Hiber Radio: የአዲሱ አብዮት ተስፋዎች -ቄሮን አደራ!

በደብረ ማርቆስ ከጣና ላይ እቧጮን ለመንቀል በመዝበት ላይ ላሉ የኦሮሞ ወጣቶች-ቄሮ አቀባበል ሲደረግ

(በሀብታሙ አሰፋ)

የጎንደር ወጣቶች የ26 ዓመቱን ወያኔ የገነባውንና በገዛ አገራቸው ከወገናቸው፣ከወንድማቸው በወገናቸው የኦሮሞ ሕዝብ ላይ እየተወሰደ ያለውን ግፍ በአደባባይ አወገዙ። <<የኦሮሞ ደም ደሜ ነው>> << በቀለ ገርባ ይፈታ፣አንዷለም ይፈታ >> ሲሉ አንዱ ለአንዱ አብሮ መቆም ምን እንደሆን አሳዩ።አዳማ ላይ ያ ተደገመ። አስገራሚው የሕወሓት ሰዎች መታወቂያ ላይ ዘርን ለይተው፣የጎሳ መስመር አበጅተው እርስ በእርስ አፋጅተው ዘላለም በጠላትነት ይተያያል ያሉት ሕዝብ ድንገት ያንን አጥር አልፎ የአንዱ ቁስል ሌላው የሚያመው መሆኑን የአባቶቹን አንድነት በጎውን ይዙ ክፉውን ጥሎ ወደፊት ለመጓዝ ማሰቡን አሳየ።

ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ዘረኛው ወያኔ በቀደደላቸው ቦይ ብቻ ሲፈሱ የነበሩ ብዙዎቹ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ያንን አጥር አልፈው በግልጽ መሔድ የጀመሩት አስቀድሞ ሕዝቡ መለያየት በቃን ስላለ ነው። ዛሬም ከሁለቱም ወገን ጥቂቶች የሁዋሊት መሔድ የሚፈልጉ አልጠፉም። አካሄዳቸው ሁለቱን ሕዝቦች ነጣጥሎ የወያኔን ዕድሜ ለማራዘም ወይም ከልዩነት ፖለቲካ እናተርፋለን ባይና ደርሶ ለሕዝብ አሳቢዎች ናቸው።የኦሮሞ ሕዝብ እና የአማራ ሕዝብ ላይ ስርዓቱ በግልጽ ጦርነት አውጇል።ይሄ ሕዝብን በማጋጨት ስልጣንን ለማቆየት መሞከር ከሽፎ ሕወሓትን ከግራ ከቀኝ ተቃውሞ ሲያጣድፈው እነ አብዲ ኢሌን ምን ለመሰለ ዓላማ ሰሞኑን መጠቀም እንደጀመረ ያሳያል። ይሄ ሁሉ ዘግናኝና አሳዛኝ ጭፍጨፋ የህወሓት ጄኔራሎች ከሁዋላ እየገፉ በሶማሌ ልዩ ሀይል የሚል ስም በተሰጠው የሕወሓት የአይሲስ ኮማንዶ የወሰደው እርምጃ ሳይቃጠል በቅጠል ካልሆነ መጨረሻው አይታወቅም።ሕወሓት እንዳሰበው ባያተርፍም በሱማሌ ልዩ ሀይል በኩል የወሰደው እርምጃ እነዚህ ሰዎች ለዚህ ሕዝብ የደገሱለት ጥፋት የት ድረስ ሊሄድ እንደሚችል ማሳያ ነው።

ባለፈው ዓመት ለሰላማዊ የእሬቻ በዓል ጥሪ ሲደረግ ከባህር ዳር እና ከጎንደር የተወሰኑ ወጣቶች ቢሸፍቱ ጥብቅ ፍተሻውን አልፈው እንደዛሬው በአደባባይ ለመጓዝ ሳይፈቀድላቸው ሔደዋል።ሕወሓት በወሰደው የሽብር እርምጃ ከአየርና ከምድር ጥይትና አስለቃሽ ጭስ ተኩሶ በዚያ ሳቢያ ከሞቱን ከሺህ በላይ ንጹሃን ስንቶቹ እዚያ ውስጥ መኖራቸውን ዛሬም የሚያውቅ የለም። ብዙዎቹ በመታወቂያቸው ላይ የተጻፈው አማራ የሚል ዘራቸው ለጥቃት እንደሚያጋልጣቸው አውቀው መታወቂያቸውን እስከመጣል ስለደረሱ በወጡበት የቀሩትን ቤቱ ይቁጠራቸው።ይሄ ትውልድ ለሰላም ለፍቅር አብሮ ለመቆም ብቻ ሳይሆን ዛሬም አብሮ ሞቷል።ትላንት አባቶቹ በጋራ ባቆዩት አገር ተከባብሮ አንዱ ለአንዱ ሆኖ ነጻነቱንና መብቱን አስከብሮ በጋራና በሰላም ለመኖር ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል።

ጣናን የወረረው እምቧጮን ለመንቀል የሚያስፈልገው ወጪ የአማራን ወይ የኦሮሞን መብቱን በሰላም ለመጠየቅ አደባባይ የወጣን ወጣት ለመግደል ሕወሓት ለጥይት፣ለመሳሪያ ለወታደር ከሚያወጣው አንድ መቶኛ አይሆንም። በሕወሓት በኩል ገድሎ አደኽይቶ አሽከር አድርጎ ለመግዛት እንጂ ለእነሱ ጣና ደረቀ፣የአማራ ሆነ የኦሮሞ እናት በሕክምና እጦት ሞተች ጉዳያቸው አይደለም። በቅርቡ የወጣው የዓለም ባንክ ጥናት ለዚህ አብይ ምስክር ነው።ፖሊሲው ትግራይ እስክትለማ ሌላው አገር ይድማ እየተገበረ ብቻ ሳይሆን ዓለም ካወቀው መቆየቱን ያሳያል።

የኦሮሞ ወጣቶች-ቄሮ እምቧጮ ላይ ለመዝመት ሲነሱ ፣ወደዚያ ሲጓዙ ላለፉት 26 ዓመታት ፖሊሲ ተቀርጾለት፣ በጀት ተበጅቶለት ሲሰራበት የበረውን የመክፈልና የማጋጨት ስራ ተራምደው አዲስ አብዮት እያካሄዱ መሆኑ የገባው ገብቶታል። መሬት ላይ ያለውን እውነታ ያልተገነዘበና  <<ሹም ካዘዘው ስሜት የወዘወዘው..>>  መሆኑ ያልተገለጠለት ዛሬም አየር ባየር ፖለቲካ ላይ ተጠምዶ ያሴራል። የልዩነት ሰበዝ ለመምዘዝ ይሞክራል።አለመታደል ማለት ይሄኔ ነው።

የጣና እምቧጮ በእነዚህ ወጣቶች ክንድ ብቻ የሚያልቅ ወይ የሚጠፋ አይደለም ።ሰው ክፉ አረምን ለመንቀል ከተባበረ በጋራ የሚገለው ፣የሚያስረው ስርዓት ላይ ለመተባበር በጋራ ለመዝመት ቢያንስ መንገድ የሚጠርግ መተሳሰብ የአብሮነት የአንድነት መሰረት ውጤት ነው። በማንነቱ የሚሳደደው ኦሮሞ በማንነቱ የዘር ማጥፋት የታወጀበት አማራ በአንድ ገበታ ቀርቦ ፣በአንድ ላይ ለአንድ ዓላማ የዘመተበትን የሰላም ተልዕኮ ባለፉት 26 ዓመታት ካለ ጠቁሙን። አገር ማዳን መስሎት የዘመተበት የባድመ ጦርነት መለስ የስጋ ዘመዶቹን ላለመውጋት እስከማቅማማትና ተቃውሞ የሔደበት ክህደት፣ ጄራሎቹ የማይቀረው ጦርነት ሲመጣ  ንጹሃን የአማራና የኦሮሞ ልጆችን ሆን ብለው በሴራ እየለዩ  የፈንጂ ማምከኛ ማድረጋቸው ያደባባይ ምስጢር ከሆነ ቆየ።

የአንድ አገር ሕዝብን በዘር ከፍሎ ለማጋጨት ሰሞኑን በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል መካከል ሕወሃት ጃስ ያለው አብዲ ኢሌና የሶማሌ ልዩ ሐይል ሰራዊት የወሰደው እርምጃ በቂ ማሳያ ነው።በዚያው በአካባቢው የሚገኘውና የአሮማያ -አለማያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሰላማዊ ጥያቄ ሳይቀር ሲጠይቁ እየገባ ሲገልና ሲደበድብ የነበረው ሰራዊት ቆሞ ሲመለከት ነበር። ይሄን ድርጊትን የተቃወሙ የኦሮሚያ ባለስልጣናት ላይ የእነ ሳሞራ ሰራዊት የግድያ ሙከራ እስከማድረግ ሄዷል። ይሄ ለውጥ እየተካሄደ መሆኑ ማሳያ አይደለም ብለው የሚያስቡና የትላንቱ የገዛ ወገኑን በሕወሃት ትዕዛዝ ሲገልና ሲያስገድል የነበረው ኦህዴድ ዛሬም ሙሉ ለሙሉ አለ ብለው የሚከራከሩ አንዳንዶች  ዛሬም ለእምቧጮው ዘመቻ የሔደውን ወጣት ዓላማ ሲያንሻፍፉት እያየን ነው።

የሕወሃት ደጋፊዎችና ዋና ወና አፈ ቀላጤዎች የኦሮሞ ወጣት-ቄሮ የጣና ራስ ምታት የሆነው እምቧጮ ላይ ለመዝመት መሄድ  ትልቅ ብስጭት ፈጥሮባቸዋል። ልክ ነው፤ ባይበሳጩ ባይናደዱ ነበር የሚገርመው። የምንደነቀው በእኛ ሰፈር ሰዎች ግራ የገባው ፖለቲካ የወያኔን ብሄረሰብ ቀን ከዚህ መሰሉ ሕዝባዊ ሐይል ለይቶ አለማየት ነው። የሕወሓት ደጋፊዎችና መሪዎችማ  ሁሌም ሊከፍሉት የፈለጉት ሕዝብ አንድ ላይ ሲቆም አይናቸው ደም ይለብሳል። ፋሺስቱ መለስ ዜናዊ ከመሞቱ በፊት አማራና ኦሮሞ አንድ ላይ የቆመ ቀን ድርጅቴ ሕወሓት ሞተ ማለት ነው አልነበረም ያለው? ። ያንን የነገሩን ወገኖች የዛሬውን ንዴት  ተከትሎ እነሱው ያቀነባበሩት ጥፋት በእነዚህ ወጣቶች ላይ እንዳይወሰድ ቄሮን አደራ እንላለን። የደብረማርቆስ ሕዝብ አደባባይ ወጥቶ ለጀግኖቹ ታላቅ አቀባበል አድርጓል። 26 ዓመት ይሄን ሕዝብ አትክፈሉት ሲል ለነበረና የአገር ጥፋት የሚከተለው በእርግጥም ወያኔ እንዳሰበልን እርስ በእርስ ስንጋጭ መሆኑን በሰሞኑ የሶማሌና የኦሮሞ ግጭት ያየ በዚያ ማግስት ይህ መሰሉ ትብብር ታላቅ ተስፋ ሰጪ ነው። ወያኔ ይህን ተስፋ ገደል ለመክተት የተለመደ ከፋፋይነቱን በልዩ ልዩ መንገድ እንደሚያደርግ አውቆ ከወዲሁ መጠንቀቅ ይገባል።

የሕወሓት ዓላማ በዚህ ብቻ አይወሰንም ። በተለይ ዛሬም እንደልቡ በሚፈነጭበት ብአዴን እና በጥቂት የኦህዴድ ታማኞቹ አማካይነት መግለጫ መሳይ በሚል ይህን ዓላማ ለማደናቀፍ እና የእነሱን የተለመደ ሕዝባዊ ትግሉንና ዓላማውን ለማጥላላት  እንዳይጠቀሙበት መጠንቀቅም ይገባል። ይሄ ወያኔ ለይስሙላ ከሚያደርገውና መብታቸው ያልተከበረ ብሄረሰቦች በጀታቸው በሕወሃት ሌቦች የሚዘረፍበት የጭፈራው የብሄረሰብ ቀን አይደለም። እሱን ማሳየት ይገባል።

በምርጫ 97 ማግስት በአዲስ አበባ በልዩ ልዩ ቦታዎች የሕወሃት ደህንነቶች ቦንብ በታክሲ ላይ ጭምር አፈንድተዋል። ካራ ቆሬ ላይ እስር ቤት ያሉ የያኔው በዶክተር መረራ ጉዲና የሚመራው ኦብኮ አባላት አውጥተው  በአንድ ቤት ውስጥ ቦንብ ሊያፈነዱ ሲሉ ራሳቸው ላይ ፈነዳባቸው ብለው አፈንድተዋቸዋል። ይሄ በወቅቱ የአሜሪካ ጉዳይ ፈጻሚዋ ቪኪ ሐልግሰን ለመንግስታቸው ድርጊቱ በሕወሐት ደህነቶች ሆን ተብሎ በተቀነባበረ ሁኔታ መፈጸሙን መረጃ ልከው ዊክሊክስ ይሄንኑ መረጃ አጋልጧል።ስለዚህም ሆን ብሎ መኪና ገደል የሚከተው፣በመኪና የሚገጨው አንዱን በአንዱ ለማነሳሳት እና ስልጣኑ ላይ ለመዝለቅ የፈለገውን ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ያለው ሕወሓት ጥፋት አብሮ ሊደገስ ይችላልና ለአማራም ሆነ ለኦሮሞ ሕዝብ የምታስቡ ወገኖች ጥንቃቄ እርምጃ እንዲወሰድ ቄሮን አደራ ክፉ ሳይነካቸው የተነሱበትን ዓላማ ፈጽመው ወደ ቀዬያቸው እንዲመለሱ ተስፋ እናደርጋለን።የአዲሱ አብዮት ተስፋዎች የአዲሱ ትውልድ አባላት ቄሮዎች በርቱ ማለት ይገባናል።

 

Hiber radio Las Vegas ይህ ህብር ሬድዮ _የወቅታዊ መረጃ ምንጭ ነው። ህብር ሬድዮ በአቤኔዘር ኮሙኒኬሽን ሴንተር እየተዘጋጀ  ከላስ ቬጋስ ከተማ፣ ዘወትር ዕሁድ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 630 ሰዓት እስከሰዓት በህብር ሬዲዮ ድህረ ገጽ ወይም በቀጥታ በስልክ ለማዳመጥ  5639993994 ወይም 563999-3988 ወይም 712-432-8451 በመረጡት ቁጥር መደወል ብቻ በቂ ነው በእንግሊዝ ለምትኖሩ 01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን፣ googel app store Hiber Radio ወደ ስልክዎ በመጫን ካልሆነም በዘሐበሻ እንዲሁም በተጠቀሱት ስልኮች ማዳመጥ ይቻላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *