅና ተቃውሞ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። ይህን የአመፅና ተቃውሞ እንቅስቃሴ በማነሳሳቱ ረገድ ዋናው ተጠያቂ የኢህአዴግ መንግስት ነው። እንደሚታወቀው አንዳንዶቻችን “ሕዝብን ለአመፅና ተቃውሞ አነሳስታችኋል” በሚል ለእስራትና እንግልት ተዳርገናል። ሰሞኑን እየታየ ያለውን የተቃውሞ እንቅስቃሴ በማነሳሳት ብቸኛው ተጠያቂ አካል ኢህአዴግና የኢህአዴግ መንግስት ነው። ታዲያ ልክ እንደ እኛ ኢህአዴግም “ሕዝብን ለአመፅ በማነሳሳት” በሚለው አንቀፅ ይከሰስልና?!

Hiber radio Las Vegas ይህ ህብር ሬድዮ _የወቅታዊ መረጃ ምንጭ ነው። ህብር ሬድዮ በአቤኔዘር ኮሙኒኬሽን ሴንተር እየተዘጋጀ  ከላስ ቬጋስ ከተማ፣ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 630 ሰዓት እስከ 8 ሰዓት በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ 5639993994 ወይም 563999-3988 ወይም 712-432-8451 በመረጡት ቁጥር መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ 01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *